ሀ ለ ሐ መ ሠ ረ ሰ ሸ ቀ በ ተ ቸ ኀ ነ ኘ አ ከ ኸ ወ ዐ ዘ ዠ የ ደ ጀ ገ ጠ ጨ ጰ ጸ ፀ ፈ ፐ
ወ ፡ ፮ኛ ፡ ፊደል ፡
በግእዝ ፡ አልፍ ፡ ቤት ፡ በአበገደ ።
በፊደልነት ፡ ስሙ ፡ ዋዌ ፤ በቍጥርነት ፡ ወ—፮ ፡ ይባላል ። እንደ ፡ ግእዝ ፡ ልማድ ፡ ባማርኛ ፡ ለቅርብ ፡ ወንድ ፡
በትእዛዝ ፡ አንቀጽ ፡ መነሻ ፡ ኹኖ ፡ ኺድ ፡ ወኺድ ፡ ቢል ፡ ዋዌነቱን ፡ ያሳያል ። ዋዌን ፡ እይ ።
ወ፡ (ው ፡ ዎ) ፤
የ(ኣ)ዐ ፡ ተለዋጭ ፤ ወይም ፡ ተወራራሽ ። ፆፍ ፡ ወፍ ፡ ዎፍ ፤ ዑቃቤ ፡ ውቃቢ ።
ወ፡ የግስ ፡ መነሻ
፡ ኹኖ ፡ በስም ፡ ሲታጣ ፡ ወጠነ ፡ ጥንት ወረሰ ፡ ርስት ፡ ይላል ።
ወ፡(ዋ ፡ ው)፤
እንደ ፡ መ ፡ የጥሬ ፡ (ስም)፡ መነሻ ፡ እየኾነ ፡ በባዕድነት ፡ ይነገራል ። (ማስ ረጃ)፡ ጠመደ ፡ ወጥመድ ፤ ነጠፈ ፡
ወንጠፍት ፤ ፈነጠረ ፡ አስፈነጠረ ፡ ወስፈንጠር ፤ ቀለመ ፡ ወቅለ ምት ፤ ሰፋ ፡ (ሰፈየ) ፡ ወስፌ ፡ ወስፋት ፡ ወሳፍቻ
፤ ዐገመ ፡ ዋገምት ፤ ረገጠ ፡ ውርጋጥ ።
ወሂድ: ዘወር በል።
ወህኒ (ማያዊ): ውሃማ፣ ቀዝቃዛ፣ የእስር፣ የግዞት ቤት፡ የወንጀለኛ፣ የነፍሰ ገዳይ ማሰሪያ፡ ዓለም በቃኝ፡ የገሃነመ እሳት ምሳሌ። ወህኒ ያሠኘው ጐድጓዳነቱና ዘቅዛቃነቱ ነው።
ወህኒ ቤት (ቶች): የወህኒ ቤት።
ወህኒ ቤቶች: የወህኒ ቤት ሰዎች፣ ወይም ሠራተኞች።
ወህኒ ዐምባ: በጐንደር የነገሥታት ልጆች የሚያድጉበት፣ የሚኖሩበት የተራራ ወህኒ፡ ወይም የወህኒ ተራራ መንደር።
ወህኒ አዛዥ: የወህኒ ሹም፡ ባንኮበር የሚሾም የእስር ዘበኞች አለቃ።
ወህኒ አገባ: አጋዘ፣ አሰረ።
ወለለ: አበዛ፣ አፈደፈደ።
ወለለ: ከፈለ፣ ሠነጠቀ፣ ከፈተ፡ ገለጠ፣ አበራ፣ አጠራ፣ አነጋ።
ወለላ: ጥሩ ማር ከዳ፣ ቀለሕ፣ ሰፈፍ፣ አሸዋ የሌለበት። (መዝሙር ፲፱:፲፱። ምሳሌ ፳፬:፲፫)። በግእዝ ጸቃውዕ ይባላል።
ወለሌ (ወይሌ): ዋይታ፣ ጩኸት፡ ከቃንዛ፣ ከመንዘር የተነሣ።
ወለሌ: ቀይ ትል፣ የልብስ ብል፣ ወለላ መስሎ የሚታይ።
ወለሌ: የገጠር ስም፡ በቡልጋ ውስጥ ያለ አገር የቅዱስ ሚካኤል ኣጥቢያ። ፪ቱም ለና ሌ ይጠብቃል። (ግጥም) "በመርፈታ ልኸን መሪ ጌታ፡ በወለሌ ልበልበት ሃሌ። "
ወለል (ሎች): ዐባጣ ጐባጣ የሌለበት ባዶ ስፍራ፣ አደባባይ፣ ሸንጎ፣ ጉባኤ። (ግብረ ሐዋርያት ፫:፲፩)
ወለል አለ: ነጋ፣ በራ፡ ጠራ፣ ጥሩ ሆነ።
ወለል አደረገ: ከፈት አደረገ፣ ወለለ።
ወለል ኾነ: ለጥ ቀጥ አለ።
ወለል: መወለል።
ወለል: በወለጋ ውስጥ ያለ ተራራ። "ከወለል እስከ የረር፡ ከየረር እስከ ጐንደር" እንዲሉ። ይኸውም ደወል ነው።
ወለልታ: ወለል ማለት።
ወለልታ: ጥራት፣ ጥሩነት። (መዝሙር ፻፬:፲፮)
ወለመ: ዘለመ፣ ወጣ ገባ አለ፡ ጠመመ፣ ዞረ፣ ተናወጠ፣ ተናጋ (ዐጥንቱ)።
ወለመጠ (ለመጠ): ጋደል፣ ዘንበል፣ ደፋ፣ ለመጥ፣ ዘለስ፣ ጐንበስ አለ፡ ለጦር፣ ለበትር፣ ለኳስ እንዳይገኝ፡ እንዳይወጋ፣ እንዳይመታ።
ወለም አለ: ጠመም አለ።
ወለም ዘለም አለ: ወዲያ ወዲህ ዘወር ገደም ዘንበል አለ።
ወለምታ: መጥመም፣ መዞር፣ መናጋት።
ወለምታ: ትርፍ ነገር፣ ጸያፍ ስተት። (ተረት) "ያፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም። "
ወለምታ: ወለም ማለት፡ ዘወርታ።
ወለሰ: ዐጠፈ፣ መለሰ፣ ቀለሰ፣ አጐበጠ (የእግር፣ የጐራዴ)።
ወለሰ: ዐፈነ፣ መልሶ መላልሶ ጣለ (የዝናም)። አበሰን እይ።
ወለሠ: ዐፈና ኾነ።
ወለስ: ዐፈነ (ዝናሙ)፣ ከፋ፣ ኣካፋ፣ ችፍችፍ አለ።
ወለሸ (ትግ): አጌጠ፣ ተቀማጠለ።
ወለሸ: ለመለመ፣ ተኛ፣ ተዘናፈለ፣ ተቈላዘመ።
ወለሸ: ጨፈረ፣ አረገረገ፣ አሸበሸበ።
ወለሼ: የወለሽ ዐይነት፡ ቅምጥል ዘንፋላ እመቤት።
ወለሽ: ውሃ የተኛበት ለም ዕርሻ፣ ፋልማ።
ወለሽ: የተኛ፣ የተቈላዘመ (ረዥም ጤፍና ሣር)።
ወለቀ: ተነቀለ፣ ፈለሰ፣ ወጣ፣ ተለየ።
ወለቀ: ደከመ፣ ሰለቸ።
ወለቀመ (ወለገመ፣ ወለገደ): ወልጋዳ ኾነ። ለቀመን እይ።
ወለቃ: ያገርና የወንዝ ስም፡ በደራ አጠገብ ያለ አገር።
ወለበ: ተሰረቀ፣ ተወሰደ።
ወለበ: ተሠራ፣ ተበጀ፣ ተመዘዘ (ወለባው)።
ወለበ: ተጠረጠረ፣ ባዶ ኾነ፡ ወጣ (ፍሬው ከቂንድ)፡ ሾለከ።
ወለባ (ዎች): የጌጥ ስም፡ እንደ እንዝርት ተበጅቶ በወይዛዝርና በመኳንንት የራስ ጠጕር ውስጥ የሚሻጥ። (ተረት) "ራስ ተላጭቶ ወለባ፣ ልባልባ ታጥቆ ዐዛባ። "
ወለባ (ዎች): የጌጥ ስም፡ እንደ እንዝርት ተበጅቶ በወይዛዝርና በመኳንንት የራስ ጠጕር ውስጥ የሚሻጥ። (ተረት) "ራስ ተላጭቶ ወለባ፣ ልባልባ ታጥቆ ዐዛባ። "
ወለብላባ: ለፍላፊ፣ ምላሰኛ።
ወለተ ሐና: የሐና ልጅ (እመቤታችን)።
ወለተ ማርያም: የማርያም ልጅ።
ወለተ ወልድ: የወልድ ልጅ።
ወለተ ጊዮርጊስ: የጊዮርጊስ ልጅ።
ወለተ ጻድቅ: የጻድቅ ልጅ።
ወለቱ: ሴት ልጁ፡ የስም ከፊል።
ወለቴ (ወለትየ): ልጄ፡ የኔ ልጅ። ከፊለ ስምም ይኾናል። ወለት እየተናበበ እንደ ወልድ የክርስትና ስም ሲኾን።
ወለት: ሴት ልጅ፡ ልጅት።
ወለነ: ተዘጋ፣ ተደፈነ፣ ደነቈረ።
ወለኔ: ያገር ስም።
ወለኔዎች: የወለኔ ተወላጆች።
ወለከፈ (ለከፈ): አጐለ፣ ስነከለ፣ አወከ (ከሥራ፣ ከመንገድ)።
ወለከፍ/ወልካፋ: ሰንካላ፣ ደንቃፋ።
ወለወለ (ወልወለ ለውለወ): ዕቃን፣ ቤትን፣ ምጣድን ጠረገ፣ አበሰ፣ ዐሠሠ፣ ዐደፈ፣ አጠራ፣ ሰነገለ፣ አጠዳ። (፪ነገ፡ ፳፩፡ ፲፫)። ኰላን እይ።
ወለወለ: ሰውን መላልሶ በጥፊ መታ፡ አቀለጠ፣ ጠፈጠፈ።
ወለወልዳ (ላቲ ይደሉ ክብር ወስብሐት፡ ወለወልዳ ሰጊድ ወአምልኮት): ለልጇም ማለት ነው። ያልተማሩ ሰዎች ግን "ወላዋይ" ብለው ይተረጕሙታል፡ ስድብ ያልኾነውን ስድብ ያደርጉታል። "አንዲት ሴት ባልንጀራዋን 'ሰኰሩ ማርያም ወለወልዳ ናትና ስለትሽን ለዠነቄ ማርያም ስጪ' አለቻት" ይላሉ፡ እንዲህም ማለቷ ካህናቱን ስትሰድብ ነው።
ወለየ (ዐረ): መረጠ፣ ለየ፡ ለሹመት፣ ለትንቢት፣ ለማንኛውም ቁም ነገር።
ወለደ (ወሊድ ወለደ): በዘር፣ በሩካቤ ግልገልን፣ ጥጃን፣ ውርንጭላን፣ ጫጩትን፣ ልጅን ከእንስት፣ ከሴት አወጣ፣ አገኘ፡ ያውራ፣ የኰርማ፣ ያለሴ፣ የሰው። ረባንና፣ ተካን እይ።
ወለደ ከበዶ: ወንድ ልጅ ለፈረስ፣ ሴት ልጅ ለበርኖስ አደረሰ።
ወለደ: ዘረዘረ፣ ዝርዝር ኾነ፡ አፈራ።
ወለደ: ያጠፋውን፣ የደበቀውን ነገር በግድ ሰጠ፣ አስረከበ።
ወለደ: ጠበቃ፣ ነገረ ፈጅ፣ ወከለ።
ወለደች: ተገላገለች።
ወለደኛ (ትግ): ዘመድ፣ ተወላጅ።
ወለዳ: ወሊድ፣ መውለድ።
ወለዳ: የእኸል ዝርዝር፣ ወርቋ።
ወለድ (ርዴ): የገንዘብ ትርፍ፡ ዐራጣ (ጥሬ)። "በወለድ ተበደረ" እንዲሉ። አተተን (ወረኘ)ን ተመልከት።
ወለድ አግድ: ዐራጣ ከልክል፡ መያዣ፣ ርስት፣ ቤት፣ ሥራ (የብድር ገንዘብ እንዳይወልድ የሚያደርግ)።
ወለድ: ወላጅ፣ ወላድ (እንደ "ልብ ወለድ" እንዲሉ) (ቅጽል)። ግልጥ ትርጓሜው የወለደው ያሠኛል።
ወለዶ: በጡት፣ በማር፣ በሞጋሳ፣ በክርስትና፣ በቆብ ልጅ አደረገ።
ወለዶ: አተረፈ፣ ዐረጠ።
ወለገ፡ ገፈፈ፡ ጭልጊ አወጣ።
ወለገ: መለገ፣ በቀስታ፣ እባብኛ ኼደ፡ ሾለከ።
ወለገመ (ለገመ): ጠመመ፡ ወልቃማ፣ ወጣ ገባ ኾነ (ተገብሮ)።
ወለገመ: አጠመመ (ገቢር)።
ወለገደ (ለገደ): ወለገመ፣ አጐበጠ (ገቢር)።
ወለገደ: ጐሰጠ (ተገብሮ)። ጠመመን እይ።
ወለገድ/ ወልጋዳ (ዶች): ወረኃ፣ ደጋን፣ እግር፡ ወልጋማ።
ወለጋ: ያገር ስም፡ ከ፲፬ቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ግዛቶች አንዱ። ወለጋ ያቅኒው ስም ነው።
ወለጎች: የወለጋ ሰዎች፡ ወይም ተወላጆች።
ወለጠ: ለወጠ (ግአዝ)።
ወለፈ (ለፈየ): ዐነከሰ፣ ዐሸድ፣ ዐሸድ አለ።
ወለፈሰ: ቀባጠረ፣ ነገር አበዛ፡ ምናም ንቴ ኾነ። ወሸለከንና፣ ወሰለተን እይ።
ወለፈተ: ወለፈሰ።
ወለፈጠ: ወለፈተ። ሞለፈጠን እይ፡ የዚህ ዘር ነው።
ወለፌ (ለፌ): ወዲህ ወዲያ። "ባፌ በወለፌ" እንዲሉ።
ወለፌንዳ: ዝኒ ከማሁ ለወለፈንድ። (ግጥም) "ነገርሽ ኹሉ የወለፌንዳ፡ ነይ ወዲህ ስልሽ አንቺ ወዲያንዲያ። "
ወለፌንድ (ዶች): የሰው ጠማማ፡ "እንብላ" ሲሉት "እንራ" የሚል።
ወሊስ: ዐፈና፣ ዕኝኝ ብላ።
ወሊባ: ሰራቂ፣ ሌባ። "አባትሽ ወሊባ እናትሽ ወሊባ" እንዲሉ።
ወሊት: የደረቀ ሆድ፡ ወይም ሌላ ነገር።
ወሊድ: መውለድ። "እከሊት በወሊድ ሞተች" እንዲሉ።
ወላ ሸግላ አለ: አፍ ሌላ ልብ ሌላ ኾነ፡ የማያደርገውን አደርጋለኹ አለ፡ ወላወለ፡ ከንቱ ተስፋ ሰጠ።
ወላ ሸግላ: ወላ አሉታ፡ ሸግላ ድላ።
ወላለቀ: የወለቀ ድርብ፡ መላልሶ ወለቀ፣ ወጣጣ።
ወላለደ: መላልሶ ወለደ።
ወላላ: ገር፣ ቅን፣ ልበ ጥሩ፡ ዐዛኝ፣ ርኅሩኅ።
ወላላዋ ርግብ: ሆዷ እመቤታችን ድንግል ማርያም።
ወላመጠ: ሳይሠራ፣ ሳያደርግ፣ ሳይጠመድ ቀረ፡ ዘወርዋራ ኾነ። የወለመጠና የወላመጠ ልዩነት ስፍራን አለመተውና መተው ነው።
ወላማጭ: የሚወላምጥ፡ እዚህ ሲሉት እዚያ፣ እዚያ ሲሉት እዚህ የሚገኝ።
ወላምኛ: የወላሞ ቋንቋ፣ የወላሞ አፍ።
ወላሞ: ወላምኛ
ወላሞ: የነገድና ያገር ስም።
ወላሞዎች: የወላሞ ተወላጆች።
ወላሴ: ላዩ መቋሚያ፣ መካከሉ መንታ፣ ታቹ አንድ የኾነ፡ ፩ እግሩ ለተቈረጠ ሰው የብብቱ ድጋፍ። በፈረንጅኛ ቤኪይ ይባላል። መንታነት የሌለውም አለ።
ወላሴ: የወላስ ወገን፡ ቋንዣውን ያጠፈ፣ የኰረተመ፣ እግረ ቀላሳ። "ያንካሴ የወላሴ" እንዲሉ ልጆች።
ወላስ: የሚወልስ፡ አጕባጭ።
ወላስማ (ሞች): የባላባት ስም፡ በይፋትና ባንኮበር አውራጃ በብዙ ስፍራ ይገኛል። የመዠመሪያው ባላባት ፈሊጥ (አወል እስማዕ) ስለ ነበረ በዘመን ብዛት ወላስማ ተባለ ይላሉ።
ወላሸግላ: መወላወል፣ ወላ።
ወላቂ: የሚወልቅ፣ የሚወጣ።
ወላቃ/ውላቂ: ውልቅ፡ የወለቀ፣ የተነቀለ፣ የወጣ፡ ንቅል። "ጥርሰ ወላቃ" እንዲሉ።
ወላበደ (ለበደ): ዘላበደ፣ ወላወለ።
ወላቢ: የሚወልብ፡ ሾላኪ።
ወላቢላ: ወላባ፣ ቀበጥ።
ወላባ (ቦች): ዝኒ ከማሁ፡ ሾላካ።
ወላባጅ (ጆች): የወላበደ፣ የሚወላብድ፡ ዘላባጅ፡ ወላዋይ፣ ፪ ልብ።
ወላባጅነት: ዘላባጅነት፣ ወላዋይነት።
ወላንሳ: ቀይ ከፈይ ወይም አረንጓዴ ባለወርቅ ዘርፍ በዙፋንና በመከዳ ላይ የሚዘረጋ፣ የሚነጠፍ።
ወላንሳ: የሴት ስም።
ወላወለ: ዘላበደ፣ ተጠራጠረ፣ ፪ ልብ ኾነ፡ ገላበጠ።
ወላወለ: ጠራረገ፣ አባበሰ፣ አጠዳዳ።
ወላዋይ (ዮች): የወላወለ፣ የሚወላውል፡ ዘላባጅ፣ ባንድ ነገር ባንድ ወገን የማይጠመድ፡ ተጠራጣሪ፣ ገላባጭ፡ በ፪ ቢላዋ የሚበላ።
ወላዋይነት: ዘላባጅነት፣ ተጠራጣሪነት።
ወላይ: የወለለ፣ የሚወልል፣ የሚከፍት፡ ከፋች።
ወላዲ: የአብ አካል የግብር ስም፡ ትርጓሜው ወላጅ።
ወላዲተ አምላክ: አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደች፣ ድንግል ማርያም (የአምላክ ወላጅ)።
ወላዲት: ወላድ፡ እናት (ግእዝ)።
ወላድ (ዶች): የወለደች፣ የምትወልድ፡ እናት፣ ባለብዙ ልጅ፣ ምክነት የሌለባት። "ወላድ በድባብ ትኺድ" እንዲሉ። ባሕርን ተመልከት።
ወላጅ (ጆች): የወለደ፣ የሚወልድ፡ አባት። (፩ዮሐ፡ ፭፡ ፩)
ወላጅነት: ወላድነት፡ ወላጅ፣ ወላድ መኾን፡ አባትነት፣ እናትነት፣ ልጅን አስገኝነት።
ወላጆች: አባት፣ እናት።
ወላጋ: የሚወልግ፡ ሾላካ።
ወላፈን: ወላፈኖች፡ የነበልባል ግርፊያ የሚያቃጥል፣ የሚልጥ።
ወላፈን: የእሳት ላንቃ።
ወላፍ (ላእፍ): በመንጠቆ ጫፍ አድርገው ዓሣ የሚይዙበት ትል።
ወላፎ (ዎች): ዐሻዳ፣ ዐሾ፣ ገመዳ። ሲኼድ እግሩን የሚገምድ ሸፋፋ።
ወሌ: የሰው ስም፡ ወለየ።
ወሌ: የወልይ ወገን፡ የኔ ወልይ።
ወል ማኅበር: ወለለ።
ወል: ብዙ ሕዝብ ማኅበር፣ በወል ላይ ያለ የተቀመጠ። ወል የወለልና የወልወል ከፊል ነው።
ወልማጣ (ጦች): የሚወለምጥ።
ወልሽ/ውልሻ: ጭፈራ፣ ሽብሸባ፣ ማረግረግ፣ እስክስታ።
ወልቃማ: ወልጋማ።
ወልቃዪቴ: የወልቃዪት ተወላጅ። "ወልቃዪቴ ብሩ" እንዲሉ።
ወልቃዪት: ያገር ስም፡ የአማራ አገር።
ወልቅ: ፍጹም ጭቃ፣ ያዛባ፣ ማጥ፣ አረንቋ።
ወልባት: ጭራሽ ጥቍር በሬ፡ ወይም ላም።
ወልባዳ: ዘልባዳ፣ ወላባጅ።
ወልካፊ: የወለከፈ፣ የሚወለክፍ፡ አጓይ፣ ሰንካይ።
ወልወል (ትግ ሐባ): ነፋስ።
ወልወል (ጽጐጕ): መኻል ሜዳ፡ አንዳች የሌለበት ስፍራ። (፩ነገ፡ ፮፡ ፴፪)። ወለልን ተመልከት።
ወልወል: በውጋዴ አውራጃ ያለ ቀበሌ።
ወልዋይ (ዮች): የወለወለ፣ የሚወለውል፡ ዐሣሽ፣ ጠራጊ፣ ሰንጋይ።
ወልይ (ዮች): የተመረጠ፣ ምርጥ፣ ልዩ፡ ነቢይ፣ ጠንቋይ፣ ቃልቻ።
ወልደ ማርያም: የማርያም ልጅ (ጌታችን)።
ወልደ ሰማዕት: የሰማዕት ልጅ። ያልተማሩ ሰዎች ግን ወልደ ሰማያት ይሉታል።
ወልደ ሥላሴ: የሥላሴ ልጅ።
ወልደ አብ: የአብ ልጅ።
ወልደ ጊዮርጊስ: የጊዮርጊስ ልጅ።
ወልደ ጻድቅ: የጻድቅ ልጅ።
ወልደኽ አጕር: ወልዶ የሚያጕር፡ ሞኝ፣ ቂል፣ ደንቈሮ (ወልደ ሀጕል)፣ የጥፋት ልጅ።
ወልደየስ: የሰው ስም፡ በግእዝ ወልደ ኢየሱስ ይባላል።
ወልደየስ: የፈረንጅ ፈትል፡ ወፍራም ማግ ባፄ ምኒልክ ጊዜ መዠመሪያ ወልደየስ የሚባል ነጋዴ ይሼጠው የነበረ።
ወልደያ: በየጁ ያለ ያገር፣ የከተማ ስም።
ወልዱ: ልጁ፡ የርሱ ልጅ (ግእዝ)።
ወልዴ (ወልድየ): ልጄ፡ የኔ ልጅ። ከፊለ ስምም ይኾናል። ወልድ ዘርፍ ይዞ ከታቦት እየተናበበ የክርስትና ስም ኹኖ ይነገራል።
ወልድ ቅብ: አዛዥ ዘድንግል ባፄ ሱስንዮስ ዘመን ያወጣው የሃይማኖት ባህል።
ወልድ ዋሕድ: ቅድመ ዓለም ከአብ አለናት፣ ድኅረ ዓለም ከድንግል ማርያም አላባት የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ልጅ ነው፡ እንደ ንስጥሮስ ባህል አካሉ ገጹ ህላዌው ኹለት አይዶለም፡ አንድ ነው እንጂ።
ወልድ ዋሕድ: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በባሕርይ ልደቱ መሳይ ተከታይ የለውም፡ ላባቱም ለናቱም አንድ ነው።
ወልድ: ከቅድስት ሥላሴ ፪ኛው አካል ቃል፡ ቅድመ ዓለም ከአብ አለናት ስለ ተወለደ ወልድ ተባለ።
ወልድ: ወንድ ልጅ (ግእዝ)። "እግዚሐር ያጥናሽ አልናት ወይ፡ ወልዳልሞታትም ወይ። " (አዝማሪ)
ወልድና: ተወላጅነት፡ መንፈሳዊ ልጅነት። ሀብተ ወልድና፣ ስመ ክርስትና እንዲሉ።
ወልዶ ተክሌ: የተክለ ሃይማኖት ልጅ። ተክሌ ከፊል ነው።
ወልዶ አይስም ዘርቶ አይቅም: ሾተላይ፡ ዕድለ ቢስ።
ወልዶ: ቦዝ። "ሰባት ወልዶ ዕቃ ቤትነት" እንዲሉ።
ወልጋማ: ጠማማ፣ ወልቃማ።
ወልፋ: ባሸንጌ ውስጥ ያለ ቀበሌ።
ወልፋሳ: የማይረባ፡ ቀባጣሪ፣ ወስላታ።
ወልፋታ: ወልፋሳ። ሰና ተ ባረብኛ ይወራረሳሉ።
ወሎ: በመንዝ አጠገብ ያለ አገር። ወሎ አቅኒው ነው። አንጎትን ይመልከቱ።
ወሎዎች: የወሎ ሰዎች።
ወሎዬ: የወሎ ሰው፡ የወሎ ተወላጅ።
ወመቴ፡ የነገድ ስም፡ በከንባታ ውስጥ ያለ ሕዝብ።
ወማይ (ዮች): የወፍ ስም፡ ጥቍር አረንጓዴ ሐር የሚመስል በዠርባው ላይ ደርዝ ዐይነት ጌጥ ያለው ወፍ። (ዘፈን) "ማሽላዬ ወማይ በላሽ ወዬ። "
ወማይ: ውሃም (ግእዝ)።
ወምበርቲ: የሐኔ ዐይነት።
ወሞ: የዠማ ስም፡ በዳር አገር ያለ ታላቅ ዥረት ከጅማ ተራራ ሥር የሚነሣ። (ግጥም) "ባሪያ እገዛ ብዬ ባሪያ ኾንኩልሽ፡ ኬላውም ተዘጋ፡ ወሞም ሞላልሽ። "
ወሰለተ፡ ወሳለተ፡ (ሰለተ)፡ ሰነፈ፡ ዋሸ፡ ዐበለ፡ ቀጠፈ፡ ባለገ፡ ማገጠ፡
መጥፎ ሥራ ሠራ (ምሳ ፲፱: ፩)።
ወሰላ ወሰልሰላ፡ የልጆች ጭፈራ አዝማች። ወሰላ ወሰልሰላ ዐንገቱ በምን ሰላ ነጭ፡ ጤፍ እየበላ እንዲሉ አባትና እናት። ወዘላን እይ፡ ፪ኛውን ሰላ ተመልከት አንቀጹ ርሱ ነው ያ አገባ።
ወሰሰ፡ ቀጠነ፡ መነመነ፡ ቀለለ።
ወሰስ፡ ነፋስ የመታው ቀጪን፡ ቀላል የስንዴና የገብስ ፍሬ። እንሻፎን ተመልከት።
ወሰራ፡ (ሰራን)፡ በዠርባው ላይ ቀይ ያለበት ነጭ ዶሮ። ጥቍር ኹኖ ቀይ ቢፈነጠቅበት፡ የጥቍር ገብስማ፡ ቀይ ኹኖ ነጭ ቢጥልበት፡ የቀይ ገብስማ ይባላል።
ወሠራ፡ ቀይና ጥቍር ዶሮ፡ ወሰራ።
ወሰበ፡ (ወሲብ ወሰበ)፡ ወተበ፡ ተበተበ፡ ጠለፈ፡ ጠመረ።
ወሰነ፡ (ወስኖ ወሰነ)፡ ደነገገ፡ ገደበ፡ መደበ፡ ወሰን አበጀ፡ አደረገ፡ ለካ፡ መጠነ፡ ከለለ፡ ደካ፡
ደነበረ፡ ደነባ፡ ዐገገ፡ ሥራት ሠራ።
ወሰነተኛ፡ (ኞች)፡ የወሰን፡ ባለወሰን፡ ወሰንን የሚጋራ፡ ድንበረተኛ።
ወሰነኛ፡ (ኞች)፡ ድንበረኛ።
ወሰኔ፡ (ወሰንየ)፡ የኔ ወሰን ማለት ነው።
ወሰኔ፡ የወንድ ስም፡ ለሴትም ይኾናል። አቶ ወሰኔ፡ አመት ወሰኔ እንዲሉ።
ወሰን፡ (ኖች)፡ ገደብ፡ ዳር፡ ድንበር፡ ትክል ደንጊያ፡ ዛፍ፡ ዕዳሪ፡ መሬት፡ ተራራ፡ ወንዝ፡
ባሕር። ደንብ፡ ሕግ፡
ትእዛዝ።
ወሰን ሰገድ፡ ከሺዋ ባላባቶች አንዱ፡ ባ፲፰፻ ዓ.ም የነበረ። ወሰን የሰገደለት ማለት ነው።
ወሰን የለኸ፡ የለሽ፡ የወንድና የሴት መጠሪያ ስም።
ወሰን ገፊ፡ ወሰንን የሚገፋ፡ ክፉ ሰው፡ ወሰን አፍራሽ፡ ወሰን ወራሽ፡ የቦታ፡ የመሬት ሌባ።
ወሰን ገፊ፡ የዛር ስም፡ ወሰራ ቀይ የጣለበት ጥሩ ነጭ ዶሮ የሚገብሩለት ዛር፡ የነፍስ ሌባ። ወሰን የተባለ ኢታምልክ ነው።
ወሰን: ወሰተኛ
ወሰከ፡ (ወስኮ ወሰከ)፡ ጨመረ፡ ጫነ (ገቢር)።
ወሰከ፡ አደፈ፡ ቈሸሸ (ተገብሮ)።
ወሰካ፡ ቃሬዛ፡ ቀላጥም።
ወሰካም፡ እድፋም፡ ባለእድፍ፡ ያደፈ፡ የቈሸሸ።
ወሰክ፡ እድፍ፡ ቍሻሻ።
ወሰወሰ፡ (ወሰሰ)፡ ቶረበ፡ በቀላል ሰፋ፡ ሸደሸደ፡ ሸለለ።
ወሰወሰ፡ እጅ እግሩን ወዘወዘ፡ እንፈራገጠ፡ ዋኘ፡ በውሃ ውስጥ ኼደ፡ ሰለከ።
ወሰወሰ: ሸከሸከ፣ ሸለለ።
ወሰው፡ ንኡስ አገባብ፡ የደስታ ቃል፡ ወ'ዎ ሰው በቁሙ፡ ዕሠይ፡ በጎ፡ ጥሩ፡ ማለፊያ፡ ደግ፡ መልካም።
ወሰው ወሰው፡ ዕሠይ ዕሠይ፡ ደግ ደግ፡ ይኹን ይኹን፡ ወሰው ወሰው በምን አማረ ጥላሽ።
ወሰደ፡ (ወሲድ ወሰደ)፡ (ዘፍ ፰: ፱)፡ ይዞ ኼደ፡ አጋዘ፡ ነዳ፡ ቀረበ፡ ገፋ፡ አገላበጠ፡
አንከባለለ፡ ሳበ፡ ጐተተ፡ ቀማ፡ ነጠቀ፡ አጠፋ፡ ከብትን፡ ገንዘብን፡ ሰውን፡ ማንኛውንም ነገር። (እንቅልፍ ወሰደው)፡ አስተኛው።
ወሰጠ፡ (ወሲጥ ወሰጠ)፡ ወደ ውስጥ አገባ፡ ወነገ።
ወሲል፡ በይፋት አውራጃ ያለ አገር።
ወሲጥ፡ አማጭ፡ አግባቢ።
ወሲፍ፡ (ዐረ፡ ወጺፍ)፡ ኰረዳ፡ ዐፍለኛ ሴት፡ ልጅ እግር።
ወሣ፡ (ወሥአ)፡ አወሣ፡ (አውሥአ)፡ አስታወሰ፡ መለሰ፡ መልስ ሰጠ።
ወሳሰደ፡ መላልሶ ወሰደ።
ወሳሳ፡ (ኦሮ)፡ ቀላጥም፡ ቃሬዛ።
ወሳብሪ፡ የግመል ጊደር፡ ባዝራ።
ወሳኝ፡ (ኞች)፡ የወሰነ፡ የሚወስን፡ ደንጋጊ፡ ገዳቢ።
