ሀ ለ ሐ መ ሠ ረ ሰ ሸ ቀ በ ተ ቸ ኀ ነ ኘ አ ከ ኸ ወ ዐ ዘ ዠ የ ደ ጀ ገ ጠ ጨ ጰ ጸ ፀ ፈ ፐ
ጠ
፡ ፱ኛ ፊደል፡ በግእዝ እልፍ ቤት በአበገደ። በፊደልነት ስሙ "ጠይት"፡ በአኃዝነት "ጠ ፱" ይባላል።
ጠ ፡ የ"ደተ" ተለዋጭ በአማርኛ። "ለደፈ"፡ - "ለጠፈ"፡ "ቦደ"፡ - "ጨበጠ"፡ "ሥርጓጕድ"፡ - "ሥርጓጕጥ"፡ "ጐርምድ"፡ - "ጐርምጥ"፡ "ወተረ"፡ - "ወጠረ"፡ "ቀበጠጠ"፡ - "ቀበተተ"፡ "ሸፈጠ"፡ - "ሸፈተ"።
ጠ ፡ የ"ጸፀ" ተወራሽ ከግእዝ ወደ አማርኛ። (ማስረጃ)፡ "ጸድቀ"፡ - "ጠደቀ"፡ "ጸግበ"፡ - "ጠገበ"፡ "ፀመረ"፡ - "ጠመረ"፡ "ፀመደ"፡ - "ጠመደ"፡ የመሰለው ሁሉ::
ጠለለ፡ (ጠሊል፡ ጠለ፡ ጠልይ፡ ጠለየ፡ ጸሊል፡ ጸለለ)፡ ረጠበ፡ ራሰ፡ ለመለመ።
ጠለለ፡ (ጸሊል፡ ጸለለ፡ ጸልሎ፡ ጸለለ)፡ ከለለ፡ ጋረደ፡ አጠላ፡ አለበሰ፡ ከደነ፡
ሸፈነ።
ጠለለ፡ ቀለጠ፡ ነጠረ፡ ጠራ፡ ጥራት አገኘ። "የጠለለ ወርቅ" እንዲሉ።
ጠለለ፡ ተለለ፡ ቀረረ፡ ሰፈፈ፡ ተንካፈፈ። ዐሩ፡ አተላው፡ ዝቃጩ በታች፡ ጥሩው፡ ጠለልታው በላይ ሆነ፡ የቅቤ፡ የጠላ።
ጠለለ: ጠራ፣ ጥሩ ኾነ።
ጠለል፡ (ጸሊል)፡ መጥለል።
ጠለል አለ፡ ተለል፡ ቀረር፡ ሰፈፍ አለ።
ጠለልታ፡ የማር ወለላ፡ ንጥር ቅቤ፡ የቅባት ፍሳሽ። ሰለለ ብለኸ ሰለልታን እይ።
ጠለመ ፣ (ደለመ) ፣ ገባ፡ ሰጠመ። ጠለቀን እይ።
ጠለመ፡ (ጠሊም፡ ጠለመ፡ ካደ። ጸልመ)፡ ጠቈረ፡ ጥቍር ሆነ፡ ከሰል መሰለ።
ጠለምቱ፡ (ጸሊም)፡ ዝኒ ከማሁ፡ ጥቍር፡ ከሰልማ፡ ሻንቅላ፡ የምጣድ ቂጥ።
ጠለሰ፡ (ጠልሰ)፡ ጠቈረ፡ ከሰለ፡ ጠፋ፡ ዐመድ ሆነ። ጠለዘንና ተለዘን እይ።
ጠለሰመ፡ ጠልሰም ሣለ፡ መሰለ፡ እበጀ በጠለስ (በማየ ሕመት)።
ጠለስ፡ (ሶች)፡ የማንኛውም ዕንጨትና ሣር ከሰል።
ጠለሸት፡ የከሰል፡ የማገዶ፡ የሸክላ ጥላት፡ ዐመድ (ኢዮ፭፡ ፯። ፵፩፡ ፲፩)።
ጠለሸት፡ ፀሓይና ነፋስ የማይደርስበት ጥቍር መሬት፡ የዛገ፡ የወረዛ ደን፡ ወይም ጥላው።
ጠለቀ ፣ ረቀቀ፡ የልብ፡ ያሳብ (መዝ፷፬፡ ፮)።
ጠለቀ ፣ ነከረ (ዘሌ፬፡ ፲፯)።
ጠለቀ፡ (ጠሊቅ፡ ጠለቀ፡ ቀለየ)፡ ዐረበ፡ ገባ። "ጀንበር ጠለቀ" እንዲሉ።
ጠለቀ፡ ቀዳ፡ ጨለፈ፡ አጠቀሰ (ሩት፪፡ ማቴ፳፮፡ ፳፫)።
ጠለቀ፡ ተነከረ፡ ተዘፈቀ፡ ታለለ (ዘፀ፳፮፡ ፴፮)።
ጠለቀ፡ ዘለቀ፡ ሰጠመ፡ ዘቀጠ።
ጠለቀ፡ ጥልቅ ሆነ፡ ጐደጐደ (ዳን፪፡ ፳፪)። ያለፈው ተገብሮ የሚመጣው ገቢር መኾኑን አስተውል።
ጠለቃ ጥልቂያ፡ ጥልቆሽ ፣ (ጥላቄ)፡ የመጥለቅ፡ የመግባት ሥራ።
ጠለቅላቃ፡ ጥልቅልቅ፡ የተጥለቀለቀ፡ በውሃ የተሸፈነ መሬት፡ ቅባት የበዛበት ወጥ። ዳግመኛም ጠለቅላቃ፡ "ጥልቅ ብዬ" ተብሎ ይተረጐማል።
ጠለዘ፡ ጠለሰ፡ ተለዘ።
ጠለየ ፣ ለመነ።
ጠለጠለ)፡ ብለኸ አንጠልጥሎን እይ።
ጠለጠለ)፡ ጠልጠለ)፡ አንጠለጠለ፡ ሰቀለ፡ ሰቀጠጠ፡ አንዘለዘለ (፪ሳሙ፡ ፳፩፡ ፲፪። ኢዮ፳፮፡ ፯። ኢሳ፵፡ ፲፪)።
ጠለጠል፡ ጠልጣላ፡ የተንጠለጠለ።
ጠለፈ፡ (ጠሊፍ፡ ጠለፈ። ዐሰቀ)፡ ሰረጀ፡ አሰናከለ፡ ድንገት በገመድ፡ በጠፍር ያዘ፡ እሰረ፡ በሬን ሌላውንም ከብት።
ጠለፈ፡ ቀሚስን፡ ግላስን፡ ለምድን፡ መጋረጃን፡
መሶብን በሐር፡ ባለቀለም አክርማ ሰፋ፡ ዘመዘመ፡ ሣለ፡ መሰለ፡ ሸለመ፡ አስጌጠ (፪ዜና፡ ፫፡ ፲፬)። "ጠለፈ" ማለት የመርፌውንም በክር መጠለፍ ያሳያል።
ጠለፈ፡ ነጠቀ፡ ነጥቆ ወሰደ፡ ልጃገረድን።
ጠለፈ: ጠልፎ ጣለ፣ አሰናከለ፣ አወደቀ።
ጠለፋ፡ ስርጀታ፡ የመጥለፍ ሥራ፡ ንጥቂያ።
ጠለፋ፡ ያቶ በዛብሽ ፈረስ። (የጠለፋ ዋስ)፡ የጊዜ፡ የድንገት፡ የመቅረቢያ ዋስ።
ጠለፎ፡ ዝኒ ከማሁ ለጠላፊ፡ ፈጣን፡ ከተፎ።
ጠሉሼ፡ ጠሉሽ፡ የወንድና የሴት ስም፡ ዘመድ እንጂ አባት እናት ያላሳደጋቸው ልጆች በዚህ ስም ይጠራሉ።
ጠሊቅ፡ ዘሊቅ፡ ጕድጓድ፡ ዋሻ፡ የማይሰሙትና የማያውቁት ቋንቋ (ኢሳ፳፱፡ ፲፭። ፴፫፡ ፲፱)።
ጠሊቅ፡ ጥልቅ (ኢሳ፶፩፡ ፲። ሕዝ፵፯፡ ፭)።
ጠላ፡ (ጠል)፣ "ጠላ" (ጸልአ) በመነሣት፡ "ጠላ" (ጠል) በመውደቅ ይለያሉ፡ ኅብርን እይ። ለሰውነት ርጥበት፡ ልምላሜ የሚሰጥ ከገብስና ከጌሾ፡ ከብቅል የተዘጋጀ መጠጥ፡ በግእዝ "ምዝር" ይባላል። ደፈደፈንና ጠነሰሰን ጦጤን ተመልከት። "ጠላ" የጠለለና የጠለየ ዘር ነው። ጠመቀን አስተውል።
ጠላ፡ (ጦለለ። ጸሊል፡ ጸለለ፡ ጸልሎ ጸለለ)፡ ጥላ ሆነ። መዠመሪያውን ጠለለ አስተውል።
ጠላ፡ (ጸልአ)፡ ነቀፈ፡ አጸየፈ፡ ተሠቀቀ፡ ሰለቸ፡ "አታሳዩኝ፡ አታምጡብኝ" አለ፡ ከመውደድ፡ ከማፍቀር ራቀ። (ተረት)፡ "ቀን ከጣለው ሁሉ ይጠላው። "
"የሚያድግ ልጅ አይጥላኸ፡ የሚሞት ሽማግሌ አይርገምኸ። " መረዘን አስተውል።
ጠላ ቤት፡ የጠላ ቤት፡ ወይም የጠላ ሹም፡ ጠላ ጠማቂ።
ጠላ አነሣ፡ ቀዳ፡ ጠላን ከአተላ ለየ።
ጠላለፈ፡ ነጣጠቀ፡ ሸላለመ።
ጠላላ፡ ሰፊ ሜዳ።
ጠላመጠጥ ጠለለ።
ጠላማ፡ የጠለመ፡ ጠቋራ።
ጠላቂ፡ የጠለቀ፡ የሚጠልቅ፡ ዋነተኛ ፀሓይ፡ ዘላቂ።
ጠላቋ፡ ያሞራ ስም (ዘሌ፲፩፡ ፲፮)። ጣልቃን፣ አሞራ ፣ ጳልቃን።
ጠላት ፣ ባለጋራ ፣ ጠላ።
ጠላት፡ (ጸላኢ)፡ የጠላ፡ የሚጠላ፡ ፀር፡ ደመኛ፡ ባለጋራ። ጥላትን እይ። (የማሪያም ጠላት)፡ ማሪያምን የማይወድ። "ይህን ያልመታ የማሪያም ጠላት" እንዲሉ እረኞች።
ጠላት በጕያ፡ እሳት፡ ተንኰለኛ ልጅ። ጕያን ተመልከት።
ጠላትነት፡ ጠላት መኾን፡ ባለጋራነት (ገላ፭፡ ፳)።
ጠላቶች፡ (ጸላእት)፡ ባለጋሮች፡ ደመኞች።
ጠላው ዞረበት፡ ማለቅለቱን ሖመጠጠ፡ ኰሽም ሆነ።
ጠላፊ፡ (ፎች)፡ የጠለፈ፡ የሚጠልፍ፡ ያዥ፡ አሳሪ፡ ነጣቂ።
ጠላፊ፡ ዘምዛሚ፡ ሸላሚ፡ አስጊያጭ (ዘፀ፴፰፡ ፳፫)።
ጠላፊነት፡ ጠላፊ መኾን።
ጠሌንዥ፡ የታናሽና የቀጯን ዕንጨት ስም፡ በወይናደጋ የሚበቅል ቅጠል፡ ያረግ ዐይነት፡ የግርሻ መድኀኒት።
ጠል ፣ ካፊያ ፣ ጠለለ።
ጠል፡ (ጸላኢ፡ ት)፡ ጥጃዋን የጠላች ላም፡ ወንድ የማትወድ ሴት። "ግብረ ጠል" እንዲሉ። ገበረን ተመልከት።
ጠል፡ ርጥበት፡ የዝናም፡ የካፊያ ዐይነት፡ አዝርዕትን፡ አትክልትን የሚያርስ፡ የሚያረሰርስ።
ጠል፡ የሰማይ ላብ፡ ካፊያ፡ የጉም ሽንት።
ጠልሰም፡ (ሞች)፡ ጠለሳም፡ ባለጠለስ፡ በያይነቱ ያስማት ሥዕል፡ ለራስ ምታት፡ ለሆድ ቍርጠት፡ ለውጋት፡ ለቍርጥማት በክታብ ውስጥ ጠንቋዮች የሚሥሉት፡ እስላሞች ባንገታቸው የሚያደርጉት የብር ወይም የወርቅ ዐሸን ክታብ።
ጠልቆ፡ ሰጥሞ፡ ዘቅጦ።
ጠልቆ ገባ፡ ጣልቃ ሆነ።
ጠልጠለ፡ ግእዝኛ ነው።
ጠልጠሌ፡ (ዎች)፡ የጠለጠል ዐይነት፡ ወገን፡ ወረጋ፡ አንዳች አልባ፡ ያዘሉ፡ ያንጠለጠሉ የሌለው።
ጠልፎ፣ ሰርጅቶ፡ አስሮ።
ጠልፎ በኪስ፡ የመኪና ስም፡ ፈጣን ሠረገላ (ኦቶሞቢል)።
ጠልፎ፡ ጭራና ደንጊያ ያለበት ገመድ፡ ዓሣ መያዣ።
ጠሎት፣ ልመና ፣ ጸለየ፡ ጸሎት።
ጠመለ)፡ አጥመለመለ፡ አዝለፈለፈ፡ አሽመደመደ፡ አምልማሎ አደረገ።
ጠመለለ፡ (ጠብለለ)፡ ዐጠፈ፡ ቈለመመ።
ጠመመ፡ (ጸመ)፡ ተጠመዘዘ፡ ገደደ። ለገመ፡ ቸል አለ፡ ተከየ፡ ከፋ፡ ጠማማ ሆነ፡ በጠባይ። ወለገደን እይ።
ጠመሰሰ፡ ጣሰ፡ ለጠሰ፡ አጋደመ። ደመሰሰን እይ።
ጠመረ፡ (ፀመረ)፡ ፩፡ አደረገ፡ ደረበ፡ ደመረ፡ ቀረቀበ፡
ጠመደ፡ አገናኘ። ጨመረን ተመልከት፡
የዚህ ዘር ነው።
ጠመረረ፡ ጠሞረረ)፡ ተጠማረረ፡ ተጠማረረ፡ ደከመ፡ ለፋ፡ ጠወለገ፡
ተጨነቀ፡ ራብን፡ ጥምን ተጣወረ፡
ቻለ። ጠበረረን እይ።
ጠመረር፡ ጠምራራ፡ የተጠማረረ፡ የሚጠማረር፡ ተጣዋሪ፡
ራብ አይፈታሽ፡ መከራ ቻይ።
ጠመቀ፡ (ጠመቀ። ጸመቀ፡ ዐጸረ)፡ ርጥብ ልብስን፡ የወይን እሸትን፡ የሴቴ ወይራ ፍሬን፡ ድፍድፍን፡ ሰፈፍን፡ አጥብቆ ጨበጠ፡ ጨቈነ፡ ተነ፡ አድፈጠፈጠ፡ ጠመዘዘ፡
እጠራ፡ አንጠፈጠፈ፡ ውሃን፡ ደምን፡ ዘይትን፡ ጠላን፡ ሠምን ለማውጣት።
ጠመቀ፡ (ጠሚቅ፡ ጠመቀ)፡ ውሃ ጨመረ፡ ዐሸ፡ መታ፡ መላ፡ በጠበጠ፡ ዘለለ፡
ድፍድፍን፡ ማርን፡ ሾመ፡ ጠላን፡ ጠጅን።
ጠመቀ፡ ረገጠ፡ አፍተለተለ፡ ጨመቀ፡ ጠመዘዘ፡ አንጠፈጠፈ፡
አጠራ፡ የልብስ፡ የወይን (ዘፍ፵፡
፲፩። መሳ፮፡ ፴፰)።
ጠመቀ፡ ደገሰ፡ አዘከረ። "ወር አይጸድቅ፡ አቦን አይጠምቅ የለም" እንዲሉ።
ጠመቃ፡ ብጥበጣ፡ ዝለላ።
ጠመቅ፡ ጠምቅ (ኣርኣያ ሐሊብ)፡ አሸታዊ ወተት፡ እሸት ሲያኝኩ ባፍ ውስጥ የሚታይ።
ጠመነ፡ (ዐረ)፡ አዋረደ።
ጠመነ፡ (ዕብ፡ ጣማን፡ ሰወረ)፡ ዐየረ፡ ቀላቀለ፡ ቀባ፡ ለቀለቀ።
ጠመነና ጣመነ እንደ በረከና ባረከ ናቸው።
ጠመኔ፡ የስንዴ ስም፡ ነጭ ስንዴ፡ ቀጪን።
ጠመኔ፡ ጠመናዊ፡ የጠመን፡ ነጭ፡ ቀይ፡ አረንጓዴ፡