ወሳዳ፡ ቀላል ሰው፡ የጠባይ፡ የግብር።
ወሳጅ፡ (ጆች)፡ የወሰደ፡ የሚወስድ፡ አንከባላይ፡ ውሃ።
ወሳፍቻ፡ የኮርቻ፣ የመጫኛ፣ የጅራፍ፣ የመጫሚያ፣ በያይነቱ የጠፍር ዕቃ ሁሉ መስፊያ፣ ወፈር ያለ አፈ ምሣር።
ወስለት፡ ወስላታ፡ (ቶች)፡ የወሰለተ፡ የሚወሳልት፡ ማጋጣ፡ ምናምንቴ፡ የማይረባ (ምሳ ፲፩: ፫፡ ፮፡ ፳፪: ፲፪፡ ፳፫: ፳፰)።
ወስላታነት፡ ወስላታ መኾን።
ወስል፡ ሦስተኛ የቀባርዋ ምት።
ወስከምት፡ (ቶች)፡ ሰከመ)፡ የውሻ ቡችላ ማሰሪያ፡ ዐጪር ማነቆ፡ በ፪ ወገን ክርክር ያለው ዕንጨት።
ወስከምት፡ መንቈር፡ የእግር ግንድ።
ወስከምት አፍ፡ ነገረኛ ሰው።
ወስከንባይ (ወዝከንባይ): የሌማት ወይም የመሶብ መክደኛ ስፌት፡ የድስት እፊያ።
ወስከንባይ፡ የሌማት መክደኛ ከነበለ።
ወስኮ፡ (ኮች)፡ ሠረገላ፡ የመንኰራኵር እንዝርት (፩ነገ ፯: ፴፡ ፴፪፡ ፴፫)።
ወስኮ፡ ቀንበር፡ በማነቆ መካከል ያለ የጫንቃ ማያ።
ወስዋሳ፡ አሳባቂ፡ ወላዋይ፡ ወረተኛ፡ ገልባጣ፡ ባንድ አይረጋ።
ወስዋስነት፡ ወስዋሳ መኾን።
ወስዋሽ፡ (ሾች)፡ የወሰወሰ፡ የሚወስውስ፡ ሸድሻጅ፡ ዋነተኛ።
ወስፈንጠር (ሮች): የሚያስፈነጥር፡ ወደ ላይ የሚወረውር፣ የሚሰቅል፣ የሚያንጠለጥል፡ የወፍ፣ የቆቅ፣ የአይጥ ወጥመድ፡ ጐባባ እንጨት። በግእዝ ፀንፈርት ይባላል፡ ሠሥና፣ ድኵላ፣ ምዳቋም ይይዛል።
ወስፈንጠር፡ ወጥመድ፡ ፈነጠረ።
ወስፈንጠር የሕዝብ፡ ወፈንጠር የካህናት ዐማርኛ ነው።
ወስፈንጠር: በቀስት የሚወረወር ቀጥተኛ እንወት፡ ወይም ብረት በጫፉ ፍላጻ ያለበት።
ወስፋቱ፡ ሞተ፡ አይርበውም፣ እኽል አልቀበልም አለ።
ወስፋት፡ (ቶች)፡ የሆድ ውስጥ ትል "ሲበዛ እንደ ወስፌ ሆድን የሚወጋ (የልጆች ግጥም)፡ ከዚህ እስከ ይፋት ይወጥርኸ ወስፋት።"
ወስፋት፡ በሆድ ውስጥ ያለ የምግብ መኪና፣ መከማቻ። ጨጓራን ተመልከት።
ወስፋት፡ ወስፋታም፡ ወስፋት ከሆዱ የሚወጣ፣ ባለብዙ ወስፋት።
ወስፋት፡ የሆድ ትል፡ ሰፋ (ሰፈየ)።
ወስፌ፡ (ዎች)፡ ግእዝ፡ መስፌ። "የስፌት ዕቃ በያይነቱና የሰገጥ መስፊያ፣ ባለእጀታ ቀጪን ብረት፣ ጝፈ ሹል። (የዣርት ወስፌ)፡ ወስፌ መሳይ የዣርት ጠጕር። (የቍራ ወስፌ)፡ ታናሽ ቅጠል።"
ወስፌ፡ ወስፌ፡ አንድ ጣት በስኵቻ ጊዜ መቀስን የሚረታ።
ወሶ፡ ዝኒ ከማሁ፡ ጐሽ። ላይሉኝ ወሶ ደርሼ ነበር እረጋ ለቅሶ እንዳለ ጠይብ።
ወረ ሸኅ፡ (ኆች)፡ የሸኅ ዑመር ተወላጆች፡ በየጁ የሚገኙ ነገዶች።
ወረ ግቡ፡ ድርስ ርጉዝ ሴት ካረገዘች ፰፡ ወሯ ዐልቆ ፱ኛ ወሯ የገባ የባተ።
ወረኃ፡ (ወርኃዊ)፡ ጨረቃ እግር፡ እግሮቹ ለጋ ጨረቃ የሚመስሉ፡ ሰው፡ አህያ። የቡዳ ድኻ የፈረንጅ ወረኃ የለውም እንዲሉ።
ወረኃዎች፡ (ወርኃውያን)፡ እግረ ወልጋዶች።
ወረሞ፡ (መቍዐል)፡ የሠባ፡ የወፈረ፡ የወረሞ በግ፡ ሙክት፡ ዳግመኛም ሥብ፡ ጮማ ተብሎ ይተረጐማል። አውላዶን ተመልከት።
ወረሞ፡ (ኦሮ፡ ኦረሞ)፡ የኦሮ ነገድ፡ ወገን፡ ጐሣ።
ወረሰ፡ (ወሪስ ወረሰ)፡ ያባት፡ የናቱን፡ የዘመዱን ርስትና ገንዘብ በሚገባ፡ በውድ ተቀበለ፡ ተረከበ፡ የራሱ አደረገ፡ ባባቱ ንብረት ተተካ። (ተረት)፡ ያለፊቱ አይቈርስ፡ ያለቤቱ አይወርስ።
ወረሰ፡ የባዕድን ይዘታ በግድ ያለ ውድ ወረረ፡ ከበበ፡ ቀማ፡ ነጠቀ፡ ዘረፈ፡ ወሰደ። (ተረት)፡ የፈሩት ይደርሳል፡ የጠሉት ይወርሳል።
ወረሰ፡ ያዘ፡ አለበሰ፡ አጠለቀ፡ ዋጠ። ድኻውን ቅማል ወረሰው፡ ዕከክ ወረሰው፡ ዝሪቱን ዐረም ወረሰው እንዲሉ።
ወረሳ፡ መውረስ፡ ዘረፋ።
ወረረ፡ ለቀመ፡ ሰበሰበ፡ አከበ፡ አከማቸ።
ወረረ፡ ከበበ፡ ዘረፈ፡ በዘበዘ፡ በረበረ፡ ማረከ። (ተረት)፡ ካዉር ምከር፡ ከረዥም ውረር። ወረሰን እይ።
ወረረን ተመልከት።
ወረራ፡ (ወለላ)፡ ጥራት፡ ጥሩነት፡ ጥዳት፡ ወዝ፡ ደም፡ ግባት። ይህ ሰው የፊቱ ወረራ ያምራል።
ወረራ፡ ለቀማ፡ ስብሰባ፡ እከባ። ኵበት ወረራ እንዲሉ።
ወረራ፡ እመም፡ ገዝም፡ አፍታ፡ ቃዳ፡ ተለላ።
ወረራ፡ ከበባ፡ ዘረፋ፡ ብዝበዛ፡ ምርኮ።
ወረር፡ አንድ ምዕራፍ (ኪሎ ሜትር) (፪ነገ ፭: ፲፱)።
ወረርሽኝ፡ የጕንፋን ወይም የወባ በሽታ፡ አንዳንድ ዘመን አየር ሲለወጥ ክረምት ውጭ እየተነሣ አገርን የሚወር፡ ኅዳር ሲታጠን የሚቀር። ራሔሎን ተመልከት።
ወረቀ፡ ሣሣ፡ ረቀቀ፡ ቅጠል መሰለ።
ወረቀ፡ ቦረቀ፡ ዘለለ፡ ጨፈረ። ወረቀ የመምህራን፡ ቦረቀ የሕዝብ ነው።
ወረቀ፡ ተፋ፡ እንትፍ አለ (ግእዝ)። መረቅን፡ ምራቅን እይ፡ የዚህ ዘሮች ናቸው።
ወረቀ፡ ወራ፡ ኣማረ፡ ታደሰ፡ ሸበረቀ፡ ወርቅ መሰለ፡ ወየበ፡ ሰጪጪ።
ወረቀት፡ (ቶች)፡ (ረቅ)፡ የብራና ዐይነት፡ ደብዳቤ፡ መጻፊያ፡ መጻፍ፡ ማተሚያ፡ ከጥጥ፡
ከዕፀዋት እንደ ሙዝ ቅጠል በሥሡ ፈረንጆች የሠሩት፡ በብራና ፈንታ የተተካ ሉሕ። የወረቀትን ሥራ የዠመሩ ሺኖች ናቸው፡ ይኸውም ከክርስቶስ ልደት በፊት ፪፻ ዓመት ነው ይላሉ።
ወረቀት፡ መላክት፡ ደብዳቤ።
ወረቀት ጣፊ፡ በወረቀት ጕዳይ የሚጥፍ፡ ደብዳቤ ጣፊ።
ወረበ፡ ሣርን፡ እኸልን፡ ዐልፎ ዐልፎ በጨደ፡ ጐረፍ ጐረፍ አደረገ፡ የደረሰውን፡ የበረቋውን፡ የደረቀውን።
ወረበ፡ ውርባ ጣለ።
ወረበ፡ ዜማን እንደ መሰለው፡ አንዱንም አንዱንም ጠቅሶ ቀነቀነ፡ አዜመ። ዜማውም፡ ንኡስ መረግድ፡ ዐቢይ መረግድ፡ ድርብ መረግድ፡ ቸብቸቦ ይባላል። ሦስቱ በከበሮና በጸናጽል፡ አራተኛው ግን ጭብጨባ ይጨመርበታል። ለዘበ ብለኸ ለዘብን እይ።
ወረበ፡ የሕፃንን ጠጕር እየዘለለ ላጩ።
ወረቤ፡ መልኳ ብጫ የኾነች ታናሽ ወፍ።
ወረቤ፡ የኔ ወረብ።
ወረብ፡ (ቦች)፡ መንፈሳዊ የካህን ዜማ፡ በምላት ሳይኾን በከፊል የሚደረግ።
ወረብ፡ ያገር ስም፡ በባሌ አውራጃ የሚገኝ ያቡነ አኖሬዎስ ገዳም፡ ዛሬ ግን እስላሞች ስለ ያዙት ኑር ሑሴን ይባላል። ዘብሔረ ወረብ እንዲል ገድለ አኖሬዎስ፡ ተክለ ሃይማኖት።
ወረቦ፡ (ኦሮሚኛ)፡ ድኵላ (የዱር ፍየል)።
ወረቦ ዋሻ፡ (የወረቦ ዋሻ)፡ የቀበሌ ስም፡ በደብረ ሊባኖስ አፋፍ ያለ ስፍራ። ቀድሞ ዘመን በዋሻው ወረቦ ያድርበት ስለ ነበረ ወረቦ ዋሻ ተባለ።
ወረተ፡ ወረሰ፡ ገንዘብ አገኘ፡ ጊዜያዊ ወዳጅ ያዘ። ወረሰና ወረተ አንድ ዘር ናቸው።
ወረተኛ፡ (ኞች)፡ ወራተኛ፡ ገልባጣ፡ ተለዋጭ፡ ተገልባጭ፡ ዕሥሥት ዐይነት ሰው፡ ዛሬ ካንዱ ነገ ከሌላው የሚገኝ፡ ባንድ አይረጋ፡ ወላዋይ፡ ፍቅሩ እንደ ገንዘብ የሚዞር፡ የኅዳር ጀንበር።
ወረተኛነት፡ ወረተኛ መኾን።
ወረቱ ዐለቀ፡ ገንዘቡ፡ ንግዱ፡ ፍቅሩ፡ ዐፍላው ተጨረሰ፡ ተፈጸመ። (በወረት በወረት)፡ በወራት በወራት፡ አንዳንድ ጊዜ፡ ዐልፎ ዐልፎ። (ግጥም)፡ በወረት በወረት ይበላል ድንች፡ እንዴት ከርማችኋል ዐዲስ አበቦች።
ወረታ መለሰ፡ ውለታን፡ ምስጋናን ከፈለ፡ እንዳደረጉለት አደረገ።
ወረታ ቢስ፡ ምስጋና ቢስ፡ ውለታ የማይመልስ፡ በልቶ ካድ።
ወረታ፡ ወሮታ፡ ውለታ፡ የገንዘብ፡ የማንኛውም ነገር ስጦታ፡ አድራጎት፡ ለደግ አድራጊ ወይም ለሌላ የሚደረግ ጥቅም፡ መልካም ሥራ፡ ምስጋና የሚያሰጥ (፪ዜና ፳: ፲፩)። ውለታ ቀንን፡ ወረታ ወርን ያያል።
ወረታ፡ ወሮታ፡ የሰው ስም፡ ምስጋን፡ ምስጋና እንደ ማለት ነው።
ወረት፡ የጊዜ ገንዘብ፡ የንግድ ዕቃ፡ ሸቀጥ (ነሐ ፲፫: ፳)። (ተረት)፡ ወረቱን የተቀማ ነጋዴ፡ ዋግ የመታው ስንዴ።
ወረት፡ የጊዜ ፍቅር።
ወረንጦ፡ (ዎች)፡ የሾኸ ማውጫ፡ ኹለት ብረት፡ ባላገር በወገቡ የሚያንጠለጥለው አንዱ ሹል መዘንጠያ፡ ኹለተኛው ጕጠት መቈንጠጫ የኾነ፡ ወይም መንቀያና መዘንጠያ በግራና በቀኝ ያለው አንድ ብረት፡ ቀረባ።
ወረኘ)፡ ተወራኘ (ተዐዝረ)፣ ተበተነ፣ ተሠራጨ፣ ተሰማራ፣ ተላለፈ፣ ተጋጠመ፣ ተዛጋ።
ወረኛ፡ ዝኒ ከማሁ።
ወረከ፡ አበረከ፡ አንበረከከ።
ወረወረ፡ (ወረወ)፡ አሽቀነጠረ፡ እጓነ፡ ጣለ። ሺሕ በመከረ አንድ በወረወረ። የያዙትን ከወረወሩ ፈሪም አይባሉ።
ወረወረ፡ ለቀቀ፡ ነደፈ፡ የፍላጻ፡ የጦር (፩ሳሙ ፲፰: ፲፩)።
ወረወረ፡ ሸጐረ፡ ቀረቀረ፡ ቈለፈ።
ወረወረ፡ በትንሽ ዋጋ ሼጠ።
ወረወረ፡ ዐይኑን አሻግሮ አየ።
ወረወረ፡ አገባ፡ አጠለቀ፡ አስታረበ፡ ጀንበርን።
ወረወረ፡ አጠጣ፡ ማግን ለድር።
ወረወረ: ቀረቀረ፣ ዘጋ፣ ደነቀረ።
ወረወረ: አንሻለለ፣ ከመ ቅጽበት አሳለፈ።
ወረዘት፡ ርጥበት ያለው፡ ትንፋገን።
ወረዛ፡ (ወሪዝ ወረዘ)፡ እዠ ራሰ፡ ረጠበ፡ የሸክላ፡ የመሬት፡ የቍስል።
ወረደ፡ (ወሪድ ወረደ)፡ ከላይ ወደ ታች መጣ፡ ዝቅ አለ፡ ሮጠ፡ ተንደረደረ። ከሰማየ ሰማያት ወረደ፡ ከድንግል ማርያም ተወለደ። (ከፈረስ ወረደ)፡ ዱብ አለ። (ባንገት ወረደ)፡ እስክስ አለ። (ዛሬ ዳኛው በእከሌ ላይ ወረደበት)፡ ጮኸበት፡ እጅግ ተቈጣው። ትከሻን አስተውል።
ወረደ፡ ወደ ውሃ ኼደ፡ ተቈለቈለ፡ ተዘቀዘቀ።
ወረደ፡ ጐናም ኾነ።
ወረደ፡ ጐደለ፡ ተቀነሰ።
ወረደ፡ ጨነገፈ፡ ተጠናወተ።
ወረደ፡ ፈሰሰ፡ ዘነመ፡ ተንዠቀዠቀ፡ ተንዶለዶለ።
ወረዳ፡ (ዎች)፡ ዝቅታ፡ ታች፡ ቍልቍል።
ወረዳ፡ ካውራጃ በታች ያለ ምክትል ግዛት፡ የብዙ ቀበሌ ዳኝነት ቤት፡ የምስለኔ መኖሪያ።
ወረዳ ወረደ፡ ከበታቹ ተጣላ፡ አለማዕርጉ ተገኘ።
ወረዳ ገዢ፡ የሻለቃ ወይም የመንግሥት እንደራሴ።
ወረዳ ፈጪ፡ ባንድ ጊዜ አደቀቀ፡ ሳይሰልቅ ቀረ።
ወረዴ፡ ዝኒ ከማሁ ለወረደ። እባብን እይ።
ወረድ፡ (ወሪድ)፡ ዝቅ መውረድ።
ወረድ አለ፡ ዝቅ አለ፡ ወረደ።
ወረገ፡ አንዳች አልባ ኾነ።
ወረገኑ፡ (ወረ ገኑ)፡ በገኑ ያሉ ቤተሰቦች፡ ወይም ቤቶች። የመንግሥት የዕርድ ከብት የሚቀለብባቸው። ወረ ወራ ሰዎች፡ ወሪ የዚህ ቤቶች ባለቤቶች፡ ፃኑ፡ በቡልጋ በኩል ያለ አገር። የኀኑ ትርጓሜ ከዳተኛ ማለት ነው፡ አሥብቶ ዐራጅነቱን ያሳያል። የወረገኑ ሹም በቀድሞ ዘመን ጸሓፌ ላሕም ይባል ነበረ። ወረገኑ የተባለ በንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ዘመን ሳይኾን አይቀርም፡ ይህም ጋልኛ ነው።
ወረጋ፡ ባዶ እጅ፡ ሌጣ፡ ያልተጫነ ከብት።
ወረጩ፡ ተረጨ፡ ቀዘቀዘ፡ በረደ (ተገብሮ)።
ወረጯ፡ ረጨ፡ ወረበ፡ ውርጭ ጣለ (ገቢር)።
ወረፈ፡ ሰዶበ፡ ፀረፈ።
ወረፈ፡ ወረበ፡ ዘለለ፡ ዐለፈ።
ወረፋ፡ (ኦሮ)፡ ተራ፡ ፈረቃ፡ ፈንታ።
ወረፍ ወረፍ አደረገ፡ እየዘለለ ዐወደ።
ወሪሳ መታ፡ ጋለበ፡ ወረረ፡ ዘረፈ።
ወሪሳ፡ ወረራ፡ ዘረፋ፡ ብዝበዛ። አፍን እይ።
ወሪራ፡ (ኦሮ)፡ አገርጋሪ ላም።
ወሪጋ፡ (አሪጋ)፡ ሳላ፡ ቀንዳም፡ የዱር እንስሳ።
ወሪጋ፡ የሴት ስም፡ የክቡር ራስ ዳርጌ እናት።
ወራ፡ (ትግ ወረየ)፡ ነገረ፡ አለ፡ አሰማ።
ወራ፡ ወረቀ፡ ብጫ መሰለ። የወራ ቅጠል እንዲሉ።
ወራረደ፡ ዘናነመ፡ ፈሳሰሰ።
ወራሪ፡ (ዎች)፡ የወረረ፡ የሚወር፡ ከባቢ፡ ዝንብ፡ ጕንዳን፡ ዘራፊ፡ በዝባዥ። የሌት ሰባሪ የቀን ወራሪ እንዲሉ።
ወራሪ፡ የጭፍራ ስም፡ የንጉሥን ዕልፍኝ፡ አዳራሽ፡ ድንኳን የሚጭን ሰራዊት።
ወራሽ፡ (ሾች)፡ (ወራሲ)፡ የወረሰ፡ የሚወርስ፡ ርስት ያዥ፡ ገንዘብ ፈላጊ፡ ልጅ፡ ዘመድ (ዕብ ፩: ፪፡ ሮሜ ፰: ፲፯)። ዐልጋን ተመልከት።
ወራሽ ቈራሽ፡ ያባቱን ቤት የሚወርስ፡ እንጀራውን የሚቈርስ።
ወራሽ፡ ዳኛ፡ ባለጋራ።
ወራሽነት፡ ወራሽ መኾን።
ወራቂ፡ ቦራቂ፡ ዘላይ፡ ጨፋሪ፡ አሣቂ።
ወራቢ፡ የወረበ፡ የሚወርብ፡ ዐጅ፡ ደብተራ።
ወራተኛ፡ የወራት።
ወራት፡ ወራቶች፡ ወሮች፡ ወር።
ወራት፡ ወራቶች፡ ዝኒ ከማሁ።
ወራና፡ (ኦሮ)፡ ጦር። ወገደ ብለኸ ወግዳን እይ።
ወራንታ፡ የስፌት ዕቃ ስም፡ እንቅብ፡ ፪ ጕርዝኝ፡ ወይም ፲ ቍና እኸል የሚይዝ።
ወራወረ፡ ጣጣለ።
ወራውረን፡ የወንድና የሴት ስም፡ ሲመሽ በሠርክ የተወለዱ ማለት ነው።
ወራውራን፡ ዝኒ ከማሁ፡ ዕርበት፡ ጥልቀት።
ወራዳ፡ (ዶች)፡ የተዋረደ፡ ኅሱር፡ ልክስክስ፡ ነውረኛ፡ ጐስቋላ፡ በጠባዩና ባመሉ (ናሖ ፫: ፲፩)።
ወራጅ፡ (ጆች)፡ የወረደ፡ የሚወርድ፡ ፈሳሽ፡ ተቈልቋይ። ውሃ ወራጅ እንዲሉ።
ወራፊ፡ የወረፈ፡ የሚወርፍ፡ ሰዳቢ።
ወሬ፡ (ወርኅየ)፡ በ፪ የሚተረጐም፡ ዐማርኛና ኅብር ንግግር። የኔ ወር ማለት ነው። ሴቲቱ ባሏን ቂጥኝ ይዞኻል አሉ ብትለው ወሬ ነው አላት። እሷ ቂጥኙ በወጣባት ጊዜ ምነው እንደዚህ አድርገኸ አታለልከኝ አለችው፡ እሱም ወሬ ነው ብዬሽ አልነበረምን አላት ይላሉ። (ግጥም)፡ አፌ አልተናገረ፡ በዦሮዬ አልሰማኹ፡ እንዲያው ታሰርኩና በወሬ ተፈታኹ።
ወሬ ለውጥ፡ ሌላ ነገር አምጣ።
ወሬ ማዱ፡ በወሬ ብቻ የሚጠቀም።
ወሬ በየደጁ፡ ልዩ ልዩ ኹኖ ይነገራል፡ ፩ዱ ከሌላው አይገጥምም።
ወሬ ነጋሪ፡ እንዲህ ኾነ ተደረገ የሚል፡
ወሬ፡ ከሰው አንደበት የሚሰማ ነገር፡ ቃል። (ተረት)፡ ወሬ ቢነግሩኸ መላ ጨምር። ለወሬ የለው ፍሬ።
ወሬ የማይቋጥርም ሰው በምሳሌ ወንፊት ይባላል።
ወሬና ወር፡ በአማርኛ ይገጥማሉ።
ወሬኛ፡ (ኞች)፡ ወሬ ወዳድ፡ የወሬ ቋት፡ ባለወሬ፡ የወሬ አባት፡ ከዕርም የማያበላ (ኤር ፶፩: ፴፩)።
ወሬኛ፡ እነግሣለኹ ባይ።
ወር፡ (ወርኅ)፡ ሠላሳ ቀን፡ ፯፻፳ ሰዓት፡ ፵፫ ሺሕ ከ፪፻ ደቂቃ። ወር የሚባሉ፡ ወር ተብለው የሚጠሩ እነዚህ ናቸው። ፩ኛ መስከረም፡ ፪ኛ ጥቅምት፡ ፫ኛ ኅዳር፡ ፬ኛ ታኅሣሥ፡ ፭ኛ ጥር፡ ፮ኛ የካቲት፡ ፯ኛ መጋቢት፡ ፰ኛ ሚያዝያ፡ ፱ኛ ግንቦት፡ ፲ኛ ሠኔ፡ ፲፩ኛ ሐምሌ፡ ፲፪ኛ ነሐሴ። እኒህም ጳጕሜን ጨምረው ፩ ዓመት ይኾናሉ። ቀናቸው፡ ፫፻፷፭ (፯)፡ ሰዓታቸው፡ ፰ ሺሕ ፯፻፷፮፡ ደቂቃቸው፡ ፭፻፳፭ ሺሕ ፱፻፰ ነው። ጳጕሜም በ፫ ዓመት ፭ ባ፬ ዓመት በዘመነ ሉቃስ ፯ ትኾናለች።
ወር ተረኛ፡ (ኞች)፡ በወር ተራ እየገባ የሚጠብቅ፡ ዘበኛ፡ ወታደር፡ ነፍጠኛ።
ወር ተራ፡ የወር ተራ፡ ሥራ፡ ዘብ፡ ጥበቃ።
ወር አይጠድቅ የለ፡ አንድ ወር የማይጠድቅ ኋላ የማይደርቅ የለ፡ ለጊዜው እንደ ዕድሉ የማይከብር ኋላ የማይዋረድ (የማይቸገር) የለ ማለት ነው።
ወርኅ፡ በግእዝ ጨረቃ ማለት ሲኾን፡ የቀድሞ ሰዎች፡ ነቢያት፡ ካህናት፡ ፩ ሌሊት፡ ፪ ሌሊት፡ እያሉ በጨረቃ ይቈጥሩ ስለ ነበረ ፴ው ቀን ወር ተባለ። በጨረቃ ግን ፳፬ ቀን ነው። ዛሬም ቢኾን ቀን የሚዠመረው ከሌሊቱ ባ፩ ሰዓት ነው።
ወርኅ፡ ወር፡ የጨረቃ ስም፡ ጨረቃ (ግእዝ)።
ወርቀ ዘቦ፡ (ወርቅ ዘቦ)፡ ወርቅ ያለበት፡ የተጠለፈበት ግምጃ፡ ካባ። ዘቦ፡ ዛብ፡ ዛቦ ማለትንም ያሳያል። ወርቀ ዘቦ ጥንታዊ ግእዝ ነው (ዘፀ ፴፱: ፰ = ፪ሳሙ ፩: ፳፬)።
ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ ጠፋ፡ የጥያቄ ቃል
ወርቁ፡ ወርቋ፡ የወንድና የሴት መጠሪያ ስም፡ የሱ፡ የሷ ወርቅ ማለት ነው።
ወርቁ: ያ ጨርቅ፡ የርሱ ወርቅ።
ወርቂት፡ ባፄ ቴዎድሮስ ጊዜ የነበረች የወሎ ባላባት።
ወርቃም፡ ብዙ ወርቅ የሚገኝበት ስፍራ (ዘፍ ፪: ፲፩፡ ፲፪)።
ወርቃም፡ ወርቅ ያለው፡ ባለወርቅ፡ የወርቅ ጌታ።
ወርቃወርቅ፡ የቅኔ ስም፡ ሠምን ትቶ በወርቅ ብቻ የሚነገር፡ የወርቅ ወርቅ ሠም ረገፍ።
ወርቄ፡ (ኦሮ)፡ ኮባ፡ ጕናጕና።
ወርቄ፡ ዝኒ ከማሁ፡ የኔ ወርቅ።
ወርቅ (ቆች) (ጸርቅ): የልብስ፡ የሸማ ዕላቂ (ሕዝ፲፫፡ ፳፡ ፳፩)።
ወርቅ፡ (ቆች)፡ በቁሙ፡ የማዕድን ስም፡ ነጭና ቀይ፡ ብጫ መሳይ ማዕድን፡ የዕንቍና የሉል፡ የአልማዝ ምክትል፡ ለሰውና ለመሣሪያ፡ ለዕቃ ኹሉ ጌጥ የሚኾን። መሶበ ወርቅ፡ ዐምደ ወርቅ፡ ራስ ወርቅ እንዲሉ (ዘፍ ፪: ፲፩፡ ፲፪)። ጠጋ፡ ዐዘበ፡
ረከበ ብለኸ መጨጊያን፡ ዛብን፡ ርካብን አስተውል።
ወርቅ ላበደረ ዐፈር፡ ለደግ አድራጊ ክፉ መመለስ (መዝ ፻፱: ፭)።
ወርቅ መርገፍ፡ የወርቅ ጌጥ፡ የመጐናጸፊያ፡ የጃን ጥላና የድባብ፡ የመሶበ ወርቅ ዘርፍ።
ወርቅ ማንካ፡ የወርቅ ማንካ፡ ከወርቅ የተሠራ።
ወርቅ ቅብ፡ ወርቅ የተቀባ ዕቃ፡ መሣሪያ።
ወርቅ በሜዳ፡ ወርቅ የሚመስል፡ ቅጠል በሜዳ የሚበቅል፡ ለብዙ ደዌ መድኀኒትነት ያለው ዕፅ። ወርቅ በዘርፍነት ሲነገር፡
ወርቅ ቡላ፡ የብጫ ነጭ ፈረስ።
ወርቅ ነሽ፡ የሴት ስም።
ወርቅ ነኸ፡ የሰው ስም።
ወርቅ ንክር፡ በወርቅ የተነከረ ጌጥ።
ወርቅ ዐልጋ፡ የወርቅ ዐልጋ፡ ከወርቅ የተዘጋጀ።
ወርቅ አካል፡ ጤናማ፡ ደኅና፡ ጕድለት የሌለበት ገላ፡ ሰውነት። ስለ ወርቅ አካል እንዲል ለማኝ።
ወርቅ አወጣ፡ ቂጥኝ አፈራ።
ወርቅ አገኘኹ፡ የሰው ስም
ወርቅ አጫዋች፡ በቤተ ክሲያን ጕልላትና ሰበሰብ፡ በዘውድ፡ በአክሊል፡ በመረሻት፡ በመሶበ ወርቅ፡ በሰገባ የተንጠለጠለ ጌጥ፡ ነፋስ ሲነካው ርስ በርሱ እየተጋጨ የሚንሿሿ፡ አንዱ ላንዱ አጫዋች፡ ድምፅ አቀባይ። የበቅሎ ዐልቦ መርገፍ ሻኵራ።
ወርቅ አፈራኹ፡ የወንድና የሴት ስም።
ወርቅ ወንበር፡ ከወርቅ የተሠራ፡ የወርቅ ወንበር።
ወርቅ ዋንጫ፡ የወርቅ ዋንጫ፡ ከወርቅ የተበጀ።
ወርቅ ውሃ፡ የሴት ስም።
ወርቅ ውሃ፡ የወርቅ ውሃ፡ በእሳት የቀለጠ።
ወርቅ ዛብ፡ የወርቅ ዛብ፡ ከወርቅ የተዘጋጀ የሽጕጥ ቋድ።
ወርቅ፡ የሐዲስ ምሳሌ፡ የሠም ምክትል፡ የብሉይ አንጻር። ሠምን ተመልከት።
ወርቅ፡ የቂጥኝ ሽሽግ ስም፡ ላመንዝራዪቱ ወርቅ መሰጠቱን ያሳያል።
ወርቅ፡ የገንዘብ ስም፡ መደበኛ ገንዘብ፡ የብር፡ የመዳብ፡ የንሓስ፡ ያሞሌ፡
የወረቀት ገንዘብ ኹሉ መሠረት፡ መያዣ፡ ዋስ። ከዚህ የተነሣ ማንኛውም ገንዘብ ወርቅ ይባላል። (ተረት)፡ ወርቅ የያዘ ቀበዝባዛ፡ እኸል የያዘ ፈርዛዛ። ገበዘ ብለኸ ግብዝን እይ።
ወርቅ ያንጥፉ፡ ዝኒ ከማሁ።
ወርቅ ይዝነምበት፡ ለደግ ሰው ቤትና ቦታ የሚነገር ምርቃት።
ወርቅ ይጠሩ፡ የሴት ስም።
ወርቅ ጣፋ፡ ወርቅ የተለበጠበት ጋሻ።
ወርቅ ጥልፍ፡ በወርቅ ክር የተጠለፈ ልብስ።
ወርቅ ጥብጣብ፡ የመላበሻው ዳርና ዳር በወርቅ ጥብጣብ የተጌጠ ካባ።
ወርቅ ጥብጣብ፡ የወርቅ ጥብጣብ።
ወርቅማ፡ ወርቅ መሳይ፡ ወርቅ ሕብር።
ወርቅብ፡ ወርቅ የሚመስል፡ ብሃ፡ ጥለት።
ወርቅዬ፡ (ወርቅየ)፡ የገብስ ስም፡ ነጭ ገብስ።
ወርቢ፡ አራተኛ የቀባርዋ ምት።
ወርቸ ከንብል፡ ዘቅዛቃ፡ ተዳፋት፡ ሸርታቴ ስፍራ።
ወርቹ የጠና፡ የጠነከረ፡ አሮጌ ዝኆን፡ ከወደቀበት መነሣት የማይችል።
ወርቻም፡ ባለወርች፡ ወርቸ፡ ትልቅ ከብት።
ወርች፡ (ቾች)፡ ጡንቻ፡ የፊት እግር (ዘሌ ፲: ፲፭)። ወርች የረገጠውን እግር አይስተውም እንዲሉ።
ወርች፡ እጅ። እከሌ እግር ተወርች ታሰረ።
ወርን እይ: (ወር የሚለውን ቃል ይመልከቱ)።
ወርካ፡ የዛፍ ስም፡ ረዥምና ሰፊ ዕንጨት፡ ደንጊያን ተጠግቶ የሚበቅል፡ ፍሬው የሚበላ። ተማሪ መምሩን እንደ ወርካ ያስፋዎ፡ እንደ ቀጤማ ያለምልምዎ እንዲል።
ወርዋሪ፡ (ዎች)፡ የወረወረ፡ የሚወርውር፡ አጓኝ፡ ሸጓሪ፡ ቀርቃሪ።
ወርዋሪ፡ በሐረርጌ ተሠርቶ የነበረ ጭፍራ ስም፡ ከጋሻ መካች ኋላ ቁሞ ጦር የሚወረውር ማለት ነው።