ብጫ፡ ሰማያዊ ዐፈር፡ የቤት መለቅለቂያ። በረቀን፡ ጨበረን ተመልከት።
ጠመን፡ ዕይር፡ መሬት፡ አቦልሴ።
ጠመንዣ፡ (ጠብ፡ መንዣ)፡ የጦር መሣሪያ፡ ነፍጥ፡ ሰናድር፡ ውዥግራ፡ ወጮፎ፡
ሳበው፡ ለበን፡ መውዜር፡ ግንጥል፡ ጐበዝ፡ አየኹ፡ የመሰለው ኹሉ። "ጠመንጃ" ቢል፡ "ጠብ መንጃ" ያሠኛል። ባረብኛም፡ "ጠበንጃ" ይባላል። ጐረሠን እይ።
ጠመንዣ ያዥ፡ ጭፍራና ደንብ።
ጠመንዣ ጠጣ፡ ጥይትን ባፉ ወደ ሆዱ አገባ።
ጠመንዦች፡ ነፍጦች፡ ሰናድሮች።
ጠመዘ)፡ አጥመዘመዘ፣ ኣልመዘመዘ፣ አፍተለተለ፣ ዐመመ (ሆድን)።
ጠመዘዘ፡ አዞረ፡ መለሰ፡ አጦዘ፡ አጠመመ፡ ገመደ፡
አከረረ፡ ከታጠበ ልብስ መልሶ መላልሶ ውሃ አወጣ፡ አፈሰሰ።
ጠመዘዝ፡ ጠምዛዛ፡ የዞረ፡ የጦዘ።
ጠመዥ፡ (ዦች)፡ የእኸል ስም፡ መልከ ስንዴ፡ ወገነ ገብስ፡ እኸል ቈሎው የሚፈካ።
ጠመደ (ፀመደ)፡ በሬን፡ ፈረስን በቀንበር፡ በሠረገላ አቈራን፡ አሰረ፡ ገዛ። ጐሽን እይ።
ጠመደ፡ ክፉኛ ጠላ።
ጠመደ፡ ጠመንዣን፡ መትረየስን አጐረሠ።
ጠመዳ፡ (ፁማዴ)፡ የመጥመድ ሥራ፡ አሰራ።
ጠመድማዳ፡ ዐንካሳ፡ ሲኼድ እግሩ የሚጣመር።
ጠመጠመ፡ (ትግ፡ ጠምጠመ። ጠወመ)፡ ሻሽን በራስ ላይ እዞረ፡ ፀመ፡ ራስን በመጠምጠሚያ ሸበለለ፡ ጠቀለለ፡ እሰረ (ዘሌ፰፡ ፱)። ጥምጥሙን ደመረ፡ ከበሰ።
ጠመጠመ: በብዙ ወገን፣ እሰረ፣ አረተ፣ አከተ።
ጠማ፡ (ጠምዐ)፡ ነከረ፡ ዘፈዘፈ፡ አራሰ።
ጠማ፡ (ጸምአ)፡ ውሃ ሻ፡ ፈለገ። (ውሃ ጠማኝ)፡ "ሰውነቴ ውሃ አምጣ አለኝ። "
ጠማ (ጸምእ)፡ መጠጠ፡ ብለሽ፡ አጠማን፡ አመጠጠን እይ።
ጠማ፡ ነሣ፡ ወሰደ። አረጋዊ መንፈሳዊ ገጽ ፫፻፵፩ እይ።
ጠማ አለ፡ መጠጥ አለ።
ጠማሚ፡ የሚጠም፡ ገዳጅ።
ጠማሚት፡ የጠመመች፡ ውልግድግድ ያለች ቃሊም፡ የዥረት ደገፍ፡ ዐቃባ፡ በላይኛው ወግዳ በጐሽ ውሃ ቈላ ያለች። "ጠማሚት ባሕር" እንዲሉ።
ጠማማ፡ (ሞች)፡ የጠመመ፡ ወልጋዳ፡ ገዳዳ መንገድ፡ ዕንጨት። ልግመኛ፡ ቸልተኛ፡ ቅንነት የሌለው ሰው (ኢዮ፭፡ ፲፫። መዝ፸፰፡ ፰። ምሳ፪ - ፲፪። ኢሳ፳፯፡ ፩። ዕን፩፡ ፬። ሉቃ ፫፡ ፭)።
ጠማማነት፡ ጠማማ መኾን፡ ገዳዳነት፡ ጠምዛዛነት፡ ልግመኛነት (ኢሳ፲፱፡ ፬)።
ጠማማዋ፡ ጠማማዪቱ፡ ያች ጠማማ (ዕብ፲፫ ' ፱)።
ጠማምነት፡ ዝኒ ከማሁ (ዘፀ፴፰፡ ፯። ፩ሳሙ፡ ፳፡ ፩። ምሳ፪፡ ፲፬)።
ጠማሪ፡ የጠመረ፡ የሚጠምር፡ ደማሪ፡ ደራሲ።
ጠማሽ፡ የጠማ፡ የፈለገ፡ የናፈቀ። "ጦር ጠማሽ" እንዲሉ።
ጠማቂ፡ (ቆች)፡ የጠመቀ፡ የሚጠምቅ፡ ጠምዛዥ (ኤር፵፰፡ ፴፫)።
ጠማጅ፡ (ጆች)፡ የጠመደ፡ የሚጠምድ፡ ገበሬ፡ ባለመንኰራኵር።
ጠማጠመ፡ የጠመጠመ ድርብ፡ ጠቀላለለ፡ ደማመረ።
ጠምላይ፡ የጠመለለ፡ የሚጠመልል፡ ቈልማሚ።
ጠምሳሽ፡ የጠመሰሰ፡ የሚጠመስስ፡ ጣሽ፡ ለጣሽ፡ ወጠምሻ።
ጠምሴ፡ ጠምሰው፡ የሰው ስም፡ ጣስ፡ ለጥስ፡ ጣሰው፡ ለጥሰው ማለት ነው።
ጠምር፡ (ፀምር)፡ የጠጕር፡ የጥጥ፡ የሐር ባዘቶ፡ ሲፈትሉት ብዙው አንድ ክር የሚኾን።
ጠምቄ፡ በይፋት ክፍል ያለ ቀበሌ።
ጠምቄ፡ የሰው ስም፡ የጠምቅ፡ ጠምቃዊ፡ የኔ ጠምቅ፡ የእሸት ፍሬ ወተቴ።
ጠምዘዝ አደረገ፡ በጥቂት፡ በመጠን ጠመዘዘ።
ጠምዘዝ፡ ዘወር፡ መለስ።
ጠምዛዥ፡ (ዦች)፡ የጠመዘዘ፡ የሚጠመዝዝ፡ ልብስ ዐጣቢ፡ አጥማሚ።
ጠምጣሚ፡ (ሞች)፡ የጠመጠመ፡ የሚጠመጥም፡ ቄስ፡ ካህን፡ ደብተራ፡
ተማሪ።
ጠምጣማ፡ ሸበላ፡ ሽንቅጥ።
ጠሞረ፡ ፪ቱን፡ ፫ቱን ፈትል ደርቦ፡ አከረረ፡ ደወረ። "ጠመረ" የካህናት፡ "ጠሞረ" የሕዝብ ነው። ሸረበን ተመልከት።
ጠሰቀ፡ በዱላ መታ፡ ደሰቀ።
ጠሰቀ፡ ጠረነቀ፡ ብዙ በላ፡ ወጠቀ፡ ጠቀጠቀ፡ እያረፈ፡ እያሸራሸረ።
ጠሰጠሰ፡ (ዕብ፡ ጣሽጤሽ፡ አጠፋ፡ ደመሰሰ)፡ (ተገብሮ)፡ ፈጽሞ አረጀ፡ አፈጀ (ኢዮ፲፫፡ ፳፰)።
ጠሰጠሰ፡ (ገቢር)፡ መታ፡ ደበደበ። ጠዘጠዘን ተመልከት።
ጠሳቂ፡ የጠሰቀ፡ የሚጠስቅ፡ ወጣቂ፡ ደሳቂ።
ጠስ፡ የፍታ ነገሥት ቃል ማሳጠሪያ።
ጠረመሰ፡ ሳይከካ ወረዳውን ፈጪ።
ጠረመሰ፡ ጠርሙስን አደቀቀ፡ ቅልን፡ ራስን ወደ ውስጥ ሰበረ፡ አገባ፡ የንጨት ዐጥርን፡ ጣራን አስተኛ፡ ጠረሰመንን ተመልከት፡ ከዚህ ጋራ አንድ ነው።
ጠረመሽት፣ ድፍኑን የተፈጨ የባቄላ ዶቄት።
ጠረማሪያም ፣ ፀረ ማርያም፣ ፀረረ።
ጠረሰ፡ (ጠርሰ፡ ፀርሰ)፡ ተቸረቸመ፡ ተሸረፈ፡ ተሰበረ፡ ውሃ ኾነ፡ "አላኝክ አልቈር" አለ፡ ደነዘ፡ የጥርስ የስለት።
ጠረሰመ፡ ፣ ሰበረ ፣ ጠረመሰ።
ጠረረ፡ (ፀረረ)፡ ትግ፡ ጠረረ፡ ዘለለ)፡ ጠላት አደረገ፡ ጠላ።
ጠረረ፡ በጣም ሞቀ፡ ገረረ፡ ጋለ፡ ተኰሰ።
ጠረረ ብለኸ ተጠረጠረን ተመልከት።
ጠረረ፡ ጥሩር አለበስ።
ጠረረ: ብለኸ ጥራርን አስተውል።
ጠረር አለ፡ ተንጣረረ።
ጠረቀ፡ (ትግ፡ ሐባ፡ ጠርከ)፡ ወጋ፣ በሳ፡ ሰመረ፡ ቸነከረ፡ ብረት አለበሰ።
ጠረቀ፡ (ጠሪቅ፡ ጠረቀ)፣ አወጋ፡ ተብዙ ወግ ተናገረ፡ ተረከ።
ጠረቀመ፡ (ጠነቀረ)፡ ወጋ፡ ወደ ገላ አገባ፡ እሾኸን፡ ሥንጥርን።
ጠረቀመ፡ አጥብቆ አሰረ፡ ዘጋ። ተመልሰኸ ጠረነቀንን ተመልከት።
ጠረቀመ፡ ዝም አሠኘ።
ጠረቀመ: ተተራከመ፣ ተሰበሰበ፣ ተጠራቀመ።
ጠረቀቀ፡ (ጠረቀ)፡ ጨርሶ በሳ፡ ተረከከ፡ ሠነጠቀ፡ ከፈለ (፪ነገ፡ ፮፡ ፴፪። ግብ፡ ሐዋ፲፮፡ ፳፬)።
ጠረቀቀ: ሠነጠቀ፣ ፈነከተ።
ጠረቃ፡ (ጠርቅዐ)፡ ሻረ፡ ተሻለው፡ እገገመ። ጠርቅዐ ጥንታዊ ዐማርኛ ነው።
ጠረቈሸ ‚ ነደለ፡ ሸነቈረ፡ ቀደደ፡ አጠፋ፡ ገሰሰ።
ጠረበ፡ (ጸረበ)፡ በመጥረቢያ መታ፡ ዐነጠ፡ ሸለተ፡ አሾለ፡ አሣሣ፡ አቀጠነ፡
አጠፈጠፈ፡ አለዘበ፡ ዕንጨትን፡ ደንጊያን፡ ዋሻን።
ጠረበበ)፡ ዘረበበ)፣ አንጠረበበ፣ ፊቱን አጠቈረ፡ አከበደ፡ አንጠለጠለ። ደረበበን (ጠረዘዘ)ን እይ።
ጠረበብ፡ ጠርባባ፡ የተንጠረበበ፡ የሚንጠረበብ፡
ፊተ ከባዳ።
ጠረባ፣ ጥርበት፡ የመጥረብ ሥራ፡ ሽለታ።
ጠረተ፡ (ጠረየ)፡ አገኘ፡ ሰበሰበ፡ ገንዘብን፡ የራሱ አደረገ።
ጠረነቀ፡ (ጠረቀ)፣ አጠበቀ፡ ጥብቅ አደረገ፡ አጥብቆ አሰረ።
ጠረነቀ፡ መታ፡ አወፈረ። ደረነቀንን እይ፣ ከዚህ ጋራ አንድ ነው።
ጠረናም፡ ባለጠረን፡ ጠረነ ብዙ፡ ጠረኑ በኼደበት፡ ባለፈበት የሚገኝ።
ጠረን፡ (ጽርኒ)፡ ሽታ፡ ጼና፡ መዐዛ፡ በሩቅና በቅርብ የሚሸት፡ ማለፊያና መጥፎ፡ ከንጨት፡ ከሣር፡ ካውሬ፡ ከንስሳ፡
ከወፍ፡ ከተንቀሳቃሽ ኹሉ፡
ከሰው የሚወጣ።
ጠረን ገላ) ፣ ገላው ጠረን ያለው፡ ጥረገቲ።
ጠረንገላ፡ (ጥሬ ገላ)፣ አካሉ፡ ገላው ያልሰለተ፡ ያልደከመ፡ ወፍራም ጕልማሳ።
ጠረንገሎ፣ ዝኒ ከማሁ።
ጠረኘ ፣ ጥርኝ መሰለ፡ ጥርኝ ጥርኝ ሸተተ።
ጠረኘ፡ ጐለመሰ፡ ጠነከረ፡ ጠረናም ኾነ።
ጠረኘ፡ ጥርኝን በጥርኝ ከፈለ፡ ያዘ፡ ጠበጠ።
ጠረከ፡ (ትግ፡ ሐባ፡ ጠርከ፡ በሳ)፡ አጐደፈ፡ በከለ፡ ኰለፈ፡ ፈጽሞ አሳደፈ፡ አጥረከረከ፡ አጕደፈደፈ፡ አለፈለፈ፡
በካከለ።
ጠረከንልከት፡ የዚህ ተቃራኒ ነው።
ጠረወዘ፡ (ጠረዘ)፡ ተንጠራወዘ፡ አዘገመ፡ ተወጫመደ፣ ተንከላወሰ፣ በቀጥታ መኼድ ተሳነው።
ጠረዘ፡ (ትግ)፡ ከአገር አሶጣ።
ጠረዘ፡ (ጠሪዝ፡ ጠረዘ)፡ ብዙውን ብራና ወይም ወረቀት አንድነት ሰፋ፡ ወሰበ፡ ጠለፈ፡ ታታ፡ ደረዘ፲ ጥራዝና ጠርዝ አበጀ፣ ሰባራ ሸክላን ጠፈረ።
ጠረዘ፡ መታ፡ ደወለ፡ ጥራዝኛ።
ጠረገ፡ (ትግ፡ ጸረገ)፡ ዐደፈ፡ አበሰ፡ ወለወለ፡ ዐሠሠ፡ አጠዳ፡
አጠራ፡ ምጣድን፡ ቤትን፡ ምድርን፡ ወፍጮን፡ ፊትን፡ ዐይንን፡ ቂጥን።
ጠረገ፡ ዐጨደ፡ ከሥር ቈረጠ፡ መነጠረ፡ ሣርን፡ ቅጠልን።
ጠረገ፡ ዛቀ፡ ጠጠ፡ ጭቃን፡ እበትን፡ ቅቤን፡ ድልኸን፡
ማርን።
ጠረገ፡ ፈጽሞ ገደለ።
ጠረገገ)፡ ጠረበበ)፣ አንጠረገገ፣ አንጠረበበ።
ጠረጋ፣ ውልወላ፡ ዐጨዳ፡ ቈረጣ፡ ምንጣሮ።
ጠረጠሰ፡ (ጠሪስ፡ ጠርሰ)፡ ፈጽሞ አረጀ፡ ጥርስ ዐጣ፡ ጨረጨሰ።
ጠረጠረ: ዐዘበ።
ጠረጴዛ፡ (ዞች)፡ ከሳንቃ የተሠራ፡ ክብ ወይም ሞላላ፡ ባላ፬ና ባለ፮ እግር፡ ገበታ፡ አውራጅ።
ጠረጴዛ፡ በቤተ ልሔም የቍርባኑን ቡሖ ዲያቆን አንከብክቦ የሚደረድርበት ዝርግ ሉሕ፣ ሳንቃ።
ጠረፈ፡ (ጠፈረ)፡ አሰረ፡ ቀረቀበ፡ አከተ። ጠረፈ ያማርኛ፡ ጠፈረ የግእዝ ነው።
ጠረፈ፡ ዳር ድንበር አደረገ፡ ወሰነ።
ጠረፍ፡ ዳር፡ ዳርቻ፡ ወሰን፡ ወደብ። "የምድር ጠረፍ"፡ "የባሕር ጠረፍ" እንዲሉ።
ጠሪ፡ (ጠራኢ፡ ጸራሒ፡ ጸዋዒ)፡ የጠራ፡ የሚጠራ፡ ና ባይ። "የሞት ጠሪ" እንዲሉ። ሲበዛ ጠሪዎች ይላል።
ጠሪቅ፡ ጠረቀ፡ ቀዘነ): ተከፈለ፡ ጠብ ጠብ አለ።
ጠራ፡ (ጠርአ፡ ጸርሐ፡ ጸውዐ)፡ ጮኸ፡ "እከሌ፡ እከሌ፡ ና፡ ወዲህ" አለ (መዝ፬፡ ፫)።