ወርውሮ ተኩሶ: "እጁን ዘርግቶ ሳይወጋ ሳይመታ ሳይዝ ቀረ ዘንጉ ጥይቱ ጊጤውን ይላማውን ዐለፈ ዘለለ።"
ወርዳሚት፡ ወርዷ የሰፋ ምድር (ኢሳ ፳፪: ፲፰)።
ወርዳም፡ ጐናም፡ ጐነ ሰፊ (ኤር ፶፩: ፪ ፶፰)።
ወርድ፡ (ርሕብ)፡ የጐን ስፋት፡ ከቁመት የሚያንስ (ዘፍ ፮: ፲፭፡ ኢዮ ፴፰: ፲፰)።
ወርድ፡ (ዐረ)፡ ጽጌ ረዳ።
ወርድ ንባብ፡ እንደ ዐቢይ ንባብ የማይቀለጥፍ፡ ጕት የሐዘን ንባብ።
ወርድ፡ ዐርብ፡ አራትያ፡ ዐምስትያ።
ወርጅ፡ (ዶች)፡ የነገድ ስም።
ወርጅ፡ ወረወረ።
ወርጎ፡ የዛፍ ስም፡ ሞፈር የሚኾን ዕንጨት።
ወሮ በላ፡ (ሎች)፡ ሕገ ወጥ ልጅ፡ ማን ዘራሽ፡ ቅሬ፡ ዘርፎ፡ ቀምቶ የሚበላ፡ ስካር፡ ምንዝር፡ ቅጥፈት፡ ሌብነት፡ ነውር ኹሉ ጌጡ።
ወሮ፡ ዘርፎ፡ በዝብዞ፡ ማርኮ። እዪው ወሮ ሲገባ እንዲሉ ሴቶች፡ ታቦት ሲነግሥ።
ወሮች፡ (አውራኅ)፡ ከ፪ ዠምሮ ያሉ ብዙዎች ፴ ቀኖች።
ወሸለ፡ ሸፈነ፡ በውስጥ አደረገ።
ወሸለ፡ ወከለ፡ ወተፈ፡ ጨመረ፡ ውሻል።
ወሸለከ፡ ወሰለተ።
ወሸላ፡ (ሎች)፡ ያልተገረዘ የወንድ ብልት ሽፍን፡ ወይም አረመኔ ሰው።
ወሸመ፡ ውሽማ ያዘ፡ ከሰው ሴት ኼዶ፡ ሌላዪቱን ወደደ፡ አመነዘረ።
ወሸመች፡ ሌላ ወንድ ያዘች፡ ካንድ ሰው ዐለፈች።
ወሸሽተር፡ የጠመንዣ ስም፡ ነፍጥ።
ወሸቀ፡ (ወሰከ)፡ ከጭቃ ካዛባ ጨመረ፡ አገባ፡ ሸጐጠ፡ ረፈቀ፡ ወዘፈ።
ወሸበ፡ (ዕብ፡ ያሻብ)፡ በቤት ተቀመጠ፡ እሳት ሞቀ።
ወሸበ፡ ተባዘተ፡ ለሰለሰ፡ ተጠቀለለ፡ ተሸበለለ፡
ዳመጦው፡ ንድፉ።
ወሸባ መግባት፡ ከሴት መራቅ፡ መታከም።
ወሸባ፡ በበረሓ የተቀመጠ፡ ሐሩረ ፀሓይ የተቀበለ፡ ጐበዝ፡ ቀስት፡ ጦር፡ ጠመንዣ የያዘ። ዐዳኝ ወሸባ እንዳለ፡ ዝኆን ገዳይ።
ወሸባ፡ አካለ ለስላሳ፡ ባዘቶ ገላ፡ ጌታ፡ ወይዘሮ።
ወሸባ አገባ፡ በቤት ውስጥ አስቀመጠ፡ መድኀኒት ሰጠ፡ እጠጣ፡ ዐከመ፡ ሙቀት አስቀበለ።
ወሸባ አገባ፡ አባዘተ፡ አለሰለሰ፡ በመታረሪያ ጠቀለለ።
ወሸባ አግቢ፡ ሐኪም፡ ወጌሻ፡ በጪ፡ ቀዳጅ፡ ዐጋሚ።
ወሸባ አግቢ፡ ባዛች፡ አለስላሽ፡ ጠቅላይ።
ወሸባ ወሸቤ፡ አያ ወሸባዬ እንዲል ዘፋኝ።
ወሸባ፡ ውሽባ፡ (ብለኔ)፡ የመታከም ሥራ፡ ባንድ ስፍራ ተቀምጦ መድኀኒት ማድረግ፡ መታጠብ፡ መታጠን፡ አፍንጫን፡ ዦሮን በጥጥ መወተፍ፡ ገላን ኹሉ መሸፈን፡ ምግብ መለየት።
ወሸባ ገባ፡ (ወሸበ)፡ ከሰው ተለየ፡ ባንድ ቤት ተዘጋ፡ ተቀመጠ፡ ታከመ፡ ታገመ።
ወሸባ፡ ፋቶ፡ ቀጪን፡ የማግ አምልማሎ፡ ጥቅልል፡ ኸብልል።
ወሸቤ፡ ወሸባዬ፡ የኔ ወሸባ።
ወሸኔ፡ የወሸን ዐይነት ወገን፡ ውብ፡ መልከ መልካም፡ ቈንዦ።
ወሸን፡ እንቋዕ)፡ የደስታ ቃል። ሖሼን፡ ደግ፡ ማለፊያ፡ ዕሠይ። ወሰውን እይ፡ ከዚህ ጋራ በምስጢር ይገጥማል። ሖሼን ዕብራይስጥ ነው።
ወሸከ፡ (ወሰከ)፡ ነገር ሠራ፡ ያንዱን ለሌላው ነገረ። ሸወከን ተመልከት፡ ከዚህ ጋራ አንድ ነው።
ወሸከሬ፡ (ሸከረ)፡ ጥቃቅን ዓሣ፡ የታላላቅ ዓሣ አሽከር፡ ትንንሽ ልጅ፡ ውሪ።
ወሸከሮች፡ ትንንሾች ዓሦች፡ ልጆች፡ ውሪዎች።
ወሸከተ፡ ቃዠ፡ ነገር አበዛ፡ እንደ ሕልም አገኝ ዐጣውን ተናገረ፡ ቀባዠረ፡ ወዣበረ፡ ዋሸ፡ ለፈለፈ። ወሸከን ተመልከት።
ወሸከት፡ ወሽካታ፡ የወሻከተ፡ የሚወሻክት፡ ቀባጣሪ፡
ቀባዣሪ፡ ፍሬ ቢስ፡ ፍሬ ፈርስኪ።
ወሸካከተ፡ እዚያም እዚያም ወሬ ነፋ፡ ቀበጣጠረ።
ወሸገረ፡ ወነገረ፡ ወነከረ፡ ግራ ቀኝ ረገጠ። ሸነገረን እይ።
ወሻሚ፡ የወሸመ፡ የሚወሽም፡ ቅንዝረኛ።
ወሻም፡ (ሞች)፡ ባለወሽ፡ ወሸ፡ ትልቅ ላም።
ወሻሸለ፡ ወታተፈ።
ወሻቂ፡ የወሸቀ፡ የሚወሽቅ፡ ወዛፊ።
ወሻቃ፡ ውሽቅ፡ የተወሸቀ፡ ርፍቅ፡ ውዝፍ።
ወሻውሽኝ፡ (ወሽ፡ አውሽኝ)፡ በደብረብርሃን አጠገብ ያለ ቀበሌ።
ወሻይ፡ የወሸለ፡ የሚወሽል፡ ወታፊ፡ ወካይ።
ወሼ፡ ዝኒ ከማሁ፡ የኔ ወሽ ማለት ነው፡ በዚህ ጊዜ ወሽ አህያ ተብሎ ይተረጐማል።
ወሽ፡ አህያን ለመንዳትና ለመከልከል፡ ለማገድ የሚሰማ ድምፅ።
ወሽ ከለል፡ የላም ብሽሽት ቆዳ፡ ወሽ ከላይ፡ ጕይዲ ግን እሽኮለሌ ይለዋል።
ወሽ፡ የጡት መሠረት፡ የግት፡ የእንገር፡ የወተት ቋት፡ ከረጢት፡ ኪስ።
ወሽላካ፡ ወስላታ።
ወሽመጥ፡ (ጦች)፡ ስመጥ)፡ ጐን፡ የሽንጥ አጠገብ፡ ጎረቤት፡ ከብብት እስከ ሙሓይት ያለ ገላ። ወሽመጥ ቈራጭ እንዲሉ።
ወሽመጥ፡ የሱሪ ወንበርና የጥብቆ የእጀ ጠባብ ሠላጤ፡ ሕፅን፡ የጠበበ ልብስ ማስፊያ።
ወሽመጥን እይ: (ወሽመጥ የሚለውን ቃል ይመልከቱ)።
ወሽማዳ፡ ወጭማዳ፡ ሸመደ።
ወሽማዳ: ዝኒ ከማሁ (ወጭማዳ)።
ወሽከለል፡ ወሽ ከላይ፡ ወሽ።
ወሽጋራ፡ ወንጋራ፡ ወንካራ።
ወቀል፡ ኹለተኛ የቀባርዋ ምት።
ወቀሠ፡ (ወቂሥ፡ ወቀሠ)፡ ሰው የሠራውን በደልና ስሕተት በሽማግሌ ፊት ወይም በሸንጎ ገለጠ። ገሠጸ፡ ተቈጣ፡ ነቀፈ፡ ዘለፈ፡ መከረ፡ የክፉ የበጎ።
ወቀሰ፡ ዘለፈ፡ ወቀሠ።
ወቀሣ ከሰሳ፡ መውቀሥ፡ መክሰስ፡ ጭቅጭቅ፡ ክርክር።
ወቀሣ፡ ዘለፋ፡ ተግሣጽ፡ ቍጣ፡ ነውር፡ ነቀፋ። (ተረት)፡ የሰጠ ቢነሣ የለበት ወቀሣ።
ወቀረ፡ (ወቂር፡ ወቀረ፡ ወገረ)፡ ወጋ፡ ጠቀጠቀ፡ ነቀሰ፡ ጥርስን በመላው።
ወቀረ፡ ተማሪን ከድንቍርና አራቀ፡ በትምርት አሠለጠነ።
ወቀረ፡ ወፍጮን፡ የግንብ ደንጊያን፡ ጠረበ፡ አበጀ፡ አሻከረ፡ አሰላ (፩ነገ ፭: ፲፰)።
ወቀራ፡ ነቀሳ፡ ጠረባ።
ወቀራብ ማለት፡ በውስጡ አንድ ነገር ሲገባ ሸምቀቆው መቃረቡን ያሳያል።
ወቀራብ፡ ወንቀራብ፡ (ቀረበ)፡ ወፍን፡ ቆቅን፡ የሚይዝ ወጥመድ፡ ወስፈንጠር፡ በግእዝ ፀንፈርት ይባላል።
ወቀራብ: ወጥመድ፣ ወስፈንጠር (ባለሸምቀቆ)፡ "በግእዝ ዐንፈርት ይባላል። "
ወቀሬ፡ (ኦሮ)፡ የፈረስ አጋሰስ፡ ገጣባ።
ወቀዘ፡ ቀጠነ፡ መነመነ፡ ኰሰሰ።
ወቀጠ፡ (ትግ ወቀጠ፡ ጥርስን፡ ገላን፡ ነቀሰ)፡ ወጋ፡ ጠቅ አደረገ፡ ፈተገ፡ ሸከሸከ፡ ደለዘ፡ እግርን፡
እኸልን፡ በርበሬን፡ ቅመምን፡ ጌሾን። ወግጠን እይ፡ ከዚህ ጋራ አንድ ነው፡ ወቀረን አስተውል።
ወቀጠ፡ ቀጠቀጠ፡ መታ፡ ገደለ፡ የበግ፡ የፍየል፡
የወይፈን ቍላን።
ወቀጣ፡ መውቀጥ፡ ቅጥቀጣ። ጐራ ብለኸ ጐሬን እይ።
ወቂ፡ (ዎች)፡ የወቃ፡ የሚወቃ፡ የሚያኼድ፡ ፈልፋይ።
ወቃ፡ (ወቅዐ)፡ ከምድር ጣለ፡ ተመቺውን መምቻ አደረገ። እከሌ እከሌን አመሬት ወቃው እንዲሉ። መታ፡ ደበደበ፡ አኼደ፡ አበራየ፡ ፈለፈለ (ኢሳ ፳፯: ፲፪)። (ዝናሙ ወቃው)፡ በብዛትና ባለማቋረጥ ዘነበበት፡ ወረደበት መሬቱን።
ወቃሪ፡ (ሮች)፡ የወቀረ፡ የሚወቅር፡ ነቃሽ፡ ጠራቢ (፪ነገ ፲፪: ፲፪)።
ወቃሽ፡ (ሾች)፡ የወቀሠ፡ የሚወቅሥ፡ ገሣጺ፡ ዘላፊ፡ ነቃፊ። ሙት ወቃሽ እንዲሉ።
ወቃሽ ከሳሽ፡ የሚወቅሥ፡ የሚከስ።
ወቃሽነት፡ ወቃሽ መኾን፡ ገሣጺነት።
ወቃቀሠ፡ ዘላለፈ፡ ተቈጣጣ፡ መካከረ።
ወቃቀረ፡ ነቃቀሰ፡ ጠራረበ፡ መታታ፡ አሸካከረ።
ወቃቀጠ፡ ቀጣቀጠ፡ ደባደበ፡ መታታ፡ ፈታተገ፡ ሸካሸከ።
ወቃዛ፡ ውቃዞ፡ መንማና፡ ደቃቃ፡ ኰሳሳ፡ እኸል፡ ከብት፡
ሰው።
ወቃጣ፡ ወቃጥ፡ ቅጥቅጥ፡ ቍላው የተቀጠቀጠ ሰው።
ወቃጭ፡ (ጮች)፡ የወቀጠ፡ የሚወቅጥ፡ ፈታጊ፡ ሸክሻኪ፡ ቀጥቃጭ። የወቃጭ አንፋሽ እንዲሉ።
ወቃጭ፡ ከሳሽ፡ የሚወቅሥ፡ የሚከስ።
ወቄራ፡ ካራ፡ ቄራ።
ወቄራ: ካራ፣ ማረጃ፣ ማወራረጃ። (ተረት): "ልጅ ያባቱን፡ ወቄራ ያፎቱን። "
ወቄት፡ (ቶች)፡ (ወቀየ)፡ የወርቅ ገንዘብ ሚዛን፡ ወይም ክፍል፡ ፩ ብር ፳ መሐለቅ ባነሣ ፩ ወቄት ይባላል፡ ይኸውም ፳፰ ግራም ነው። ወቄት ወርቅ እንዲሉ። አበትን እይ።
ወቅለምት፡ ካራ ቀለመ፡ መቅለምት።
ወቅለምት፡ ዝኒከማሁ።
ወበሪ: የኦሮ ስም፣ በሺዋ ካሉት ከኦሮ ባላባቶች አንዱ።
ወበራ የሚለው ቃል በሐረርጌ ክፍለ ሀገር ያለ አገርና ነገድን ያመለክታል።
ወበራ: እብሪተኛ ሆነ፣ ቀበጠ።
ወበራ: ጠገበ፣ ሸሸ፣ ወገሸ።
ወበቀ: ጋለ፣ ሞቀ፣ ተኮሰ፣ ላብ ላብ አለ።
ወበቅ: ግለት፣ ሙቀት፣ ሀሩር።
ወበበ: ተከተለ፣ በስተኋላ ሆነ።
ወበብ ወበብ: ተረታዊ የድመት ዘፈን ("ከተል ከተል")።
ወበብ: የወበበ፣ የሚከተል፣ ተከታይ ደጀን።
ወበነነ: ተወባነነ፣ ኮራ፣ ተጓደደ።
ወበኔ: ኩራተኛ።
ወባ: የበሽታ ስም፣ የቆላ በሽታ፣ አስራቦ ከሚባል ትንኝ የሚመጣ። በአረብኛ "ወባእ" ይባላል።
ወባሪ: የወጫበረ፣ የሚወግበር።
ወባቂ: የሚወብቅ ስፍራ።
ወባት፡ "ኀላፊ" ከሚለው ቃል ጋር ተያይዟል (ዋበን ይመልከቱ)።
ወባት (ቶች): በፈቃዱ ጠበቃ የሆነ፣ የጠብ የነገር ኃላፊ።
ወባት እና ውበት
ወባት ገባ: ለተጨነቀ አገዘ፣ ረዳ ("አይዞህ እኔ አለሁልህ አለ")።
ወብራ: የጠገበ፣ ጥጋበኛ፣ ቀበጥ። (ተረት) "የባልቴት ወብራ የክረምት ብራ"።
ወቦ ሸማኔ: የነብር አይነት አውሬ፣ ዛፍ ላይ የሚወጣ።
ወቦ/ዎቦ: ስመ ጭፍራ ደጀን፣ የኋላ ጦር።
ወቦ: የኮከብ ስም፣ አባት ኮከብ ባለብዙ ጭፍራ።
ወቧራ: ብናኝ፣ ደቃቅ ዐፈር፣ አሸዋ (ኢዮብ ፴፰፡ ፴፰። መዝሙር ፩፡ ፬)። "በግእዝ፡ ጸበል፡ ይባላል።"
ወተረ (ወቲር፣ ወተረ): ሳበ፣ ገተረ፣ ወጠረ፣ ዘረጋ፣ ለጠጠ።
ወተር: የሸረሪት ድር፣ ወይም ዝሓ።
ወተር: የገጠር ስም፣ በሐረርጌ አውራጃ ያለ ቀበሌ።
ወተበ፡ ሠራ፡ አበጀ፡ አጠፈጠፈ፡ አከበበ። ተና፡ ሰ፡ ተወራራሽ ስለ ኾኑ፡ ወተበና ወሰበ አንድ ዘር ናቸው።
ወተበ፡ ወሰበ፡ ወሸለ፡ ጠመጠመ፡ የገመድ።
ወተተ: ዋተተ፡ ዞረ፣ ባከነ፣ ተንከራተተ፡ ወዲያና ወዲህ አለ፡ ብዙ ሥራ ሠራ፣ ባተለ፡ ወተት ሲንጡት እንደሚዋልል ማለት ነው።
ወተታም: ባለወተት፡ ወተተ፣ ብዙ ላም፣ እናት ዕንጨት።
ወተታሞች: ላሞች፣ እናቶች፣ ዕንጨቶች።
ወተት አለ: ወተት ፈለገ፣ ጠየቀ። (ጥት) ወተት አለ: ዋተተ።
ወተት አንዠት: ወተት የሚመስል አንዠት።
ወተት: ሐሊብ፡ ከናት ባሕርይ የሚገኝ የእንቦሳ፣ የግልገል፣ የውርንጭላ፣ የቡችላ፣ የሕፃን ምግብ። (ተረት): የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል። (ያህያ ወተት): የተፈተነ፣ የሳል መድኀኒት።
ወተት: የወርካ፣ የሾላ፣ የበለስ፣ የቍልቋል፣ የቈለቈል፣ የቅንጭብ፣ የሞይደር፣ የቋንዶ፣ የጥፍርአንዶ፣ የሌላውም ዛፍና ሐረግ ሁሉ ነጭ ደም።
ወተወተ (ወተተ፣ ወሰወሰ): ጐተጐተ፣ ነዘነዘ፣ ዘበዘበ፡ ዕረፍት ነሣ።
ወተድ: ካስማ፡ የካስማ ዓይነት።
ወተፈ (ወተበ፣ ወሸለ): ሣርን፣ ጭድን፣ ቅጠልን፣ ወርቅን ሸጐጠ፡ ከደነ።
ወታሪ: የወተረ፣ የሚወትር፡ ሳቢ፣ ገታሪ፣ ወጣሪ።
ወታቢ፡ የወተበ፡ የሚወትብ፡ ጠምጣሚ።
ወታቦ፡ (ዎች)፡ እንደ ዋዲያት፡ እንደ ጕርዝኝ ኾኖ ከእበትና ካመድ የተሠራ ዕቃ።
ወታተፈ: ሸጓጐጠ፣ ወሻሸለ።
ወታደር (ሮች): ዝኒ ከማሁ፣ የጦር ሰው፣ ነፍጠኛ (፪ዜና ፲፯፡ ፪፡ ዮሐ፲፰፡ ፫)።
ወታደር ኾነ: ብረት አነሣ፡ ለጌታ ዐደረ፡ ጦርነት ተማረ።
ወታደር ዋቶ ዐደር: እንዲሉ።
ወታደር: ነፍጠኛ ፥ ወተተ፥ ዋተተ።
ወታደርነት: ወታደር መኾን።
ወታፊ: የወተፈ፣ የሚወትፍ፡ ከዳኝ።
ወታፋ: ውትፍ፡ የተወተፈ፡ ደካማ፣ ዐቅሙ ቢስ።
ወትሮ (ወትር): ንኡስ አገባብ። ዘወትር፡ በየጊዜው። ዘወትርን እይ።
ወትዋች (ቾች): የወተወተ፣ የሚወተውት፡ ጐትጓች፣ ነዝናዥ።
ወቸገል: የዥብ አለቃ፡ ወይም አውራ፣ ዋና ዥቦች ሁሉ የሚፈሩትና የሚሸሹት፣ የሚገለሉለት፣ እንደ ቄስ እንደ ንጉሥ የሚያከብሩት (አረጋዊ መንፈሳዊ ገጽ ፲፬)። ቀመርን እይ።
ወነሼ፡ (ዋኖስየ)፡ የሴት ስም፡ የኔ ዋኖስ፡ ዋኖሴ፡ አጫዋቼ፡ ወይም የወለሼ ለውጥ ይመስላል።
ወነቀፈ፡ (ነቀፈ፡ ነገፈ)፡ ወለከፈ፡ ዐነቀፈ። ነገፈ ግእዝኛ ነው።
ወነበደ፡ ላተ፡ ነጠቀ፡ ቀማ፡ ወንበዴ ኾነ።
ወነበደ፡ ደነበረ፡ ሸሸ፡ ሮጠ፡ ጋለበ፡ ሸመጠጠ።
ወነቶ፡ የመሬት መደደቂያ፡ ጣምራ ብረት ያለው ደንጐራ፡ የጕራጌ ሥራ።
ወነነ፡ አኰራ፡ ጀነነ፡ ቈነነ።
ወነነ፡ ወነገ፡ ወሰጠ።
ወነን፡ ዋኒን፡ (ትግ ሐባ)፡ እርዌ፡ አራዊት (መዝ ፷፰: ፴፡ ፸፱: ፪)።
ወነከረ፡ (ነከረ)፡ ወነገረ።
ወነወነ፡ (ወነነ)፡ ወዘወዘ፡ ነቀነቀ፡ ቈላ፡ አወላወለ፡ የዥራት።
ወነወና፡ የሽንብራና የጤፍ ኅብስት በበርበሬና በቅባኑግ የተዘጋጀ፡ የላስቶች ሥራ።
ወነዘፈ፡ (አወነዘፈ)፡ ለበሰ፡ አጣፋ።
ወነደመ፡ (አኀወ)፡ ወንድም አደረገ።
ወነጀለ፡ (ወነጌለ)፡ በወንጀል ከሰሰ፡ አሳጣ፡ ኀጢአተኛ፡ ዐመፀኛ አደረገ፡ ስም አከፋ፡ አረከሰ፡ በውነት ወይም በሐሰት፡ በደለ።
ወነጀለ፡ ወንጀል ሠራ፡ አደረገ፡ ዐመፀ፡ በደለ።
ወነጀረ፡ ወነገረ፡ ውንጅርኛ አስኬደ፡ አፈነጀረ።
ወነጀበ፡ ወለከፈ፡ ደነቀፈ።
ወነገ፡ ወነጠ፡ ወሰጠ፡ ወነነ፡ ወዘወዘ።
ወነገረ፡ (ነገረ)፡ ወነከረ፡ ደነቀረ።
ወነጌ(ገ)ለ፡ ወነጀለ፡ ዐመፀ፡ በደለ (መሳ ፪: ፲፩፡ ኤር ፲፮: ፲፪)።
ወነጠ፡ (ናጠ)፡ ወነገ፡ ወዘወዘ።
ወነጨፈ፡ (ወጪፈ)፡ ሰፋ፡ ታታ፡ አበጀ፡ ቈዳን፡ ገመድን።
ወነጨፈ፡ ደንጊያን ወረወረ፡ ለመቄ ለደመኛ (፩ሳሙ ፲፯: ፵፱)።
ወነፈለ፡ (ነፈለ)፡ ሥራን፡ ረዳ፡ ጕልበት አበደረ።
ወኒ፡ (ኦሮ: ኦኔ፡ ልብ)፡ ኀይል፡ እልክ።
ወኒያም፡ ባለወኒ፡ እልከኛ፡ ኀይለኛ፡ ልበኛ፡ ጐበዝ።
ወና፡ (ኦሮ: ኦና)፡ ባዶ ቤት፡ ወይም አስቀድሞ ቤት ኑሮበት ጠፍ የኾነ ስፍራ፡ የፈረሰ ፣ የተፈታ።
ወናሄ፡ ፍሬው ንጣት፡ ነጭነት ያለው ዛፍ። ጥርሱ ወናሄ ይመስላል እንዲሉ።
ወናጊ፡ የወነገ፡ የሚወንግ፡ ወናጭ።
ወናግ፡ (ሐረርና ሱማሌ)፡ አንበሳ። ዳግመኛም በሱማልኛ ማለፊያ ማለት ይኾናል።
ወናግ ሰገድ፡ ያፄ ልብነ ድንግል ስመ መንግሥት፡ አንበሳ የሰገደለት ማለት ነው።
ወናጭ፡ የወነጠ፡ የሚወንጥ፡ ወናጊ። (ጥነ) መወነጥ፡ መወነግ፡ መወዝወዝ።
ወናፍ (ፎች): በቁሙ፡ የቀጥቃጭ፣ የባለጅ፣ የአንጥረኛ መሣሪያ። ከወደ መያዣው ጠርብና ጠፍር በስተጫፉ ቀጪን የብረት አሸንዳ ያለበት ስልቻ፣ ነፋስ መስጫ፣ የከሰል ማንደጃ። (ተረት):
"ፍየል መንታ ትወልድ አንዱ ለወናፍ ሌላው ለመጻፍ"። "ዥብ የኔ ስለው ወናፌን ቀማኝ"።
ወናፍ፡ በቁሙ ነፋ (ነፍኀ)።
ወናፍ: አባ ንፋው፡ የሰማውን የማይደብቅ ሰው፣ ዕንብርተ ቀዳዳ።
ወን(ም)በርቲ: የሐኔ፣ የዋልሴ ዓይነት መሣሪያ (በሁለት ወገን ስለት ያለው)፡ ወንበራዊ።
ወንቃፊሎ፡ ዝኒ ከማሁ፡ ወንቃፍነት ያለው፡ ሎ አለው ማለት ነው።
ወንቃፍ፡ (ፎች)፡ ፈ ቀላሳ፡ እንደ ካስማ ያለ ረዥም ዕንጨት፡ ከዛፍ ላይ ደረቅ ዕንጨት ስቦ መስበሪያ፡ ማውረጃ።
ወንቋራ: የጨነቈረ፡ አንድ ዐይኑን ያደከመ።
ወንበረተኛ (ኞች): የትምህርት ጓድ፣ ዦሮ ጠምዛዥ።
ወንበር (ምንባር): የማንኛውም ሰው መቀመጫ (ከእንጨት የተሠራ፣ በቈዳ የተጠፈረ ቋንጤ)። "በርጩማን" ተመልከት።
ወንበር (ምንባር): የግእዝ፡ ወንበር የአማርኛ ነው። ሲበዛ "ወንበሮች" ይላል። "ከንፈርን" ተመልከት።
ወንበር፡ መቀመጫ፡ ነበረ።
ወንበር ዘረጋ: በወንበር ተቀምጦ ትምህርት አስተማረ። (ዳግመኛም ወንበር ማለት አትሮንሱን ያሳያል)።
ወንበር ዘረጋ: ትምርትን ነገረ፣ አስተማረ።
ወንበር ገፋ: ያዳፋኝን ግብር ገበረ፣ ያስታጓይን ማኅበር ደገሰ ተከታዩ።
ወንበር ገፍ: ሦስተኛ የግብር ተረኛ።
ወንበር: ሥራ፣ ግብር።
ወንበር: የሱሪ ኮርቻ ትክል። መቀመጫነቱን ሲያዩ "ወንበር" ብለውታል። ባላገርም "ወንበር" በማለት ፈንታ ወምበር ይላል፡ ይኸውም "መና"ና "ነ" ተወራራሽ ስለሆኑ ነው። "ወንበር ፲፲፱ ዓመት ተረፈ ንኡስ ቀመር"።
ወንበር: የንባብ፣ የዜማ፣ የትርጓሜ ትምህርት። "ወንበር" ያሰኘው የመጽሐፉ አትሮንስ ይመስላል።
ወንበር: የዳኛ ስም፡ በወንበር ተቀምጦ የሚፈርድ ዳኛ "ወንበር" ይባላል። "ቀኝ ወንበር"፣ "ግራ ወንበር" እንዲሉ። በግእዝ ግን (ወንበር) ተቀመጥ ማለት ነው።
ወንበርማ: በሱሪ ወንበር ጐን የሚውል ሾጣጣ ማለት ነው።
ወንበርማ: በጐዣም ግዛት ያለ ቀበሌ። "ወንበር መሳይ"፣ "ባለወንበር" ማለት ነው።
ወንበርሲጣ፡ (ዩንበርሲቲ)፡ ቤተ-ደራስያን፡ ወመምህራን።
ወንበርነት: ዳኝነት፡ ዳኛ መሆን።
ወንበሮች: መቀመጫዎች፣ በርጩሞች፡ ዳኞች።
ወንበዴ፡ (ዶች)፡ የወንበድ፡ ነጣቂ፡ ቀማኛ፡ በደን በጐድጓዳ ስፍራ በባሕር ዳር ተደብቆ የሚቀማ፡ ቀምቶ የሚሸሽ (ዮሐ ፲: ፩: ፰፡ ማቴ ፳፯: ፴፰)። (ተረት)፡ ጕልበት የሌለው ወንበዴ፡ ትርፍ የሌለው ነጋዴ። (ረቂቅ ወንበዴ)፡ አታላይ፡ ናዝራዊ፡ ባሕታዊ፡ መነኵሴ።
ወንበዴነት፡ ነጣቂነት፡ ቀማኛነት።
ወንባጅ፡ ወንበድ፡ የወነበደ፡ የሚወነብድ፡ ኦሮቢ ሸሽታ። ወንበድ አልተለመደም።
ወንት፡ የአካንዱራ ጨዋታ፡ ፪ቱን ደርቦ ሲወጋ ወንት ይላል።
ወንካላ፡ ዐንካሳ (ነከለ)።
ወንካላ: ከዚህ ጋር ተመሳሳይ። "ወንካራንና ወልካፋን" አስተውል።
ወንካሎች: ዐንካሶች።
ወንካራ፡ (ሮች)፡ ወንጋራ።
ወንዘረጭ፡ (ረቃዬ ውሒዝ)፡ ወንዝን የሚረጭ፡ የወዠቦ ዐይነት፡ ቡልማ፡ ጕሬዝማ፡ ወፍ፡ ዥራተ ረዥም፡ እወንዝ ገብቶ እየተንደፋደፈ የሚታጠብ፡ የማሽላ ጠር።
ወንዛም፡ ባለወንዝ፡ ወንዝ ያለበት፡ የበዛበት ስፍራ።
ወንዛወንዝ፡ የወንዝ ወንዝ፡ ብዙ ወንዝ።
ወንዛድምቅ፡ (ወንዝ አድምቅ)፡ በወንዝ ዳር የሚበቅል ዕንጨት፡ የቅጠሉ ሰበከት ነጭ፡ ወዙ አረንጓዴ የኾነ፡ ወንዝ አድማቂ ዛፍ። ሲበዛ ወንዛድምቆች ይላል።
ወንዝ፡ (ሙሓዝ)፡ የውሃ መፍሰሻ፡ መውረጃ። ደረቅ ወንዝ እንዲሉ። (የጠጅ ወንዝ)፡ ኣሸንዳ።
ወንዝ፡ (ውሒዝ)፡ የምድር ወዝ፡ ዥረት፡ ዠማ፡ ፈሳሽ ውሃ፡ ትልቁም ትንሹም።
ወንዝ ለወንዝ ኼደ፡ ውሃን ተከትሎ ቍልቍል ወረደ።
ወንዝ አመቴ፡ (ዎች)፡ (የወንዝ አመቴ)፡ የወንዝ ገረድ፡ ሴት ባሪያ፡ ዓሣ ለቃሚ አሞራ፡ ታላቅ ቤተ ሠሪ።
ወንዞች፡ (ወሓይዝት)፡ ዥረቶች፡ ዠሞች፡ ፈሳሾች (ምሳ ፭: ፲፯፡ ሕዝ ፴፮: ፬: ፮)።
ወንደ ገሪ፡ የጋኔን ስም፡ ወንድን የሚገራ ማለት ነው (፩ነገ ፲፱: ፬)።
ወንዱ፡ ጐበዙ አይፈር ለፊቱ። (ሽለላ)፡ የሞላሌ ልጅ፡ ሞላሌ ወንዱ፡ እንደ መዳኒት ይበቃል አንዱ።
ወንዱን ከሴቷ ለመለየት: ወንድ ሙሽራ፣ ሴት ሙሽራ።
ወንዳወንዴ፡ በስተቀኝ በኩል በምድር ተተክሎ ከሸማኔ መጠቅለያ የሚዋደድ አንድ ፈ ሹል ዕንጨት።
ወንዳወንዴ፡ የመዝጊያ ቍላ፡ በደፍና በጕበን ውስጥ የሚሰካ።
ወንዳወንድ፡ ብርቱ ሴት፡ ድምጠ ወፍራም።
ወንዳወንድ፡ የወንድ ወንድ፡ ሐርበኛ።
ወንዳገረድ፡ (ወንድ አገረድ)፡ ወንድን ግርድ የሚያደርግ፡ ወንድ አርካሽ፡ ወንድነት ከገረድነት ያለው፡ ሴት አውል፡ አሰዳቢ፡ የወንድ ግርድ፡ ወንድ ሲኾን ቀሚስ አጥልቆ እንደ ገረድ የሚሠራ፡ የሚፈጭ፡ የሚቈላ፡ የሚጠምቅ፡ የሚጋግር፡
የሚፈትል፡ የገረድ ጓድ፡ ባለጌ፡ ነውረኛ፡ ዐጓጕል፡ ከኹሉ ኣለኹ የሚል፡ ሴት አይሉት ወንድ ፈናፍንት።
ወንዴ፡ (ተባዕታይ)፡ ወንዳዊ፡ የወንድ ወገን፡ ዐጅሬ፡ ጠንካራ ዕንጨት፡ ከሴቴው ጋራ የሚከተብ።
ወንዴ ሬት፡ ጥርስ ያለው።
ወንዴ ቍልቋል፡ ሻካራ ቅርፍርፍ።
ወንዴ ቃጫ፡ በላንፋው መካከል እስኪታዊ ዕንጨት ያለበት የቆመበት።
ወንዴ፡ ብርጕድ፡ የተመጠነ።
ወንዴ ዐፈር: መረሬ፡ ጥቍር መሬት (ጥቁር አፈር)።
ወንዴ፡ የቍልፍ መክፈቻ።
ወንዴ፡ የገሣ ዕንጨት።
ወንዴዎች፡ ወንድዮች፡ የመዝጊያ ቍላዎች፡ ወይም እግሮች (፩ነገ ፯: ፶)።
ወንድ፡ (ወልድ፡ ዕድ)፡ እሱና አንተ የሚባል የሩቅና የቅርብ ሰው። ተባት፡ የሴት ባል፡ ገዢዋ፡ አሳዳሪዋ፡ በጽሕም፡ በድምፅ፡ በትእምርተ ተባዕት፡ በጡት፡ በብዙ ወገን ከሴት ልዩነት ያለው፡ ብርቱ፡ ጐበዝ። እከሌ ወንድ ወጣው እንዲሉ። ቅጽል ሲኾን ወንድ ልጅ ይላል። ሴትን ተመልከት።
ወንድ በ፪ እግሩ አጥልቆ በወገቡ ላይ የሚታጠቀው: (የልብስ ዓይነት)።
ወንድ በኾንሽ፡ የሴት ስም፡ ምኞታዊ ስየማ።
ወንድ በወሰን፡ የሰው ስም፡ ጠላት ሲመጣ በወሰን የሚቆም ወንድ ማለት ነው።
ወንድ ወሰን፡ (የወንድ ወሰን)፡ የሰው ስም፡ የወንድ ድንበር መጨረሻ።
ወንድ ወጣው፡ ዠብዱ ሠራ፡ ስመ ጥር ኾነ።
ወንድሙ፡ የሱ ወንድም።
ወንድማማች፡ (ወንድም ዐማች)፡ የወንድሙን መንትያ እት እንደ አዳም ጊዜ ያገባ፡ ወንድምነት ካማችነት ያለው። እትን ተመልከት።
ወንድማማች፡ በትውልድ ሐረግና በምግባር በሃይማኖት አንድነት ያለው ማኅበር (ግብ ሐዋ ፩: ፲፮፡ ፪: ፳፱)።
ወንድማማቾች፡ (ወንድሞች ዐማቾች)፡ ወንድሞችና ዐማቾች የኾኑ፡ ሥጋ ልደት፡ ደም ጥልቀት ያላቸው ቤተ ዘመዶች፡ ተወላጆች፡ ጋብቾች።
ወንድማም፡ ባለወንድም።
ወንድማሞች፡ ወንድም ያላቸው፡ ባለወንድሞች።
ወንድሜ ነኸ፡ የሰው ስም።
ወንድሜ፡ የኔ ወንድም፡ ያባቴና የናቴ ልጅ።
ወንድም፡ (ዕድኒ)፡ ም ዋዌ ነው፡ ወንድም ሴትም እንዲሉ።
ወንድም፡ (ወልደ እም)፡ ያባት ምሳሌ፡ የናት ልጅ፡ ካባትም የተወለደ፡ ወይም አባት ከሌላይቱ ሴት የወለደው፡ እናት ከሌላ ወንድ የወለደችው፡ ያንድ ወገን ወንድም። ያጎት፡ ያክሥት ልጅ፡ የቅርብ ዘመድ ሳይቀር ወንድም ይባላል፡ በግእዝም እኅው ነው።
ወንድም ለሌለው፡ አባት ልጁ ወንድሙ ተብሎ ይሰየማል።
ወንድም ነኸ፡ የሰው ስም።
ወንድም አገኘኹ፡ ወንድም ሲያምረኝ፡ ወንድም ተገኝ(ኘ)፡ የሰው ስም፡ ወንድም የሌላቸው ኣባትና እናት ለልጃቸው ይኸን ስም ያወጣሉ።
ወንድም ገዜ፡ የሰው ስም፡ ወንድም ወለደ አበጀ ማለት ነው።
ወንድም ጋሼ፡ ያጎት፡ ያክሥት፡ የቤተ ዘመድ ልጅ፡ መጥሪያ።
ወንድሞች፡ (አኀው)፡ ከኹለት በላይ ያሉ ያባት የናት ልጆች፡ ቤተ ዘመዶች፡ ባልንጀሮች፡ ማኅበሮች (ግብ ሐዋ ፪: ፴፯፡ ፩ጢሞ ፭: ፩)።
ወንዶች፡ (ዕደው)፡ ተባቶች፡ ባሎች፡ እነሱና እናንተ የሚባሉ የሩቆችና የቅርቦች ሰዎች።
ወንጀለኛ፡ (ኞች)፡ ዐመፀኛ፡ በደለኛ፡ ከዳተኛ፡ ጥፋተኛ፡ ሽፍታ፡ ዳንዴ፡
ወንበዴ፡ ቀማኛ፡ የቀን ወራሪ፡ የሌት ሰባሪ፡ ቤት ኣቃጣይ፡ ነፍሰ ገዳይ፡ ቋንዣ ቈራጭ።
ወንጀል፡ (ሎች)፡ ዐመፅ፡ ክዳት፡ ግፍ፡ በደል፡ ሕገ ወጥ ሥራ፡ ቋንዣ መቍረጥ፡ ቤት ማቃጠል፡ ነፍስ መግደል፡ የመሰለው ኹሉ። አንዳንድ መምህራን ጌታችን ወንጌልን በማስተማሩ የአይሁድ ካህናት በጲላጦስ ዳኝነት ከሰው፡ እንደ ክፉ አድራጊ ስለ ሰቀሉት፡ ዳግመኛም በጕዲት ዘመን ወንጌል የተገኘበት ክርስቲያን ስለ ተቀጣ፡ ከዚያ ወዲህ በፈላሾች አነጋገር በልማድ (ወንጌል) ወንጀ(ጄ)ል፡ ባረብኛም እንጅል፡ (ወንጌላዊ) ወንጀለኛ ተባለ ይላሉ። ወነጌለን ቡዳን ጠይብን ፀረረ ብለኽ ፀርን ተመልከት።
ወንጀል ሠራ): ቋንዣ ቈረጠ፣ ቤት አቃጠለ።
ወንጀል፡ ዲያብሎስ አዳምና ሔዋን የርሱ ባሮች እንደ ኾኑ ጽፎ በዮርዳኖስ የጣለው መጽሐፈ ዕዳ፡ ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ የደመሰሰው፡ እንደ ወንጀሉ ይደምሰኝ እንዲል ማለኛ። በሲኦልም የነበረውን የስቅለት ለት ዐርብ በሠርክ ነፍሳትን ሲያወጣ እንደ ሠም አቅልጦ አጥፍቶታል።
ወንጂ፡ ባሩሲ ክፍል ካዋሽ በስተ ቀኝ ያለ ቀበሌ፡ ዛሬ የሱካር መኪና የተተከለበት።
ወንጃ፡ ርሳታ፡ ዝንጋታ፡ ወፈፍታ።
ወንጃ አለ፡ ረሳ፡ ዘነጋ፡ ወፈፈ።
ወንጃ አደረገ፡ አስረሳ፡ አዘነጋ፡ አወፈፈ። ደጃች ውቤ ከገዙ ዠምሮ ወንጃ ያደርገኛል እንዳለ ስሜኔ።
ወንጃይ፡ (ዮች)፡ የወነጀለ፡ የሚወንጅል፡ ከሳሽ፡ ስም አርካሽ።
ወንጅ፡ ያገር ስም፡ በጅባት ውስጥ ያለ ወረዳ። ወንጅ በግእዝ መጽሐፍ ይገኛል።
ወንገረዝ፡ ከገመር የሚያንስ ዝንጀሮ።
ወንጋራ፡ (ሮች)፡ ወንካራ።
ወንጌ፡ ከነገደ ጋፋት አንዱ። ታሪከ ታየ ተመልከት።
ወንጌለ ወርቅ፡ ገበታው የወርቅ የኾነ፡ በወርቅ የተለበጠ ወንጌል።
ወንጌላዊ፡ የወንጌል ሰባኪ፡ ሐዋርያ፡ የወንጌል መምር።
ወንጌል፡ (ሎች)፡ የመጽሐፍ ስም፡ ፬ ሰዎች የጻፉት፡ የክርስቶስን አምላክነትና ሰውነት፡ የሠራውን ታምራት፡ የተቀበለውን መከራ የሚያስረዳ መጽሐፍ። ትርጓሜውም የምሥራች ማለት ነው ይላሉ።
ወንጌል፡ ወንጀል፡ በደል (ኤር ፲፬: ፯)፡ ወነጀለን አስተውል።
ወንጝፋ፡ ተራማጅ።
ወንጠፍት፡ ማጥሪያ፡ ነጠፈ።
ወንጠፍት: የወይን፣ የጠጅ፣ የጠላ፣ የቅቤ፣ የዘይት፣ የቅባኑግ ማጥለያ፣ ማጥሪያ (ዝርዝር፣ በለሲ፣ ወንፊት፣ ሽቦ፣ ዝተት)።
ወንጨሬ፡ የወንጪር ዐይነት፡ የአጫብር አውራጃ ቁም ዜማ።
ወንጨር፡ (ትግ)፡ የቆመ ጠጕር።
ወንጫፊ፡ የወነጨፈ፡ የሚወነጭፍ።
ወንጭት፡ ሰጪሶ ውስጥ ያለ ወንዝ።
ወንጭት፡ በደራና በመርሐ ቤቴ መካከል ያለ ታላቅ ዠማ።
ወንጭፈኛ፡ (ኞች)፡ ወንጭፍ የያዘ፡ ባለወንጭፍ፡ አዝመራ ጠባቂ፡ ወይም ጭፍራ (፪ነገ ፫: ፳፭)።
ወንጭፍ፡ (ፎች)፡ (ሞፀፍ)፡ በድል ነጐድ የጠጠር አርቆ መወርወሪያ፡ የሰብል መጠበቂያ፡ የወፍ ማብረሪያ፡ የጠላት ማጥቂያ።
ወንፈለኛ፡ (ኞች)፡ ወንፈል ያለበት፡ ባለወንፈል፡ ገበሬ፡ ሠራተኛ።
ወንፈል፡ (ሎች)፡ ዛሬ ላንዱ ነገ ለሌላው የሚሠራ፡ የመረዳዳት ሥራ፡ ዕኚ።
ወንፈል አወጣ፡ የወንፈልን ብድር ከፈለ።
ወንፈስ፡ ያገር ስም፡ ነፈሰ።
ወንፈስ: በተጕለት ውስጥ ያለ አገር። "ወንፈስ ዐማኔል" እንዲሉ።
ወንፊት (ቶች) (መንፌ): በቁሙ ከካክርማ፣ ከስንደዶ፣ ከሽቦ የተታታ የስፌት የብረት ዕቃ።
ወንፊት፡ የዶቄት መንፊያ፡ ነፋ (ነፈየ)።
ወከለ (ወክሎ ወከለ): ኣመነ፣ ተካ፡ ወኪል፣ ተጠሪ፣ ቶፋ አደረገ፡ "ጥፋቱም ጥፋቴ ልማቱም ልማቴ" ብሎ።
ወከበ (ወኪብ ወከበ): ቸኰለ፡ ጥድፊያ አደረገ።
ወከከ (ወኪክ ወከ): ተሠነጠቀ፣ ተተረተረ (ቋጥኙ፣ ሸክላው)።
ወከከ: ደከመ፣ ሰለተ፣ ዛለ (ሰው)።
ወከክ ማለት: መሠንጠቅ፡ ድክም ዝርግት ማለት፣ መዛል።
ወከክ አለ: ሰተት ዘግ ዟ አለ፣ ወደቀ፣ ተዘረጋ፣ ተኛ።
ወከወከ (ወከከ): ጐተጐተ፣ ወገሰ።
ወከፈ (ወኪፍ ወከፈ): ዐደለ፣ ሰጠ፣ አቀበለ።
ወከፍ: የሚሰጥ፡ አቀባይ።
ወኪል (ሎች): የተወከለ፣ የታመነ፡ እሙን፡ ተጠሪ፣ ቶፋ (የሥራ፣ የነገር)።
ወኪልነት: እሙንነት፣ ታማኝነት፣ ተጠሪነት፣ ቶፍነት።
ወካ (ወክሖ ወክሐ): አወካ፡ ፎከረ፣ ደነፋ፣ ጮኸ፡ ተንጫጫ፡ ግርግር አለ።
ወካዎ ደቢቴ (ኦሮ): "ደኅና ተመለስክ ወይ?" ገዳይ ገድሎ ሲመለስ የሚዘፈን ዘፈን። ምስጢሩ "እዱኛችን ተመለሰ፣ ድል አገኘን" እንደ ማለት ነው። ዳግመኛም ካዎ "ደግ ማለፊያ ዘመን" ማለት ይኾናል።
ወካይ (ዮች): የወከለ፣ የሚወክል፡ በጽፈት፣ ባጤ ይሙቱ ምትክ ሰጪ።
ወክዋኪ: የወከወከ፣ የሚወከውክ፡ ጐትጓች።
ወክፈሌ (ኦሮ): ድኗል ወይ፡ ተርፋል ወይ።
ወክፈሌ: በቡልቻ ውስጥ ያለ አገር። (ያመንዝራ ሴት ግጥም) "የወክፈሌ ጥጥ ተው አትንቀጥቀጥ፡ ባለቤቱ መጡ መጥረቢያ ሊያወጡ። "
"ርጋ፡ ይወጣሉ ደጋ። (መጥረቢያው) ያውልኹ እማገሩ፡ ክፉ አትናገሩ። ያውልኹ እወፍጮ ሥር፡ አታውቁት ይመስል። ያውልኹ ዐልጋ ውስጡ፡ ላይ ላይ አትርገጡ። "
ወኮ ወኮ አለ: አቅራራ፡ ተንደቀደቀ፣ ተድረቀረቀ።
ወኮ: በደብረ ሊባኖስ ባሻገር ያለ ቀበሌ። ወካዎንን ይመልከቱ።
ወኺድ: ወግድ ኼደ።
ወኺድ: ዘወር በል፡ ወግድ፡ ራቅ። 'ወ' ዋዌ ነው።
ወዎ: የኋላ ጦር ደጀን፣ የፊታውራሪ አንጻር፣ ጓዝ ጠባቂ፡ የወደቀ አንሺ፣ የሞተ ቀባሪ። ወቦን ይመልከቱ፣ ከዚህ ጋር አንድ ነው።
ወዎነት: ደጀንነት።
ወዘላ: ለጋ ወጣት፣ ቈንጆ። ወሰላንን ይመልከቱ፡ ከዚህ ጋር አንድ ነው።
ወዘመ (ዘየመ): ዋዜማ ቆመ፡ ዘንበል ቀና አደረገ (በዜማ፣ በማሕሌት፣ በዘፈን፣ በንቅልፍ ምክንያት ሰውነትን)። ዘየመንን ይመልከቱ።
ወዘረ (ወዚር ወዘረ): አስጌጠ፣ ሸለመ።
ወዘበሬታ (ዋዛ በረታ): ዝኒ ከማሁ፡ አገኘ፣ ዐጣ።
ወዘበሬታ: አገኝዐጣ፣ ዛበረ።
ወዘተ: በፍም ላይ አለጕልቻ ነ (ማድጋን፣ ምንቸትን፣ እንስራን) አስቀመጠ፡ በውስጡ ያለውን ለማፍላት፣ ለማሾቅ፣ ለማንገርገብ፣ ለመቀቀል፣ ለማንፈር።
ወዘት: በእሳት ላይ ወይም አጠገብ መቀመጥ። (ተረት) "ጭድ ይዞ ወዘት፡ ሳል ይዞ ስርቆት። "
ወዘት: የመወዘት ሥራ። "በወዘት ፈላ" እንዲሉ።
ወዘና ቢስ: ለዛ ቢስ፣ ክቾ፣ አከቻማ። ለነገሩ ጣዕም፣ ለመልኩ ማማር የሌለው። በወላምኛ ግን "ወሀና ልብ" ማለት ነው።
ወዘና: ውበት። ወዛንን ይመልከቱ።
ወዘና: ውበት፣ ደም ግባት፣ መልክ፣ ለዛ።
ወዘወዘ: ናጠ፣ ሰበቀ፣ ነቀነቀ፣ ቈላ፣ አዋዠቀ፣ አንገሸገሸ። (ሕዝ፴፪፡ ፲። ናሖ፪፡ ፫) ወሰወሰንን ይመልከቱ።
ወዘገ (መዚግ መዘገ): ፈተለ፣ መሀዘ፣ ሳበ፣ ጐተተ፣ አቀጠነ፣ አረዘመ፣ አከረረ (የድር፣ የማግ)። ዘወገንን ይመልከቱ።
ወዘፈ (ወዚፍ ወዘፈ): ወዘተ፣ ረሰከ፣ ረፈቀ፣ ጐለተ፣ አስቀመጠ፣ ቊጭ አደረገ፣ አጋደመ፡ ተወ፣ አስታጐለ።
ወዘፍ (ፎች): ዘለሳ፣ የተኛ፣ የተጋደመ፣ የዘላን ዐጥር። (ነሐ፰፡ ፲፭)
ወዘፍዛፋ: ውዝፍዝፍ፡ የወዛፋ ወዛፋ፡ ደንዳና፣ ወፍራም ሰው።
ወዛ (ውሕዘ፡ ዐረ ወዘዐ): ወዛም ሆነ፡ ላበ፣ አዠ፡ ከንጣት ራቀ፡ ዘይትና ቅቤ የተቀባ መሰለ፣ ራሰ፡ ተቅለጠለጠ።
ወዛሚ: የወዘመ፣ የሚወዝም፡ ዋዜማ ቋሚ።
ወዛም: ባለወዝ፣ ወዙ ጭፍጭፍ የሚል፣ በድሎት ኗሪ። (ተረት) "ወዛም ገማ ቢሉ፡ የነጭ ወሬ ነው። "
ወዛች: የወዘተ፣ የሚወዝት፡ የሚጭን፣ አስቀማጭ።
ወዛፊ: የወዘፈ፣ የሚወዝፍ፡ አስቀማጭ፣ አስታጓይ።
ወዛፋ: ውዝፍ፡ የተወዘፈ፡ ከተቀመጠበት የማይነሣ፡ ውዝት፣ ቅምጥ፣ ርፍቅ፣ ርብክ፡ የጭቃ፣ የእበት ዓይነት።
ወዝ (ወሕዝ): ላብ፣ ላበት፡ የነገር፣ የዜማ ጣዕም፡ የቆዳ፣ የልብስ፣ የገላ ነክ ወዝ ያረፈበት። (ሕዝ፵፬፡ ፲፰) በስተዐይኑ በኩል ያለ የንጀራ መልክ፣ የሰበከት አንጻር። ወዝ ለቅጠልም ይነገራል።
ወዝዋዛ: ውዝውዝ፡ የተወዘወዘ፡ ነቅናቃ።
ወዝዋዥ (ዦች): የወዘወዘ፣ የሚወዘውዝ፡ ነቅናቂ፣ ሰባቂ።
ወዝገብ (ዘገበ አዘገበ): በላይ መንታነት፣ በታች አንድነትና ሹልነት ያለው (ጥድና ወይራ)፡ ከካብ ዐጥር ጋር ዐብሮ የተሠራ፡ ሹለቱ በስተውጭ ያሾተለ።
ወዠለ: ጐተተ፣ ሳበ። ወሸለንን ይመልከቱ።
ወዠመ: አረዘመ፣ ሳበ፣ ጐተተ።
ወዠብ: ዝናምና ነፋስ።
ወዠብ: የምታምር፣ መልከ ቀና፣ ምሉ ሴት።
ወዠድ: ቦታ። ወጀድን ይመልከቱ።
ወዣበረ: ዛበረ፣ ነገር ሳተ። ዘባረቀን ይመልከቱ።
ወየበ: ወረቀ፣ ወራ፣ ብጭጭ አለ፡ ወይባ መሰለ።
ወየነ: ከፍ አለ፡ ዐየለ፣ በረታ፡ ውሃ እንዳልተደባለቀበት ወይን ማለት ነው። (መዝ፸፭፡ ፰)
ወየወ (ዐውየወ): ወይ፣ አወይ፣ ወዮ፣ ዋይ፣ ውይ አለ፡ አለቀሰ፣ ጮኸ።
ወየው: የሐዘን ቃል፡ ወዮ። "ወየው እኔ"፡ "ወየው ዓለም" እንዲሉ።
ወየዘረ (ወዘረ): ተጌጠ፣ ተሸለመ፡ አማረ፣ ተዋበ።
ወያኔ (ዎች): የወያን ወገን፡ ብርቱ፣ ጨካኝ ሕዝብ።
ወያን: ጦር ጠማሽ፡ ግዳይ ፈላጊ።
ወዬ (ወይ ዬ): ዝኒ ከማሁ። "ማሽላዬ ወማይ በላሽ ወዬ። " ዬን እይ።
ወይ (ሁ ኑ): ጥያቄ! የጥያቄ ቃል እንደ ን ያለ፣ ንን የመሰለ። "እከሌ መጥቶ ኼደ ወይ?" (ግጥም) "እንዴት ነኸ እንዴት ነሽ አንባባልም ወይ፡ ሰው ካባቱ ገዳይ ይታረቅ የለም ወይ፡ እቴ ነች እላለሁ፡ ወንድሜ ነው በዪ(ይ)፡ የነፍስማ ነገር ቀርቶ የለም ወይ። " (ዘፍ፲፪፡ ፲፫)
ወይ (ሆይ): የጥሪ መልስ፡ አቤት፣ እመት። (ተረት) "ሳይጠሩት ወይ ባይ፡ ሳይስጡት ተቀባይ። "
ወይ (አው ሚመ): አማራጭ ቃል፡ "ወይ እኔ ወይ አንተ"፡ "ወይ እጅ ወይ ልጅ"። አንድን ይመልከቱ።
ወይ (ኦ): ቃለ አንክሮ፡ ወይም አጋኖ በጭንቅ ጊዜ፡ ፍችው ወዮ። "ወይ ጕድ"፡ "ወይ ጣጣ"፡ "ወይ ታሪክ"፡ "ወይ አንተ ግሩም"። ዎን፣ ሆይን ይመልከቱ።
ወይ ማያ: አፍ፣ ጊዜ፣ ተራ ስም።
ወይ ባይ: ሲጠሩት ወይ የሚል፣ ወይ ብላ፡ ሰሚ፣ ታቦት።
ወይል (ሎች): ቅርፊቱ እንደ ገመድ ተሸልቅቆ የሚወጣ ዛፍ። እረኞች ዕንወቱን ጥይት፣ ቅርፊቱን ጠመንዣ አድርገው ይተሱታልና፡ "የጠመንዣ እንጨት" ይሉታል።
ወይም (ወሚመ): ም ዋዌ ነው። ወይን ወይንን (ወይ ወይን) ለይተው የማያውቁ ጻፎች ግን ወይም በማለት ፈንታ ወይንም እያሉ ይጽፋሉ፡ ስሕተት ነው። አኃኖንን፣ አይንን (ቍ፲፭) ይመልከቱ። ፪ኛውን ወይ አስተውል።
ወይም: አማራጭ ቃል፡ ወይ።
ወይስ: ስ አፍራሽ ነው። (ያዕ፫፡ ፲፪) "ሰውዮ ነገ ትመጣለኸን፡ ወይስ ትቀራለኸ። "
ወይስ: አማራጭ ቃል፡ ወይ።
ወይራ (ሮች): ጥንካሬው የታወቀ ዛፍ። ቀጥታው ሞፈር፣ ፍልጡ ሜሮን የሚሆን፣ ወንዴ ዘይት፡ ፍሬው የማይበላ። ዳግመኛም ቅጠሉ ለጠላ ጋን፣ ፍልጡ ለወተት ዕቃ ይታጠናል፡ በግእዝም አውልዕ ይባላል።
ወይራም: ወይራ በዝቶ የበቀለበት፣ ዶን የኾነበት ስፍራ።
ወይራምባ (የወይራ ዐምባ): ያምባ፣ የመንደር ስም፡ ወይራ ያለበት ቀበሌ (በወግዳና በቡልጋ የሚገኝ)።
ወይባ: ቡክቡካ የጪስ እንጨት፡ የወይባ ፍልጥ፡ ወይም ቡጥ።
ወይባ: የዛፍ ስም፡ መናኞች ቅርፊቱን ወቅጠው፣ አፍልተው ልብሳቸውን እየነከሩ የሚያቀልሙበት እንጨት። ከዚህ የተነሣ ዳባውም ሸማውም ወይባ ይባላል። (ዓሞ፬፡ ፬) "ወይባ ለባሽ" እንዲሉ።
ወይብ: ዝኒ ከማሁ።
ወይብማ: ወይባ መሳይ፣ የወይባ ዓይነት (ከብት፣ ወፍ)።
ወይኒቱ: የሴት ስም።
ወይና (ሱማሌ): ትልቅ (በመጠን፣ በክብር)። "የሺ ወይና"፡ "የሺ ወይናዬ" እንዲሉ ሴቶች የሰርግ ለት "የሺ እመቤት" ሲሉ።
ወይናሐራ (ወይና ሐራ): በደንከሊ በረሓ ያለ የነገድና የአገር ስም፡ በአዳልኛ ጌቶች፣ ባለማዕርጎች ማለት ነው ይላሉ። ወይና ትልቅነታቸውን፡ ሐራ ጦረኛነታቸውንና ጨዋነታቸውን ያሳያል። ይኼውም ሊታወቅ አዳሎች ያተኛነትንና አመንዝራነትን እንደ ውርደት ይቈጥሩታል።
ወይናም: የወይን ተክል የሚሆንበት ቦታ፡ ባለወይን፣ የወይን ጌታ።
ወይናደጋ (ወይና ደጋ): በቈላና በዋና ደጋ መካከል ያለ አገር፡ አየሩና ዝናሙ መጠነኛ የኾነ፡ ለሰው ኑሮ የሚስማማ። ፪ ወንድማማች በደጋና በቈላ ሲኖሩ ቈለኛው የኑሮ ጥቅም ቢያጣ ደገኛው "ወይ ና ደጋ" አለው ይላሉ። ነደደን እይ። ዳግመኛም ወይነ ደጋ (ደጋ ወይን): ወይን የሚያበቅል ደጋ ያሠኛል።
ወይናግፍት (ወይና ግፍት): የንጨት ስም፡ የቅጠሉ ዱቄት ለጣለበት የከብት ዐይን መድኀኒት የሚሆን። ገፈተን ይመልከቱ።
ወይን (ኖች): ከታወቁት አትክልት አንደኛው፡ ፍሬው ምግብና መጠጥ የሚሆን ሐረግ፡ ግንዱም፣ ቅጠሉም፣ ፍሬውም ወይን ይባላል።
ወይን ዐምባ: ወይን የበቀለበት፣ ያለበት መንደር።
ወይን አደረገ (አውየነ): ውሃን ለወጠ፡ ወይን ጠጅ አደረገ። (ዮሐ፬፡ ፵፮)
ወይን እሸት (የወይን እሸት): በቁሙ፡ የሴት ስም።
ወይን ጠጅ (የወይን ጠጅ): ከወይን የተጣለ፣ የተዘጋጀ መጠጥ።
ወይን ጠጅ: ጥለት ቀለም ወይን ጠጅ የሚመስል፡ ሰማያዊ።
ወይንማ (ወይናዊ): መልኩ ወይን የሚመስል ከብት።
ወይንጌ (ጌ ወይን): የወይን ምድር፡ በወግዳ ውስጥ ያለ የጌ ተክለ ሃይማኖት አገር።
ወይኖ: የሰው ስም፡ በላተኛ ገበሬ። (ተረት) "ወይኖ ዐረሰው፡ ወይኖ ጐረሠው። "
ወይዘሪት: ለልጃገረድ የስም ቅጽል፡ በ፲፱፻፵፫ ዓ.ም የካቲት ፳፬ ቀን ከሻለቃ ነጋ ኀይለ ሥላሴ የተሰየመ።
ወይዘር (ሮ): ዐረ ወዚር፡ የተሾመ፣ የተሸለመ፣ መኰንን፣ ባለማዕርግ፣ የነገሥታት ዘር፣ መልከ መልካም፣ ባለሽሩባ። ወይዘሮ በጐንደር ለወንድና ለሴት ይነገራል። (አልቃሽ ስላቶ ሰይፉ፡ "የትም ዞሮ የትም ዞሮ ዞሮ ሚዳ ወደቀ ያ ወይዘሮ። ")
ወይዘሮ (ዎች): እግዝእት፡ የወይዘር፣ የሀብታም፣ የባላባት ሚስት፣ እመቤት፡ ተሸፍና፣ ታጅባ የምትኼድ። ሮ ማክበርንና ማጋነንን ያሳያል። "የወይዘሮ ምስጢር ማጌጥና መሸለም ነው፡ ቀይ ዐፈርን ያፈር ወይዘሮ" እንዲሉ።
ወይዘሮ ዕንቍላል: የዛር እመቤት፡ ቀይ እንስት ዶሮ የሚገበርላት። "ይህ ነገር ምትሀት እንጂ፡ እውነት አይዶለም" (የህዝብ እምነት)።
ወይዘሮ: የባለጠጋ ሚስት፣ እመቤት። "ወይዘሮ ለሴት ቅጽል ነው።"
ወይዛዝር (ሮች): ወይዘሮዎች፣ እመቤቶች። "ወይዛዝርት"፣ "ወይዛዝርቶች" ማለት ስሕተት ነው። ወዘረን ይመልከቱ።
ወይጦ (ዎች): የነገድ ስም፡ በጣና ዙሪያ ተሠርቶ በቀስት ጕማሬ እያደነ የሚኖር ሕዝብ፡ ጕማሬውም ከባሕር የሚወጣው ዘፈን ሲሰማ ነው።
ወይፈን (ተይፈን): በበሬና በወገዝ መካከል ያለ አጕሬሣ፡ ለመጥቃት፣ ለመገረፍ የደረሰ፡ ወይም ቀንቶ የሚያርስ፣ ያልተወቀጠ፣ ያልተቀጠቀጠ።
ወይፈኖች (ተያፍን): ፪ እና ከ፪ም በላይ ያሉ ብዙዎች። (ኤር፶፡ ፳፯)
ወይፋፍን (ኖች): ወይፋፍን ውስጠ ብዙ፡ ወይፋፍኖች ወይፈኖች ማለት ነው። (ሕዝ፵፭፡ ፳፫) (ግጥም) "ወዴት ኼዱና አባት በሮቹ፡ ፈሩን አጠፉት ወይፋፍኖቹ። "
ወዮ (ኦ): ወየው፡ የማክበርና የማጋነን፣ የማድነቅ ቃል፡ ሲነገርም ምንኛ ይከተለዋል። "የክርስቶስ በድንግልና ተፀንሶ መወለድ ወዮ ምንኛ ድንቅ ነው!" ወዮ የ ወየው ከፊል መኾኑን ልብ አድርግ፡ ተመልሰህ ፰ኛውን ወይ አስተውል።
ወዮ (ወይ ወይሌ አሌ): የማስፈራራትና የዛቻ ቃል፡ ትርጓሜው ዋይ። (ራእ፱፡ ፲፪)
ወዮ ወዮ: ወየው ወየው፡ ዋይ ዋይ (ተመላልሶ ሲነገር)። (ራእ፰፡ ፲፡ ፲፫) በመጨረሻውም ለት እየተጨመረበት በስምንት ሰራዊት ይዘረዘራል።
ወዮለት (ወይ ሎቱ): ወዮ ለርሱ፡ ወዮታ አለበት፡ ይገባዋል። (ኢሳ፳፱፡ ፳)
ወዮላት፡ (ወይ ላቲ): (ራእ፲፰፡ ፲)
ወዮላቸው፡ (ወይ ሎሙ):
ወዮላችኹ፡ (ወይ ለክሙ): (ራእ፲፪፡ ፲፪)
ወዮልሽ፡ (ወይ ለኪ):
ወዮልን (ወይ ለነ): ወዮ ለኛ፡ ወዮታ አለብን፡ ይገባናል።
ወዮልኝ፡ (ወይ ሊተ):
ወዮልኸ፡ (ወይ ለከ):
ወዮታ፡ ወዮ ማለት፡ ወዮ።
ወዮታ: ወዮ ማለት፡ ዋይታ፣ ለቅሶ።