ጠራ፡ (ጸርየ)፡ ጥሩ ሆነ፡ ከመደፍረስ፡ ከመጨለም ራቀ፡ ወለል አለ፡ ጠለለ፡ የጠላ፡ የጠጅ፡ የሰማይ፡ የውሃ፡
የደም።
ጠራ ፣(ጸርይ) ፣መጥራት።
ጠራ፡ በደብረ ብርሃን አውራጃ ካንጎለላ በላይ ያለ አገር።
ጠራ፡ በጽፈት፡ ነገረ፡ አዘዘ፡ አስታወቀ። (ዋስ ጠራ)፡ "ተዋሰኝ" አለ። (ስም ጠራ)፡ አነሣ፡ አወሣ።
ጠራ፡ ነጻ፡ ጠዳ፡ የልብስ።
ጠራ አለ፡ በጥቂቱ ጠራ።
ጠራ: በራ፣ ጸደለ፣ አማረ፣ ተዋበ (የፊት)።
ጠራረበ፡ ዐናነጠ፡ ሸላለተ፡ አቀጣጠነ።
ጠራረገ፡ ዐጨደ፡ ቈራረጠ፡ መነጠረ።
ጠራረገ፡ ኣባበሰ፡ ወላወለ።
ጠራራ፡ (ሐሩረ ፀሓይ)፡ የገረረ፡ ገራራ፡ ብርቱ ሙቀት ያለው፡ "ጠራራ ፀሓይ" እንዲሉ።
ጠራራ፡ መላልሶ ጠራ።
ጠራቂ፡ (ቆች)፡ የጠረቀ፡ የሚጠርቅ፡ ምስማር መቺ፡ ቸንካሪ፡ ብረት አልባሽ። "ነገር ባዋቂ፡ ብረት በጠራቂ" እንዲሉ።
ጠራቢ፡ (ቦች)፡ የጠረበ፡ የሚጠርብ፡ ዐናጢ፡ ቅዱስ ዮሴፍ፡ የጌታችን ሞግዚት። "ዐልጋ፡ ሳንቃ፡ ዋልታ፡ ኮርቻ፡ ገበቴ፡ ድግር፡
ጠራቢ"
እንዲሉ።
ጠራች፡ (ጸርየት፡ ነጽሐት)፡ ነጻች፡ ደ (አበባዋ) ቆመች ሴቲቱ።
ጠራዥ፡ (ዦች)፡ የጠረዘ፡ የሚጠርዝ፡ ጥራዝ ሰፊ፡ ተማሪ።
ጠራጊ፡ (ዎች)፡ የጠረገ፡ የሚጠርግ፡ ወልዋይ፡ መንጣሪ። "መንገድ ጠራጊ" እንዲሉ።
ጠራጠር፡ (ፀረ፡ ፀር)፡ የጠር ጠር፡ የጠላት ጠላት፡ ነብር፡ የሚዘል፡ የሚወረወር።
ጠራጠር፣ ነብር፣ ጠረረ።
ጠራጠርማ፡ (ፀራዊ)፡ ነብርማ ፍየል፡ ነጭና ጥቍር ጠጕር ያለበት፡ ዥጕርጕር።
ጠር ፣ በቁሙ፣ ጠረረ።
ጠር፡ (ሮች)፡ ፀር)፡ ጠላት፡ ደመኛ።
ጠር ከል፡ ፣ ፀር ከል ፣ ፀረረ።
ጠር፣ የወር ስም፡ ጣራ።
ጠርሙስ፡ (ሶች)፡ በቁሙ የባሕር ዕቃ፡ ቃሩራ፡ የብርሌና የብርጭቆ፡ የመስተዋት ዐይነት፡ ያረቄ ማምጫ፡ ማስቀመጫ፡ ሲሰብሩት እንደ ምላጭ ያለ ስለት ይወጣዋል።
ጠርሙዝ፡ በላዩ ፬ የብረት ጫፍ ያለው ዘንግ ከበሎታ ጋራ የሚያዝ። "ጠርሙዝ በሎታ" እንዲሉ። በቀድሞ ዘመን የንጉሥ የሥልጣኑ ምልክት ነበር ይባላል (ዝ፪፡ ፱)። ጠር ጥሩ፡ ሙዝ ብረት፡ ጥሩ ብረት ማለት ይመስላል። ሙዝን ተመልከት።
ጠርቀለም፡ የመዳብ ስም፡ መዳብ። "ጠርቀለም ቀለበት" እንዲሉ። ጠርቀለም ትግሪኛ ነው፡ "ጥሩ ቀለም" ማለት ይመስላል። ሙዝን ተመልከት።
ጠርቂ፡ የጠረቃ፡ የሚጠረቃ።
ጠርቃሚ፡ የጠረቀመ፡ የሚጠረቅም፡ አሳሪ፡ ዘጊ።
ጠርቃቂ፡ የጠረቀቀ፡ የሚጠረቅቅ፡ በሺ።
ጠርቅ፡ ወግ ዐዋቂ፡ ተናጋሪ። "ወገ ጠርቅ" እንዲሉ።
ጠርቅ፡ የቅርብ ወንድ ትእዛዝ፡ አንቀጽ።
ጠርቡሽ፡ (ሾች)፡ ፊት የግሪክ፡ ኋላም የቱርክ ቆብ፡ የጦር ሰራዊት መለዮ።
ጠርብ፡ (ቦች)፡ ጸርብ)፡ የጥድ፡ የዝግባ፡ የቍልቋል፡ የሌላውም ዕንጨት ኹሉ፡ ቀጥታ ያለው ረዣዥም ፍልጥ፡ ለግድግዳና ለጣራ፡ ላጥር ሥራ የሚኾን (፬ነገ፡ ፮፡ ፱)።
ጠርቶ፡ (ጠሪኦ፡ ጸሪሖ፡ ጸዊዖ)፡ "ኑ" ብሎ፡ አሽከር፡ ጎረቤቶቻችንን ጠርቶ መጣ።
ጠርናቂ፡ የጠረነቀ፡ የሚጠረንቅ፡ አጥባቂ፡ አሳሪ፡
አወፋሪ።
ጠርዋዛ ፣ ወጭማዳ፡ ከልዋሳ፡ የቦና ጥጃ፡ መሳይ።
ጠርዛም፡ ባለወፍራም ጠርዝ ልብስ።
ጠርዝ፡ (ዞች)፡ የሸማ ወርድ ዳርቻ፡ በውግ ጐንና ጐን ያለ የመጣፍ ዳር፡ የጽፈት መነሻና መጨረሻ። ጥንፍን ተመልከት።
ጠርጠር አለ፡ ዐጕልኛ ጮኸ፡ የከረረ ድምጥ ሰጠ በገናው።
ጠርጣሳ፡ ጥርሱ የረገፈ ሽማግሌ።
ጠሮ ዐረግ፡ ጥሩ ዐረግ፡ ብርቱ ጠንካራ፡ ቁመቱ በጣም የዘለለ፡ የረዘመ፡ ከታሰረ የማይፈታ፡ ቀፎ የሚኾን። ጠሮ ያሠኘው እንደ ዕንጨት ደረቅ መኾኑና እጅ መውጋቱ ነው።
ጠሮ፡ ዐውሎ ነፋስ፡ የመርከብ ጠር፡ ወይም ሾተሌ።
ጠሮ፣ ጠላት፥ዐውሎ፣ ጠረረ።
ጠሮ፡ ጠር።
ጠቀለ፡ ዋሸ፡ ቀጠፈ (ግእዝ)።
ጠቀለለ ፣ ፈጸመ፡ ጨረሰ፡ የሥራ፡ የነገር። "ሰውየው ባለጋራውን ቢገድል ዳኛው ጠቀለልክ" አለው።
ጠቀለለ፡ (ጠቅለለ)፡ ሰበሰበ፡ ኰሰተረ፡ ሸበለለ፡ ጠመጠመ፡ ሸፈነ፡
ክብ አደረገ፡ ማቶት ሠራ። ከፈነንና፡ ገነዘን ተመልከት።
ጠቀለለ፡ ገደለ፡ አሳረፈ። እንቆቅልሽ "የዥብ ዐር ላሙቅልኸ፡ በዱላ ልጠቅልሽ" እንዲሉ ልጆች።
ጠቀመ፡ (ጠቀበ)፡ ስፌት፡ ሰፋ፡ ጣፈ፡ ደረተ፡ ለገበ።
ጠቀመ (ጠቂም፡ ጠቀመ፡ ገነባ። ጠቀመ፡ በቍዐ)፡ ሥራ፡ ያዘ፡ አገለገለ፡ እጠገበ፡ በቃ፡
ረባ
(ኢዮ፳፪፡ ፪። ማቴ፲፰፡ ፲፭። ግብ፡ ሐዋ፲፰፡ ፳፯)።
ጠቀሚታ፡ ጥቃሚ፡ ዝኒ ከማሁ ለጥቅም (ባቊዕ)።
ጠቀማ፡ የስፌት፡ ሥራ።
ጠቀም፡ (ጠቂም)፡ መጥቀም። "ዐገም ጥቅም" እንዲሉ።
ጠቀሰ፡ (ትግ)፡ ጐበጠ፡ ተቀለሰ። ጥንቅሽን እይ፡ የዚህ ዘር ነው።
ጠቀሰ፡ (ጠቂስ፡ ጠቀሰ፡ ቀጸበ)፡ በጣትና ባይን ጠራ፡ አመለከተ (ሉቃ፩፡ ፲፪። ፭፡ ፯። ግብ፡ ሐዋ፳፬፡ ፲)።
ጠቀሰ፡ ነካ፡ ሳበ፡ ጐተተ፡ አቀረበ፡ ጫረ፡ ፍግን፡
ግባስን።
ጠቀሰ፡ እከሌ፡ እንዲህ ብሏል እያለ መሰል ተባባሪ ቃል አመጣ፡ ምስክር አደረገ።
ጠቀሰ፡ ኰሰተረ፡ ተረኰሰ፡ መብራትን።
ጠቀሰ: ጓጐጠ፣ ወ”፡ አነ፡ አተ”።
ጠቀሡ ፣ በቅንድብ ጠራ፣ ጠቀሰ።
ጠቀሳ፡ የመጥቀስ ሥራ።
ጠቀስ፡ የሚነካ፡ ነክ።
ጠቀረ ፣ (ጠቂር፡ ጠቀረ)፡ ጠቈረ።
ጠቀራ፡ ጠቀሮ፡ (ጠቀር)፡ የጪስ ስልባቦት።
ጠቀራም · ጠቀር የለበሰ፡ ባለጠቀር።
ጠቀነ፡ (ቀጠነ። ትግ፡ ጠቀነ፡ ለጠፈ)፡ ተከተፈ፡ ተፈረፈረ፡ አነሰ፡ ታናሽ ሆነ። ዳግመኛም ጠቀነ በትግሪኛ ስም "አጠፋ፡ ሆዱ ተጣበቀ" ተብሎ ይተረጐማል፡ ምስጢሩ ከማሳነስና ከማነስ አይወጣም።
ጠቀጠቀ፡ (ትግ፡ ጠቅጠቀ)፡ ብዙ ጊዜ ወጋ፡ በሳ፡ ነቀሰ፡ ፊትን፡ ፍሬን፡ ወረቀትን፡
ድድን። ተከተከን እይ፣ ከዚህ ጋራ አንድ ነው።
ጠቀጠቀ፡ ረገጠ፡ ረመረመ፡ መሬትን።
ጠቀጠቀ፡ አበዛ፡ በግድ ጨመረ፡ አገባ፡ በላ፡ ወጠቀ፡ መላ ምግብን፡ ሆድን።
ጠቀጠቀ፡ አጠጋጋ፡ አቀራረበ፡ ወንፊትን፡ ሸማን።
ጠቀጠቀ፡ ደፈነ፡ ደበቀ፡ ሸሸገ፡ ሰወረ፡ ዘጋ፡ ሸፈነ፡
ጨፈነ፡ ዦሮን፡ ምስጢርን፡ ምድርን።
ጠቀጠቀ: ወጋ፣ በላ።
ጠቂ፡ የጠቃ፡ የሚጠቃ፡ ኣውራ፡ ኵርማ።
ጠቃ ፣(ጠቅዐ ደወለ)፡ ወጋ፡ ሰረረ፡ ጊደርን።
ጠቃ፡ ዐይን አወጣ፡ አፈሰሰ፡ አሞራው።
ጠቃለለ፡ ጠቀላለለ፡ ጠማጠመ፡ ሸፋፈነ።
ጠቃሚ፣(ጠቃቢ፡ በቋዒ)፡ የጠቀመ፡ የሚጠቅም፡ የሚረባ፡ ረቢ፡ ጣፊ፡
ለጣፊ፡ ደራች።
ጠቃሚዎች፡ የሚጠቅሙ፡ ሰፊዎች።
ጠቃሽ፡ (ሾች)፡ የጠቀሰ፡ የሚጠቅስ፡ አቅራቢ።
ጠቃቀመ፡ ሰፋፋ፡ ጣጣፈ፡ ዶራረተ።
ጠቃቀነ፡ አናነሰ።
ጠቃቃሚ፡ የጠቃቀመ፡ የሚጠቃቅም።
ጠቃጠቀ፡ ዥግራ አስመሰለ፡ አዥገረገረ፡ ወጋጋ፡ በሳሳ።
ጠቃጠቅማ፡ ዥግርማ፡ ባለጠቃጠቆ።
ጠቃጠቆ፡ (ዎች)፡ የጥቍርና የነጭ ነጠብጣብ፡ የፈንጣጣ ጠባሳ፡ እንስሳም ጠቃጠቆ ይባላል።
ጠቃጠቋም፣ ዝኒ ከማሁ።
ጠቈመ፡ (ጠቀመ)፡ ተፈላጊ ነገር ያለበትን ስፍራ ነገረ፡ አመለከተ።
ጠቈመ፡ ዠርባን በጥፍሩ ወጋ አደረገ፡ ማረ፡ ዐከከ።
ጠቈመ፡ የድርን ጕጥ በጣቱ ነካ፡ "ማን አለ"፡ ሳበ፡ ዐረቀ፡ ኣስተካከለ።
ጠቈረ፡ (ጠቀረ፡ ጸልመተ)፡ ተለወጠ፡ ጨለመ፡ ጥቍር ሆነ፡ ጥቀርሻ፡ ከሰል፡ ቍራ መሰለ፡ ማዲያት ለበሰ፡ ጐሰቈለ። ጠቀረ የግእዝ፡ ጠቈረ የአማርኛ ነው።
ጠቈረ: ከሰል መሰለ።
ጠቈርት፡ ባመድ ተጐንፎ የጠቈረ ዘንጋዳ፡ ጠላ የሚኾን።
ጠቅ፡ (ጠቂዕ)፡ መጥቃት።
ጠቅ አደረገ፡ ንክስ አደረገ፡ ነደፈ።
ጠቅላላ፡ ጠቅላላው፡ መላው፡ ኹሉ፡ አንድ ሳይቀር።
ጠቅላይ፡ (ዮች)፡ የጠቀለለ፡ የሚጠቀልል፡ ዋና፡ የበላይ። "ጠቅላይ ግዛት"፡ "ጠቅላይ አለቃ" እንዲሉ።
ጠቅላይ ግዛት፡ በውስጡ ብዙ አውራጃ ያለው የትልቅ መስፍን አገር።
ጠቅላይ ፍርድ ቤት፡ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲሉ።
ጠቅላይነት፡ ዋናነት፡ የበላይነት።
ጠቅል፡ የቀዳማዊ፡ ዐጤ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፡ ፈረስ፡
ስም፡ "ሰብስብ፡ ኰስትር፡ መላውን ጠረፍ አንድ አድርግ" ማለት ነው። "አባ ጠቅል"፡ "ጠቅል ተፈሪ" እንዲሉ።
ጠቅሎ፡ ሸብልሎ። "አገር ጥሎ ቈርበት ጠቅሎ" እንዲሉ።
ጠቅጣቂ፡ የጠቀጠቀ፡ የሚጠቀጥቅ፡ ደፋኝ፡ ወፍ፡ ጉም፡
ጭጋግ።
ጠቅጣቃ፡ የተቀራረበ፡ የተጠጋጋ፡ ርቀቱ የመርፌ ጐን መጠን የኾነ፡ ወንፊት፡ የዘርዛራተቃራኒ፡ ባምስትያ የተሠራ ኩታ፡ ጥቅጥቅ ያለ።
ጠቋሚ (ዎች)፡ የጠቈመ፡ የሚጠቍም፡ አመልካች። "ጠቋሚ ጠቃሚ" እንዲሉ።
ጠቋሚነት፡ ጠቋሚ መኾን።
ጠቋራ፡ የጠቈረ፡ ከሰልማ፡ ምጣድ ቂጥ።
ጠቋር፡ ዛር፡ ክፉ መንፈስ፡ የጨለማ ጭፍራ፡ ጥቍር እግረ ቀይ፡ ወይም እፈቀይ ዶሮ የሚገብሩለት።
ጠቋቈረ፡ ጨላለመ፡ መላልሶ ጠቈረ።