ወደ (ወእደ): ዐቢይ አገባብና በቂ ቅጽል። "መልክተኛ ወደ ላከው ተመለሰ። "
ወደ ላይና ወደ ታች ተወረወረ፡ በገደል፡ በግንብ፡ በምሰሶ ላይ ፈጥኖ ዐለፈ፡ ተንሻለለ፡ ገበሎው፡ እባቡ፡ እንሽላሊቱ: (የእንቅስቃሴ አይነት)።
ወደ ስናቅ፡ ወደ ሰርን ወጣ፡ ዐፈነ፡ ሰነፈጠ፡ ትን አለ፡ ዐነዘዘ: (የእንቅስቃሴ አይነት)።
ወደ ውስጥ ገባ: ሠረገ።
ወደ ዛፍ ወይም ወደ ሌላ ነገር ላይ ወጣ: (የእንቅስቃሴ አይነት)።
ወደ: የቦታ ደቂቅ አገባብ። "ወደ ምድር ወረደ፡ ወደ ሰማይ ወጣ። "
ወደ: ጊዜ፣ ሰዓት። "ወደ ማታ እመጣለሁ። "
ወደለ: በወዴላ ላይ ጨመረ።
ወደለ: ወፈረ፣ ደነደነ (ተገብሮ)።
ወደላት (ቶች): ከወሸኸሬ የሚበልጥ፣ ከብልጫ የሚያንስ፣ ከወደ ሆዱ ወፍራም የሆነ ዓሣ።
ወደል (ሎች): ወፍራም፣ ደንዳና፣ ትልቅ፣ ግዙፍ ("ወደል አህያ" እንዲሉ)።
ወደል ድጓ: መዝገብ ድጓ።
ወደል ጋዝ (ወደል ጓዝ): የጓዝ መኛ አጋሰስ፣ ምስንጅር ("የነፋስ ወደል ጋዝ" እንዲሉ)።
ወደመ: ጠፋ፣ ታጣ፡ ዕልም አለ።
ወደሰ (ወድሶ ወደሰ): አመሰገነ፡ ምስጋና አቀረበ፣ ሰጠ።
ወደረ (ወተረ): ገመደ፣ ጠመረ፡ ትክክል አደረገ።
ወደረ: እሰጥ አለ፡ ውርርድ ተከለ።
ወደረ: ጠመጠመ፣ ጋዳ፣ አሰረ። (ተረት) "አገር ያደረው ዘንዶ የወደረው። "
ወደረኛ (ኞች): ጠላት፣ ባለጋራ፣ ተቃዋሚ፣ ተቃራኒ፣ ተፈካካሪ። (ሉቃ፩፡ ፸፩)
ወደራ: በመንዝ ክፍል ያለ አገር።
ወደሬ: የኔ ወደር፣ እኩያዬ፣ አቻዬ።
ወደር የለኸ/የለሽ: የወንድና የሴት መጠሪያ ስም።
ወደር: እኩያ፣ አቻ፣ ጣምራ፡ ባል ወይም ሚስት።
ወደሮ (ዎች): ወፍራምና ረዥም ገመድ፡ ዛፍን፣ በሬን ጠልፎ የሚጥል፡ "ወደሮ ሰጕራጌ ነው"፡ በአማርኛ ደበል ይባላል።
ወደቀ (ወዲቅ ወድቀ): ተጣለ፣ እንቦፍ አለ፡ ተጋደመ፣ ተኛ፡ ነጠበ፣ ተገደፈ። (ማቴ፯፡ ፳፯)
ወደቀ: አደጋ ጣለ። (፩ሳሙ፡ ፳፪፡ ፲፰)
ወደቀ: ደኸየ፣ ከሰረ፣ ተዋረደ፡ ረከሰ።
ወደቀበት: ተጣለበት፣ ተዘረጋበት ("መሬቱ ቀላድ ወደቀበት" እንዲሉ)።
ወደበ: ወደብ ሠራ፣ አደረገ፣ አበጀ፡ ደለደለ፣ አስተካከለ።
ወደብ: የባሕር ዳር ሐይቅ፣ በር፣ መግቢያና መውጫ፣ የመርከብ መቆሚያ፣ መጠጊያ፣ ማረፊያ።
ወደቦች: ምጥዋ፣ ዓሰብ፣ ኦቦክ፣ ጅቡቲ፣ ዘይላ፣ በርበራ፣ መቃድሾ።
ወደቴ: ጕልማሳ፣ ዘዋሪ።
ወደነ: ልብሱን ከትከሻው በታች ዝቅ አደረገ፡ ክንዱን አወጣ፡ አደገደገ (ለማደል፣ ለማሳለፍ)። ቦደነን ይመልከቱ፡ ከዚህ ጋር አንድ ነው።
ወደነ: አሰረ፣ ቈረኘ፣ ቀረቀበ፣ አያያዘ።
ወደወደ (ወደ): መላልሶ ወዲያው ወዲያው መታ፣ ደበደበ፡ በጦር ወጋ፣ አማሰለ፣ ወከወከ።
ወደዚህ (ወዶ እዚህ): ወደዚህ ቦታ።
ወደዚያ (ወደ እዚያ): ወደዚያ ቦታ።
ወደዚያ በቂ። የዚያ፣ የነዚያ፣ የርሱ፣ የነርሱ ጠቃሽና በቂ።
ወደዚያ: በቂ።
ወደየ: ጨመረ፣ ዶለ፣ አገባ (ግእዝ)።
ወደደ (ወዲድ ወደ): ፈቀረ፣ አፈቀረ፣ ፈቀደ፣ አመነ፡ ወዳጅ አደረገ። (ዮሐ፲፫፡ ፴፬) ምሳሌ: "ወዶሽ ከተደፋሽ ቢረግጡሽ አይክፋሽ" (ተረት)።
ወደደ፡ በዙሪያ ዐጨደ፡ ሠራ።
ወደደ፡ ከበበ፡ ዞረ፡ (የፊተኛው እንዳይኼድ፡ የኋለኛው እንዳይከተል እንዳይለጥቅ) አገደ፡ ከለከለ፡ መለሰ።
ወደደ፡ ከበደ፡ ተነ፡ ቀፈፈ። "ዛሬ ቀኑ ወድዷል። "
"ፊቴን ይወድደኛል። "
ወደደ፡ ከፈለ፡ ቈረጠ፡ ቀደደ፡ ሠነጠቀ።
ወደደ: ዐበረ፣ ገጠመ፣ አንድ ኾነ (በሥራ፣ በንግድ)።
ወደድ: ወዳድ ("ማሪያም ወደድ" እንዲል ፈላሻ)። ቢትወደድን ያስተውሉ።
ወዲህ (ወደ ይህ): ወደዚህ በኩል፣ እዚህ።
ወዲህ ማዶ: ወንዙን ሳይሻገሩ፣ በዚህ በኩል።
ወዲህና ወዲያ: ወደዚህና ወደዚያ። (ምሳ፳፮፡ ፪)
ወዲህኛው (ወደ ይህኛው): ቅርብ ስፍራ፣ ይህ ዓለም።
ወዲያ (ወደ ያ): ሩቅ፣ ወዲያ። ምሳሌ: "ከግዜር ወዲያ ፈጣሪ፡ ከባለቤት ወዲያ መስካሪ፡ ከጠጅ ወዲያ አስካሪ። "
ወዲያ ማዶ: ወንዙን ተሻግሮ፣ አልፎ።
ወዲያ ወዲያ: እዚህም እዚያም።
ወዲያ: በኋላ። "ከነግ ወዲያ"።
ወዲያ: በፊት። "ከትላንት ወዲያ"።
ወዲያልኝ ወዲያ: የጥላቻና የነቀፌታ ቃል ነው። ይራቅልኝ፣ ይወገድልኝ፡ አይኑን አያሳየኝ ማለት ነው።
ወዲያልኝ: ለኔ ወዲያ፣ መራቅ፣ መወገድ፣ መለየት አለኝ፡ ምናኔ ይገባኛል።
ወዲያኛው (ወደ ያኛው): ሩቅ ስፍራ፣ መንግሥተ ሰማይ።
ወዲያው: ቶሎ፣ ቸኩሎ፣ ፈጥኖ፣ ቀጥሎ።
ወዲያዎች/ወዲያኞች: በሩቅ፣ በወዲያ ያሉ ሰዎች፣ ከብቶች፣ ስፍራዎች።
ወዳሚ: የሚወድም፡
ጠፊ።
ወዳምቃ: በታች ወግዳ ውስጥ ያለ አገር (የቅዱስ ሚካኤል አጥቢያ)።
ወዳሪ: የወደረ፣ የሚወድር፡ ገማጅ፣ አሳሪ።
ወዳሽ (ወዳሲ): የወደሰ፣ የሚወድስ፡ አመስጋኝ።
ወዳቂ: የሚወድቅ፣ የሚተኛ፣ ተዋራጅ ("የአባያ ልጅ ወዳቂ" - ተረት)።
ወዳቂ: የማይነሣ የግእዝና የአማርኛ ንባብ።
ወዳቃ: ዘባጣ፡ ዋዲያት ምድር።
ወዳቢ (ዎች): የበረሃ በሬ፣ ቀንዱ የላም የሚመስል እንስሳ።
ወዳቢ: የወደበ፣ የሚወድብ፣ ወደብ ሠሪ።
ወዳቦ: ከደቦል የሚያንስ ዝንጀሮ፣ ጨውቴ።
ወዳኝ: የወደነ፣ የሚወድን፡ ቦዳኝ፣ አሳሪ፣ ቀርቃቢ።
ወዳይ: የወደለ፣ የሚወድል፡ ጫኝ።
ወዳደቀ: መላልሶ ወደቀ፣ ተንጠባጠበ።
ወዳዴ: የወዳድ ወገን፣ ወይም የሚያፈቅር። "ሆያ ሆዬ ጕዴ፡ ዝና ወዳዴ" እንዲሉ ልጆች።
ወዳድ: የሚወድ፣ አፍቃሪ ("ሰው ወዳድ" - ፍቅረኛ)።
ወዳጁ: የርሱ ወዳጅ።
ወዳጃ (ኦሮ): ምሕላ፣ ሌሊት ድቤ እየመቱ ሲጮኹት የሚያድሩ ጩኸት፣ ልመና።
ወዳጄ ልቤ: ከብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የተጻፈ ልብ ወለድ መጽሐፍ።
ወዳጄ ነኸ: የሰው ስም።
ወዳጄ: የሰው ስም።
ወዳጄ: የኔ ወዳጅ።
ወዳጅ (ጆች): ወዳድ፣ የወደደ፣ የሚወድ፡ ባለል፣ ታማኝ። (ምሳ፲፰፡ ፳፬። ዮሐ፲፭፡ ፲፭) "ያንዠት የልብ ወዳጅ" እንዲሉ። "የከንፈር ወዳጅ" (በመሳም ብቻ ልጃገረድን ወዳጅ የሚያደርግ ጉልማሳ)።
ወዳጅ ዘመዴ ምነው: የመሰንቆ ምት አዝማች።
ወዳጅ ገዛ፣ ጠላት ገዛ፡ አበጀ። (ተረት)፡ "ግዛኝብለው ለመሸጥ አሰበኝ"።
ወዳጅ: ውሽማ።
ወዳጅነት: ወዳጅ መሆን፣ ባለልነት።
ወዳጆ: በወዳጃ የተገኘ ልጅ ስም።
ወዳጇ: የርሷ ወዳጅ።
ወዴህ: ወዲህ።
ወዴላ: ከኮርቻ በስተኋላ ያለ ጠፍር (ከበቅሎና ከፈረስ ዥራት የሚገባ)፣ ከወደ ስሩ የወፈረ፣ የዳጐሰ። ሌላ ስሙ አቡነ ዘለብ።
ወዴላ: የመጫኛ ሌበቻ።
ወዴሶ: የአገር ስም። ኦሮ ዋንዛን "ወዴሳ" ይለዋልና፡ "ዋንዛ ያለበት ዋንዛም" ማለት ነው።
ወዴት (ወደ የት): የጥያቄ ንኡስ አገባብ (የት?)።
ወዴት ነው: የት አለ።
ወዴት አለ: የት ተቀመጠ።
ወዴት ኼደ: የት ዐለፈ።
ወዴት: ጥያቄ። ወደን ይመልከቱ።
ወድሏል: ወፍሯል፣ ደንድኗል፡ ውዴላን ጭኗል።
ወድድ፡ የሰው ስም፡ "ክፈል፡ ጣክበብ" ማለት ነው።
ወዶ ገባ (ቦች): የዶማ፣ የመጥረቢያ ዛቢያ (በተፈጥሮው ጐባጣ ቀላሳ ስለሆነ ሳይታረቅ የተዋደደ)።
ወዶ ገባ: በፈቃዱ ሎሌ የነበረ ሰው። ምሳሌ: "ወዶ ገባ ልብሱ ዳባ" (ተረት)።
ወዶ: ፈቅዶ።
ወዶማ (ኦሮ): የበጎች በሽታ፡ አፍንጫቸውን እያፈነ ትንፋሽ የሚከለክላቸው (ኩልኩልት፣ ደደቆ)።
ወዶን አይሥቁ: አሉታ በጽድቅ ይፈታል፡ ዐዘነተኛው ፈቅዶ ጥርሶቹ ይሥቁን ማለት ነው። ቈለ ብለው ቂልን ይመልከቱ።
ወዶወዶ አለ (ሀበበ): ናቀ፣ ሰደበ፣ አጸየፈ፣ አረካከሰ፡ "አይበሉ በሉ" አለ።
ወዶወዶ: ወዲያ ወዲያ፣ ቢያክ ቢያክ ("ወዶወዶ በነጕንጭት ለምዶ" - ግጥም)።
ወጀበ (ወጊብ ወገበ): ተገበ፣ በረደ።
ወጀበ: ተገበ፣ በረደ።
ወጀብ: ተግብ፣ ውሽንፍር፡ ክረምት ሲገባ ከነፋስ ጋር የሚመጣ ዝናም ነው። (ምሳ፳፭፡ ፳፫። ኢሳ፳፭፡ ፲፡
፬። ናሖ፩፡ ፫)
ወጀወጀ: ወገወገ።
ወጀድ (ዶች): አረ ወጀደ (አገኘ)፡ ቦታ፣ የአትክልት ስፍራ (በአጥር፣ በቅጥር የተከበበ)። (ሚክ፫፡ ፲፪) በግእዝ ዐጸድ ይባላል። "ዘሩ ወገደ ነው፡ የሎጥን ከአብርሃም መለየት ያሳያል። " ወዠድ ተብሎም ሊጻፍ ይችላል።
ወጀድ: መካነ መቃብር። (ዘፍ፳፫፡ ፲፫፡ ፲፯፡ ፲፱፡ ፪፡ ፳)
ወጆ: ጉማ ዋጀን ያመለክታል፡
የነፍስ ዋጋ፣ ጉማ፣ ከብት፣ ገንዘብ (ሰማንያ ብር)።
ወገ ጠርቅ፡ ብዙ አይነት ወግ የሚናገር፣ በችንካር ምላሱ የፊተኛውን ከኋለኛው ጋር የሚያጋጥም ሰው።
ወገል (ሎች): ይህ ቃል ማረሻን፣ ድግርን እና ሞፈርን የሚያያይዝ የብረት መሳሪያ አይነት ነው። ከላይ ቈላፋነት ያለው እና ከታች ቀለበትነት ያለው ሲሆን፣ የሜንጦና የውሲያን የመንዘሮር አይነት ነው። የበሬና የገበሬ ዕቃ አካል ነው።
ወገል ጤና: ይህ በዋድላ ደላንታ ክልል ያለ አገር ስም ነው።
ወገሜት: ባዶ አሬራ፡ ቅቤ የወጣለት ወተት።
ወገሜት: ከባዶ ዐገመ ጋር የተያያዘ ቃል ነው።
ወገሰ (ወጊስ ወገሰ): ጐተጐተ፣ ወተወተ (በነገር፣ በሥራ)። ሞገተን እና ከሰን የሚሉትን ቃላት እንድትመለከቱ ይመክራል።
ወገረ (ወጊር ወገረ): በደንጊያ መታ፣ ደበደበ። (፩ነገ ፲፡ ፲፪፡ ፲፡
፲፰። ፪ዜና፡ ፳፬፡ ፳፩። ዮሐ፲፡ ፴፩፡ ፴፪። ፲፩፡ ፰)
ወገረ: ድንጋይ ጣለ፣ ቈለለ፣ ከመረ።
ወገረት: እድፈ ከል፣ ግልድም ሽርጥ፣ የሥራ ልብስ (ከሥራ በኋላ የሚጣል)። በግእዝ መክፌ ይባላል፡ ፈረንጆችም ታብሊዬ (apron) ይሉታል።
ወገረት: ወረወረች፣ ጣለች (ግእዝ)።
ወገራ: በስሜንና በደንቢያ መካከል ያለ አገር።
ወገራ: ድብደባ፣ የድንጋይ ምት።
ወገሬ (ወገራዊ): የወገራ ሰው።
ወገር (ወግር): ሞላላ ዳስ፣ ሰቀላ (በላዩ ብዙ እንጨት የተጣለበት)።
ወገርት (ቶች): የሽቱ እንጨት ስም ነው። ስሩ ማጠንት የሚሆን፣ ቅጠሉ በወይና ደጋ የሚበቅል፣ እፍም ላይ ሲጥሉት ሽታው የሚጣፍጥ ነው።
ወገርኛ: ሞላላኛ ቤት፣ ሰቀልኛ።
ወገሮ: ስልሶ ሰርመዲ ቀጸላ ሻሽ ጦሊት አይነ ርግብ (በራስና በፊት ላይ የሚጣል)። በግእዝ ግን መታው፣ ጣለው ማለት ነው።
ወገሸ: ተቈጣ፣ ወነበደ፣ በረረ፣ ሮጠ፣ ፈረጠጠ።
ወገበ (ወጊብ)፡ ወገብ ያዘ፣ ዐነቀ፣ በወገብ ተጠመጠመ።
ወገበ ቀጪን/ወገበ ቀላል፡ ዘላይ፣ መር ባይ፣ ተወርዋሪ (ፈጣን)።
ወገበ ነጭ፡ በትክክል ትምህርት ተምሮ ያላወቀ ሰው፣ ደጐባ።
ወገቡን ሞከረ፡ ዕዳሪ ወጣ፣ ተናጻ፣ ኰሳ ዐራ።
ወገቤን አለ፡ ደከመ፣ ዐለቀ፣ ገንዘቡ ሳይበቃ ቀረ።
ወገብ (ቦች) (ሐቋ)፡ የመቀነትና የጥብጣብ/የትጥቅ ማያ።
ወገብን፡ ዝተገተ፡ ሰበረ፡ አነከተ፡ ጐተተ: (የእንቅስቃሴ አይነት)።
ወገብጌ፡ ጥብጣብ፣ ቀበቶ የሚገባበት (የሱሪ ጫፍ)።
ወገቦ፡ የዥራተ ረዥም ዠርባው ጥቁር፣ ሆዱ ቀይ ወፍ።
ወገተ: አወጋ፣ አወራ።
ወገት: ወግ፣ ወሬ። ወጋን ይመልከቱ።
ወገነ: ዘመደ ማለት ወይም ወገን አደረገ ማለት ነው።
ወገነኛ: ወገን ያለው፣ ባለወገን፣ ዘመደ ብዙ።
ወገን (ኖች): የሩቅ ዘመድ፣ ዘር፣ ጐሣ፣ ትውልድ፣ ነገድ ያመለክታል። (ዘዳ፳፱፡ ፲፡ ፰። ሉቃ፳፫፡ ፩)
ወገን ሆነ: ተዘመደ፣ ዘመድ ተባለ።
ወገን ለየ: ከሁለት ተከፈለ፣ ለጥል ወገን።
ወገን ተነዳበት: ከብት ረገጠው፣ ኼደበት (ለምሳሌ የጤፍ እርሻው በወንጀለኛው እንደራስ ዓምዶ)።
ወገን ጠባቂ: ጐረደማን፣ እረኛ።
ወገን: የከብት፣ ያጋሰስ መንጋ።
ወገን: ደግሞ ጐን፣ ቀበሌ፣ በኩል፣ ዘንድ፣ ክፍል ማለት ነው። ምሳሌ: "ለጦርነት በናንተ ወገን በርቱ፡ በኛ ወገን ግድ የለም። "
ወገን: ፍጥረት፣ ዓይነት ማለት ነው። ምሳሌ: "የአውሬ የወፍ ወገን የሰማይ የምድር ወገን" እንዲሉ።
ወገንነት: ወገን መሆን፣ ዝምድና፣ ዘመድነት።
ወገኛ (ኞች)፡ ባለወግ፣ ነበርነ ባይ፣ አበል ያለው፣ ባለማዕርግ፣ እንደነበረ የሚያወጋ።
ወገወገ፡ ዋጋ መላልሶ ነገረ።
ወገዘ (ወጊዝ)፡ አወገዘ።
ወገዝ (ዞች)፡ ከጥጃ በላይ/ከወይፈን በታች ያለ(ች) ከብት።
ወገዝማ፡ በጠራ ውስጥ ያለ ቀበሌ።
ወገደ (ወጊድ)፡ ለየ፣ አገለለ፣ አራቀ።
ወገገ፡ ከፈተ፣ አበራ፣ ብርሃን አሳየ (ከጎህ በኋላ)።
ወገግ አለ፡ ተከፈተ፣ በራ፣ ጥቂት ታየ፣ ፈገገ።
ወገግ፡ የታላቅ ተራራ ስም (በሐረርጌ ቆላ)፣ ከምድር ከፍ ስላለ ወገግታ ስለሚያገኝ ተባለ።
ወገግታ፡ "ወግ" ማለት።
ወገግታ፡ የንጋት/የጧት ብርሃን፣ የሰማይ/የምድር ፈገግታ።
ወገጠ፡ አስቸገረ፣ አስጨነቀ፣ አወከ፣ አፈቸለ፣ ወጠረ፣ አላናግር፣ አላስኬድ አለ።
ወገጠ፡ ወቀጠ።
ወገጥ፡ ችግር፣ ጭንቅ፣ ሁከት።
ወገፈ (ዐረ ወቀፈ ቆመ): ፈጽሞ አረጀ፣ ደከመ፣ መኼድ መራመድ አቃተው፣ ቆመ፣ አረፈቀ፣ እቤት ዋለ።
ወጊ፡ የሚወጋ፣ ለታሚ፣ አብሪ ("ጥላ ወጊ ፋና ወጋ")።
ወጊት፡ ሰውን የምትወጋ እሾኸ አፍ ዓሣ።
ወጋ (ወግአ) - የተለያዩ ትርጉሞች፡ "ወጋ" የሚለው ቃል እንደ አውድ ሁኔታ የተለያዩ ትርጉሞች አሉት: መወጋት (መቆስል/መውጋት): ትርጉም፡ ጓጐጠ፣ ጐጐመ፣ ለተመ፣ ተመተመ፣ ሸቀሸቀ፣ ደነጐረ፣ ደደቀ፣ ዘረከተ፣ ሸበለቀ፣ ጠቀጠቀ፣ ጠቅ አደረገ፣ ነደፈ፣ ጠቆመ (በቀንድ፣ በጦር፣ በአንካሴ፣ በሹል ነገር፣ በመርፌ፣ በወስፌ፣ በሾኸ፣ በጥፍር)።
ወጋ፡ ለኮሰ፣ አበራ።
ወጋ፡ መታ፣ ወበቀ፣ ጐዳ፣ አሳመመ። ምሳሌ፡ "ፀሐይ ወጋው"፣ "እንባ ሲሻኝ አይኔን ጪስ ወጋኝ"።
ወጋ፡ በገበጣ ጉድጓድ አራተኛ ጠጠር ጨመረ፣ አስቀመጠ።
ወጋ ወጋ አደረገ፡ በቀላል ሰፋ፣ ጸለየ፣ ፈታ። ምሳሌ፡ "እንደ ድኻ ፍታት ወጋ ወጋ አርጉና..." (ግጥም)።
ወጋ፡ ጻፈ፣ አመለከተ (ጠመንዣን)።
ወጋሪ (ሮች): የወገረ፣ የሚወግር፣ መቺ (ሰውን በድንጋይ የሚደበድብ)። (ሉቃ፲፫፡ ፴፬)
ወጋሪ: ዓሣን ወርውሮ በድንጋይ ላይ የሚጥል፣ የሚመታ ("ዓሣ ወጋሪ" እንዲሉ)።
ወጋሪ: ጭራ የተተበተበበት ድንጋይ በጫፉ የታሰረበት የክር መንታ ገመድ ወደ ባህር የሚጥል (ለመያዝ)።
ወጋየሁ (ወግ አየሁ)፡ የወንድና የሴት ስም።
ወጋጅ፡ የወገደ፣ የሚወግድ፣ የሚያርቅ፣ አግላይ።
ወጋገረ: መታታ፣ ደባደበ፣ ጣጣለ (ድንጋይ ወርውሮ፣ እንጨት ቈርጦ)።
ወጋግራ (ሮች): ባላ ደገፋ (በላዩ ክባስ ወይም ዘንዶ ተጥሎበት) በሰበሰብና በስተውስጥ ጣራ የሚደግፍ፣ የሚሸከም ነው።
ወጋጭ (ጮች)፡ የወገጠ፣ የሚወግጥ፣ አስቸጋሪ፣ አዋኪ፣ አፈቻይ፣ ወጣሪ።
ወጋፋ: የወገፈ፣ ደካማ ሽማግሌ በሬ።
ወጌሻ (ኦሮ): ሐኪም፣ ዐዋቂ፣ ልበ ብርቱ፣ እጀ ብልህ። የተወጋ የሚያድን፣ የተሰበረ የሚጠግን፣ ጠጋኝ (በበሽታ ላይ የሚወገሽ)።
ወጌሾች: ሐኪሞች፣ ዐዋቆች።
ወግ (ወግዕ)፡ እጅግ የቆየ/የዘገየ ዜና፣ ወሬ፣ ነገር፣ የታሪክ አይነት (እንዲህ ነበር)። ደንብ፣ ሥርዓት፣ ልማድ።
ወግ ለጠጠኝ፡ የተግደርዳሪ ሰው ስም።
ወግ፡ በአይኑ የሚወጋ የሚያሳምም ("ዓይነ ወግ")።
ወግ አነሣ፡ ከድግስ ቤት የልቅናውን ወሰደ።
ወግ ዓዋቂ፡ ሽማግሌ፣ መምር።
ወግ፡ የካህናት አለቆች አበል (አንድ ዳቦ፣ አንድ እንስራ ጠላ፣ ታናሽ ሥጋ፣ 20 እንጀራ)።
ወግ ደረሰኝ፡ የሰው ስም (የፈጣሪ ምርቃት ሆነልኝ ማለት ነው)።
ወግር: ቁልልታ፣ ጉባ፣ ኮረብታ።
ወግዳ፡ የአገር ስም (ከተጉለት የሚዋሰን)። ወግዳውያን ጦረኛ በመሆናቸው ጋሎች "ወግዳ ወራና" ይሉታል።
ወግዴ/ወግዳዊ፡ የወግዳ ሰው።
ወግድ፡ ትእዛዝ አንቀጽ ("አርቅ፣ አግልል ሰውነትህን")።
ወግዶች/ወግዳውያን፡ የወግዳ ተወላጆች።
ወግፋል: ደክሟል፣ አረፍቋል።
ወጠምሻ (ጠመሰሰ): ውዲላ፣ ጠምሳሽ፣ ጐበዝ፡ ገላው ጥርንቅ ያለ፣ ወፍራም፣ ጠዘል፣ ደቦል (ሰው)።
ወጠረ (ወቲር ወተረ): ነፋ፣ ቀበተተ፡ ዘረጋ፣ ሳበ፣ ለጠጠ፣ ገተረ (የሆድ፣ የብራና፣ የድንኳን)።
ወጠረ: አኰራ፣ ቈነነ። "ቶሎ ቶሎ ና ምን ይወጥርኻል። "
ወጠረ: ያማርኛ፡ ወተረ: የግእዝ ነው። ተረንን ይመልከቱ።
ወጠረ: ጠየቀ፣ ወገጠ፣ አስቸገረ።
ወጠቀ (ዕብ፡ ያጻቅ): ዐጨቀ፣ ጨመረ፣ ጠቀጠቀ፣ አብዝቶ በላ፣ ጠሰቀ።
ወጠነ (ወጢን ወጠነ): ማንኛውንም ሥራ ዠመረ፣ ፈለመ፣ ቀደመ፣ መሠረተ።
ወጠወጠ (ትግ፡ ወጥወጠ፡ ሰበቀ): ወዘወዘ (ጦርን)፡ አሞጠሞጠ፣ ወጥ ሠራ፣ ቈላ፣ ጠበሰ፣ ቀቀለ፣ አማሰለ።
ወጠጠ: ወጠረ፣ ገተረ፣ ቀተረ።
ወጠጤ (ዎች): የወጠጥ ዓይነት፣ ወገን። በጥቦትና ባውራ መካከል ያለ፣ ለመስረር ለመጥቃት የደረሰ ፍየል፣ በግ። (ዘሌ፬፡ ፳፭)
ወጠጤ ወጠጦ ሆነ: ከጥቦት በለጠ።
ወጠጥ: የወጠጠ፣ የሚወጥጥ፡ ገታሪ፣ ቀታሪ።
ወጠጦ: ዝኒ ከማሁ።
ወጠጦች: ወጠጤዎች።
ወጣ (ቅጽል): የወጣ። "ቤተ ወጣ" እንዲሉ።
ወጣ (ወፂእ): መውጣት።
ወጣ (ወፅአ): ከውስጥ ወደ ውጭ ኼደ፣ በቀለ፡ ተወለደ፡ ታየ፣ ተገለጠ። ወለቀንን ይመልከቱ።
ወጣ አለ: ብቅ አለ።
ወጣ ገባ አለ: ብቅ ጥልቅ አለ።
ወጣ ገባ: መጥፎ መንገድ፣ አስቸጋሪ፡ ዐጓጕል፣ ሥርጓጕጥ ስፍራ።
ወጣ: ሠረጠ።
ወጣ: በላይ ሆነ፣ ተገለበጠ (የቅቤ፣ የቂጥኝ፣ የሌላም ነገር)።
ወጣ: ተለየ፣ ተወገደ። (ሰቈ፱፡ ፲፱) (ግጥም) "ሰተት ብለኸ ገብተሽ ሰተት ብለኸ ውጣ፡ አንድ ነገር ቢሉኸ እኔ በጕድ ልውጣ። "
ወጣ: ተነገረ፣ ተሰማ። (ተረት) "ካፍ ከወጣ አፋፍ። "
ወጣ: ተጐለጐለ፣ ተዘረገፈ። (፪ዜና፡ ፳፩፡ ፲፱)
ወጣ: አደገ፣ ቁመት ጨመረ።
ወጣ: ከምድር (ከታች) ወደ ዛፍ፣ ወደ ላይ፣ ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ አለ፡ ዐረገ። (ግብ ሐዋ፩፡ ፪፡ ፲፩)
ወጣ: ዘለቀ፣ ረሰ (ዳዊቱን)።
ወጣ: ፈለቀ፣ ተቀመጠ፣ ዐደረ። "ዛር ወጣበት" እንዲሉ።
ወጣሪ(ዎች): የወጠረ፣ የሚወጥር፡ ለጣጭ፣ ታሪ፣ ወጋጭ፣ አስቸጋሪ፡ ደበናንሣ፣ ፋቂ።
ወጣቂ: የወጠቀ፣ የሚወጥቅ፡ ጠቅጣቂ፣ በላተኛ።
ወጣት፡ ልጅ፡ ሽንጠ' መልካም፡ ሽንቅጥ፡ ፎጠና፡ ጠምጣማ: (የወጣትነት ገጽታ መግለጫ)።
ወጣት: ልጅ እግር።
ወጣት: ገና የሚያድግ ልጅ እግር፡ አዲስ ለጋ ቀንበጥ። ጣትን ይመልከቱ፡ የዚህ ከፊል ነው።
ወጣቶች: ልጅ እግሮች፡ ቀንበጦች።
ወጣን ተመልከት። (የሽንብራ አፍንጫ): እጅግ በጣም ትንሽ ጫፍ፡ ዐጪር ሰው፡ የወንድ ብልት።
ወጣኝ (ኞች/ወጣኒ): የወጠነ፣ የሚወጥን፡ ዠማሪ፣ ፈላሚ።
ወጣጣ: በቃቀለ፣ ብቅ ብት አለ፡ ወላለቀ።
ወጥ (ወፅእ): የምግብ ስም፡ የንጀራ መበያ (ከድልህና ከሹሮ፣ ከአትክልት፣ ከሥጋ፣ ከክክ)፡ በቅቤ ወይም በዘይት ተቀቅሎ የተዘጋጀ። (ተረት) "ወጥ ቢጣፍጥ እጅ ያስመጥጥ። "
"ወጡ ሳይወጠወጥ ወስከንባዩ ቂጥ። "
"ለወጡም ዕዘኑለት፡ ከንጀራውም ብሉለት። "
"ም ነው ለወጡ፡ ጐዦ ሲወጡ። " የወጥ ምስጢር፣ በጭልፋ ወይም በንጀራ ከድስት ከምንቸት መውጣት ነው።
ወጥ ሠሪ: ወጥ የሚሠራ ወይም የምትሠራ ሰው።
ወጥ ሠራ): ቀቀለ፣ አበሰለ።
ወጥ ቤት (ቶች): የወጥ መሥሪያ፣ ወጥ ማብሰያ ቦታ።
ወጥ ቤት: ወጥ ቀቃይ ገረድ ወይም ወንድ (፱ ሳሙ፡ ፱፡ ፳፫፡ ፳፬)።
ወጥ: ናስ፣ ማሰር፣ ጠመንዣ መካከለኛ።
ወጥ: የወጣ፣ የመጣ። "ባሕረ ወጥ ጐራዴ"፡ "ሥረ ወጥ" እንዲሉ።
ወጥመድ (በቁሙ): ጠመደ።
ወጥመድ፡ (ዶች)፡ ያንበሳ፡ የነብር፡ ያይጥ፡ የወፍ፡ ያሞራ፡
ያውሬ ኹሉ መያዣ፡ መግደያ። (ያሣ ወጥመድ)፡ መግለቦ፡ መቃጥን፡ መንጠቆ፡ ዘረ፡ መትር፡
ቋኛት፡ ቀፎ፡ መረብ፡ ሻታ። ስማርድን፡ ገትን፡ ወስፈንጠርን፡ አሽክላን እይ።
ወጥመድ ገባ፡ በወጥመድ ተያዘ፡ ታነቀ።
ወጥዋጣ: ለግላጋ፣ ሹል።
ወጦች (ወፃእያን): የወጡ።
ወጦች: የወጥ ዓይነቶች በብዙ ጭት ውስጥ ያሉ።
ወጨፈ (ወፂፍ ወፀፈ): አግድም ዘነመ፡ ወጨፎ ሆነ። ወነጨፈንን ይመልከቱ፡ የዚህ ስርዋጽ ነው።
ወጨፎ: ውሽንፍር፣ ዶፍ፡ ነፋስ ያለው ዝናም (ዝናብ)።
ወጪ (ወፃኢ): የሚወጣ፣ የሚያርግ፣ የሚያድግ፡ ሽቅብ ኻያጅ።
ወጪ ወራጅ: ሽቅብና ቍልቍል የሚኼድ።
ወጪ: ከሣጥን ወጥቶ ልብስና ጕርሥ፣ ሌላም ተፈላጊ ነገር የሚገዛበት፡ ለምንደኛ፣ ለሠራተኛ፣ ለያተኛ፣ ለሎሌ የሚሰጥ ገንዘብ። "ገቢና ወጪ" እንዲሉ።
ወጪ: የወር ጨው።
ወጪመደ (ጠመደ): ጨመደደ።
ወጪመድ/ወጭማዳ (ዶች): ውትርትር፣ ግትርትር፡ ትክክል የማይረግጥ፣ የማይኼድ።
ወጪዎች: የሚወጡ (ሰዎች፣ ገንዘቦች)።
ወጪፎ: የጣሊያን ጠመንዣ (ወጨፎ)፡ ያሠኘው የሚጐርሠው ጥይት ብዛት ነው። ውዥግራ አንድ ጐራሽ ሲሆን እሱ አምስት ጐራሽ ነውና።
ወጫበረ (ጨበረ): በነገር ሳተ።
ወጭት (ቶች): ወጽሐ፡ ጣባ፣ ድስት፣ ደቅ፣ ጻሕል፣ ሳሕን፡ የመሰለው ኹሉ። (ዘኍ፯፡ ፲፬፡ ፲፱) በግእዝ ሞጻሕት ይባላል። አብሽን፣ ገበቴን ይመልከቱ።
ወፈ ንስር፡ ኹለት የበገና ዥማት (አውታር)፡ ቃናው እንደ ወፈ ያሬድ የኾነ። ምስር ቃናን እይ።
ወፈ ያሬድ፡ (ዖፈ ያሬድ)፡ ድምጠ መልካም የያሬድ ወፍ፡ ጕሬዝማ፡ ባገራችን ደን ውስጥ ተባቱና እንስቱ በወፍራምና በቀጯን ድምጥ ሲዘምሩ ይታያሉ።
ወፈ ያሬድ፡ ንስር ቃና፡ ለቅዱስ ያሬድ ዜማ ያስተማረ፡ በግእዝ አሮድዮን ይባላል (ማር ይሥ ፳፰: ፫)።
ወፈ ገነት፡ (ፆፈ ገነት)፡ የገነት ወፍ፡ ጣዎስ፡ እመቤታችን።
ወፈ ገዝት፡ ትምርት የሌለው ሰው፡ ወፍ ገዛች።
ወፈረ፡ (ወፊር፡ ወፈረ፡ ተሰማራ)፡ ገዘፈ፡ ደነደነ፡ ዳጐሰ፡ ከበደ፡ ሠባ፡ ሰፊ ኾነ፡ አከለ፡ አካል ጨመረ። (ተረት)፡ ከወፈሩ ሰው አይፈሩ።
ወፈር፡ (ወፊር)፡ ዳጐስ።
ወፈር አለ፡ ዳጐስ፡ ደንደን፡ ለበስ አለ።
ወፈቀ (ጸፈቀ): ደንጊያ ጫነ፡ ረገጠ፡ ለሰቀ፡ ለጥ ቀጥ አደረገ ርጥብ ጨፈቃን።
ወፈንጠር (ወፈ ጠር): የወፍ ጠር (ዓሞ፫፡ ፭)።
ወፈፈ፡ እንደ ወፍ ብድግ ብድግ፡ ብር ብር አለ፡ አበደ፡ ተቈጣ።
ወፈፌ፡ የወፈፈ፣ እብድ።
ወፈፍ አለው፡ ግልፍ አለው፡ ቍጣ ተሰማው (ግብ ሐዋ ፳፮: ፲፩)።
ወፈፍተኛ፡ (ኞች)፡ ግልፍተኛ፡ ቍጡ፡ እብድ (ምሳ ፳፪: ፳፬)።
ወፈፍተኛነት፡ ግልፍተኛነት፡ እብድነት። ወንጃን እይ።
ወፈፍታ፡ ግልፍታ፡ ቍጣ።
ወፋ፡ (ኦሮ፡ ፆፋ)፡ ንዱ፡ አሳዱ።
ወፋ ውጊያ፡ (ውጊያ ወፋ)፡ የመንዳት፡ የማባረር ጦርነት፡ በየጁ አውራጃ ሲደረግ የነበረ።
ወፋሪ፡ የሚወፍር፡ ደንዳኝ።
ወፋራሽ፡ (ወፍ ዐራሽ)፡ ወፍ ፍሬውን ዐርቶት ሰው ሳይተክለው በዱር የበቀለ ጌሾ፡ ዐውቆ በቀል።
ወፋር፡ የወፈረ፡ ገዛፍ።
ወፋንቍር፡ (ወፍ አንቍር)፡ የቅጠል ስም፡ እንቡጡን ወፍ የሚያነቍረው ለስላሳ ቅጠል።
ወፋፍራም፡ (ሞች)፡ ውፋሬና ብዛት ያለው።
ወፌ ቆመች፡ ሕፃን መቆም ሲዠምር የሚባል፡ የሚነገር፡ ወፌ ማለት የልጁን ፪ እጅ ያሳያል።
ወፍ፡ (ፎች)፡ (ዖፍ)፡ ፪ እግርና ፪ ክንፍ ያለው የየብስ፡ የባሕር ተንቀሳቃሽ፡ ያሞራ ወገን፡ ወደ ሰማይ እየበረረ ባየር ላይ የሚሰፍ፡ የሚንሳፈፍ፡ ያየር መንገደኛ፡ የነፋስ ዋነተኛ። ተባቱም እንስቱም ወፍ ይባላል። (ተረት)፡ ወፍ እንዳገሯ ትጮኻለች።
ወፍ፡ በሠረገላ (ጋድም) ላይ የቆመ ዕንጨት፡ አኳዃኑ ወፍኛ ይመስላል።
ወፍ፡ ብጫ የሚያስመስል የሐሞት ብዛት በሽታ። መድኀኒት ጠጥቶ ሲያስታውኩት ሐሞቱ የሌት ወፍ ክንፍ ይመስላልና ወፍ ተባለ።
ወፍ አርግፍ፡ ክፉ ቡዳ፡ ያይኑ አስተያየት ስንኳን ሰውን ወፍ የሚያረግፍ ጠይብ። ይህም ልማዳዊ የስሕተት ባህል ነው።
ወፍ አእላፍ፡ ብዙ ወፍ ማለት ነው። ከወፍ አእላፍ አብላኝ እንዲል ገበሬ።
ወፍ እግር፡ ጫፍና ጫፉ የወፍ እግር የሚመስል ጥልፍልፍ የክር ገመድ።
ወፍ ዋሻ፡ (የወፍ ዋሻ)፡ የተራራና የደን ስም፡ በይፋት ወረዳ በጣርማበር በታች ያለ ቀበሌ።
ወፍ፡ ያፈርሳታ ወይም ያውጫጭኝ ምስክር፡ ዐይኔ አይቷል፡ ጆሮዬ ሰምቷል ብሎ ምሎ ተገዝቶ፡ ሥዕል ወግቶ የሚናገር፡ እውነተኛ ወይም ሐሰተኛ አመልካች። ወፍ መባሉ ሰሎሞን በምሳሌው (ኢትሕሚ ሰብአ ውስተ ቤትከ፡ እስመ ፆፈ ሰማይ ያወፅኦ ለነገርከ) ይላልና ነው። ዳግመኛም ጠላት በስውር ገፍቶት ገደል ገብቶ የጠፋው (የሞተው) ሰው ሬሳ አሞራ ሲያንዣብብ በመመልከት ይገኛልና፡ ስለዚህ ነው። ሐሰተኛውም የጨለማ ወፍ ሰይጣን እንደ ኾነ ይታወቃል።
ወፍ ጠጭ፡ በውስጡ ያለውን ውሃ ወፍ የሚጠጣው የግርሽጥ አበሳ።
ወፍለቅ፡ የርካብ ጠፍር፡ እንደ ወፍ ክንፍ በኮርቻ ግራና ቀኝ ቍልቍል የተለቀቀ፡ የተንጠለጠለ። የርካቡ ቀለበትነት ወፍ የሚለቅ፡ የሚያሾልክ ስለ ኾነ ወፍለቅ ተባለ።
ወፍላ፡ ያገር ስም፡ በስተስሜን በኩል ያለ ኣገር፡ የአላማጣ አፋፍ።
ወፍራም፡ (ሞች)፡ ወፍር ያለው፡ ባለወፍር፡ ጠብደል፡ ደንዳና፡ ግዙፍ፡ ጕልሕ፡ ጐነ ሰፊ።
ወፍራምነት፡ ወፍራም መኾን፡ ደንዳናነት፡ ሰፊነት።
ወፍር፡ ውፋሬ፡ ግዘፍ፡ ድንዳኔ።
ወፍኛ፡ የወፍ አቀማመጥ ኹኔታ፡ ወይም ጩኸት።
ወፍጮ (ዎች) (መፍጽሕ፣ ማሕረጽ): እኸል መፍጫ፡ መከርተፊያ፡ በሰው እጅ፡ ባህያ፡ በግመል፡ በውሃ፡ በኤሌትሪክ ኀይል እየዞረ የሚፈጭ መዘውር ያለውና የሌለው፡ ዐይናማ ደንጊያ (ዘዳ፳፬፡ ፮) (እህል የሚፈጭበት መሳሪያ)።
ወፍጮ መድፊያ: ከሆሳዕና ዋዜማ የሚቀድም ዐርብ ቀን፡ ወፍጮ መድፊያ ማለት ለመጅና ለቅምጥ ወፍጮ ነው የሚስማማው (የዐርብ ቀን ሥርዓት)። ካርብ ማታ ለቅዳሜ አጥቢያ ዠምሮ እስከ እጅ ማማሻ (የዳግም ትንሣኤ ማግስት) ድረስ ኹለት ሰንበት መፍጩት የለም (የወፍጮ መድፊያ ክልከላ ጊዜ)። በባላገር ግን የቅዳሜ ሹር ለት ይፈጫል (በገጠር ያለው ልማድ)።
ወፍጮ፡ መፍጫ፡ ፈጩ።
ወፍጮ ቤት: የወፍጮ ቤት፡ ወፍጮ የተተከለበት፡ ያለበት (ወፍጮ ያለበት ቦታ)።
ዋ እቴ ቢቸግርሽ: ባታውቂበት።
ዋ: ምእላድ (ከሳ-ከሽ-ከሻዋ)።
ዋ: ቃለ አጋኖ ሆይ ("አባቴዋ፣ እናቴዋ")።
ዋ: የሩቅ ሴት ዝርዝርና መለዮ።
ዋ: የአማርኛ ራብዕ ሥረይ (በ-ዋ-ቧ)።
ዋ: የዛቻና የማስፈራራት፣ የሀዘን ቃል ("ዋ ዛሬ ጉድ ይፈላል!")።
ዋሐደ: አዋሐደ፣ ተዋሐደ (የካህናት)፡ ዋደ: ተዋዋዶ፣ አዋዋደ (የሕዝብ አነጋገር ነው)።
ዋሐድ: አንደኛ የቀባርዋ ምት።
ዋሕድ: በወዲያኛው
ዋሕድ: አንድ ብቻ፣ ኹለትነት የሌለው።
ዋሕድና በኵር (ዋሕድ ወበኵር): ዋሕድ በወዲያኛው፡ በኵር በወዲህኛው፡ ባምላክነትና በሰውነት ማለት ነው።
ዋለ (ውዒል ወዐለ): በሥራ፣ በነገር፣ በማንኛውም ጕዳይ ከጧት እስከ ማታ ቀኑን ኹሉ በመጠኑ ቈየ፣ ነበረ። "እከሌ ሲሠሪ ዋለ"፡ "ተቀምጦ ዋለ"፡ "ሲኼድ ዋለ"።
ዋለ: ረዳ፣ ዐገዘ፣ አዳነ። "ዛሬ እግዜር ዋለልኝ" እንዲሉ።
ዋለለ (ወልወለ): ዋዠቀ፣ ተነቃነቀ፣ ዛበረ፡ ወዲያና ወዲህ አለ። (ሉቃስ ፲፪:፳፱)
ዋለሉ: የሰው ስም፡ ጠላቶች ዛበሩ ማለት ነው።
ዋለብኸ ዐደረብኸ: የእንቆቅልሽ መልስ ላልሰጠ የሚነገር ቃል፡ ቈየብኸ፣ ዘገየብኸ ማለት ነው።
ዋለገ: ወለገ።
ዋሊ (ወዓሊ): የዋለ፣ የሚውል (ሰው)።
ዋሊ: ዋልድባ (ግእዝ)።
ዋሊያ (ማዕነቅ ዋኖስ መንጢጥ) (ዋኔ፣ ዋኒያ): የርግብ ዐይነት ወፍ ከቡያ የምትበልጥ ከርግብ የምታንስ። (ዘሌ፭:፯። ማሕ፪:፲፪። ኤር፰:፯)
ዋሊያ (ውዕላ): የዱር ፍየል ፪ ቀንዱ ብዙ ዕርከን ያለው። ዋላን እይ።
ዋሊያ ፈረስ: በአባይና በአትባራ ገማ ዳር የሚገኝ እንስሳ እንደ ፈረስ የሚጋልብ፡ የድኵላ ወገን ቀንዱ ወደ ኋላ የተመለሰ፡ ቁመቱ ፫ ክንድ።
ዋሊያት: ዐፈና፡ ዋለ።
ዋሊያት: የቀን ሙሉ ዝናም፣ ዐፈና።
ዋሊያዎች: ዋኔዎች። (ዘሌ፲፪:፰)
ዋላ (ውዕላ): የዱር፣ የበረሓ እንስሳ (የፍየል ወገን)። (፬ነገ፡ ፬፡ ፳፫። ኢዮ፴፱፡ ፩። መዝ፵፪፡ ፩። ማሕ፪፡ ፲፯። ፰፡ ፲፬)። ዳግመኛም መምህራን ውዕላን "ዋሊያ" ይሉታል። ዋኔን እይ።
ዋላላ: ዝኒ ከማሁ።
ዋላይ: የዋለለ፣ የሚዋልል፡ ልብ የወጭት ውሃ።
ዋል (ዐል): ለቅርብ ወንድ ትእዛዝ አንቀጽ። "ታመኻልና እደጅ አትውጣ፡ እቤት ዋል!"
ዋል (ውዒል): መዋል።
ዋል ተንጉሥ: የሰው ስም፡ "ከንጉሥ ጋራ ዋል" ማለት ነው።
ዋል ዐደር አለ: ዋለ ዐደረ፡ ጥቂት ቀን አሳለፈ።
ዋልሴ (ዎች): ደጋናዊ፣ ጐባጣ፣ ካራ። ስለቱ እንደ ማጭድ በስተውስጥ የኾነ።
ዋልታ (ወልተወ፣ ወልታ): የባጥ ገበታ ጣራ መወጠኛ፡ በመካከሉ የምሰሶ ፍ መግቢያ ሰፊ ቀዳዳ፡ በዙሪያው ለመር መጥለፊያ ብዙ ብስ ያለው፡ በስተላይ ውቅር በስተታች ጭምጭሚት የሚደረግበት። አቀማመጡ (ኹናቴው) እንደ ወልታ (ጋሻ) ስለ ኾነ ዋልታ ተባለ።
ዋልቴ: ከፊለ ስም።
ዋልቴ: የዋል ተንጉሥ ከፊለ ስም። "መኰንን ዋልቴ" እንዲሉ።
ዋልካ: መረሬ፣ ጥቍር መሬት። ወልቅን ተመልከት።
ዋልድቢት (ትግ): ደርብ ሰገነት፡ መጨረሻ ፎቅ፡ ዕንቍላል ግንብ።
ዋልድባ: የአማራ አገር በስሜንና በወልቃዪት አጠገብ የሚገኝ።
ዋልድባ: የገዳም ስም፡ በጸለምት በረሓ ውስጥ ያለ ሥርዐተ ጽኑ ገዳም ማኅበረ ሳሙኤል። (ተረት) "አንዳንድ ቀን በዋልድባ ይዘፈናል"። የፍጹምነት ማዕርግ ስለሚገኝበት ባልድባ ተባለ። በግእዝ ዋሊ ይባላል። ዋልድቢትን ተመልከት። "አባ ከየት መጡ? ከዋልድባ" እንዲሉ ልጆች።
ዋልድቤ (ዋልድባዊ): የዋልድባ ሰው፡ መነኵሴ።
ዋልድቤ እንግዳ: ባ፲፰፻ ዓ ∙ ም በደብረ ሊባኖስ የነበሩ መነኵሴ፡ የዋልድባ ሊቅ።
ዋልድቦች: የዋልድባ ሰዎች፡ መነኵሴዎች፣ ተዋሕዶዎች።
ዋልጋ (ጎች): የሚመልግ፣ የሚሾልክ፡ ወላጋ አውሬ (የበግ ግልገል ጠላት)፡ የቀበሮ ዓይነት (ዐመድማ)።
ዋልጌ (ዋልጋዊ): የዋልጋ ወገን፡ ተንኰለኛ፣ ክፉ ሰው።
ዋመሳ፡ ረዥም ፣ ጦር ።
ዋመራ: ዐንገቱ የሚታሰር ርኰት፣ ረዘም ያለ።
ዋመነ: ቋመጠ፣ ጓጓ፣ ጐመዠ፣ ሠየ፡ እዱር ገባ ለግዳይ።
ዋመን: ደን፣ ዱር፣ ካ፣ ችፍግ ያለ ቅጠል፣ ጠለሸት። ዎማና ዋመን ግእዝ ዖም ካለው ይወጣሉ።
ዋሜራ: ያጎዳ ዐንገት፣ መለልታው ቀጥታው፡ አንጓ የለሽ። "ዋሜራ እግር" እንዲሉ።
ዋሰ) ወሐሰ፡ አዋሰ፡ (አውሐሰ)፡ የሚመለስ ዕቃና ከብት፡ ለጊዜው ሰጠ፡ አበደረ።
ዋስ፡ (ሶች)፡ (ዋሕስ)፡ ተያዥ፡ መድን፡ ዐላፊ። የዋስ ተጋች፡ የቈማጣ ፈትፋች። የእጅ፡ የጠለፋ፡ የመሳሳቢያ፡ የሥራት፡ የበሰላ ዋስ እንዲሉ።
ዋስ ተቀበለ፡ ዋስ በራሴ አለ፡ ራሱን ዋስ አደረገ።
ዋስ አለ፡ ዋስ አስጠራ።
ዋስ ዐጋች፡ ዋስን የሚያግት፡ የዋስን ዕቃ ለጊዜው የሚወስድ፡ የሚይዝ።
ዋስ ዐጋች፡ የዛር ስም፡ የቀይ ገብስማ ዶሮ የሚገብሩለት ዛር።
ዋስ የለሽ፡ ወስላታ ሰው።
ዋስላ፡ (ዐረ)፡ የትንባኾ ቅጠል።
ዋስማ፡ እሾኸ ያለበት ተክል።
ዋስትና፡ ዝኒ ከማሁ።
ዋስትናውን አስወረደ፡ አራቀ፡ አስወገደ።
ዋስነት፡ ዋስ መኾን።
ዋስዳ፡ የቀርበታ ጠፍር፡ ማንጠልጠያ ገመድ።
ዋስዳ፡ ጋንን ከነጠላው አንሥቶ መውሰጃ ክብና ወፍራም የንዶድ ዐረግ ማቶት።
ዋሪ፡ (ዎች)፡ ጥቍር ወፍ፡ ማማት፡ ማይ።
ዋሪ፡ ወረገኑ።
ዋሪ ዋሪ፡ እንዲል አገዳ ጠባቂ። (ማለት) ማታ ማለት ነው።
ዋር፡ የጣቃ፡ የመዳ፡ ዕጥፋት፡ ዱራ በሚባል ብረት የሚለካ።
ዋርማ፡ ሞላላ፡ አንኮላ፡ ጠላ መጠጫ።
ዋርሳ፡ የሚስት እት፡ የእቷን ባል የምትወርስ (ሩት ፩: ፲፭)።
ዋርሳ፡ የባል ወንድም፡ የወንድሙን ሚስት የሚወርስ (ዘዳ ፳፭: ፭፡ ፯)።
ዋርሳዪቱ፡ የወንድም ሚስት፡ የባሏን ወንድም የምትወርስ (ዘዳ ፳፭: ፯፡ ፱)። ምራትን እይ።
ዋርዳ፡ (ትግ ዋሪ፡ ወማይ)፡ ጥቍረት፡ ጥቍርነት ያለው ወፍ፡ ማማት (ኤር ፰: ፯)።
ዋርዳ ሳሙና፡ ጠጕሩ ጥቍረት ከቅላት ፈገግታ ያለው በቅሎ።
ዋርዴ፡ የዋርዳ ወገን፡ ወይም ዐይነት በቅሎ፡ ጥቍሬ፡ ጠቋሬ ማለት ነው፡ ላህያም ይነገራል።
ዋሸ፡ (ሐሰወ)፡ ኳሸ፡ ዐበለ፡ ቀጠፈ፡ ሐሰት ተናገረ። (ተረት)፡ ዋሽ ቢሉኝ እዋሻለኹ፡ ነፋስ በወጥመድ እይዛለኹ።
ዋሸ: ቀጠፈ፣ ሰደበ፣ ዐማ፣ ነቀፈ፣ አፌዘ፣ አላገጠ፣ አሾፈ፣ ምፀት ተናገረ።
ዋሸራ፡ በጐዣም ክፍል ያለ አገር።
ዋሸራ ተክሌ፡ የዋሸራ ተክሌ፡ ስመ ጥር የቅኔ መምር።
ዋሻ፡ (ዎች)፡ በገደልና በተራራ፡ በቋጥኝ ውስጥ ያለ የተፈጥሮ ሕንጻ፡ ወይም የጥንት ሰዎች እየጠረቡ፡ አራዊትም እየፋሩ፡ እየቈፈሩ፡ ያበጁት ጥንታዊ ቤት፡ ማደሪያ፡ መኖሪያ። (የሌባ ዋሻ፡ የቀማኛ መሸሻ)፡ እምነተ ቢስ፡ ወስላታ ሰው። በተባትና በአንስት ሲነገር።
ዋሻ ሚካኤል፡ (የዋሻ ሚካኤል)፡ በእንሳሮና በጎሐ ጽዮን፡ በታች አባይ ዳር በዋሻ ውስጥ ያለ ታቦት። ዋሻ ግእዝ ወሥአ ካለው ይወጣል፡ ሲጮኹ ቃል ይመልሳልና።
ዋሻም፡ ዋሻ ያለበት፡ የበዛበት፡ ባለዋሻ ስፍራ።
ዋሻዋ፡ ያች ዋሻ፡ የርሷ ዋሻ።
ዋሻው፡ ያ ዋሻ፡ የርሱ ዋሻ (ዘፍ ፳፫: ፲፯)።
ዋሻዪቱ፡ ያች ዋሻ (ዘፍ ፳፫: ፳)።
ዋሽንት፡ ወስፌ፡ ወሳፍቻ፡ የስፌት መሣሪያ፡ ሰፋ (ሰፈየ)።
ዋሽንት፡ ዋሽንቶ፡ (ቶች)፡ ዛጕፍ፡ ከመቃ (ሸንበቆ)፡ ከቀርክሓ የተበጀ የዘፈን መሣሪያ፡ በትንፋሽና ባ፬ ጣት ድምፅ የሚሰጥ፡ ባላ፬ ብስ። በትግሪኛ እንዱር ይባላል። ዋሽንት፡ ዋሻ ከማለት ይሰማማል፡ በግእዝ መሠረቱ ወሥአ ነው።
ዋሽንት፡ የዛፍ ስም፡ ቅርፊቱ በየጊዜው እየተቀረፈ የሚታደስ የቈላ ዕንጨት።
ዋሾ፡ (ሐሳዊ)፡ የዋሸ፡ የሚዋሽ፡ ዐባይ፡ ቀጣፊ። አፍን እይ።
ዋሾች፡ ዐባዮች፡ ቀጣፎች።
ዋሾች፡ ዋሻዎች (ኢዮ ፴፰: ፵)።
ዋቀራ፡ የውቅር ሥራ፡ የጣራ ዥመራ፡ ቋጠራ፡ ጥረቃ።
ዋበ (ወሀበ): ሰጠ፣ አቀበለ፣ አስረከበ (ሀብት፣ ገንዘብ፣ ከብት)።
ዋበ: አሳመረ፣ አቆነዠ።
ዋቢ (ዎች) (ወሃቢ): የሰጠ፣ የሚሰጥ፣ ሰጪ፣ አቀባይ። (ተረት) "ዋቢ ያለው ይወጣል፣ ዋቢ የሌለው ይሰምጣል"።
ዋቢ ሸበሌ እንዲሉ: (የወንዝ ስም)።
ዋቢ ሸበሌ: በሱማሌ ቋንቋ "ነብር ሸበል" ስለሚባል የንብ፣ የነብር ዥረት ማለት ነው።
ዋቢ ንብ፣ ሸበሌ ነብር፡ በተገናኝ፡ ንብና ነብር ያለበት ወንዝ ማለት ነው: (የወንዝ ስም ትርጓሜ)።
ዋቢ: የቀበሌ ስም (በእነዋሪ አቅራቢያ ያለ የሥላሴ አጥቢያ)።
ዋቢ: የወንዝ ስም (ታላቅ ዠማ ከአሩሲ ተነስቶ ከወደ ባሌ በውጋዴ በኩል የሚወርድ)። በጋልኛ "ድንጉል ውሃ ቀጂ ንብ" ማለት ነው።
ዋቢነት: ሰጪነት፣ ሰጪ መሆን።
ዋታች: የዋተተ፣ የሚዋትት፡ ባካና፣ ተንከራታች፣ ባተሌ።
ዋቶ ዐደር: ያገርንና የመንግሥትን፣ የሃይማኖትን ነጻነት ለመጠበቅና ለማስከበር ዞሮ፣ ተንከራቶ፣ መከራ አይቶ፣ ዐጥንቱን ከስክሶ፣ ደሙን አፍስሶ የሚያድር።
ዋቶ: ዞሮ፣ ባክኖ።
ዋቸላ: ኬሻ፡ የጭረት ምንጣፍ። አመከዝን እይ።
ዋቸው: የሩቆች ወንዶችና ሴቶች የአንቀጽ ዝርዝር። እነሱ እነዚያን አወቋቸው።
ዋችኹ: የቅርቦች ወንዶችና ሴቶች የአንቀጽ ዝርዝር። እነሱ እናንተን አወቋችኹ።
ዋነተኛ፡ (ኞች)፡ የሚዋኝ፡ ዋና ዐዋቂ፡ ወስዋሽ፡ ቋትለኛ፡ ቀዛፊ። (ጥና) ዋና፡ ዐይነተኛ ሰው።
ዋነነ፡ (ትግ ወነነ)፡ ዋና ኾነ፡ ወረሰ፡ የራሱ አደረገ፡ ያዘ።
ዋነኛ፡ የዋና ወገን።
ዋነኛነት፡ ዋና መኾን፡ ዐይነተኛነት።
ዋኒያ፡ ዋሊያ፡ ዋኔ።
ዋና፡ (ኖች)፡ ታላቅና ዐይነተኛ ሰው፡ የግብር፡ የጠባይ፡ የመጠን፡ አውራ፡ ባለቤት፡ መደበኛ፡
ግንባር ቀደም፡ አለቃ፡
በኵር። (ተረት)፡ ከጠጅ ወዲያ ኣስካሪ፡ ከዋና ወዲያ መስካሪ።
ዋና፡ ቀዘፋ፡ ውስወሳ፡ ቁሞ ተንጋሎ በዠርባ በደረት የሚደረግ የባሕር ላይ መንገድ።
ዋና ነገር፡ ማለፊያ፡ ጥሩ።
ዋና ዋናው፡ ትልቅ ትልቁ፡ አበታ፡ አበታው።
ዋና ጐደል፡ ትርፍ ሲፈልግ ዋናው የጐደለበት።
ዋና: ዋነተኛ
ዋኔ፡ (ዋኖስ)፡ በቁሙ፡ ዋሊያ። ትርጕሙ፡ (ተዋናዪ) ተጫዋች፡ የአየር ዋነተኛ ማለት ነው። ሲበዛ ዋኔዎች ይላል። ዋኒያ በመባል ፈንታ ዋሊያ ተብሏል።
ዋኔ ተዋኔ፡ (ተዋናዪ)፡ የፈላስፋ ስም፡ በጐዣም አውራጃ የነበረ ታላቅ ሊቅ፡ ቅኔን የፈጠረ፡ ባሕረ ምስጢሩን ዋኝቶ የመረመረ! ቁም ነገር ባለው ፍልስፍና ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ሲጫወት የኖረ። ደቀቀ ብለኸ ደቀ እስጢፋን ተመልከት።
ዋንታ፡ ዝኒ ከማሁ፡ ፪ ሰው ባንድ ጦር አጣምሮ መውጋት፡ ደርቦ መግደል።
ዋንኬ፡ ላታም በግ፡ የዱረኒ፡ ወይም የሌላ።
ዋንክ፡ መና፡ ከንቱ፡ ብላሽ። ዛሬ አቶ እከሌ ዋንክ ለዋንክ ውሎ መጣ።
ዋንዛ፡ (ዞች)፡ የታወቀ ዛፍ፡ ዕንጨቱ ጽላት፡ ዋልታ፡ ቈሬ፡ ገበቴ፡ ሳንቃ፡ መቃንና ጕበን፡ ቀንበር፡ ዐልጋ፡ ሌላም ዕቃ የሚኾን፡ የማይነቅዝ፡ ፍሬው የሚበላ።
ዋንዛጌ፡ (ጌ ዋንዛ)፡ ያገር ስም፡ በታችኛው ወግዳ ሰሜን በተጕለት ያለ አገር። ዋንዛ ያለባት ምድር ማለት ነው።
ዋንጫ፡ (ጮች)፡ (ነጠጠ)፡ ከቀንድና ከንጨት፡ ከብርና ከወርቅ በማንጠጥና በመፋቅ የተበጀ የውሃ፡ የጠላ፡ የጠጅ፡ የኮሶ መጠ። የእጅ ዋንጫ፡ የጋሻ ዋንጫ እንዲሉ።
ዋንጫ ልቅለቃ፡ ዐጠባ፡ ዕጥበት።
ዋንጫ ልቅለቃ፡ ውዝዋዜ፡ ጭፈራ፡ እስክስታ።
ዋኖስ፡ (ሶች)፡ ዋኔ። ዋኖስ ግእዝኛ ነው።
ዋኘ፡ (ዋነየ)፡ ባሕርን በእጁና በእግሩ ሠራ፡ ቀዘፈ፡ ወሰወሰ። በውሃ ውስጥ ተጫወተ፡ ቍልቍልና ሽቅብ፡ አግድም ሰለከ፡ ሾለከ፡ ተንቀሳቀሰ፡ ተላወሰ፡ ላይ ላዩን ሰፈፈ፡ ተንካፈፈ፡ ተሳበ፡ ተጐተተ።
ዋኚ፡ የዋኘ፡ የሚዋኝ።
ዋዕይ፡ (ውዕየ)፡ የፀሓይ፡ የእሳት ግለት፡ ወበቅ፡ ሐሩር፡ ብርቱ ሙቀት።
ዋካ: በኵሎ ውስጥ ያለ ዋና ከተማ፡ በግእዝም ብርሃን ማለት ነው።
ዋዋ (ወህውሀ): ጣመ፣ ጣፈጠ። መረቃን አስተውል።
ዋዋ (ዋ): ዋይ ዋይ፡ ወዮ ወዮ።
ዋዋ: የቁራ ጩኸት።
ዋዋቴ: የዓረግ ስም፡ ጥርስ ሲፍቁበት የሚጣፍጥ ዓረግ።
ዋዌ: የአገባብ ስም፡ ልዩ ልዩነት ባለው ስምና አንቀጽ መጨረሻ እየተጨመረ የሚነገር ፊደል፡ ይኸውም ም ነው። በመ ተራ ምን ተመልከት።
ዋው: የፊደል ስም፡ ፮ኛ (6ኛ) ፊደል ወ። ትርጓሜው ሚንጦ ዘለበት፣ ከዋዌ ጋር አንድ ነው።
ዋዘኛ (ኞች): ዋዛ ተናጋሪ፣ ዋዛ ወዳድ፣ ባለዋዛ፣ ቀልደኛ። (መዝ፩፡ ፩። ምሳ፱፡ ፯፡ ፰)