ጠበለተኛ (ኞች)፡ ወደ ጠበል የሚኼድ፡ ጠበል ጠጭ።
ጠበል (ሎች)፡ (ጠቢል፡ ጠበለ)፡ በዱር፣ በገደል፣ በተራራ የፈለቀ ውሃ፡ ክርስቲያን ሁሉ በሥላሴ፣ በማርያም፣ በመላእክት፣ በጻድቃን፣ በሰማዕታት ስም የሚጠመቅበት (ዮሐ፭ = ፪፡ ፫፡ ፬፡ ፯። ፱፡ ፯)። "ያቦ" "የጊዮርጊስ ጠበል" እንዲሉ።
ጠበል ረጨ፡ የተቀደሰ ውሃን በቤት ውስጥና በወላድ ላይ ወረወረ፡ በተነ።
ጠበል፡ በጋን የተመላ፡ ተደግሞበት የፈላ ማየ ጸሎት።
ጠበል ተጠመቀ፡ በጠበል ተነከረ፡ ታጠበ። "ፈለቀን" እይ።
ጠበል አስመታ): አስጠመቀ።
ጠበል፡ የመቍረርት ውሃ፡ ቍርባን ውጭ የሚጠጣ። "ቅዳሴ ጠበል" እንዲሉ።
ጠበል፡ የማኅበር፣ የዝክር፣ የተዝካር፣ የቍርባን፣ የክርስትና ጠላ። ትግሮች ግን "ጸበል" ይሉታል፡ የስሕተት ስሕተት ነው።
ጠበል፡ የገብስ ስም፡ ቶሎ የሚደርስ ለጠላ የሚፈለግ ገብስ።
ጠበል ጠዲቅ፡ ጠበል እንዳለፈው፡ ጠዲቅ ዳቦ።
ጠበል ጠጣ፡ ፉት አለ፡ ረካ ስለ ጤናው።
ጠበሰ፡ (ጠቢስ፡ ጠበሰ)፡ በነዳድ፡ በፍም፡ በድስት እያገላበጠ አበሰለ፡ ቈላ፡ አንቃቃ፡ አደረቀ፡ አመጠጠ፡
እሸትን፡ እንጀራን፡ ሥጋን። (ተረት) "ክስ በክሱ፡ ሥጋን በኵበት ጠበሱ። "
ጠበሰ፡ በጥይት መታ፡ ይኸውም አቃጠለ ካለው ይገባል።
ጠበሰ፡ ተኰሰ፡ አቃጠለ፡ ፈተነ፡ አፈላ፡ ሸክላን፡
ቅቤን፡ ወርቅን።
ጠበሳ፡ የመጥበስ ሥራ።
ጠበረ፡ (ፀመረ)፡ መጠብር፡ መጣብር ሠራ፡ አስጌጠ፡ ሸለመ፡ አሳመረ፡ ግንብን፡
ግድግድን፡ ጋሻን፡ ሕንጻን፡ ክዳንን፡ ሸማን። ጠመረን እይ።
ጠበረ፡ ቀነፈ፡ ጠረቀ፡ ገጠመ፡ ጣፋን።
ጠበረረ፡ በጣም ሠማ፡ ጋለ፡ ግለቱ ክልክ ዐለፈ፡ ገረረ፡ ሊጥ ባሰፉበት ጊዜ ቸሰስ አደረገ፡ በንጀራ ሰበከት ዐይን አወጣ፡ ያዘ፡ አለቅም አለ፡ እንጀራን፡ ምጣዱ።
ጠበራ፡ ሥሥ ክዳን፡ አካርሚኝ፡ ዐልፎ ዐልፎ ደረጃ ያለው ጌጠኛ። "ጠበራ ክዳን" እንዲሉ።
ጠበራ፣ ታቹ ግንብ፡ ላዩ ግድግዳ የኾነ የቤት ሕንጻ።
ጠበራ ዋልታ እንዲል ትግሬ፣ "ጣፋ ጋሻ" ሲል።
ጠበራ፡ ጣፋ፡ የጋሻ ጌጥ።
ጠበቀ፡ (ዐቀበ፡ ኀለወ፡ ኖለወ)፡ (ገቢር)፡ አየ፡ ተመለከተ፡ አገደ፡ ከለከለ፡ ሐይ አለ፡ እንዳይኼድ፣ እንዳይጠፋ፣ እንዳይነካ አደረገ (ሕዝ፴፫፡ ፭)።
ጠበቀ (አፉን)፣ አፉ እንዳመጣ ከመናገር ተጠነቀቀ።
ጠበቀ፡ (ጠቢቅ፡ ጠበቀ)፡ ጥብቅ ሆነ፡ ከረረ፡ (ተገብሮ)፡ ልልነት ዐጣ።
ጠበቀ፡ ቈየ። "ቀን ለምሳ ጠብቀንኸ ነበር፡ ሳትመጣ ቀረሽ። "
ጠበቀት (ቶች)፡ ነትራካ ነገር፡ ወዳድ።
ጠበቀኝ እጠብቅኻለኹ አለ፡ ዛተ፡ ሰውን ለመምታት፡ ለመግደል።
ጠበቃ (ቆች)፡ አፍ፡ ነገረ ፈጅ፡ የነገር አባት፡ ተማጋች። ዶለተን እይ።
ጠበቃነት ጠበቃ መሆን።
ጠበቄ፣ የሰው ስም።
ጠበቅ ፣ (ጠቢቅ)፡ መጥበቅ።
ጠበቅ፡ (ትግ)፡ ዝበሎ፡ ከደንጊያ፣ ከገደል የሚጣበቅ።
ጠበቅ አለ፡ ጠበቀ።
ጠበቅ አደረገ፡ አጠበቀ።
ጠበቅ፡ አግድ፡ ከልክል። "እጀ ጠበቅ" "ሕገ ጠበቅ" እንዲሉ።
ጠበበ፡ (ጠቢብ፡ ጠበ)፡ ለቀመ፡ አዋሰበ፡ አሠባጠረ (ቀጠቀጠ፡ አነጠረ፡ አፈሰሰ ብረትን፣ ብርን፣ ወርቅን)። "የጊዜና ኀላፊ ትንቢቱም ይጠብብ ይጠብባል" ይላል።
ጠበበ፡ (ጸበ)፡ ጠባብ ሆነ፡ ስፋት ዐጣ፡ አነሰ፡ ጨነቀ። "የጊዜና ኀላፊ ትንቢቱ ይጠብ ይጠባል ቢል እንጂ፡ ይጠብብ ይጠብባል አይልም"።
ጠበበ፡ ዐዲስ ጥበብ አወጣ፡ ፈለሰፈ።
ጠበብ፡ (ጸቢብ)፡ መጥበብ።
ጠበብ አለ፡ አነስ አለ፡ ሳይበቃ ቀረ።
ጠበተ፡ (ትግ)፡ ሊጥን አፈሰሰ፡ አሰፋ፡ ጋገረ።
ጠበንጃ፡ ነፍጥ፡ ጠመንዣ።
ጠበኛ (ኞች)፡ ጠብ ወዳድ፡ ባለጠብ፡ ጥለኛ (ምሳ፳፮፡ ፳፬)። "የጠበኛ ፈስ ዐይን ያፈስ" እንዲሉ።
ጠበኛነት፡ ጠበኛ መሆን።
ጠበደለ፡ ወፈረ፡ ደነደነ፡ ደለመጠ።
ጠበጠበ፡ (ጠብጠበ)፡ ገረፈ፡ ሸነቈጠ፡ መታ፡ ባለንጋ፡ ባርጩሜ።
ጠበጠበ፡ በለጠ፡ አወራረደ፡ ጠባ።
ጠበጠበ፡ ቸኮለ፡ ፈጠነ፡ ቀለጠፈ፡ ገሠገሠ፡ ቶሎ ቶሎ ኼደ፡ ተራመደ።
ጠበጠበ፡ ነፈገ፡ ሠሠተ።
ጠበጠበ፡ ጥብጣብ ሰፋ፡ ጐነጐነ።
ጠቢ፡ (ጠባሒ)፡ የበለጠ፡ የሚበልት፡ በላች።
ጠቢ፡ (ጠባዊ)፡ የጠባ፡ የሚጠባ፡ ሕፃን፡ እንቦሳ፡ ግልገል፡ ውርንጭላ።
ጠቢ፡ (ጸባሒ)፡ የጧት ጠባቂ፡ ዘበኛ።
ጠቢ፡ አሳባቂ። "ዦሮ ጠቢ" እንዲሉ።
ጠቢብ፡ ብልህ፡ ዐዋቂ፡ ፈላስፋ፡ አስተዋይ (ኤር፱፡ ፳፫)። ሲበዛ በግእዝ "ጠቢባን"፡ በአማርኛ "ጠቢቦች" ያሰኛል። "ጠይብን" እይ።
ጠባ፡ (ጠበወ)፡ ሳበ፡ ጐተተ፡ መጠጠ፡ መጠመጠ፡ ለገለገ፡ መገመገ፡ የናቱን ጡት ጠጣ፡ ተመገበ (ሉቃ፲፩ - ፳፯)። "አውራን" "ዐገመን" እይ።
ጠባ፡ (ጠብሐ፡ ዐረደ)፡ ገፈፈ፡ በለጠ፡ ብልት አወጣ፡ አወራረደ፡ ቈረጠ።
ጠባ፡ (ጸብሐ)፡ ወገገ፡ ፈገገ፡ ነጋ፡ ጧት ሆነ። "ጠባ ለኪዳን"፡ "መሸ ለቁርባን"።
ጠባ፡ (ጸብአ)፡ ጠላ፡ ወጋ፡ ወጋጋ ሆድን።
ጠባ፡ ባተ፡ ገባ። "መስከረም ጠባ" እንዲሉ። ይኸውም ሁለት ወር ክረምት መጨለሙን፣ ፀሐይ አለመታየቱን ያስረዳል።
ጠባ፡ ወተትና ማር የነካውን የወንድና የሴት አውራ ጣት ወዳፉ አገባ፡ ጐረሠ፡ የጡት ልጅ ለመባል::
ጠባሲት፡ (ጥብስት)፡ የተጠበሰች፡ የተንቃቃች፡ ጋሬ መያዣ።
ጠባሲት፡ እንደ ግእዝ የምትጠብስ፡ እንዳማርኛ ጠባሳዊት፡ ጠባሳ ያለባት ማለት ነው።
ጠባሳ (ሶች)፡ የተቃጠለ፡ የአስቴ ተኵስ፡ ቈስሎ የነበረ የገላ፡ ምልክት፡ ተተኵሶ የዳነ፡ በሕመሙ ጊዜ የነበረውን ትኵሳትም ያሳያል።
ጠባሴ፡ (ጠባሲ)፡ ዝኒ ከማሁ፡ በግእዝ ግን "ጠባሽን" ማለት ነው፡ ነገደ ብለኸ ነጋዴን እይ።
ጠባሴ ኮሶ፡ (ጠባሳዊ፡ ኮሶ)፡ እሳት የፈጀው ጠባሳ፡ የኮሶ ዛፍ ደብረ ብርሃን አጠገብ ያለ።
ጠባሴ ኮሶ፡ ኮሶን ከእንጀራ ጋራ የሚያግፈለፍል፡ ወይም ለጠጪው በፍም ተኩሶ የሚሰጥ (የምትሰጥ)።
ጠባሪ፡ የጠበረ፡ የሚጠብር፡ አስጊያጭ፡ አሳማሪ።
ጠባሽ (ሾች)፡ የጠበሰ፡ የሚጠብስ፡ እፍሊ። "ቅቤ ጠባሽ" እንዲሉ። (ተረት)፡ "እንወራረድ፡ አህያ እንረድ። እኔ ጠባሽ፡ አንተ ጐራሽ። "
ጠባቂ ፣ ከሰንጠረዥ መጫወቻ አንዱ።
ጠባቂ (እንባ)፡ ፍርድ ጐደለ፡ ድኻ ተበደለ የሚል ያገር ተቈርቋሪ።
ጠባቂ፡ ዘበኛ፡ ስልብ፡ ጃንደረባ።
ጠባቂ፡ የጠበቀ፡ የሚጠብቅ፡ አጋጅ፡ እረኛ፡ መላከ ውቃቢ (መዝ፻፵፩ - ፫። ሕዝ፴፬፡ ፭፡ ፲፪። ዳን፬፡ ፲፫፡ ፳፫)።
ጠባቂነት፡ ጠባቂ መሆን፡ እረኝነት።
ጠባቃ፡ ዝኒ ከማሁ ለጥብቅ፡ ለጣቃ።
ጠባቆች፡ እረኞች፡ ስልቦች፡ ዘበኞች፡ ጳጳሳት፡ ነገሥታት፡
መኳንንት
(ኤር፳፫፡ ፩። ሕዝ፴፬፡ ፪፡ ፯፡ ፰። ዳን፬፡ ፲፯። ኤፌ፬፡ ፲፩)።
ጠባበሰ፡ መላልሶ ጠበሰ፡ ተኳኰሰ።
ጠባቢ፡ የጠበበ፡ የሚጠብብ፡ ሸማኔ፡ ጥበብ ሠሪ፡ ፈልሳፊ።
ጠባባ፡ ሁለት ሦስት ጊዜ ጠባ።
ጠባባ፡ እጅግ በጣም ጠባብ፡ የተራራ መካከል መንገድ፡ በጐን የሚያስኬድ።
ጠባብ (ቦች)፡ የጠበበ፡ የሚጠብ፡ ሸልቋቁቻ። "እጀ ጠባብ" እንዲሉ። "ደረትን" እይ።
ጠባብነት፡ ጠባብ መሆን።
ጠባቴ ፣ ዳኛ፡ ጸባቴ።
ጠባይ (ዮች)፡ (ጠብዐ፡ ጠባይዕ)፡ በቁሙ፡ የፍጥረት ሁሉ ሥር መሠረት፡ ባሕርይ፡ ባሕሬ፡ መሬት፡ ውሃ፡ ነፋስ፡
እሳት።
ጠባይ፡ ዐመል፡ ከጠባይ የሚገኝ የተፈጥሮ ግብር። "ጠባየ ክፉ" "ጠባየ መልካም" እንዲሉ።
ጠብ፡ (ጸብእ)፡ ጥል፡ ዐምባጓሮ፡ ውጊት። "ዕለተ ጠብ" እንዲሉ።
ጠብ፣ መንጠብ፡ መውደቅ። "ነጠበን" እይ፡ ዘሩ እርሱ ነው።
ጠብ ርግፍ አለ፡ ፈራ፡ ወደቀ፡ ምድር ሳመ።
ጠብ አለ፣ (ነጥበ)፡ ነጠበ፡ ወደቀ፡ ከመሬት ዐረፈ።
ጠብ አንሺ፡ አጫሪ፡ ጠብ ጀማሪ፡ ተንኳሽ፡ ቈስቋሽ።
ጠብ አይልም፡ ከንቱ አይሆንም፡ ሳይፈጸም አይቀርም። "እከሌ የተናገረው ነገር እምድር ጠብ አይልም"።
ጠብ አደረገ፡ አነጠበ፡ የውሃ፣ የእንባ፣ የደም።
ጠብ ዠመረ: አጫረ፣ አነሣ።
ጠብ ጠብ አለ፡ ተንጠባጠበ።
ጠብ ጠብ አደረገ፡ አንጠባጠበ።
ጠብታ፡ የውሃ ነጥብ። ጠብ።
ጠብታ፡ የውሃ፣ የመድኃኒት ነጥብ። "፩ ጠብታ ፪ ጠብታ" እንዲሉ።
ጠብታ፡ ጠብ ማለት።
ጠብታዎች፡ ጠብቶች፡ ነጥቦች፡ ጠፈጠፎች።
ጠብት፣ የጦር መሣሪያ።
ጠብደል፡ ወፍራም፡ ያልተማረ፡ ዲላ፡ አካሉ ልቅልቅ ያለ፡ የደለመጠ።
ጠብደሎች፡ ጠባድልት፡ ወፍራሞች፡ ውዲሎች።
ጠብጣቢ፡ የጠበጠበ፡ የሚጠበጥብ፡ ገራፊ፡ በላች፡
ገሥጋሽ።
ጠብጣባ፡ ችኩል፡ ፈጣን፡ ቀልጣፋ፡ ሯጭ፡ ንፉግ፡
ቀብቃባ። ጣቢን ተመልከት፡ ከዚህ ጋራ አንድ ነው።
ጠቦ፡ የሰው ስም፡ አስቀድሞ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፡ ኋላም የአፄ ምኒልክ በገና መቺ የነበረ ድንክ።
ጠቦ፡ የራስ ደረሶ ፈረስ ስም።
ጠቦተ፡ ደረቀ፡ እንደ ጡብ ሆነ። "ሆዱ ጠቡታል" እንዲሉ።
ጠቦት፡ የበግና የፍየል በጠጥ ከመሬት ጋራ ተቀላቅሎ የደረቀ ጐደዳ።
ጠቦት፡ ጥቦት፡ በግልገልና በወጠጤ መካከል ያለ ታናሽ በግ ወይም ፍየል፡ እየጠባ ያደገ (ዘፍ፴፰፡ ፲፯፡ ፳)። ቀንዱ ያልከረከረ፡ ጥፍሩ ያልዘረዘረ፡ ጸጕሩ ያላረረ ነው። ተባቱም እንስቱም ጥቦት ይባላል።
ጠቦት፡ ጥቦት ጡት የተወ ግልገል። ጠባ።
ጠቦት ፊት፡ መልኩ የማያምር ሰው።
ጠነሰ ፣ አረገዘ፣ ፀነሰ።
ጠነሰሰ፡ (ፀንሰ)፡ እንስራን ሀጠበ፡ ጌሾና ብቅልን አዋሐደ፡ በጠበጠ።
ጠነሰሰ፡ ፀነሰ፡ አረገዘ።
ጠነቀ፡ (ትግ፡ ጠንቀመ)፡ አጫረ፡ ጐዳ፡ መረዘ። ጨነቀን ተመልከት።
ጠነቀረ፡ (ጠቀረ)፡ ገባ፡ ጠለቀ፡ የጀንበር።
ጠነቀረ)፡ ጠረቀመ)፣ ተጠናቀረ፣ ተጠራቀመ፣ ተሰበሰበ፣ አንድነት ሆነ፣ ተከማቸ።
ጠነቀቀ፡ (ጠንቀቀ)፡ አለስሕተት ሠራ፡ ጻፈ፡ አነበበ።
ጠነቀቀ፡ አተጋ፡ አነቃ።
ጠነቀቀ፡ አዘጋጀ፡ ኰሰተረ፡ ከወነ፡ አስተካከለ፡
መላ ፈጸመ፡ ጨረሰ።
ጠነቈለ፡ (ጠንቈለ)፡ መላ መታ፡ አረተ፡ የናትንና ያስጠንቋይን ስም ጠየቀ፡ ኮከብ ቈጠረ፡ መጣፍ ገለጠ፡ ሞራ ኣየ፡ ጠጠርና ወሌ ጣለ። "በዚህ ቀን ያስፈራኻል፡ በዚህ ጊዜ ይቀናኻል፡ የኋላ የኋላ ትሾማለኸ፡ ስም ታወጣለኸ፡ ማዕርግ ታገኛለኸ" አለ።
ጠነቈለ፡ ጠቅ አደረገ፡ ወጋ፡ ደነቈለ፡ ዘነቈለ፡ አነቈረ። ተነኰለን እይ፡ የዚህ ተለዋጭ ነው።
ጠነበሰ፡ ጠነበዘ። ጪነበሰን እይ።
ጠነበረ፡ (ነበረ፡ ጸበረ)፡ ደነበረ፡ ጠነበዘ።
ጠነበር፡ ጠንባራ፡ ደነበር፡ ደንባራ።
ጠነበዘ፡ (ትግ፡ ጠንበሰ)፡ ታወረ፡ ደነበዘ፡ ሰከረ።
ጠነበዝ፡ ጠንባዛ፡ ዕውር፡ ደንባዛ፡ ሰካር።
ጠነበፈ፡ ገደለ፡ አወደቀ፡ ጥንብ አስመሰለ። "ወታደሩ ዝንጀሮውን በጥይት ጠነበፈው። "
ጠነበፈ፡ ጥንብን ጣለ፡ አጋደመ።
ጠነባ (ጸንጰወ። ትግ፡ ጠ ንበወ)፡ ገማ፡ ጥንብ ሆነ፡ ክፉኛ ሸተተ። ጠነበፈን እይ።
ጠነነ፡ (ጸነ)፡ ዘነበለ፡ ቅር አለ፡ ቅር አሠኘ። ትግሪኛ ግን ጠነነን "ደፈረ" ይለዋል።
ጠነከረ፡ ጠና፡ ከረረ፡ ደረቀ፡ ጠጠረ። "ጠነከረ" ተንከራ ከማለት የወጣ ነው።
ጠነከረ፡ ጨከነ፡ በረታ።
ጠነወተ)፡ ጼነወ)፡ ተጠናወተ፡ በክፉ ተጠባበቀ፡ ተተናኰለ፡ ተቃወመ (፪ጢሞ፡ ፬፡ ፲፭)።
ጠነዘ፡ ደነቈረ፡ ደነዘ።
ጠነዘ፡ ፈጽሞ ደረቀ፡ ቀለዘ፡ ከቸለ።
ጠነዛ፡ ጠነከረ፡ አልበስል አለ፡ እሳት ስላነሰው ተበላሸ፡ ውሃን መጠጠ፡ በሥራት ሳይቀቀል ቀረ። (ተረት)፣ "ሴት ከበዛ ጐመን ጠነዛ። "
ጠነዛን አስተው: (ጠነዛ የሚለውን ይመልከቱ)።
ጠነየ ተዛውሮ፡ ጠየነ ተብሏል።
ጠነገረ፡ ጠነበረ፡ ታወረ።
ጠነገር፡ ጠንጋራ፡ ጠነበር፡ ጠንባራ፡ ዕውር።
ጠነገደ፡ ገደለ፡ ፈጀ፡ ጨረሰ፡ ፈጸመ፡ በቸነፈር።
ጠነጋ፡ (ተፀንግዐ፡ ተፀፍረ)፡ ተበጀ፡ ተታታ፡ ተዋሰበ፡ ተጠፈረ፡ ተለጋ፡
ጥንጉ።
ጠነጠነ፡ (ትግ፡ ጠንጠነ)፡ ፈገጠ፡ ተወ፡ ፈነረ፡ ወረወረ፡ አሽቀነጠረ (ገቢር)።
ጠነጠነ፡ (ጸንጸነ)፡ ነቀዘ፡ ዐመድ ዶቄት ሆነ፡ ተበላሸ።
ጠነጠነ፡ መታ፡ ደበደበ፡ አቦነነ። "እከሌ እከሌን በዱላ ጠነጠነው። "
"ለኔ ብሎ እንደ ሆነ ይጠንጥነው። "
ጠነጠነ ብለኸ፡ ፫ኛውን አጠናጠነን ተመልከት።
ጠነጠነ፡ ፈጽሞ አረጀ፡ አፈጀ። "የጠነጠነች ባልቴት" እንዲሉ (ተገብሮ)።
ጠነፈፈ)፡ ጠፈፈ። ትግ፡ ጸንፈፈ፡ ጨለጠ)፡ አጠነፈፈ፡ ማሰሮን ዘቀዘቀ፡ የንፍሮ ውሃን አፈሰሰ፡ አንጠፈጠፈ፡ ከመኻል ወደ ዳር አወጣ።
ጠኒ፡ (ዎች)፡ ጸናሒ)፡ የሚቀመጥ፡ የሚቈይ። "ደጀ ጠኒ" እንዲሉ።
ጠኒያም፡ ጠኔ የያዘው ሰው፡ ባለጠኔ፡ ራብተኛ፡ ትጋረኛ።
ጠና፡ (ጸንሐ)፡ ተቀመጠ፡ ቈየ። "ደጅ ጠና" እንዲሉ።
ጠና፡ (ጸንዐ)፡ ጠነከረ፡ በረታ፡ ጨከነ። "ውርዴ ቍስል ይጠናበታል (ይበረታበታል)። " ጸናን እይ።
ጠና፡ አረጀ።
ጠና: ጠነከረ፣ በረታ።
ጠናዛ፡ ክችሌ፡ ደንቈሮ፡ ደነዝ፡ ደደብ፡ ነገር የማይገባው።
ጠናግል፡ የፈረስ አንባር ማያ። ጠናግል ብዛትን እንጂ አንድነትን አያሳይም።
ጠኔ፡ (ጠነየ። ትግ፡ ጠመየ፡ ራበ። ጢመት፡ ራብ)፡ ብርቱ ራብ፡ ከልክ ያለፈ፡ ራስ የሚያዞር፡ ዐይን የሚያጨልም፡ ጥኑ ችጋር።
ጠንሳሽ፡ የጠነሰሰ፡ የሚጠነስስ።
ጠንቀቅ በል፡ ኰስተር በል።
ጠንቀቅ አለ፡ ዝኒ ከማሁ፡ ኰስተር አለ።
ጠንቀኛ፡ (ኞች)፡ አጫሪ፡ ክፋተኛ፡ ነገረኛ፡ ተንኰለኛ፡ መርዘኛ። "እከሌ እጁ ጠንቀኛ ነው፡ የመታው አይድንም። "
ጠንቀኛነት፡ ጠንቀኛ መኾን፡ መርዘኛነት።
ጠንቃቂ፡ የጠነቀቀ፡ የሚጠነቀቅ፡ ኰስታሪ።
ጠንቃቃ፡ የተጠነቀቀ፡ ኰስታራ፡ ትጉ፡ ንቁ፡ ዝግጁ።
ጠንቃቃ፡ ጥንቅቅ ያማርኛ፡ ጥንቁቅ የግእዝ ነው።
ጠንቃቃነት፡ ኰስታራነት።
ጠንቅ፡ (ተንክ)፡ ክፉ ነገር፡ ጥል፡ ተንኰል፡ ሰበብ፡ መርዝ፡ መዘዝ፡
ሳንክ። ጠነቈለ ብለኸ፡ ጠንቋይን እይ።
ጠንቅ፡ ነዋሪ፡ ዕመም፡ ምች፡ ዐደር፡ ጠባላ፡ ዕትራት። "የወባ ጠንቅ"፡ "የፈንጣጣ ጠንቅ" እንዲሉ።
ጠንቋይ፡ (ዮች)፡ (ጠንቅ፡ ዋይ)፡ የጠነቈለ፡ የሚጠነቍል፡ መሠሪ፡ ማርተኛ፡
አስማተኛ፡ አፍዝ አደንግዝ፡
ዐዚም፡ ደጋሚ፡ ኮከብ ቈጣሪ፡
የተናገረው ጠብ የማይል። የምድር ዐዋቂ፡ የማይሞት ሰው የሚያድን፡ ጠጠርና ጨሌ ጣይ፡ መጣፍና ሞራ ገላጭ፡ ሥር ማሽ፡ ቅጠል በጣሽ (ዘዳ፲፰፡ ፲፩። ፪ዜና፡ ፴፫፡ ፮)።
ጠንቋይነት፡ መለኛነት፡ ጝርተኛነት፡ አስማተኛነት (ኤር፲፬፡ ፲፬)።
ጠንበለል፡ (ጠብለለ)፡ ያረግ ስም፡ በዋልታ ዙሪያ ጮምጮሞ የሚኾን ዐረግ። (ግጥም)፡ "እኔ እንቢ አሻፈረኝ እወጣለኹ ደጋ፡ ዐንገቷ ይመስላል የጠንበለል ለጋ። "
ጠንባሳ፡ ጠንባዛ።
ጠንቧ አለ፡ እንደ ጥንብ ፈነዳ፡ ተሠነጠቀ፡ ተተረተረ፡ ዕባጩ፡ ቀርበታው።
ጠንቷል፡ አርጅቷል።
ጠንከር፡ መጠንከር።
ጠንከር አለ፡ ጠነከረ።
ጠንካሪ፡ የሚጠነክር።
ጠንካራ፡ (ሮች)፡ የጠነከረ፡ ከራራ፡ ደረቅ፡ ብርቱ፡ ጐበዝ፡
የማይበገር፡ የማይፈታ (ኢዮ፵፩፡
፯። ምሳ፲፰፡ ፲፬። ሕዝ፳፮፡ ፲፩)።
ጠንካራ ዕንቍ (ግእዝ): ጠንካራ የከበረ ድንጋይ።
ጠንካራነት፡ ጠንካራ መኾን።
ጠንክ፣ ጠባሳ፣ ጠንቅ።
ጠንክር፡ ጥና፡ በርታ።
ጠንክሮ ሠራ፡ ጠንክሮ ተዋጋ እንዲሉ።
ጠንክሮ፡ በርትቶ።
ጠንገላ፡ ግልገል ሰኰና።
ጠንገሎ፡ ወፍራም ሰው፡ ጠረንገላ።
ጠንጣኝ፡ የሚመታ፡ የሚደበድብ፡ መቺ፡ ደብዳቢ።
ጠንጣኝ፣፡ የጠነጠነ፡ የሚጠነጥን፡ ነቃዥ፡ ብሳና፡
የመሰለው ኹሉ።
ጠንፉ፡ የሰው ስም፡ ጠርዙ፡ ክፈፉ፡ የርሱ ጠርዝ።
ጠንፉ፡ ያ፡ ጠንፍ።
ጠንፋ፡ ጠርዟ፡ ክፈፋ፡ የርሷ ጠርዝ።
ጠንፌ፡ የወንድና የሴት ስም፡ ትርጓሜው የጠንፍ፡ የኔ ጠንፍ።
ጠንፍ፡ (ጥንፍ)፡ ጠርዝ፣ የንጨት፡ የብረት ዙሪያ፡ ክፈፍ፡ ያማረ፡ ያጌጠ፡ የተሸለመ፡
ባለሰንበር ሥራ። ዘንዶ፡ ማቶት፡ ክባስ።
ጠንፍ የለሽ፡ የሴት ስም።
ጠንፍ የለኽ፡ የሰው ስም፡ ጠርዝ (ወሰን) የለኸ።
ጠንፎች፡ ጠርዞች፡ ሰንበሮች።
ጠኸነነ፡ ጀነነ፡ አኰራ፡ ጠፈነነ።
ጠኸኘ፡ (ጨከነ። ጠሐነ)፡ መታ፡ ጠዘለ፡ ደሰቀ፡ ደበደበ።
ጠኸኘ፡ ጠገረረ፡ አስቋፈ።
ጠኸኘ፡ ፈጨ፡ አደቀቀ።
ጠወለ)፡ አጥወለወለ (አንኮለለ)፣ ልብ መታ፣ አናወጠ፣ አዞረ።
ጠወለገ፡ (መጽለወ፡ ጸምሐየ)፡ ልምላሜው፡ ርጥበቱ ተቀነሰ (ኢሳ፲፭፡ ፯)።
ጠወለገ፡ ተለወጠ፡ ጠቈረ፡ ፊቱ ብር አለ።
ጠወለግ፡ ጠውላጋ፡ (ጽምሑይ)፣ የጠወለገ።
ጠወረ፡ (ጾረ፡ አጾረ)፡ አስቻለ፡ አስለመደ።
ጠወረ፡ አስማለ፣ "ጡር ይድረስብኝ" አሠኘ።
ጠወረ፡ ጦረ።
ጠወሬታ፡ ማላ፡ የሐሰተኛ ሸክም።
ጠዋሪ፡ የሚጠውር፣ አስቻይ፣ አስለማጅ።
ጠዋሪ፡ የሚጦር፣ ጧሪ፣ ረዳት (አስ፪። ፳)።
ጠውለግ አለ፡ ለወጥ አለ።
ጠውላጊ፡ የሚጠወልግ፡ ቅጠል፡ ልጅ።
ጠዘለ፡ (ደዘለ)፡ መታ፡ መደወተ፡ ጠረዘ።
ጠዘለ፡ አደነደነ፡ ኣወፈረ።
ጠዘል፡ የወፈረ፡ ወፍራም፡ ጥረገቲ።
ጠዘረ፡ ነፋ፡ ዘጠረ።
ጠዘዘ)፡ ጥዝ አለ፡ ዕዝ አለ፡ ጮኸ፡ የንብ፡ የዝንብ፡ የተርብ፡ የጥንዝዛ፡
የዥማት።
ጠዘጠዘ፡ (ጠዘዘ)፡ ነደፈ፡ ወጋ፡ የጥንዝዛ፡ የንብ፡ የተርብ፡
የጥይት።
ጠዘጠዘ፡ ነዘነዘ፡ ነዘረ፡ የቍስል፡ የዕብጠት።
ጠዛይ፡ የጠዘለ፡ የሚጠዝል፡ መቺ፡ አወፋሪ።
ጠዝጣዥ፡ የጠዘጠዘ፡ የሚጠዘጥዝ፡ ነዳፊ።
ጠየመ፡ በቅላትና በጥቍረት መካከል ሆነ፡ የመልክ።
ጠየም፡ መጠየም።
ጠየም አለ፡
ጠየመ፡ ጠይም ኾነ።
ጠየረ፡ (ጠይሮ፡ ጠየረ)፡ አሠፃረ፡ አበረረ፡ አከነፈ።
ጠየረ፡ አዘጋጀ፡ አደራጀ።
ጠየቀ፡ (ጠይቆጠየቀ)፡ እህ አለ፡ መረመረ፡ የከሰ (ዮሐ፬፡ ፶፪)። "የት ነበርኸ፡ ምን ሠራኸ" አለ።
ጠየቀ፡ ሞገተ፡ "ተጠየቅ" አለ።