ዋዘኛ(ኝ)ነት: ዋዘኛ መሆን። (ምሳ፬፡ ፲፪)
ዋዘኛ: ክራር መቺ። "ዋዘኛስ ክራረኛ" እንዲሉ።
ዋዛ (ትግ ዋዘየ): አፌዛ፣ ዘበተ፣ ቀለደ።
ዋዛ (ዘርቅ ተውኔት): ቀልድ፣ ፌዝ፣ ዘበት፣ ቧልት፡ ቁም ነገር የሌለበት ጨዋታ። (ኤፌ፭፡ ፬) "አለዋዛው ዋዛ፡ ቅቤም እያወዛ። "
"ዋዛ ለቁም ነገር" ብላቴን ጌታው እንዲሉ።
ዋዛ ፈዛዛ: የፈዛዛ ዋዛ፡ ወይም ፈዛዛ ዋዛ፡ ብላሽ፣ ረበ ቢስ፣ ከንቱ ነገር።
ዋዜማ (ዋይ ዜማ): ከዋና በዓል አስቀድሞ የሚውል ቀን፡ በዚያ ጊዜ የሚባል ዜማ፡ የሚበላ ድግስ።
ዋዜማ: ፬ኛ (4ኛ) የቅኔ ስም፡ ባላ፭ ቤት፣ የዋዜማ ቅኔ።
ዋዠቀ: ተነቃነቀ፣ ተወዛወዘ (የጥርስ)።
ዋዠቁ: የሰው ስም፡ "ጠላቶች በፍርሃት ተነቃነቁ" ማለት ነው።
ዋዣቂ: የዋዠቀ፣ የሚዋዥቅ፡ ተነቃናቂ።
ዋዥማ: በመረሬ ከእህል ሁሉ መካከል የሚበቅል ቅጠል፡ የከብት መኖ፡ ካበበ በኋላ እሾኻም ይሆናል።
ዋዥምቢት: ጥቁር ትል፣ እህል አጥፊ።
ዋዥራት: የነገድ ስም። ዋጅራትን ይመልከቱ።
ዋየ: ዋይ አለ፡ ዐዘነ፣ ተከዘ፣ ቈዘመ፣ ተወዘወዘ፣ አለቀሰ፣ አነባ።
ዋየል: የሮማይስጥን ፊደል ካዕብ፣ ሣልስ፣ ራብዕ፣ ኃምስ፣ ሳብዕ የሚያደርግ የአቤት ፊደል።
ዋየት: የወሎንና የሺዋን ግዛት የሚለይ ወንዝ (በጃማ ውስጥ የሚወርድ)።
ዋዩ: በወግዳ ክፍል ያለ ቀበሌ። ዋዬ አቅኒው ነው።
ዋዩን ነገረ: ብሶቱን ለሰው ገለጠ፣ አስታወቀ።
ዋዬ (ዋይ ዬ): ወዮ ዬ። "ዋዬ አሰሩኸ ወዬ። "
ዋይ (ወይ ወዮ): የሐዘንና የለቅሶ ጩኸት፣ ጸጸት፡ ምኞትንም ያሳያል። "ዋይ ነዶ"፡ "ዋይ ንድድ"፡ "ዋይ ንዴት"። ዋንን ይመልከቱ፡ የዚህ ከፊል ነው።
ዋይ ሸሸ: ተበላሸ፡ ወዮ ተለየ፡ ፈረሰ፣ በሰበሰ።
ዋይ አለ: ጮኸ።
ዋይ ዋይ: ወዮ ወዮ። (አልቃሽ) "ዋይ ዋይ የት ትኼዳለኽ፡ የቈየኸ፡ እንደኹ ትረሳለኸ። "
ዋይ የለሽ: የላሊበላ ሚስት፡ ግድ የለሽ፣ ዐሳብ የለሽ ማለት ነው።
ዋይ: ጕዳይ፣ ግዳጅ፣ ዐሳብ፣ ችግር፣ ብሶት።
ዋይታ (ወይሌ): ዋይ ማለት፣ ወዮታ፣ ጩኸት። (፪ሳሙ፡ ፫፡ ፴፬። ዓሞ፰፡ ፱፡ ፫)
ዋይታ: ዋይ ማለት፡ ዋይ።
ዋይክማ: የንጨት ልጓም፣ ልጓጥ፡ በአመለኛ ወደል ጋዝ፣ ባጋሰስ አፍ ውስጥ ግራና ቀኝ በገመድ ታስሮ የሚንጠለጠል፣ መብለ ከልክል፣ ደጋናዊ እንጨት። በሕዝብ አነጋገር "አሽክማ"፣ "አይክማ"፡ በግእዝ ዝማም ይባላል። ዋይክማ የቤተ ክህነት ነው።
ዋዲያት (ቶች): ሰፊ የሸክላ ዕቃ፣ የንቅብ አይነት ጐድጓዳ፡ ዱቄትና ውሃ ተጨምሮ ሊጥ የሚታሽበት፣ የሚቦካበት። ዳካንን ይመልከቱ።
ዋድላ ደላንታ: ዋድላና ደላንታ።
ዋድላ: በየጁ ክፍል ያለ አገር።
ዋድሎች: የዋድላ ተወላጆች፣ የዋድላ ሰዎች።
ዋጀ (ትግ ዋገየ): ወጆ ሰጥቶ ገዛ (ከሞት፣ ከባርነት ለማዳን)። ቤዠን እና ዋጋን የሚሉትን እንድትመለከቱ ይመክራል።
ዋጀ: ገበየ። ምሳሌ: "ሲያረጁ አንባር ይዋጁ" (ተረት)።
ዋጅለት: እርስት፣ ዓደር መሬት፣ ዓረም መጣያ፡ ትርጓሜው ለከብትህ ግዛለት ማለት ነው።
ዋጅራት (ቶች): በትግሬ ውስጥ ያለ ነገድ ስም፡ የሽፍታ፣ የቀማኛ፣ የወያኔ፣ የነፍሰ ገዳይ ማኅበር። ዋጅራት "ወገረ" ከሚለው የወጣ ይመስላል፡ ትርጓሜውም ደበዳቢ ማለት ነው።
ዋገምት (ቶች): ከቀንድ የተበጀ የበሽተኛን ደም መሳቢያ፡ መምጠጫ፡ መሰብሰቢያ፡ የሐኪም መሣሪያ፡ ጫፉ በሠም የጠበበ።
ዋገምት አፍ: የዋገምት አፍ፡ አፉ ዋገምት የሚመስል ሰው።
ዋገምት: ከማገሚያ እና ዐገመ (ትርጉም ያለው) ጋር የተያያዘ ቃል ነው።
ዋጊኖስ: የደጋ አባሎ ባለፀጉር ተክል ነው። ስሩና ፍሬው ለደም ተቅማጥ መድኃኒት ይሆናል። ቅጠሉም ቀጥቅጦ በውሃ ዘፍዝፎ ብልትንና አይንን እንዳይነካ ተጠንቅቆ ገላን ቢቀቡት ከዕከክ ያድናል። ሌላ ስሙ ጉፋ ይባላል።
ዋጋ (ትግ ዋገየ)፡ የሥራ መለኪያ፣ የለውጥ መሣሪያ፣ የአንድ ነገር መግዣ (ገንዘብ፣ ወርቅ፣ ብር፣ አሞሌ)። ልውጥ፣ ለውጥ።
ዋጋ ሰበረ፡ አዋረደ (ዐሥር ቢሉት አምስት አለ)።
ዋጋ ቈለለ፡ አበዛ፣ ከልክ አሳለፈ።
ዋጋ ቈረጠ፡ ይህን ያህል ውጣ! ውረድ የለም አለ፣ ርግጡን ተናገረ።
ዋጋ ቢስ፡ ፈሎ ቢስ፣ ረበ ቢስ፣ ዋጋ የሌለው፣ የማይረባ፣ ከንቱ፣ ምናምን፣ ብላሽ ነገር።
ዋጋ አሳረረ፡ ከፍ አደረገ፣ አብልጦ ሰጠ።
ዋጋ አዋረደ፡ አሳነሰ፣ ዝቅ አደረገ።
ዋጋ አፋረሰ፡ እንዳይሸጥ/እንዳይገዛ አደረገ።
ዋጋ የለውም፡ አይረባም፣ አይጠቅምም።
ዋጋዬ፡ የወንድና የሴት ስም ("የኔ ዋጋ፣ ምንዳዬ" ማለት ነው)።
ዋግ (ሐመዳ)፡ የእህል በሽታ (ድልህ መሳይ)፣ ዝናብ በበዛ ጊዜ ከውርጭና ከአመዳይ የተነሳ የሚመጣ።
ዋግ መታው፡ እህሉን ፍሬ አልባ አደረገው፣ መና አስቀረው።
ዋግ፡ ሹም)፡ የዋግ ሹም፣ የዋግ መስፍን፣ ጌታ።
ዋግ፡ በላስታ ውስጥ ያለ አገር ("ዋግ ሹም")።
ዋግምቦ (ዎች): ይህ የነብርና የዓሣ መያዣ ወጥመድ ሲሆን እንደ ቀፎ የተሰራ ነው። ለተጨማሪ መረጃ ስማር ድን የሚለውን እንድትመለከቱ ይጠቁማል።
ዋግምቦ: ይህ ደግሞ የፈረንጅ ድርና ማግ ማደሪያ ወይም መደወሪያ ነው። በላይና በታች ፪ (2) ቀጫጭን እንጨቶች የተሰኩበት ሲሆን፣ እነሱም በክር ወይም በገመድ ጫፍና ጫፋቸው ተቆራኝቷል። ሌላ ስሙ አንከርት ነው። ዋግንቦ ተብሎም ሊጻፍ ይችላል።
ዋግራ: የሬትና የሽቱ ቅመም፣ ወይም መሞቂያው ግርግራት። የዘይት ሽቱ በልብስ ላይ የሚርከፈከፍ። ዑድንን ይመልከቱ።
ዋጠ (ውኂጥ ውኅጠ): ሰለቀጠ፣ ለክ አደረገ፣ በላ። (ተረት) "ይህን ብትሰጥ ምን ትውጥ። "
"ትልቁ ዓሣ ትንሹን ዓሣ ይውጣል"።
ዋጠ: አጠለቀ፣ አሰጠመ፣ አሠረገ።
ዋጠኔ: ማሽላ፡ የማሽላ ዓይነት።
ዋጠው: በላው፣ ሰለቀጠው። አባን ይመልከቱ።
ዋጠው: ብላው፣ ሰልቅጠው።
ዋጣ (ትግ): አዝማሪ፣ መሰንቆ መቺ።
ዋጣ: ቁስል።
ዋጥ (ውኂጥ): መዋጥ።
ዋጥ ሰልቀጥ አደረገ: ዋጠ ሰለቀጠ።
ዋጥ ዋጥ አደረገ: ኹለት ጊዜ ዋጠ።
ዋጨራ: የሰው ስም፡ "ኀይሌ ዋጨራ" እንዲሉ።
ዋጭ (ወኃጢ): የዋጠ፣ የሚውጥ፣ የሚሰለቅጥ። "እባብ ዋጭ"፡ "ዶሮ ዋጭ" እንዲሉ።
ዋጮ: የዛፍ ስም፡ እንቅርታም፣ እሾኸ ያለው፣ የቈላ እንጨት (የግራር ወገን)።
ዋጮራ: የወፍ ስም፡ ቀለሙና መልኩ ከደረቱ በላይ ሰማያዊ፣ ከደረቱ በታች ብጫ የኾነ፣ አፈ ሹል ወፍ።
ው (ውእቱ): ያ፣ እሱ፣ እርሱ።
ው/ዋ: መለዮ ("በሬው ተኛ፣ ጥጃዋ ትፈነጫለች")።
ው: ለሩቅ ወንድ በሚነገር አንቀጽ ጫፍ እየተጨመረ ዝርዝር ምእላድ ይሆናል።
ው: ሲጨመርበት በስም ምትክና በደቂቅ አገባብ
"ፍ"
እየታከለ ዝርዝር ምእላድ ይኾናል።
ው: በራብዕና በኃምስ በሳብዕ ፊደል በሚወርስ ጥሬ (ስም) በመድረሻ እየገባ ለሩቅ ወንድ ዝርዝር ይሆናል። (ገላ-ገላው፣ ሥጋ-ሥጋው)።
ውሃ (ሆች): ውሕሀ (ምሕወ)፡ ከ፬ቱ (4) ባሕርያት አንዱ፣ ፪ኛው (2ኛው)፡ የርጥበት፣ የልምላሜ ሥር መሠረት፡ በቀን ብዛት ሜዳውን ገደል የሚያደርግ፣ ፈሳሽ ባሕርይ ይዞ ኻያጅ፡ እድፍን ሁሉ የሚያነጣ፣ የሚያጠራ፡ እንደ መስተዋት ፊትን የሚያሳይ። (ምሳ፳፯፡ ፲፮። ዘፍ፩፡ ፮፡ ፯) በርጥበቱ ከመሬት፡ በውዕየቱ (በመቃጠሉ) ከእሳት፡ በጽልመቱ ከነፋስ ይሰማማል። (ተረት) "አኹን ሊያልፍ ውሃ አደረገኝ ድኻ። "
ውሃ ሆነ: ቀለጠ (በረዶው፣ ጨው)።
ውሃ ሆነ: ጠረሰ፣ ማኘክ ተሳነው።
ውሃ ልክ: የውሃ ልክ፡ በውስጡ ውሃ ያለበት መለኪያ (ባለመስተዋት፣ ጠፍጣፋ፣ ፬ (4) ማእዘን እንጨት)፡ የግንብና የማንኛውም ሕንጻ ማስተካከያ።
ውሃ መቅጃ: ዦር ባላገር ውሃ የሚቀዳበት ስፍራ፡ አንኮላ።
ውሃ ሙላት: የውሃ ሙላት፡ ጐርፍ፣ ፈረሰኛ።
ውሃ ሥንቁ: አገር ግዛት፣ ማደሪያ፡ ያልተሰጠው ደጀ ጠኒ ጭፍራ።
ውሃ ሥንቁ: የደስታ ተክለ ወልድ ወንድ አያት (የአባት አባት) የስም ቅጽል፡ መደበኛ ስማቸው የምሩ።
ውሃ ቀጠነ: የግፍ ንግግር።
ውሃ ቅዳ: ውሃ መልስ፡ የማይረባ ሥራ፡ የጣሉትን ማንሣት፣ ያነሡትን መጣል።
ውሃ ቋጠረ: አቈረሰጪ፣ ጐረበ።
ውሃ በላ: ባለጌ፣ እንዳገኘ የሚናገር፣ የሚሠራ።
ውሃ በላው: አሰጠመው፣ ዋጠው፡ ወሰደው፣ ይዞት ኼደ፣ ነጐደ፡ አንከባለለው፣ ነዳው።
ውሃ እናት (የውሃ እናት): ሰረጋ ውሃ ላይ የምትዞር፣ የምትሽከረከር፣ ተንቀሳቃሽ ዕንዝዝ መሳይ። በግእዝ ከመዝ ፊካትም ትባላለች።
ውሃ እናት: የድጕስ መሣሪያ።
ውሃ ወረደ: ወደ ምንጭ፣ ወደ ወንዝ ውሃ ሊቀዳ ኼደ (አገደመ፣ ወጣ)።
ውሃ ወራጅ: ወደ ውሃ የሚወርድ፣ የሚኼድ፡ አግዳሚ፣ ኻያጅ ("ውሃ ወራጅ ዳኛ" እንዲሉ)። ዳኘን ይመልከቱ።
ውሃ ወጣበት: የበሬው፣ የፈረሱ ኰቴ መካከሉ ታመመ፡ ውሃ ቋጠረ።
ውሃ ውሃ አለ: ጠላው ቀጠነ፡ በሽተኛው "አኹንም አኹንም ውሃ ስጡኝ" አለ።
ውሃ ገብ: ውሃ የሚገባው መሬት፣ ባለመስኖ።
ውሃ ጠጪ (ስተዪ ማየ፡ ሰታዬ ማይ): ከብት ውሃ የሚጠጣበት ጊዜ (ቀትር፣ አውራ ተሲያት፣ ፮ (6) ሰዓት)።
ውሃ ፈረድ: ውሃ የለየው፣ የከፈለው አውራጃ፣ ወረዳ፣ ቀበሌ፣ አገር፣ መሬት።
ውሃማ: ውሃ የበዛበት ስፍራ።
ውሃን፣ በሶን ተመልከት።
ውሃዋ: ውሃዪቱ፡ ሴቴ ውሃ፣ ያች ውሃ። (ዘፍ፩፡ ፳፩)
ውሃዋ: የርሷ ውሃ።
ውሃው ዐለቀ: አንዱን አገር ለቆ ወደ ሌላው ኼደ።
ውሃው: ወንዴ ውሃ፣ ያ ውሃ። (፪ነገ፡ ፫፡ ፳፪)
ውሃው: የርሱ ውሃ።
ውህነት: ውሃ መሆን፡ የውሃ ባሕርይ።
ውለ ቢስ: ውልን የማያከብር።
ውለታ (ዎች): ጥቅም፣ ረብ፣ መልካም ሥራ፣ ቁም ነገር (አንዱ ላንዱ ያደረገው)። ወረታን እይ።
ውለታ ቢስ: ሰው የዋለለትን ወሮታ የማይመልስ።
ውለናሜ: የቍልምጫ ስድብ፡ የኔ ውለ ናም ማለት ነው።
ውለናም (ሞች): ውለን ያለበት።
ውለን (ውዒለነ): እዱር ውለን ማታ መጣን።
ውለን: የዦሮ መስሚያ በሽታ፡ ድንቍርና፣ አለመስማት።
ውለን: ደንቈሮ፡ ወለነ።
ውለን: ጨሃ፣ ዳባ፣ ሳም ስፍር።
ውለኛ (ኞች): ቁም ነገራም።
ውለኸ ግባ: የምርቃት ቃል፡ "እኼድክበት አትቅር፡ እቤትኸ ተመለስ። "
ውሊንጣ: የታናሽ ወፍ ስም።
ውሊጥ ውሊጥ አለ: ግራና ቀኝ ረገጠ፡ ከመንገድ ወጣ፡ አካኼድ ለወጠ።
ውላ (ኦሮ): ፉካ፣ መስኮት።
ውላጄ (ቍልዔየ): የኔ ውላጅ፣ አገልጋዬ፣ የወለዶኸ፡ ልጄ።
ውላጅ (ቍልዔ): እናቱና አባቱ በጌታቸው ቤት የወለዱት ባሪያ፡ የፍናጅ አባት። "የላሜ ልጅ ያውራዬ ውላጅ" እንዲሉ። አውራ ያባቱ፣ ላም የናቱ ምሳሌዎች ናቸው። (ኤር፪፡ ፲፬)
ውላጆች: ባሮች፣ አገልጋዮች።
ውላጋ (ለዓት): የሰይፍ፣ የጐራዴ ላት፣ እጀታ፣ መክድ፣ ደም ዐፋሽ። (መሳ፫፡ ፳፪)
ውላጤ (ጥወ): መለወጥ።
ውል (ሎች/ውዕል): ቶሎ የሚፈታ እስራት፣ ቍጥር ባለመሳቢያ።
ውል አለ: ትዝ አለ፡ ታሰበ፣ አማረ፣ ተናፈቀ።
ውል አለ: ትዝ አለ፡ ወለወለ።
ውል: ውሳኔ፣ ደንብ፣ ገደብ፣ ስምምነት። "እከሌና እከሌ በውል ታረቁ። " ያገራቸውን ቋንቋ የማያከብሩ ሰዎች ግን ውልን "ኮንትራት" ይሉታል።
ውልል: የተወለለ፡ ክፍት፣ ንቃቃት ራስ።
ውልምጥ ውልምጥ አለ: መላልሶ ወለመጠ።
ውልምጥ: የወለመጠ።
ውልምጥምጥ አለ: ተወለማመጠ።
ውልምጥምጥ: ዝውርውር፣ ዘወርዋራ።
ውልቃት: ንቅላት፡ የእግርና የእጅ ዐጥንት መውለቅ።
ውልቅ አለ: ንቅል ውጥት ፍልስ አለ።
ውልቅ: ደካማ፣ ስልቹ፣ ዝንጉ። "ልበ ውልቅ" እንዲሉ።
ውልቅልቅ አለ: ንቅልቅል አለ፡ ተውለቀለቀ።
ውልቅልቅ: የተውለቀለቀ፡ ንቅልቅል፣ ፍልስልስ።
ውልቅም: ውልግምም።
ውልቅምቅም አለ: ውልግምግም አለ።
ውልቅምቅም: ውልግምግም።
ውልባረግ: የጕራጌ ነገድና አገር።
ውልብ አለ: ታይቶ ጠፋ፡ ከመጽበት ዐለፈ፡ ወላባ ኾነ።
ውልብ: የወለበ፡ እሸቱ ከውስጡ የወጣ የስንዴ፣ የገብስ ራስ፡ ጥርጣሪ፣ ገለባ፣ የፍሬ ልብስ፣ ቈረቈንዳ።
ውልብልቢት (ቶች): ጫፍ፡ የእሳት ላንቃ፡ የኮባ፣ የንሰት፣ የሙዝ፣ የዘንባባ፣ የተምር ሸለም።
ውልብልብ: የተውለበለበ።
ውልብኝ (ወልብ): ያገዳ ፍሬ እሸት። "የማሽላ ውልብኝ" እንዲሉ።
ውልብኝ: የማሽላ እሸት፡ ወለበ።
ውልታ: ውል ማለት፡ ትዝታ፣ ማማር፣ አምሮት።
ውልታ: የወንድና የሴት ስም።
ውልክፋ: የንጨት ስም፡ በወይናደጋ ቈላ የሚበቅል ዛፍ፡ እንደ ተልባ የሚማልግ ማላጋ፡ ልጡ ማሰሪያ፣ መሰንከያ (የሰባራ አሞሌ መሰነጊያ ይኾናል)።
ውልክፍክፍ አለ: ስንክልክል አለ።
ውልክፍክፍ: ስንክልክል፣ ድንቅፍቅፍ።
ውልወላ: ጠረጋ፣ ዕሠሣ፣ ስንገላ።
ውልውል (ውልዋሌ): ጥርጥር፣ ማመንታት። ፪ኛውን ው አጥብቅ።
ውልውል አለ: ትዝ ትዝ አለ።
ውልውል አለ: ውንውን አለ፡ ተወዛወዘ፣ ተነቀነቀ።
ውልውል: ባንድ ዐይነት ጥለት ተመቶ የተሠራ ሸማ።
ውልውል: የተወለወለ፣ የተመታ፣ የታሠሠ፡ ዕሥሥ፣ ስንግል።
ውልደት: ልጅ የተወለደበት ቀን፡ ወይም ዕድሜ። "እከሌ እከሌን በውልደት ይበልጠዋል። "
ውልደት: የተወለዱበት አገር። "ውልደትኸ የት ነው?" እንዲል ባላገር።
ውልድ (ልደ ቤት): እናቱ ከጌታዋ የወለደችው ዲቃላ። "የቤት ውልድ" እንዲሉ።
ውልድ አለ: ድንገት ተገለጠ። "ዐሳሬ ውልድ አለ" እንዲል ባላገር።
ውልድ: መወለድ፡ የነገር አባት፣ ጠበቃ፣ ፍጅብኝ መኾን። "ውልዱም ውልዴ ርቱም ርቴ" እንዲሉ።
ውልዶች: ጠበቆች።
ውልግም: በታችኛው ወግዳ ቈላ ከዠማ በስተግራ ያለ አገር፡ ደንጐላጕል፣ ሥር ጓጕጥ ስፍራ፣ ቀበሌ።
ውልግም: ዝኒ ከማሁ።
ውልግምግም አለ: ተወለጋገመ።
ውልግምግም: የተወለጋገመ፡ ውልቅምቅም።
ውልግድ: ውልግም፡ የጐበጠ፡ ጐባጣ።
ውልግድግድ አለ: ጐባበጠ፡ ጕብጥብጥ አለ።
ውልግድግድ: የተወለጋገደ፡ ውልግምግም።
ውልጮ: መላጣ። "የራሱ ውልጮ ያስቀምጣል ዶጮ" እንዲል ገና ተሳዳቢ።
ውልጮ: የተራራ ስም፡ በሜታና በግንዶ በረት መካከል በሙገር በላይ ያለ ገደል።
ውሎ ማዋያ: ማስለቀሻ፣ ሰፊ ሜዳ፣ ማርገጃ።
ውሎ ማዋያ: እንዲሉ።
ውሎ ተዋለ: አለሬሳ ተለቀሰ።
ውሎ አዋለ: በመስቀል፣ ባጐበር፣ በተምሳሊት ከጧት እስከ ማታ አስለቀሰ።
ውሎ ውሎ: ከቤት።
ውሎ ገባ: ጧት ኺዶ ማታ ተመለሰ፣ መጣ። በፈረንጅ "አሌ ረቱር" ይባላል።
ውሎ: ሩቅ አገር የሞተ ሰው ለቅሶ (ከረፋድ እስከ ምሽት የሚደረግ)።
ውሎ: ቀን ሙሉ ቈይቶ።
ውሰት፡ ዝኒ ዓዲ ከማሁ፡ ትውስት።
ውሰና፡ (ውሳኔ)፡ ድንገጋ፡ ግደባ፡ ምደባ።
ውሲያን፡ (ኖች)፡ መንዘሮር፡ የዕቃ መስቀያ፡ ማንጠልጠያ። ወሳኝነትንና ውስንነትን ያሳያል።
ውሲያን፡ መንዘሮር።
ውሳጣዊ፡ የውስጥ።
ውስ ክስ፡ ጥጃን፡ ግልገልን ባንድነት ሐይ ማያ ቃል።
ውስ፡ የጥጃ፡ የወገዝ መከልከያና ማገጃ ድምፅ (ጥሽ) ወሽን የመሰለ፡ ተው፡ ወኺድ እንደ ማለት ያለ።
ውስልትልት፡ ፍጹም ወስላታ፡ ልክስክስ።
ውስልትና፡ ዝኒ ከማሁ፡ ምግጠት።
ውስብስብ፡ የተወሳሰበ፡ ውትብትብ፡ ጥልፍልፍ።
ውስትና፡ ዝኒ ዓዲ ከማሁ፡ ለዋስነት።
ውስን፡ (ውሱን)፡ የተወሰነ፡ ድንግግ፡ (ጥብ) ጥብቅ፡ ክልል።
ውስኪ፡ የእንግሊዝ ዐረቄ፡ ከሶዳ ጋራ የሚጠጣ የመኳንንት መጠጥ።
ውስወሳ፡ ሽድሸዳ፡ ዋና።
ውስውስ፡ የተወሰወሰ፡ ሽድሽድ፡ ሽልል፡ ሽክሽክ።
ውስድ፡ (ውሱድ)፡ የተወሰደ።
ውስድ አደረገ፡ በፍጥነት ወሰደ።
ውስጠ ልግም፡ ሀኬት፡ ተንኰል፡ ዕጥፍ፡ ሽሩባ።
ውስጠ ምስጢር፡ የውስጥ ምስጢር፡ ነገሩ ያልተገለጠ፡ የረቀቀ፡ የጠለቀ።
ውስጠ ብዙ፡ ሕዝብን፡ ሰውን የመሰለ ቃል።
ውስጠ ተንኰል፡ የሆድ፡ የልብ ጥመት።
ውስጠ ወይራ፡ (ሮች)፡ የቅኔ መምሩን ለመምታት በደበሎው ውስጥ የወይራ ዱላ የያዘ የቅኔ ተማሪ።
ውስጠ ወይራ፡ የቅኔ አገባብ ስም፡ አገባቦቹም ፰ ናቸው። መጽሐፈ ሰዋስው ፫፻፲ኛ ገጽ ተመልከት።
ውስጠ ዘ፡ ባነጋገሩ እንደ ግእዝ ዘ፡ እንዳማርኛ የ፡ የሚገለጽበት ቅጽል። ሰማያዊ ብሎ ዘሰማይ፡ የሰማይ ማለቱን ያሳያል።
ውስጠ ገበዝ፡ የገበዝ ወኪል፡ ግምጃን፡ ዕጣንን፡ ዘይብን የሚጠብቅ፡ የውስጥ ገበዝ።
ውስጠኔ፡ ባለውስጥ፡ ውስጠ ክፍት፡ ውዥሞ። ኔ ውስጣም ማለትን ያሳያል።
ውስጠኛ፡ ዝኒ ከማሁ (፩ነገ ፯: ፲፪፡ ኢሳ ፲፮: ፲፩)።
ውስጡ: ዐውደ ነገሥት፡ ሐሰተኛ ባሕታዊ፣ ጠንቋይ።
ውስጡን ለቄስ፡ ከቄስ በቀር ሌላ የማይሰው አበሳ።
ውስጣውስጡ፡ የውስጡ ውስጥ፡ ወክፈሴን እይ።
ውስጣውስጥ፡ የውስጥ ውስጥ።
ውስጥ፡ (ጦች)፡ መካከል፡ ሆድ፡ ባዶነት፡ ክፍትነት ያለው ኹሉ። ልብ፡ ቡጥ፡ በውስጥ ያለ ነገር።
ውስጥ ለውስጥ ተወራ: (ጐማ)።
ውስጥ ዐወቅ፡ የወዳጅ ጠላት።
ውስጥ እጅ፡ (እራኅ)፡ ከዳፍ እስከ ጣት ጫፍ ያለ፡ የባይበሉብሽ አንጻር፡ የእጅ ውስጥ።
ውስጥ እግር፡ ሰኰና፡ መርገጫ፡ መኬጃ፡ የእግር ውስጥ።
ውስጥ ውስጡን ኼደ፡ ዋኘ፡ ወሰወሰ።
ውስጥ ውስጥ አለ፡ ውንግ ውንግ አለ፡ ተወሰጠ።
ውስጥ፡ ደቂቅ አገባብ፡ ከሰው ስም በቀር በኹሉ ይገባል፡ በ፡ ከዘርፍ ጋራ ይቀድመዋል። በሴት ውስጥ፡ በባሕር ውስጥ። ፩: አገባቦች በመነሻነት ሲሰማሙትና ባለ * አማካይነት ሲነገር፡ እስከ ውስጥ፡ ወደ ውስጥ፡ የውስጥ፡ ከውስጥ፡ ውስጥ ለውስጥ ይላል። በስምም ቢገባ፡ ቦታን እንጂ ስምን አያሳይም። በግእዝ መሠረቱ ውስተ(ጠ) ነው።
ውረቃ፡ ማማር፡ ሽብረቃ።
ውረባ፡ መወረብ።
ውረድ በሌ፡ የሚያፈስ ቤት።
ውረድ፡ ተቈልቈል። (ሽለላ)፡ ውረድ እንውረድ ተባባሉና፡ ኣስደበደቡት አፋፍ ቆሙና።
ውሪ፡ (ዎች)፡ ታናሽ ልጅ፡ መንከት፡ ኵታራ፡ ውርውር ባይ፡ ተመላላሽ፡ ውርጋጥ።
ውሪ፡ ውርጋጥ ወረወረ።
ውራ፡ የሰርዶ ዐይነት ሣር፡ ማሳን የሚወር።
ውራ፡ የሰርዶ ዐይነት ወረረ።
ውራጅ፡ አሮጌ ልብስ፡ ያለቀ፡ የደቀቀ ጨርቅ፡ ከለባሽ አካል የወረደ።
ውር አለ፡ ድመትን ጠራ።
ውር፡ ውሮ፡ የድመት መጥሪያ፡ ወረረ።
ውር፡ ውሮ፡ የድመት መጥሪያ፡ ያይጥ ወራሪ ማለት ነው።
ውር፡ የተወረረ፡ የተዘረፈ።
ውርም፡ ውርጭ ያለበት፡ የበዛበት፡ ባለውርጭ ስፍራ፡ የውሃ ዳር አጠገብ።
ውርስ አደረገ፡ ውርር፡ ክብብ አደረገ።
ውርስ፡ የተወረሰ ርስት፡ ገንዘብ፡ ወይም ሰው።
ውርር፡ መውረር።
ውርር አደረገ፡ ወረረ፡ ክብብ አደረገ።
ውርርድ፡ ውድድር፡ ቍትቻ፡ ክርክር፡ ሙግት፡ ማር፡ በቅሎ፡
ፈረስ፡ አሞሌ።
ውርሻ፡ ሹም የወረሰው። (ተረት)፡ እከሌ የዋለበት ሸንጎ ዐይጥ የገባበት ርጎ። ርጎውን ለውሻ፡ እሱንም ለውርሻ።
ውርባ፡ ሌሊት ከአየር የሚወርድ፡ ውርጭን እይ።
ውርብ፡ የተወረበ፡ ሣር፡ ዜማ።
ውርንጫ፡ (ጮች)፡ ውርንጭላ፡ (ሎች)፡ ያህያ ግልገል፡ ተባቱም አንስቱም ውርንጫ፡ ውርንጭላ ይባላሉ (ማቴ ፳፩: ፪፡ ፭)። ላ በግእዝ አላት ማለት ስለ ኾነ፡ እናቲቱን ያስተረጕማል።
ውርኝት፡ ዐራጣ፡ (ወረኘ)።
ውርኝት፡ ወለድ፡ ዐራጣ፡ ለተበዳሪ የሚሰጥ፡ የሚበተን፡ የትርፍ ትርፍ እንዲያመጣ። ርኝትን ተመልከት።