ጠየቀ፡ ጐበኘ፡ ፈቀደ፡ "እግዜር ይማርኸ"፡ "አምላክ ያውጣኸ" አለ።
ጠየተ፡ መታ፡ ገደለ፡ በጥይት።
ጠየተ፡ ብዙውን እሸት ባንድነት ሰብስቦ አሰረ።
ጠየተ፡ ጥይት ሠራ፡ አበጀ፡ አሳመረ።
ጠየፈ፡ ጸየፈ፡ ጸያፍ ኾነ።
ጠያር፡ (ሮች)፡ የግመል ሠጋር፡ በራሪ።
ጠያቂ፡ (ቆች)፡ የጠየቀ፡ የሚጠይቅ፡ መርማሪ፡ የካሽ፡ ሞጋች። (ተረት)፡ "አጥብቆ ጠያቂ እናቱን ይረዳል። "
"ወሬ ለጠያቂ፡ ገበጣ ላዋቂ። "
ጠያቂና ተጠያቂ፡ አስጠንቋይና ጠንቋይ፡ ሞጋችና ተሞጋች።
ጠያች፡ የጠየተ፡ የሚጠይት፡ የሚያስር፡ አሳሪ፡
ጥይት ሠሪ።
ጠያየቀ፡ መራመረ፡ ሞጋገተ።
ጠያይም፡ (ሞች)፡ ብዙ ጠይም።
ጠዬ፡ (ዎች)፡ የታናሽ ዛፍ ስም፡ በትር የሚኾን፡ ወንዴ፡ ሰፋ፡ ሻካራ፡ ጕጣም።
ጠይማት፡ ብልጫነት፡ ንጣት የሌለው፡ ቅጠልማ ዓሣ።
ጠይም፡ (ሞች)፡ ጥቍር አይሉት ቀይ፡ መካከለኛ ሕብር፡ ቅጠልያ፡ የመልክ አቦልሴ። "ጠይም አህያ" "ጠይም ሰው" እንዲሉ። ይኸውም ከቅላት ይልቅ ወደ ጥቍረት የሚያደላ ስለ ኾነ (ጸሊም፡ ጸሊማዊ) ተብሎ ሊተረጐም ይቻላል። ወደ ቅላት ቢያደላ ግን "የቀይ ዳማ" ይባላል።
ጠይምነት፡ ጠይም መኾን።
ጠይብ፡ (ጠቢብ)፡ ባለጅ፡ ቀጥቃጭ፡ ብረተ ሠሪ፡ ሸክለኛ፡ አንጥረኛ፡ ሸማኔ፡ ፋቂ፡ ዐራቢ፡
ዐናጢ፡ ትርጓሜው ብልኅ፡
ፈላስፋ፡ ሥራን ሁሉ ዐዋቂ ማለት ነው። በብሉይም ጥበብና ዕውቀት ማስተዋል የመላባቸው ባስልኤልና ኤልያብ ሌሎችም ነበሩ (ዘፀ ፴፩፡ ፪፡ ፮)። (ተረት)፡ "ይምሰል አይምሰል፡ የጠይብ እጁ ተከሰል። "
"ጠይብ በገል ይበላል። " በሥራ ፈቶች ዘንድ ግን "ጠይብና ቡዳ" የስድብ ስም ነው፡ "ሸክላ ቧጣጭ"፡ "ብረት አዝባጭ"፡ "ቍቲት በጣሽ"፡ "ጠፍር ነካሽ" ይሉታል። ወንጀልን እይ፡ የአማርኛ ገበታዋሪያን ተመልከት (ገጽ፡ ፴፪-፴፫)። በአረብኛም "ይን አጥብቆ ጠይብ" ደግ ማለፊያ ማለት ነው፡ ከጦቢት ጋራ ይሰማማል።
ጠይቦች፡ (ጠቢባን)፡ ባለጆች፡ አንጥረኞች፡ ዐዋቆች፡ ቍንጣሮች።
ጠይቦች፡ ተጣሉ፡ ተጥዶ በወጣ ምጣድና ድስት ቂጥ ላይ ብዙ የእሳት ነጠብጣብ ሲጋጭ ታየ።
ጠይት፡ ጤት፡ የፊደል ስም፡ ጠ። "ውብ" ማለት ነው።
ጠደቀ፡ ጸደቀ። "ጠደቀ" የሕዝብ፡ "ጸደቀ" የካህናት አማርኛ ነው። ጠለጠለ ብለኸ ተንጠለጠለን እይ።
ጠደቅ፡ የጠደቀ። (የገና ግጥም)፡ "በሰማይ የጠደቅ በምድር ያስታውቃል፡ ተከንፈሩ ተርፎ ጥርሱ ጣይ ይሞቃል። "
ጠደፈ፡ (ጸድፈ)፡ ገደል ገባ፡ ተንከባለለ፡ ትኰለ።
ጠደፍዳፋ፡ የችኩል ችኩል።
ጠዲቅ፡ (ጸዲቅ፡ መጥደቅ)፡ ስለ ጽድቅ የሚጋገር ዳቦ፡ አነባበሮ፡ ድፎ፡ መክፈልት፡ ሰአልናከ። "ጠበል ጠዲቅ" እንዲሉ።
ጠዳ፡ (ዐረ፡ ጸደዐ፡ ገለጠ። ጻዕደወ)፡ በራ፡ ጠራ፡ ነጣ፡ አማረ፡ ጥሩ፡ ጥዱ ሆነ። ጸዳን እይ።
ጠዳ፡ ያገር ስም።
ጠዳቂ፡ ጸዳቂ።
ጠዳፊ፡ የሚጠድፍ፡ ተንከባላይ፡ ቸኳይ።
ጠዴቻ፡ (ኦሮ)፡ የንጨት ስም፡ ዐጣጥ።
ጠድፍ፡ (ጸድፍ)፡ ገደል፡ መያዣ፡ መጨበጫ፡ መርገማ፡ መቈንጠጫ፡
መቆሚያ የሌለው፡ የገባበትን የሚያንር፡ የሚያንከባልል።
ጠዶ፡ (ዎች)፡ ዕንጨቱና ቅጠሉ እንደ ጌሾ ጠላ የሚሆን ዛፍ።
ጠጀ፡ (ሜሰ)፡ ማርን እጋን ውስጥ ጨመረ፡ አገባ፡ ዐሸ፡ በጠበጠ፡ አዘጋጀ፡ አጣራ። ሥሩ በግእዝ ጸገየና ጸገወ ጸደና ናቸው።
ጠጃም፡ ባለጠጅ፡ መኰንን፡ ሴት፡ ወይዘሮ። ደረቀንና ሁለተኛውን ጠራ ተመልከት።
ጠጅ (ጆች)፡ ከውሃ፡ ከማር፡ ከጌሾ ተዘጋጅቶ የተጣራ መጠጥ። (ተረት)፡ "ከመልካም ጠላ ክፉ ጠጅ፡ ከመልካም ጎረቤት ክፉ ልጅ። "
"በተሓ ጠጅ" "ለጋ ጠጅ" "የደረቀ" "የኖረ" "የከረረ ጠጅ" እንዲሉ። ዘነበለን እይ።
ጠጅ መልከኛ፡ የጠጅ ሹም።
ጠጅ ሣር፡ (የጠጅ ሣር)፡ ሽታው እንደ ጠጅ የሚጣፍጥ ሻካራ ሣር፡ ከተክል የሚቆጠር፡ በአውዳመት ቀን በጠጅ ቤት የሚጐዘጐዝ። ዳግመኛም በበረሓ ስለሚለመልም "ጣይ ሣር" ይባላል።
ጠጅ ቤት (ቶች)፡ ጠጅ የሚጣልበትና የሚቀመጥበት ቤት።
ጠጅ ቤት፡ የጠጅ ቤት አዛዥ ሴት።
ጠጅ አሳላፊ፡ ጠጅ ሰጪ፡ ዐዳይ።
ጠጅ አነሣ፡ ቀዳ፡ ከአንብላ ለየ።
ጠጅ፡ ከወይን ፍሬ የተደራጀ መጠጥ። "ወይን ጠጅ" እንዲሉ።
ጠጅ ጠጅ አለ፡ ሸተተ፡ ጣፈጠ።
ጠጅ ጠጅ፡ የዜማ ሥረይ።
ጠጅ ጣለ፡ ጠጀ።
ጠጆ፡ የጥጃ በሽታ (ጠዳ)።
ጠጆ፡ የጥጃ በሽታ፡ የሚያከሳው፡ የሚያመነምነው።
ጠገረ ፣ ጠገራ ሠራ፡ ቀጠቀጠ፡ አበጀ።
ጠገረ፡ ሼጠ፡ ለጠገራ ለወጠ። "የጠገራ ላም" እንዲሉ። ጠገረን ሼጠ ማለት የጕራጌ ቋንቋ ነው። ተገረን እይ።
ጠገረረ፡ ቀስ አሠኘ፡ አስቋፈ። "ቶሎ ቶሎ ና፡ ምን ይጠገርርኻል" እንዲል ባላገር።
ጠገረረ፡ አበዛ፡ አከበደ።
ጠገራ ፣ ባንድ ወገን ስለት ያለው፡ በራሳም ዕንጨት ቀዳዳ የተዋደደ፡ መፍለጫ፡ ባለ ሁለት ማእዘን። ጠገራ መባሉ እንደ ምሣር ጕረሮ ስለሌለውና ለጠገራው ልሳን ስላወጡለት ነው። ዙሓን ተመልከት።
ጠገራ (ሮች)፡ መሣሪያ ያልኾነ፡ ያልተበጀ ብረት።
ጠገራ ብር፡ መዳብና ንሐስ፡ ኒኬል ወረቀት ያይዶለ፡ ጥሩ ብር፡ ወይም የብር ጠገራ።
ጠገሮ፡ በይፋት ክፍል ያለ አገር።
ጠገበ፡ (ጸግበ)፡ ሆዱ መላ፡ ረካ፡ መብል ተወ፡ ሰለቸ፡ በቃኝ አለ፡ ተነፋ፡ ወፈረ። ከዚህ የተነሣ ሰውን ናቀ፡ ተቤተ፡ ኰራ። (ተረት)፡ "ካልጠገቡ አይዘሉ፡ ካልዘለሉ አይሰበሩ። ባለጌ የጠገበ ለት ይርበው አይመስለውም። "
ጠገበ፡ አረገዘ፡ ከበደ፡ ደረሰ፡ የሴት ሆድ ጠገበ፡ ቀረበ፡ ተጠጋ።
ጠገበች፡ ከበዶች፡ የሴት፡ የእንስት።
ጠገብ፡ (ጸጊብ)፡ መጥገብ።
ጠገብ አለ፡ ኵራት ዠመረ።
ጠገብ፣ ዝኒ ከማሁ። "ጥቀርሻ ጠገብ" እንዲሉ።
ጠገተ፡ ላምና ጥጃን አገናኘ፡ ዐለበ፡ ኣንፋፋ፡ ወተትን። "እከሌ ስንት ይጠግታል (ልባል)" እንዲሉ።
ጠገነ፡ (ትግ፡ ጸገነ)፡ አሰረ፡ ጠቀለለ፡ ዐከመ፡ ፈወሰ፡ አዳነ፡
ዐደሰ፡ ስብራትን፡ ቤትን።
ጠገነ፡ ጠቀመ፡ ዐገዘ፡ ረዳ፡ ደገፈ፡ ሰውን (፪ዜና፡ ፳፱፡ ፫። ኢሳ፴፡ ፳፯)። ተገነን ተመልከት።
ጠገን፡ ፈውስ፡ ጥቅም፡ ጠቀሜታ።
ጠገዴ፡ በስሜን አውራጃ ያለ አገር። ሕዝቡ አማርኛና ትግሪኛ የሚናገር።
ጠገገ፡ (ጠግዐ፡ ይመ)፡ ደረቀ፡ ተሰበሰበ፡ መሻር፡ መዳን ዠመረ፡ ቅርፊት ያዘ፡ የቍስል።
ጠገገ፡ ጠገግ ሆነ፡ ተጠፈረ፡ ተታታ፡ ያልጋ።
ጠገግ (ጎች)፡ አንዲት የሰንሰለት ብረት፡ ሞላላ ቀለበት። የመጋረጃ ቀለበትም ጠገግ ይባላል።
ጠገግ፡ ምንጣፍ የሌለበት፡ ባዶ፡ ያልጋ ጠፍር፡ ደረቅ። "ጠገግ ዐልጋ" እንዲሉ።
ጠገግ አለ፡ ጠገገ።
ጠጕረ ላሑ፡ ጠጕሩ ሯ፡ የሣሣ፡ የተለጠሰ።
ጠጕረ ሠሪ፡ ሽሩባ የምትሠራ፡ የምትመሽጥ ሴት።
ጠጕራም፡ (ጸጓር)፡ ባለጠጕር፡ ጠጕሩ የበዛ፡ የረዘመ፡ ናዝራዊ፡ ጐፈር፡ ዳፍሎ።
ጠጕር፡ (ጸጕር)፡ ጭገር፡ ባሕርያዊ የገላ ልብስ፡ የሥጋ ሣር፡ በእንስሳና በአውሬ፡ በወፍ፡ በሰው አካል ላይ የሚበቅል።
ጠጕር ሠራ): ጐነጐነ፣ ዐሸመ፣ ቈነነ።
ጠጋ ፣ (ፀጊዕ)፡ መጠጋት።
ጠጋ፡ (ትግ፡ ፀግዐ)፣ ዕዳሪ አወጣ፡ ጨፈለቀ፡ ተረተረ።
ጠጋ፡ (ጠግዐ፡ ፀግዐ)፡ ጥግ አደረገ፡ ያዘ (ዕብ፲፩፡ ፳፩)። "ተጠጋ" እንጂ "ጠጋ" አልተለመደም።
ጠጋ፡ (ጸገወ)፡ ሰጠ፡ ቸረ።
ጠጋ፡ (ጸጋ)፡ ስጦታ። ጸጋንና ባልን ተመልከት።
ጠጋ፡ ሞጋጋ፡ ከሲታ፡ ሞጌያም፡ ጕንጪ ደረቅ።
ጠጋ አለ፡ ለጠቅ አለ።
ጠጋ ጠጋ አለ፡ ለጠቅ ለጠቅ አለ።
ጠጋቢ፡ የሚጠግብ፡ ሀብታም።
ጠጋች (ቾች)፣ የጠገተ፡ የሚጠግት፡ የሚያልብ፡ ዐላቢ።
ጠጋኝ (ኞች)፡ የጠገነ፡ የሚጠግን፡ ቊስል አሳሪ፡ ዐዳሽ፡ ረዳት።
ጠጋዛብ፡ (ጸጋ፡ ዘአብ)፡ የሰው ስም፡ ያቡነ ተክለ ሃይማኖት አባት፡ የአብ ስጦታ ማለት ነው።
ጠጋጋ ፣ የጠገገ፡ ጐድኑ ጠገግ የመሰለ ጋ።
ጠጐረ፡ (ጸጕሮ ጸጐረ)፡ ጠጕር አወጣ፡ አበቀለ፡ ጨጐረ።
ጠጠ (መጠጠ): ወርሶ ጠረገ፣ አወጣ (ምንም ሳያስቀር - ቅቤን፣ ድልኸን፣ ማርን፣ ቡሖን፣ ጭቃን፣ ዐዛባን)።
ጠጠ: (ይህ ቃል ትርጉም አልተሰጠውም፣ ምናልባት የሌላ ቃል አካል ሊሆን ይችላል)
ጠጠረ፡ (ትግ፡ ዐፀረ)፡ ጠና፡ ጠነከረ፡ በረታ፡ ደነጋ።
ጠጠራም፡ ጠጠር ያለበት፡ የበዛለት ስፍራ፡ ባለጠጠር።
ጠጠር (ሮች)፡ (ፀፀር)፡ ታናሽ የደንጊያ ቅንጣት፡ ባቄላና ዐተር የሚያካክል፡ ከነዚህም የሚበላልጥ።
ጠጠር ጣይ (ዮች)፡ ጠጠር የሚጥል፡ የሚበትን፡ "እንዲህ ይኾናል፡ ይደረጋል" የሚል መለኛ፡ ጠንቋይ፡ ርተኛ። ወሌን አስተውል።
ጠጠተ፡ (ጸጸተ)፡ ቈጪ፡ እተከዘ፡ "ምነው ባልሠራኹት፡ ባላደረግኸት" አሠኘ። "ጠጠተ" የሕዝብ፡ "ጸጸተ" የካህናት ነው።
ጠጠት ፣ (ጸጸት)፡ ቍጭት፡ ንስሓ፡ ዐዘን፡ ትካዜ።
ጠጡ፡ ለሩቆች ወንዶችና ሴቶች ኀላፊ አንቀጽ፡ ለቅርቦች ወንዶችና ሴቶች ትእዛዝ አንቀጽ ይኾናል። "እነሱ ጠጡ" "እናንተ ጠጡ"።
ጠጣ፡ (ትግ፡ ጸጸወ)፡ ፉት፡ ጕንጭ አለ፡ ጕርጕጭ አደረገ፡ ተጐነጨ፡ ሰቸ፡ ማገ፡ ሸመጠጠ፡ ጨለጠ (ሰቈ፩፡ ፬)። (ተረት)፡ "ልጅና ጦጣ ውሃ ይጠጣ። " የሽጕጥንና የጠመንዣን ጥይት፡ የትንባኾን ጪስ ወደ ሆድ አገባ። (እንባውን ጠጣ)፡ ሳያለቅስ ቀረ።
ጠጣ፡ ለቅርብ ወንድ የሚነገር ትእዛዝ አንቀጽ። "ጠጣኸ" "ትጠጣለኸ" "ጠጣ"።
ጠጣ ጠጣ አደረገ፡ ጭልጥ ጭልጥ አደረገ።
ጠጣ: ዥው አደረገ። "ሰቸ፡ ካማራ፡ ይልቅ፡ በጕራጌ፡ ይነገራል።"
ጠጣሪ፡ የሚጠጥር፡ ጠንካሪ።
ጠጣው፡ የራስ ወሌ ፈረስ። (ግጥም)፡ "ዐሥር ደጃዝማች የደገሰውን፡ የወሌ ፈረስ ጠጣው ብቻውን። " ኣባን ተመልከት።
ጠጣጣ፡ መላልሶ ጠጣ።
ጠጥ (ጦች): ደድ፣ ጭርሶ የሰረቀ። "ማጠጥ ሌባ" እንዲሉ።
ጠጥ (ጦች): ደድ፣ ጭርሶ የሰረቀ። "ማጠጥ ሌባ" እንዲሉ።
ጠጥ፡ ዝኒ ከማሁ ለጠጪ፡ ሰች። "ቀለመ ጠጥ" እንዲሉ።
ጠጪ (ጮች)፡ የጠጣ፡ የሚጠጣ፡ መጠጥ ወዳጅ። ውሃን አስተውል። (ያህያ) ውሃ ጠጪ)፡ ሐሳቡን ሲያደርግ ሲሠራ የማይታወቅበት ሰው።
ጠጪነት፣ ጠጪ መኾን፡ መጠጥ ማብዛት።
ጠጭ፡ ዝኒ ከማሁ። ወፍን እይ።
ጠፈረ፡ (ጠፊር፡ ጠፈረ፡ ፀፈረ)፡ በጠፍር አጥብቆ አሰረ፡ ገረፈ፡ ታታ፡ ጠለፈ፡ ማገረ፡ ጐለበ፡
ከብትን፡ ሰውን፡ ዐልጋን፡ ጣራን፡ ከበሮን።
ጠፈረ፡ (ጸፈረ)፡ ጥፍርን በጥፍር ቈረጠ፡ ከረከመ፡ እንስሳ በተወለደ ጊዜ።
ጠፈራ፡ የመጠፈር ሥራ።
ጠፈር፡ (ሮች)፡ ትት፡ ማገር፡ ጨምጨሞ፡ ጭምጭማት፡ የቤት ጣራ በቈዳ፡ በገመድ የታሰረ፡ የተማገረ። ጨበጠ ብለኸ፡ በጣን ተመልከት።
ጠፈር፡ ላይኛው የበገና ጋድም፡ ከታናናሽ ዕንጨትና ከጠፍር ቍራጭ ጋራ ፲ሩ የበገና አውታሮች (ዥማቶች) በላዩ ተጠምጥመው የታሰሩበት። ዕንጨቶቹና ቍርጥራጭ ጠፍሮቹም ማጥበቂያና ማላሊያ፡ ቅኝት መስጫ ናቸው።
ጠፈር፡ ሰማይ፡ የምድር ባጥ፡ በውሃ የተጠፈረ (ዘፍ፩፡ ፯፡ ፯፡ ፰)።
ጠፈር ደፈር፡ ጠፈር እንዳለፈው፡ ደፈር የገመገም ጫፍ። ደፈረን እይ።
ጠፈነ፡ (ጸፈነ። ትግ፡ ጠፈነ ጭቃ ለጠፈ)፡ ጠለፈ፡ አሰረ፡ ዘጋ።
ጠፈነነ፡ ጀነነ፡ ኣኰራ። ጠኸነነን ተመልከት።
ጠፈነን፣ ጠፍናና፣ የተጠፈነነ፡ ጅንን፡ ኵሩ።
ጠፈጠፈ፡ (ጸፍጸፈ)፡ ጥፍጥፍ አበጀ፡ አሞለሞለ፡ ጋገረ፡ በጣቱ ወጋ፡ አሰነበረ፡ አቦየ፡ ዐተመ፡ እበትን፡
ሊጥን።
ጠፈጠፈ፡ ሸሸ፡ ተጣጋ፡ የሆድ (ተገብሮ)።
ጠፈጠፈ፡ በጥፊ መታ፡ ወለወለ፡ ጕንጭን (ገቢር)።
ጠፈጠፈ፡ አነጠፈ፡ መረገ፡ ለበጠ፡ መሬትን በደንጊያ፡ በስሚንቶ፡ በሉሕ (፪ዜና፡ ፫፡ ፮)።
ጠፈጠፍ፡ (ነጸፍጻፍ፡ ነጠብጣብ)፡ የገደል፡ የዋሻ፡ የጣራ ፍሳሽ፡ ብዙ ጠብታ (ዘዳ፴፪፡ ፪)።
ጠፈጠፎች፡ ፍሳሾች፡ ጠብታዎች።
ጠፈፈ፡ (ትግ፡ ጸፈፈ። ጽሕየ) ቈለጩ፡ ጠራ፡ ጥሩ ሆነ፡ ሰማዩ።
ጠፈፈ፡ መድረቅ ዠመረ፡ ጤዛው፡ ጭቃው፡ ሥጋው። "ጠፈፈ" አልተለመደም።
ጠፈፈ፡ ዐለቀ፡ ተጨረሰ፡ ቆመ፡ በራ (አባራ)፡ ዝናሙ።
ጠፈፍ አለ፡ ዝኒ ከማሁ።
ጠፊ፡ የሚጠፋ፡ ኰብላይ። "ይህ ዓለም ዐላፊ ጠፊ ነው። "
ጠፋ፡ (ጠፍሐ)፡ አነዘረ፡ ፈተለ።
ጠፋ፡ (ጠፍአ)፡ ኰበለለ፡ ታጣ፡ ሞተ፡ እሽከሩ።
ጠፋ፡ (ጸፍዐ)፡ በጥፊ መታ። ጸፋን እይ።
ጠፋ፡ ተሰረቀ፡ ተወሰደ፡ ተበላ፡ ገንዘቡ፡ ከብቱ።
ጠፋ፡ ተረሳ፡ ተዘነጋ።
ጠፋ፡ ተደመሰሰ፡ ተበላሸ፡ ፈረሰ፡ ተፈታ፡ ባዶ ሆነ፡ ከተማው፡ አገሩ፡ መልኩ፡ ነገሩ።
ጠፋ፡ ታወረ፡ ተሰወረ፡ ወደመ፡ ዕልም አለ፡ ተደረገመ፡ ዐይኑ፡ እሳቱ።
ጠፋ፡ አጨበጨበ፡ እጁን ቸብ ቸብ አደረገ።
ጠፋ: ጐደለ፣ ተበደለ።
ጠፋሪ፡ (ዎች)፡ የጠፈረ፡ የሚጠፍር፡ የሚታታ፡ አሳሪ፡ ገራፊ፡
ጣራ ሠሪ።
ጠፍ ሆነ፡ ባድማ ሆነ።
ጠፍ ማለት፡ ተግ ማለት፡ ማባራት።
ጠፍ፡ ባዶ፡ ወና ቤት፡ ያልቀና፡ ያልታረሰ መሬት። "ለም ከጠፍ" እንዲሉ።
ጠፍ አለ፡ መጠጥ አለ።
ጠፍ አለ፡ መጠጥ አለ፣ ጠፈፈ።
ጠፍ አለ፡ ከነውር፡ ከጸያፍ ነገር፡ ከልጅነት ጠባይ ራቀ፡ ዐፍላው ዐለፈ።
ጠፍ አደረገ፡ ፈጸመ፣ ከወነ፣ አቀለጠፈ (ሥራን)።
ጠፍ፡ የጠፋ፡ የታጣ። "የጠፍ ከብት። "
"የጠፍ መሬት" እንዲሉ። ብሪካን እይ።
ጠፍ ያለ፡ መጠጥ ያለ፡ ጠፍተኛ የኾነ፡ የጠዳ። ጠነፈፈን እይ፡ የዚህ ዘር ነው፡ ነ በስሯጽነት ገብቶበታል።
ጠፍ ጨረቃ፡ የታጣች፡ ያልወጣች፡ ያልታየች ጨረቃ።
ጠፍር፡ (ሮች)፡ በቁሙ ከተለፋ ቅሪላ የተቀደደ፡ የተተለተለ፡ የተተነተነ፡ እንደ ልጥ፡ እንደ ገመድ ማሰሪያነት ያለው፡ ልም ዕቃ። "የመጫኛ"፡ "የቀርቃባ"፡ "የማነቆ"፡ "የምራን"፡ "የመርገጥ ጠፍር" እንዲሉ። (ያልጋ ጠፍር)፡ ደረቅ ትት፡ ፊት ርጥብ የነበረ ቈዳ።
ጠፍር ነካሽ፣ የበቅሎና የፈረስ ዕቃ ሰፊ፡ የሐሜት ስም።
ጠፍተኛ፡ (ኞች)፡ ጠፍታ ያለው፡ ባለ ጠፍታ፡ ዐዋቂ፡ ጨዋ፡ ምራቁን የዋጠ።
ጠፍተኛነት፡ ጠፍተኛ መኾን።
ጠፍታ (ጽሕየት)፡ ጥራት፡ ጥሩነት፡ ጨዋነት።
ጠፍታ፣ ጥራት፡ ጠፈፈ።
ጠፍጣፊ፡ የጠፈጠፈ፡ የሚጠፈጥፍ።
ጠፍጣፋ፡ (ፎች)፡ ጽፍሕ)፡ ዝርግ፡ ስታታ፡ ምጣድን፡ ሰፌድን የመሰለ፡ ዐሰላ። "ጠፍጣፋ ደንጊያ" እንዲሉ።
ጡ ሆድ፡ ሆደ ትንሽ።
ጡሊ፣ ቅል፣ ጦለ።
ጡሊ፡ የቃልቻ ቅል።
ጡሊያም፡ ጡሊ ተሸካሚ፡ ባለጡሊ እስላም።
ጡል ፣ ንዝህላል፣ ጦለ።
ጡል፡ በጐዣም ክፍል ያለ ወንዝ።
ጡል፡ ንዝህላል፡ ዝንጉ። "ልበ ጡል" እንዲሉ።
ጡልጡል አለ፡ ተንጦለጦለ።
ጡረተኛ (ኞች)፡ ጡረታ ወዳድ፡ ባለጡረታ፡ ተጠዋሪ፡ ያገር አባት፡ ወይም እናት፡ በሰው ትከሻ ዐዳሪ፡ ራሱን የማይችል። "የልጅ ጡረተኛ" እንዲሉ። ወንድና ሴትን ለመለየት "ጡረተኛው" "ጡረተኛዋ" ይሏል።
ጡረታ ገባ፣ ተጦረ፡ በሰው እጅ ዐደረ።
ጡረት፡ ጡረታ፡ (ጹረት)፡ ያረጀ፡ ያፈጀ ሽማግሌን መጦር፡ ርዳታ፡ ሸከማ።
ጡረኛ (ኞች)፡ ግፈኛ፡ በደለኛ።
ጡር፡ (ጽዉር)፡ ሸክም የኾነ፡ ሽል፡ ጌጥ።
ጡር፡ (ጽዉር)፡ የክፉ ሥራ ብድራት፡ ፍዳ፡ በሰው ላይ የጫኑት ቀንበር፡ ጭቈና፡ በደል፡ ቅጣት፡ መስቃ፡ ተግዳሮት። "እከሌ በድኻ ላይ ግፍ አብዝቶ ነበርና ጡር ደረሰበት። "
ጡር፣ ቅጣት፣ ጦረ፡ ጠወረ።
ጡር ተፋ፡ ማለ።
ጡር ትፋ፡ ማል።
ጡር ነው፡ ግፍ ነው።
ጡር አለበት፡ ሰውን በድሏል።
ጡር፡ ጥር፡ (ጸዋሪት)፡ የተሸከመች፡ የያዘች። "ነፍሰ ጡር" "ደንገ ጥር" እንዲሉ።
ጡርቂያም፡ የፈሪ ወገን፡ ፈሪ ያለበት፡ የፈሪ ፈሪ። ጨረቀንን እይ።
ጡርቅቂ፡ የተወጋ ፈሪ፡ ሴትማ።
ጡብ (ቦች)፡ (ጥብዖት)፡ ከቀይ ዐፈር የተበጀ አራት ማዕዘን ሸክላ፡ ለግንብ የሚሆን (ዘፀ፭፡ ፰፡ ፲፬፡ ፲፰፡ ፲፱)። "ጠቦተን" ተመልከት።
ጡብ፡ ለጣራ ክዳን የሚደረግ ሸክላ፡ ቀናፋ።
ጡብ አለ፡ ዱብ አለ።
ጡብ፡ ዱብ።
ጡብ ጡብ አለ፡ ዱብ ዱብ፡ መር መር አለ፡ ዘለለ፡ ጮቤ መታ።
ጡታም፡ ወሻም፡ ባለ ትልቅ ጡት።
ጡታም፡ ጡት ያለው ሰንና፣ ማንቆርቆሪያ፣ ክስኩስት፣ መስቴ፣ የነሐስ፣ የቆርቆሮ፣ የሸክላ።
ጡት፡ (ጥብ)፣ የእንገር፣ የወተት ሥጋዊ ቋት፡ የበሰለ ደም ከረጢት፡ ኪስ፡ በሴት፣ በእንስት ደረትና ሆድ ጕያ ተደርድሮና ተንጠልጥሎ ያለ፡ ባለ፪፣ ባለ፬፣ ባለ፰ ፍንጭ።
ጡት በቁሙ፣ ጠባ፡ (ጠበወ)።
ጡት ተጣባ፡ ተዛመደ፡ አባትና ልጅ ተኳኋነ።
ጡት አስጣለ፡ አስተው፡ አስለቀቀ።
ጡት አስጣይ፡ ታናሽ ወንድምና እህት ጡት ያስተው፣ ያስተወች።
ጡት አዘራር፡ የተንኮል ዐሳብ ወይም ዘዴ።
ጡት አጣባ፡ የጡት ልጅ አኳኋን።
ጡት ጣለ፡ ተወ (ኢሳ፳፰፡ ፱)።
ጡቶች (አጥባት)፡ ሁለትና ከሁለት በላይ ያሉ (ማሕ፩፡ ፲፫። ሕዝ፲፮፡ ፯)።
ጡንቻ፡ (ዎች)፡ ጠና። ጸንዐ)፡ ወርች፡ ከብብት እስከ ኵርማ ያለ የእጅ ክፍል፡ መካከሉ ዐይጥ የሚባል፡ የግእዝ ስሙ፡ መዝራዕት ነው።
ጡንቻም፡ ባለወፍራም ጡንቻ።
ጡንቻን እይ፡ የዚህ ዘር ነው።
ጡንጡን፡ ሊያ።
ጡንጡን አለ፡ ቸኰለ፡ ሮጠ።
ጡጢ፡ ፈስ።
ጡጢያም፡ ጣጤ፡ ፈሳም።
ጡጥ አለ፡ ጣጥ አለ፡ ተፈሳ።
ጡጥ አደረገ፡ (ጣጣ)፡ ጣጥ አደረገ።
ጡጥ፡ የፈስ ድምፅ።
ጡጥ ጡጥ አደረገ፡ ፈሱን አንጣጣ፡ መላልሶ ፈሳ።
ጡጦ፡ የላስቲክ ጡት።
ጡጫ፡ (ጡጥ)፡ አንድነት የታጠፈ፡ የተኰረተመ የእጅ ጣት፡ ቡጢ፡ ኵርኵም (ዘፀ፳፩፡ ፲፰)። "ከዳገት ሩጫ ከባለጌ ጡጫ ሰውረኝ" እንዲል ባላገር።
ጢ፡ የዜማ ምልክት (አንቀጥቃጢ)።
ጢል፡ መንጠልጠል።
ጢል አለ፡ ስቅል ሲል አለ፡ ተንጠለጠለ።
ጢሎሽ ፣ መንጠልጠል: (ጠለጠለ).