ውርወራ፡ የጦር፡ የፍላጻ፡ ንድፊያ፡ ቅርቀራ፡ ሽጐራ፡
ደንጊያ መጣል (ሉቃ ፳፪: ፵፩)።
ውርውር፡ (ውርው)፡ የተወረወረ፡ ጦር፡ ማግ፡ ሰው፡ ኳስ።
ውርውር አለ፡ (አንበስበሰ)፡ ተመላለሰ፡ የሕፃን፡ የባለክንፍ።
ውርውር አለ፡ እጠልቅ እጠልቅ፡ ርግብ ርግብ አለ።
ውርውርታ፡ (ነበስባስ)፡ ውርውር ማለት፡ የፀሓይ መግባት፡ ጥልቅልቅታ፡ ርግብግብታ።
ውርውርጭ፡ የውርጭ ውርጭ፡ ብዙ ውርጭ።
ውርዘት፡ ላብ፡ የድካም ወዝ።
ውርዬ፡ የኔ ውሮ፡ የኔ ድመት፡ ብሴ፡ ቍልምጫን ያሳያል።
ውርደት፡ መዋረድ፡ ዕጦት፡ ንጣት፡ ጕስቍልና፡ ድኽነት (ምሳ ፲፩: ፪፡ ፲፰: ፲፪)።
ውርዴ፡ (ዎች)፡ ቂጥኝ የወጣለት፡ የረገፈለት፡ ከገላው የወረደለት ሰው። ቂጥኛም ከውርዴ ይጫወታል እንዲሉ።
ውርድ፡ ትችት፡ የነገር ሐተታና ማስረጃ። ውርድ ነዢ እንዲሉ። ሰማይ አይታረስ፡ ውሃ አይጠበስ፡ አባት አይከሰስ። ሰማይ በመብረቅ ይታረሳል፡ ውሃ በምንቸት ይጠበሳል፡ አባት በወንጀል ይከሰሳል (አቶ አጐናፍርና ልጃቸው አቶ ሀብተ ማርያም)።
ውርድ፡ የወረደ፡ የተለየ። ውርድ ከራሴ እንዲሉ።
ውርጂ፡ ያንተን ይስጠኝ ፈረስ።
ውርጂብኝ፡ ሳይታሰብ ድንገት በሰው ላይ የወረደ አደጋ።
ውርጂብኝ፡ ባለማቋረጥ የተደረገ ቍጣ፡ መዓት።
ውርጃ፡ ጭንገፋ፡ የፅንስ፡ የሽል፡ መጪንግፍ።
ውርጋጥ (ጦች)፣ ሲራገጥ፡ ሲላፋ፡ ሲጫወት፡ የሚውል፡ ልጅ።
ውርጋጥ፡ የሚራገጥ ልጅ፡ ረገጠ።
ውርጫ፡ የወንድና የሴት መጠሪያ ስም፡ የኔ ውርጭ ማለት ነው።
ውርጭ፡ (አስሐትያ)፡ በበጋ ከአየር የሚወርድ ቀዝቃዛ ውርባ፡ ቡቃያ አጥፊ፡ መስተዋት እየመሰለ በውሃና በምድር ላይ የሚጋገር፡ ቅቤ አድርቅ፡ አፍንጫ አቅልጥ (ዘፀ ፲፮ - ፲፬)።
ውርፍ፡ (ፎች)፡ የተወረፈ፡ የተሰደበ፡ ስዱብ።
ውርፍነት፡ ውርፍ መኾን።
ውሸተኛ፡ (ኞች)፡ ሐሰተኛ፡ ዋሾ፡ ውሸታም ዐብሎ አይደክም።
ውሸታም፡ (ሞች)፡ ባለውሸት፡ ሐሰተኛ፡ ጽድቁ።
ውሸት፡ ኵሸት፡ ሐሰት፡ ዕብለት፡ ቅጥፈት።
ውሹቴ፡ የገረጣ ጽጌ ረዳ።
ውሺት፡ እንስት ውሻ፡ የስድብ ቃልም ይኾናል። ወሽ፡ ውሻ፡ ውስ ማለት የቋንቋው መሠረት አንድ ነው፡ አውሬነትንና እንስሳነትን በዋሻ ማደርን ያሳያል።
ውሻ፡ (ሾች)፡ (ዐረ፡ ዋሕሽ፡ አውሬ)፡ በቤት የሚኖር፡ ለማዳ አውሬ፡ በፈጣሪ ትእዛዝ ከዥብ፡ ከተኵላ፡ ከቀበሮ በጥንተ ፍጥረት ተለይቶ ከአዳም (ከሰው) ጋራ የሚኖር፡ የቤት ዘበኛ (፪ጴጥ ፪: ፳፪፡ ራእ ፳፪: ፲፭)። ስሙንም ጌቶቹ ተለባብሶ እያሙ፡ ፍቅር እያሙ፡ ሤራ ሳያጠሩ ክፉን ችላ ይሉታል። ተባቱም እንስቱም ውሻ ይባላል። (ተረት)፡ ባለቤቱን ካልናቁ ውሻውን አይመቱ። ዥብ ከኼደ ውሻ ጮኸ። የወረት ውሻ፡ ስማ ወለተ ጴጥሮስ። ውሻ የጌታዋን ጌታ አታውቅም። ውሽማን ተመልከት።
ውሻ በጨው አይቀምሰውም፡ ምን ጊዜም አይፈለግም።
ውሻ ያገኘው ሊጥ፡ ሞኝ ያገኘው ፈሊጥ እንዲሉ።
ውሻል፡ (ሎች)፡ ሽብልቅ፡ የሥራ ማስተካከያ፡ በጐደለ መሙሊያ፡ የዕርፍ ማቃኛ፡ ሥንጥር፡ ቶፋ። (የነገር ውሻል)፡ ስርዋጽ።
ውሻነት፡ ውሻ መኾን፡ መባል፡ ልክስክስነት።
ውሻው አለቀሰ፡ ስለ ራበው ወደ ፈጣሪ ጮኸ፡ ተማለለ።
ውሻው፡ ያ ውሻ፡ የርሱ ውሻ።
ውሽል፡ የተወሸለ፡ ውክል።
ውሽልሽል አለ፡ ውትፍትፍ አለ፡ ተውሸለሸለ።
ውሽልሽል፡ የተውሸለሸለ፡ ቀላል፡ ሥራ።
ውሽማ፡ (ውሻማ)፡ አመንዝራ ወንድ ወይም ሴት፡ ውሻዊ፡ የውሻ ዐይነት ወገን። ውሽማ ለሴትም ኾነ ለወንድ ጠላት ሲኾን በስሕተት ወዳጅ ይባላል። (ተረት)፡ ውሽማዋን ብታይ ባሏን ጠላች።
ውሽምብር፡ ቍትቻ፡ ውሽንብር።
ውሽምነት፡ ውሽማ መኾን።
ውሽሞች፡ አመንዝሮች፡ ወንዶችና ሴቶች።
ውሽሽ፡ (ሰከሕካሕ)፡ ዐሠር፡ ገለባ።
ውሽሽ፡ ሥሩ ድንችና ሽንኵርት የሚመስል በስሜን የሚገኝ ቅጠል።
ውሽሽ አለ፡ ተንሻፈፈ።
ውሽሽ፡ ጤና ማጣት።
ውሽቅ አለ፡ ተወሸቀ።
ውሽን፡ ዝኒ ከማሁ፡ ለወሸን።
ውሽንብር፡ ውሽምብር፡ በጨዋታ የሚደረግ ውርርድ፡ ቍትቻ።
ውሽንግር፡ ዐይነ ጠማማ፡ ሸነገረ።
ውሽንፍር፡ አግድም የሚዘንም ዝናም፡ ወጨፎ።
ውሽግርግር፡ ውንግርግር፡ ውንክርክር።
ውሾ፡ ውሻ ፊት፡ ገጸ ከልብ እንድሪስ። እጀታው በውሻ አፍ አምሳል የተሠራ ሎንዶን፡ ጐራዴ። ቃለ አስተሐቅሮም ይኾናል። (ተረት)፡ ውሾን ያነሣ ውሻ ይኹን፡ ውሻ አይበላሽ ጥል የሚያስቸግር።
ውሾ ውሾ አለ፡ አረከሰ።
ውቂያ፡ ድብደባ፡ አኼዶ፡ ፍልፈላ።
ውቃም፡ አመንዝራ ወንድ፡ የምሳሌ ስድብ ነው።
ውቃም፡ ውቃጭ ያለበት፡ ባለውቃጭ።
ውቃሪ፡ የፍወጮ ድቃቂ፡ የደንጊያ ዱቄት።
ውቃበ ቢስ፡ ሰይጣናም ሰው።
ውቃቢ፡ (ዐቃቢ)፡ ጠባቂ መልአክ።
ውቃቢ፡ (ዑቃቤ)፡ ጥበቃ፡ የዘብ ሥራ። መላከ ውቃቢ እንዲሉ። ዐቀበን ተመልከት።
ውቃቢ ራቀው፡ ሸሸው፡ ተለየው።
ውቃቢ ቀረበው፡ ተጠጋው፡ ጠበቀው።
ውቃቢ አስራቀ፡ ሰዶበ፡ አዋረደ፡ ክብርን ነሣ፡ ገፈፈ።
ውቃቢ፡ ክፉ መንፈስ፡ ዛር፡ ቆሌ፡ የጋኔን ዘበኛ።
ውቃቢ፡ ደግ መንፈስ። (ተረት)፡ ሐሰት ቢናገሩ ውቃቢ ይርቃል።
ውቃጭ፡ እሾኸ የወጋው የውስጥ እግር ዕብጠት፡ ወይም ቍስል።
ውቃጭ፡ የሙቀጫ ገለባ፡ ንፋሽ፡ ደቃቅ ዐሠር።
ውቅ፡ (ውቁዕ)፡ የተወቃ፡ ምት፡ ፍልፍል፡ ከእብቅ ያልተለየ ፍሬ።
ውቅሥ፡ (ውቁሥ)፡ የተወቀሠ፡ የተገሠጸ።
ውቅራት፡ ንቅሳት፡ የድድ ውግታት፡ ጥቍራት።
ውቅር፡ (ውቁር)፡ የተወቀረ፡ ጥርብ፡ ሻካራ፡ ስል፡ የደንጊያ፡ ወፍጮ።
ውቅር ዐዋቂ፡ በልብ ውጋት፡ በምስማር ጠራቂ።
ውቅር፡ የጣራ ውጥን ዥምር (ምሳ ፳፭: ፳፬)።
ውቅሮ፡ የዋሻ ቤት ተወቅሮ ተጠርቦ የተሠራ።
ውቅሮች፡ አንዳንድ ጠርቦች፡ ዥምሮች።
ውቅያኖሳዊ፡ የውቅያኖስ፡ ደሴት፡ አገር፡ በውቅያኖስ ውስጥ ያለ። ፈረንጆች ፆሲያንያ ይሉታል።
ውቅያኖስ፡ (ቀላይ)፡ የጥልቅና የሰፊ ባሕር ስም። ባሜሪካና በእስያ መካከል ያለው ፓሲፊክ፡ በእስያና ባፍሪቃ መካከል የሚገኘው የህንድ ውቅያኖስ፡ ባሜሪካና ባውሮጳ ባፍሪቃ መካከል የተዘረጋው አትላንቲክ ይባላል። ሌሎችም ካውሮጳ በላይ (በሰሜን)፡ ባሜሪካና ባፍሪቃ በታች (በደቡብ) የተንጣለሉ ውቅያኖሶች አሉ፡ የኹሉም ቍጥር ፭ ነው።
ውቅያኖሶች፡ (ቀላያት)፡ ጥልቆች፡ ሰፋፊ ባሕሮች።
ውቅጥ፡ (ውጉእ)፡ የተወቀጠ፡ ፍትግ፡ ሽክሽክ። ውቅጥ በርበሬ እንዲሉ።
ውበታም: ውበት የተሰጠው።
ውበቴ: የሰው ስም፣ የኔ ውበት ማለት ነው።
ውበት፡ "ማማር" ማለት ነው (ዋበን ይመልከቱ)።
ውበት: ማማር፣ ደም ግባት፣ ወዝ፣ ላህይ።
ውቡ/ውቢት/ውቢቱ: የወንድና የሴት ስም።
ውቤ: የኔ ውብ ተብሎ ይተረጎማል።
ውብ (ውሁብ፣ አዳም፣ ሠናይ፣ ልሑይ): የተዋበ፣ የተሰጠ፣ የቆነዠ፣ ቆንጆ፣ ሸጋ፣ መልከ መልካም፣ ደመ ግቡ።
ውብ ነህ/ነሽ: የወንድና የሴት መጠሪያ ስም።
ውብ አየሁ: የወንድና የሴት ስም።
ውብ እሸት: የወንድና የሴት ስም።
ውብ የሻው: የሴት ስም፣ ቆንጆ የፈለገው ማለት ነው።
ውብ: ሸገነ።
ውብነት: ውብ መሆን፣ ቆንጅና።
ውቦች: የተዋቡ፣ የሚያምሩ ቆንጆዎች (ወንዶችና ሴቶች)።
ውተፋ: ሽጐጣ፣ ከደና።
ውታፍ (ፎች): መወተፊያ፡ ክዳን፣ ሣር፣ ቅጠል፣ ቡሽ።
ውት፡ (ዋተተ)፡ የምድር ላበት፡ የብላጊ ምልክት፡ የጉም ዐይነት፡ ከሰው አፍ በብርድ ጊዜ ጪስ እንደሚወጣ፡ ይህም እንደዚያ ነው። አስታና፡ ጓሳ፡ ደን፡ ተራራ ባለበት ስፍራ ይበዛል። ውት ጣለ፡ ውቱን ጐተተ እንዲሉ።
ውትር ውትር አለ: ግትር ግትር አለ። (ተረት): ከውትር ውትር ይነሣል በትር።
ውትር: የተወተረ፡ ውጥር፣ ዝርግ።
ውትርትር: የተውተረተረ፡ ግትርትር።
ውትብ፡ የተወተበ፡ ጥምጥም፡ ሸለ።
ውትብትብ፡ የተውተበተበ፡ ውሽልሽል፡ ውስብስብ።
ውትወታ: ጕትጐታ፣ ንዝነዛ፣ ዝብዘባ።
ውትውት: የተወተወተ፣ የተነዘነዘ፡ ጕትጕት፣ ንዝንዝ።
ውትፋት: ክድናት።
ውትፍ አለ: ሽጕጥ አለ፡ ተወተፈ።
ውትፍ ውትፍ አለ: ሽጕጥ ሽጕጥ አለ።
ውትፍትፍ አለ: ተውተፈተፈ።
ውትፍትፍ: የተውተፈተፈ፡ ውሽልሽል፣ ውትብትብ፡ የማይረባ ሥራ።
ውነጋ፡ ውዝወዛ።
ውንብድና፡ ዝኒ ከማሁ፡ ንጥቂያ፡ ሩ።
ውንክርክር አለ፡ ውንግርግር አለ።
ውንክርክር፡ የተወነካከረ፡ ውንግርግር።
ውንውን አለ፡ ተወዘወዘ፡ ተነቀነቀ፡ ውዝውዝ አለ።
ውንውን አደረገ፡ ዝኒ ከማሁ፡ ውዝውዝ አደረገ።
ውንዥቅ፡ የወይን ሖምጣጤ።
ውንጀላ፡ መወንጀል።
ውንጅር፡ (ሮች)፡ ያይጥ፡ ዓሣ፡ ሰው የማይበላው።
ውንጅርጅር፡ ፍንጅርጅር።
ውንግ ውንግ አለ፡ ውስጥ ውስጥ አለ።
ውንግ፡ የተወነፃ፡ የተወሰጠ።
ውንግርግር፡ ውንክርክር።
ውንግርግር፡ ውንክርክርን እይ።
ውንጥ ውንጥ አለ፡ ውንግ ውንግ፡ ውዝውዝ አለ።
ውንጥ፡ የተወነጠ፡ ውንግ፡ ውዝውዝ።
ውኪ/ውኪያ (ወክሕ): ፉከራ፣ ድንፋታ፣ ጫጫታ፣ ፍጅት፣ ግርግርታ፣ ጩኸት። ውካታን ይመልከቱ፡ ከዚህ ጋር አንድ ነው።
ውካታ (ወከተ): የብዙ ሰው ድምፅ፣ ቱማታ፣ ጩኸት። (ኢዮ፴፡ ፲፬። ሆሴ፲፡ ፯፬)
ውክል (ውኩል): ዝኒ ከማሁ ለወኪል (ልክ እንደ ወኪል)።
ውክልና: ወኪል መኾን፡ ወኪልነት።
ውዛጊ: ነጠላ ፈትል፡ የዝሓና፣ የግራ ክር።
ውዝት: የተወዘተ ሸክላ፡ ውዝፍ፣ ርፍቅ (ሰው)።
ውዝወዛ: ሰበቃ፣ ንቅነቃ፣ ንጦሽ። (ሕዝ፳፡ ፵)
ውዝዋዜ: ውዝውዝታ፡ መወዝወዝ፣ እስክስታ፡ የሐዘን፣ የመከራ ንቅናቄ። (ኢሳ፳፱፡ ፪። ሮሜ፰፡ ፳፪)
ውዝውዝ አለ: ተወዘወዘ።
ውዝውዝ: ንዝንዝ፣ ውዝግብ፣ ጭቅጭቅ።
ውዝጋት: መዘጋ፣ ጕተታ (የፈትል)።
ውዝግ: የተወዘገ፣ የተሳበ ፈትል።
ውዝግብ: አተካራ፣ ጭቅጭቅ፣ ንዝንዝ።
ውዝግዝግ: ም(እን)ዝግዝግ፣ ቅዝምዝም።
ውዝፍ አለ: ተወዘፈ።
ውዝፍ: ተዠምሮ የተተወ፣ ያላለቀ ሥራ፡ ወይም ሳይሠራ የቀረ፣ የታጐለ ግብር። (ተረት) "ውዝፍ ለሹም፡ ጥንብ ለዥብ። "
ውዥልዥል: ጐታታ፣ ጕትት፣ ውዥምዥም።
ውዥምዥም: ረዥም ጕትት (ልብስ፣ ክንፍ)፡ ወይም ሌላ ነገር እንደ ዓረብ ውዥሞ ያለ።
ውዥሞ: ውስጠ ክፍት እንጨት፣ መቃ፣ ብረት፣ የጪስ አሸንዳ፡ ባለመጠጫ፣ የትንባሆን ጪስ ስቦ የሚጠጣበት። ሲበዛ "ውዥሞች" ይላል። ዘነዘናንን ይመልከቱ።
ውዥቅ ውዥቅ አለ: ውዝውዝ አለ።
ውዥቅ: የዋዠቀ፡ ንቅንቅ።
ውዥኝ (ኞች): የታናሽ እንጨት ስም፡ በጐኑ ከቅጠል በቀር ዓጽቅና ጕጥ የሌለው፣ መላላ፣ ቀጭን እንጨት (ችቦ የሚሆን)።
ውዥግራ: ነፍጥ፣ ጠመንዣ። በፈረንጅኛ "ፉዥግራ" ይባላል።
ውየባ: ውረቃ።
ውይ (ወይ ወዮ ዋይ): ሰው ከሞተ በኋላ ወይም በመርዶ ጊዜ መዠመሪያ የሚደረግ ዋይታ፣ ጩኸት፣ ቍቁታ። "ዛሬ ሌሊት እከሊት ውይ አለች። "
ውይ ተባለ: ሆነ፣ ተደረገ (ጩኸቱ)።
ውይ ውይ ውይ: ሬላ ሲጓዝ የሚባል ጩኸት፣ ቍዘማ፣ የሐዘን ዜማ፣ እንጕርጕሮ። ወይ፣ አወይ፣ ወዮ፣ ዋይ፣ ውይ ንኡስ አገባቦች ናቸው። ከነዚሁም ወይ፣ ዋይ የግእዝ፡ የቀሩት ያማርኛ።
ውይብ አለ: ወየበ።
ውይብ: የወየበ።
ውይይት: የሐዘን ንግግር፣ የለቅሶ ጭውውት።
ውደሳ: የምስጋና ስጦታ።
ውደራ: ጥመራ፣ አሰራ።
ውዲላ (ሎች): መጥፎ ጐረምሳ፡ ውፋሬንም ያሳያል። ጠዘለ ብለው ጠዘልን ይመልከቱ።
ውዳሞ: የጠፋ እህል፣ አዝመራ፣ ሣር።
ውዳሴ ማርያም: የመጽሐፍ ስም፡ የማርያም ምስጋና (ቅዱስ ኤፍሬም የደረሰው የሰባት ቀን ጸሎት)፡ በዳዊት መጨረሻ የሚጻፍ።
ውዳሴ አምላክ: የመጽሐፍ ስም፣ የጸሎት መጽሐፍ (ከቅዱስ ባስልዮስ፣ ከቅዱስ ኤፍሬም፣ ከሌሎችም ቅዱሳን አበው የተደረሰ አስተዋፅኦ)፡ ትርጓሜውም "የአምላክ ምስጋና" ማለት ነው።
ውዳሴ ከንቱ: ብላሽ፣ የማይረባ ምስጋና። (ግጥም) "ቅዳሜ ተረግዘሽ እሑድ ተወልደሽ፡ ሰኞ ክርስትናሽ ማግሰኞ ሰርግሽ፣ ገብሬል አሳላፊ ሚካኤል፡ ወጥ ቤት፡ አሳራጊው አባ ተክለ ሃይማኖት። "
ውዳሴ: ምስጋና።
ውዳቂ: የተጣለ፣ ጥንብ፣ በክት።
ውዴ: የኔ ውድ፣ ፍቅሬ፣ ስምሜ።
ውዴላ: በአቡነ ዘለብ ላይ፣ ከደኃራይ በስተኋላ ያለ ጭነት።
ውዴታ: ውድ፣ መውደድ፣ ፈቃድ።
ውድ ነኸ/ነሽ: የወንድና የሴት ስም።
ውድ: ምስክር፣ እማኝ (በከሳሽና በተከሳሽ መካከል ምስክርነቱ የተወደደ)።
ውድ: የተሰካ ስክ፣ ዛቢያ፣ እርፍ፣ ሶማያ፣ እጀታ።
ውድ: የተወደደ፣ የተፈቀረ፣ የተጨበጠ፡ የነብር ቂንጥር።
ውድ: ፍቅር፣ ፈቃድ። (ዮሐ፲፭፡ ፫) "አለውድ በግድ" እንዲሉ።
ውድል: የተወደለ፡ ውድን፣ ውድር (ከኮርቻ ጋር የታሰረ)።
ውድማ አስፈሬ: የሐበሻ ንጉሥ ስም ነው። ትርጓሜው ውድማን የሚያስፈራ። የነበረበት ዘመን ፱፻ (900) ዓ.ም.፡ ሁለተኛው ደግሞ ፲፬፻ (1400) ዓ.ም. ነው።
ውድማ አርዕድ: የኢትዮጵያ ንጉሥ ስም ነው። የነበረበት ዘመን ፲፫፻ (1300) ዓ.ም.፡ ውድማን አንቀጥቅጥ ማለት ነው።
ውድማ አውድማ: አወደ።
ውድማ: ደን፣ ጫካ፣ ዎማ (ከአውሬ በቀር ሰው የማይኖርበት)፡ መግቢያ፣ መውጫ፣ መተላለፊያ የሌለበት፡ ጥንት ሰው ኑሮበት ኋላ ጠፍ የሆነ ስፍራ። (ዘሌ፳፮፡ ፴፩። ፩ሳሙ፡ ፳፫፡
፳፬። መዝ፻፪፡ ፮)
ውድም አለ: ጥፍት አለ (የመብራት፣ የዓይን)።
ውድም: ውድማ (ጥሬ)፣ ጥንታዊ አማርኛ ነው። አንበሳን ይመልከቱ።
ውድም: የወደመ (ቅጽል)።
ውድራት: እስራት፣ ጥምጥማት።
ውድር: እሰጥ የተባለ (ማር፣ በቅሎ፣ ፈረስ)።
ውድር: የተወደረ፣ የተጋዳ፣ የታሰረ፡ እስር (ዛፍ፣ እንስሳ፣ ሰው)።
ውድቀት (ድቀት): መውደቅ፣ መርከስ፡ ነውር፣ ርክስና፣ ኅሳር፣ ውርደት። (ምሳ፰፡ ፲፪። ኤር፮፡ ፳፩)
ውድቂያ: ዝኒ ከማሁ።
ውድቃን (ውዱቃን): የወደቁ፣ የተጣሉ፡ ልማዱ ግን "የወደቀ" ነው።
ውድቅ (ውዱቅ): የወደቀ፣ የተዋረደ፡ ወራዳ።
ውድቅ አለ: ድንገት ፈጥኖ ወደቀ።
ውድቅ: የአንብር አይነት ምልክት።
ውድቅት: ድቅድቅ፣ ጥቅጥቅ ጨለማ፡ ዐይን ቢወጉ የማይታይ፣ ሰው የሚወድቅበት፣ የሚሰናከልበት፡ ወይም የሚተኛበት፣ የሚጋደምበት፣ የመኝታ ጊዜ። በግእዝ ግን ድን አላልቶ የወደቀች ተብሎ ይተረጎማል።
ውድነት: ውድ መሆን፣ አለመርከስ።
ውድን: የተወደነ፡ ቡድን፣ ቅርቅብ።
ውድድር (ሮች): ፍክክር፣ ክርክር፣ ውርርድ።
ውጁ: የተዋጀ፣ የተገዛ፣ ግዝ፣ ባሪያ ወይም ሌላ።
ውጉዝ (ዞች)፡ የተወገዘ፣ የተገዘተ፣ ግዝት፣ የተለየ ("ውጉዝ ከመ አርዮስ")።
ውጊ/ውጊያ/ውጊት፡ ጦርነት፣ የጦርነት ሥራ፣ ግድያ፣ ንድፊያ።
ውጋት (ውግአት)፡ መውጋት፣ መወጋት (በሽታ)።
ውጋት፡ የሰውነት ክፍልን እንደ ጦር የሚወጋ ህመም (መጋኛ)። (የውጋት)፡ በዋገምት ማገም፣ በብርጭቆ መንጠቅ (አስማት፣ መድኃኒት)።
ውጋዝ፡ የሱማሌ ባላባት፣ ዳኛ ሠሪ፣ ቀጪ።
ውጋዴ፡ በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ ያለ አገር።
ውጋገን/ውጋጋን፡ ከጧት አስቀድሞ የሚታይ ጸዳል (ያጥቢያ ኮከብ ጊዜ)። ከምድር/ከሰማይ በሩቅ የሚታይ የፀሐይ/የጨረቃ/የመብረቅ/የእሳት ብርሃን ፍለጋ ምልክት።
ውግ (ጎች) (ውጉእ)፡ የተወጋ ገላ።
ውግ፡ የብራና ጥቁም፣ የገበጣ ጠጠር። የጠመንዣ ጽሑፍ ምልክት፣ የሻለቃ ስም።
ውግረት: መውገር፣ ወገራ፣ መወገር።
ውግራት: የድንጋይ ምት።
ውግር (ውጉር): የተወገረ፣ የተደበደበ።
ውግር: በሺዋ ክፍል በተጉለት ጫፍ ያለ አገር።
ውግታት (ቶች)፡ ነዳላ ቁስል፣ ጦር የወጋው፣ ቀስት የነደፈው የገላ ሽንቁራት።
ውግዣ/ውግዘት፡ ግዘታ፣ ልየታ።
ውግድ፡ የተወገደ፣ ልዩ፣ ሩቅ።
ውግጥ (ውጉእ)፡ የተወገጠ፣ የታወከ፣ የተወቀጠ።
ውጠራ: ልጠጣ፣ ግተራ፣ ጥየቃ።
ውጠና (ውጣኔ): ዥመራ፣ ፈለማ፣ ቀደማ፣ ምሥረታ።
ውጡ (ውፁእ): ዝኒ ከማሁ ለወጥ። "ዕገውጡ" እንዲሉ።
ውጣኝ (ኞች): የድር ፈትል ዥምር፡ ታናሽ ልቃቂት።
ውጤታ/ውጤት: ፍሬ፣ ምርት፡ ዐላባ።
ውጤታ: አወጣጥ። "ውጤታው አማረ" እንዲሉ።
ውጥ (ውኁጥ): የተዋጠ፣ ስልቅጥ።
ውጥራት: ውጥርነት፣ ዝርግነት።
ውጥር (ውቱር): የተወጠረ፣ የተሳበ፣ የተገተረ፡ ልጥጥ፣ ግትር፣ ኵሩ።
ውጥር አለ: ንፍት ቅብትት አለ።
ውጥርነት: ቍንንነት፣ ኵሩነት።
ውጥት አለ: ፈጥኖ ወጣ፣ ብቅ አለ።
ውጥት: መውጣት።
ውጥኔ: የውጥን፡ በቀይና በብጫ መካከል ያለ ቀለም፡ ቅላቱ ፈገግ ያለ፡ ፈገግታን የወጠነ ጥለት (የብርቱካን ዓይነት)።
ውጥን (ኖች/ውጡን): የተወጠነ፣ የተዠመረ፡ ዥምር ስፌት፡ የተፈለመ፣ ፍልም። (መዝ፻፴፱፡ ፲፮)
ውጥን ቅጥ: ዓይነቱ ቅጡ ውጥን የኾነ። ስንዴ ብቻ አይሉት ገብስ፡ ባቄላ ብቻ አይሉት አተር፡ በያይነቱ ድብልቅና ቅይጥ፣ ዝንቅ የልመና እህል ምስ የሚሆን።
ውጥን ጨራሽ: የመ ሳድስ ም የተወጠነውን ቃል የሚጨርስ (ለምሳሌ አብርሃም ሞተ ካለ በኋላ ይሥሐቅም ማለቱን ያሳያል)።
ውጥጥ: የተወጠጠ፡ ግትር፣ ዙሩ።
ውጦሽ: የኮሶ፣ የመድኀኒት መዋጥ፣ አዋዋጥ።
ውጪ (ፃኢ): ወደ ውጭ ኺጂ።
ውጪ ነፍስ: የጣር ብዛት። "ውጪ ነፍስ ግቢ ነፍስ" እንዲሉ በጣረ ሞት ጊዜ።
ውጪና ደብልቂ: ጠበኛ ሰው።
ውጭ አገር: የሌላ መንግሥት አገር።
ውጭ፡ ውሪ፡ ሙሊ፡ የሰው፡ የዝንጀሮ ልጅ። (ጫጫ)፡ አንጫ፡ አንቻቻ፡
አስጮኸ። ዘሩ በግእዝ ጣእጥኣ ነው።
ውጭ: እዳሪ፣ ዱር፣ ከቤት ከቅጥር በአፍኣ ያለ።
ውጭ: ውሪ፣ ጪ።
ውጭ: ጉዳይ፡ ከውጭ አገር መልእክተኞች ጋር የሚፈጸም ነገር።
ውፈራ፡ ውፋሬ፡ ድንዶና፡ የአካል፡ የመጠን፡ የጐን ጭመራ።
ውፍረት፡ ወፍር፡ ስፋት፡ መወፈር።
ዉ አለ: ተበጠሰ።
ዉ: የካዕብ ፊደል ሁሉ ድምፅ ሥርና መሰረት።
ዉዉ: የውሻ ጩኸት፡ "ያው ያው" እንደ ማለት ነው።
ዎ (ኦ): ሆይ ("ዎ አምላክ፣ ዎ ክርስቶስ")።
ዎ: ለቅርብ ወንድና ሴት በስምና በአንቀጽ መጨረሻ እየገባ የርስዎታ ዝርዝር ምእላድ ይሆናል (ርስ-ርስዎ፣ ቤት-ቤትዎ)።
ዎ: የሳብዕ ፊደል ድምፅ ሥረይ።
ዎሆ (ሆይ): በአኺዶ ጊዜ ለበሬ የሚዜም ቃል፡ የዘፈን አዝማች። "ዎሆ በሬ" እንዲል ገበሬ። ዎ የሐባብ፡ ሆ የሆይ ከፊል ነው።
ዎሎ (ላሎ): ሰፊ ሱሪ፣ የሚዋልል፡ ቦላሌ።
ዎማ (ፆም): ብዙ ሣርና ያረም ቅጠላቅጠል።
ዎማ ዋጠው: ሣር ቅጠል አጠለቀው።
ዎች፡ (አ፡ ው፡ ት)፡ የማብዛት ቃል። ዐዋቂ፡ መነኵሴ፡ ሥራ፡ ዶሮ ያለውን፡ ዐዋቂዎች፡ መነኵሴዎች፡ ሥራዎች፡ ዶሮዎች፡
ማለቱን ያሳያል። ሰማዮች፡ ባሕሮች፡ ወንዞች፡ ቤቶች ቢል፡ ዎን፡ ጐርዶ ነው።
ዎች፡ በታቦት ስም መጨረሻ እየተጨመረ ለብዙዎች ካህናት በቂ ይኾናል። (ማስረጃ)፡ ገብርኤሎች፡ ጊዮርጊሶች፡ ሚካኤሎች፡ ማሪያሞች፡ ሥላሴዎች።
ዎች፡ ባገር ስም ጫፍ እየታከለ በበቂነት ሕዝብና ነገድን ያስተረጕማል። (ማስረጃ) ሺዋ፡ ሺዎች፡ ጐዣም፡ ጐዣሞች፡ ጐንደር፡ ጐንደሮች፡ ትግሬ፡
ትግሮች።
ዎች ፋንዶን፡ ዮች ፋንድያን ይከተላል።
ዎዎ: ሆይ ሆይ። ዎን ይመልከቱ።
No comments:
Post a Comment