ጢሎሽ ፣ የመንጠልጠልና የግልብጮ ጨዋታ።
ጢማም፡ (ጸሓም)፡ ጢመ ረዥም፡ ጢመ ብዙ፡ አሮንን፡ አባጽሕማን፡ ኣቦን የመሰለ ሰው፡ ሪዛም።
ጢም፡ (ጽሕም)፡ የጕንጭና ያገጭ ጠጕር፡ የተባት ምልክት፡ ከ፳፭፡ ዓመት በላይ የሚያቀነቅን፡ የሚያድግ ሪዝ። (ተረት)፡ "ጢም የሌለው መምር፡ ዐጸድ የሌለው ደብር። "
ጢም አለ፡ (ጸሐመ)፡ መላ፡ ተንተረፈፈ፡ ቲፍ አለ ውሃው።
ጢሞ፡ ዝኒ ከማሁ፡ ባለጢም፡ ጢሙ የበዛ፡ የረዘመ። ዳግመኛም "ሞ" ኣክብሮን ወይንም አኅስሮን ያሳያል።
ጢሞች፡ ሪዞች። (ጥም) ጢም፡ (ጽሒም)፡ መምላት።
ጢቅ መርጨት፣ ጤቀ።
ጢቅ አለ፡ ምራቁን ረጩ፡ ሰው ናቀ።
ጢቅታ፡ ጢቅ ማለት፡ ወይም ምራቅ።
ጢቆሽ፡ ጠባብ የውሃ መርጫ፡ እንደ ውዥሞ ያለ፡ ከዚያም የጠበበ።
ጢብኛ (ኞች)፡ ክብ የኾነ ታናሽ ዳቦ፡ በቅጠል የተጋገረ፡ በለከትና በሽልጦ መካከል ያለ። ጣቢታን ተመልከት፡ የዚህ ዘር ነው።
ጢን፡ (ጢም)፡ መጥገብ፡ መስከር፡ የሆድ መምላት፡ መኵራት።
ጢን አለ፡ (ጢም፡ አለ)፡ ጠገበ፡ ሰከረ፡ ፈጽሞ ኰራ፡ በልቡ ኵራት መላበት።
ጢንጦ፡ የመሬት ድርሻ፡ ትንትን፡ ዕጣ፡ ታናሽ ክፍል።
ጢጢ፡ ዐለንጋ፡ ጅራፍ፡ ከተልባ እግር የተዘጋጀ (ግእዝ)።
ጣ አለ ፣ ጮኸ። ጣጣ።
ጣ አለ፡ ድምፅ ሰጠ፡ የክፋይ።
ጣለ፡ (ጸዐለ፡ ጠሐለ)፡ ገደፈ፡ ፈነረ፡ ወረወረ፡ አሽቀነጠረ፡ ጠነጠነ፡
ተወ፡ ዕቃን፡ አገርን፡ ሃይማኖትን (፪ዜና፡
፳፩፡ ፲)።
ጣለ፡ በርካሽ ሺጠ።
ጣለ፡ አደረገ። "ዐሳቡን በሰው ጣለ" እንዲሉ። ቀላድን እይ።
ጣለ፡ ከስም፡ ነው።
ጣለ፡ ጨመረ፡ አገባ። በኋላ እየተነገረ እንዳወራረዱ ይፈታል። (ኣብሲት ጣለ)፡ ላገ፡ አማሰለ። (አደጋ ጣለ)፡ በድንገት ይታሰብ ወጋ፡ መታ፡ ገደለ። (እንጀራ ጣለ)፡ በገበታ ላይ አስቀመጠ። (ደረቱን ጣለ)፡ ደበሎ ወይም ለምደኛ ለበሰ። (ዳስ ጣለ)፡ ሠራ፡ አበጀ፡ አዘጋጀ። (ዝናም ጣለ)፣ አዘነመ፡ አወረደ። (ዦሮውን ጣለ)፡ ቀቀረ። (ሐሳቡን ጣለ)፡ ዐረፈ፡ ተዘለነ፡ "ምን አለብኝ" አለ። (ኀፍረቱን ጣለ)፡ ገለጠ፡ ተጋለጠ። (ጠጅ ጣለ)፡ በጠበጠ። (ጥላ ጣለ)፡ አጠላ፡ ፀሓይን ከለለ፡ ጋረደ፡ ከለከለ። (ጥለት ጣለ)፡ ሠራ፡ እዋሰበ። (ክምር ጣለ)፡ ናደ፡ ዘረጠጠ። (መጋረጃ ጣለ)፡ ዘረጋ፡ ጋረደ። (መልሕቅ ጣለ)፡ ለቀቀ፡ አወረደ፡ ቸከለ። (መሥመር ጣለ)፡ ረሳ፡ ዘነጋ፡ ዘለለ ቃልን። (መቀጮ: ጣለ)፡ ዳኛው ጥፋተኛን ዕዳ አስከፈለ።
ጣለ: መታ፣ ደበደበ። ምሳሌ: "ወታ እህልን በለበት።"
ጣሊያኑ: ያ ጣሊያን።
ጣሊያን (ኖች): የኢጣሊያ ሰው ወይም ሕዝብና ነገድ። ጣሊያኖችም አገሪቱን "ኢታሊያ"፣ አንዱን ሰው "ኢታሊያኖ"፣ ብዙዎቹን
"ኢታሊያኒ"
ይላሉ።
ጣሊያን፡ የሮም ሰው ፣ ኢጣሊያ።
ጣሊያኖቹ: እነዚያ ጣሊያኖች።
ጣሊያኗ: ያች ጣሊያን።
ጣላ፡ (ጸዐልኦ)፡ የቅርብ ወንድ ትእዛዝ አንቀጽ፡ "ልቀቃ" "ወርውራ" ማለት ነው።
ጣላ ፣(ጽዑል)፡ የተጣለ፡ የጥጥ በሽታ። "ቀይ ጣላ" እንዲሉ።
ጣል ፣(ጥሒል)፡ መጣል።
ጣል አደረገ፡ ርግፍ አደረገ።
ጣል፡ ዝኒ ከማሁ። "ቆበ ጣል" እንዲሉ።
ጣል ጣል አደረገ፡ አረካከሰ።
ጣልቃ፡ በ፫፡ ፊደል መካከል የገባ ልዩ ፊደል።
ጣልቃ፡ አለተራው፡ አለስፍራው መግባት፡ መገኘት።
ጣልቃ ገባ፡ በሌላ ሥራ ወይም ነገር መካከል ዘው አለ።
ጣመ፡ (ጥዕመ፡ ጠዐመ)፡ ቀመሰ፡ በጥቂቱ በላ። "እከሌ ወባ ስለ ተነሣበት ዛሬ እኸል ሳይጥም ዋለ። "
ጣመ፡ (ጥዕመ፡ ጠዐመ)፡ ጣፈጠ፡ ጣፋጭ ሆነ። (ተረት)፡ "ጣመኝ፡ ድገመኝ። "
"ላህያ ማር አይጥማት። " (ግጥም)፡ "እግዜር ሲቈጣ በትር አይቈርጥም፡ ያደርጋል እንጂ ነገር እንዳይጥም። "
ጣመ ቢስ፡ ለነገሩ ጣም የሌለው፡ ለዛ ሲስ፡ ለዛ ሙጥጤ።
ጣመተ፡ (ጻመተ)፡ ተጨረሰ፡ ዐለቀ፡ ጠፋ፡ ተቃጠለ።
ጣመተ፡ ተፈጨ፡ ደቀቀ።
ጣመነ፡ (ጻመወ፡ ጸመወ)፡ አደከመ፡ አጓጐለ፡ አለተተ፡ እግርን።
ጣመን፡ (ጻማ)፡ የሙሓይት ድካም፡ ጕጕለት፡ ጓጓላነት። "መንገደኛው ጣመኑን አረገፈ። "
ጣሚ፡ የሚጥም፡ ጣፋጭ።
ጣሚ፡ የቀመሰ፡ የሚቀምስ፡ ቀማሽ።
ጣማ (ጻመወ፡ ጻማ)፡ ድካም፡ ልፋት።
ጣማ ገንዘብ፡ (ንዋየ ጻማ)፡ የጣማ ገንዘብ፡ ዐርሶ፡ ቈፍሮ፡ ወጥቶ፡ ወርዶ፡ ነግዶ ያገኙት፡ ያተረፉት፡ የለፉበት፡ ላብ ያፈሰሱበት፡ የድካም ዋጋ፡ ደሙ ወዝ።
ጣም፡ (ጣዕም)፡ መጣፈጥ፡ ጥፍጥነት። (ተረት)፡ "የነገር ጣም በዦሮ፡ የእኸል ጣም በጕረሮ። "
ጣም፡ ብዛት፡ ብዙነት።
ጣም ዐጣ፡ ሳይጣፍጥ ቀረ፡ መጣፈጥን አላገኘም።
ጣምራ፡ (ሮች)፡ ባልና ሚስት፡ በሕግ፡ በሥርዐት የተጣመሩ፡ የፍቅርና የኑሮ፡ የሩካቤ አንድነት ያላቸው።
ጣምራ ጦር፡ ባላንድ፡ ጕረሮ፡ ባለኹለት አፍሬ፡ መንታ ጦር።
ጣሠ፡ ፣ ነደለ፡ አፈረሰ፡ ፣ ጣሰ።
ጣሰ፡ (ፀሐሰ። ትግ፡ ጠሐሰ)፡ ወደደ፡ ገፋ፡ ከፈለ፡ ሰበረ፡ ረገጠ፡ አስተኛ፡
ነደለ፡ ቀደደ፡ አፈረሰ፡ ጥሻን፡ ሰብልን፡ የጦር ሰራዊትን፡
ድልድልን፡ ዐጥርን፡ ዳኛን፡ ልጓምን። ጣሰሰንን እይ፡
ከዚህ ጋራ አንድ ነው።
ጣሰ፡ ሠራ፡ መሸጠ፡ ሽሩባን።
ጣሰ፡ ያገዳ እኸልን ፈጩ።
ጣሰሰ፡ ጣሰ፡ አወደቀ።
ጣሳ፡ (ሶች)፡ ከታኒካ የተሠራ ዕቃ፡ ክብና ፬ ማእዘን፡ የጥዋ፡ የዋን፵ መጠን፡ ከነዚህም የሚበልጥ፡ ከባሕር ዘይትና ፍራፍሬ ምግብ የሚመጣበት።
ጣሴ፡ ጣሰው፡ የወንድ መጠሪያ ስም።
ጣስ፡ (ዝ)፡ ባሬታ መክፈያ፡ የሽንት፡ የልባም መቀበያ።
ጣስ፡ ዝኒ ከማሁ። "አጋም ጣስ" እንዲሉ።
ጣስ፡ የቅርብ ሰው ትእዛዝ፡ አንቀጽ።
ጣረ፡ (ጽዕረ)፣ ተጨነቀ፡ ተጋ፡ ለፋ፡ ደከመ።
ጣረ ሞት (ጻዕረ፡ ሞት)፡ የሞት ጭንቅ፡ ወይም ክፉ የሞት መልክተኛ (መልኦከ፡ ሞት)፡ የኀጢአተኛን ነፍስ ከሥጋ የሚለይ አስከሬናም፡ ጥርሳም መስሎ የሚታይ። ካህናት ግን "ጸረ ሞት" ይሉታል (፪ዜና፡ ፳፩፡ ፲፱)።
ጣረ ሞት፡ ጥርሰ ገጣጣ፡ ጥርሱ ተከንፈሩ ተርፎ ጣይ የሚሞቅ ሰው።
ጣረት ጋይ ፣ ጣረ።
ጣረት፣ ጋይ ብዙ ድካም ያለበት።
ጣረኛ፡ (ኞች)፡ ጭንቀታም፡ ጣረ ብዙ፡ ባለጣር።
ጣሪ፡ የጣረ፡ የሚጥር፡ የሚለፋ፡ ትጉህ፡ ሠራተኛ።
ጣራ፡ (ዎች)፡ ጠየረ)፡ ባጥ፡ ጠፈር፡ እንደ ጃን ጥላ፡ እንዳጐበር፡ እንደ ወስከንባይ፡ በላይ የተዘረጋ፡ ከንጨት፡ ከሸማ፡ ከበርኖስ የተበጀ (የተሰፋ)። በግእዝ ጢሮት ይባላል። ደራንና ዘባን ተመልከት።
ጣራ፡ መጨረሻ ስንኝ፡ ወይም ግጥም። ገደገደ ብለኸ ግድግዳን እይ።
ጣራ፡ ጣራ፡ አየ)፡ ዐይኑን አፈጠጠ፣ እግሩን አንፈራገጠ፣ እሞት አፋፍ ደረሰ። "ውጪ ነፍስ ግቢ ነፍስ" አለ።
ጣር፡ (ጻዕር)፡ ጭንቅ፡ ምጥ።
ጣር ኾነ፡ ለሞት ቀረበ።
ጣር ጋር፡ (ገዓረ፡ ጻዕር)፡ የጣር ጩኸት።
ጣርማ፡ የጸድቅ ስም፡ ጻዕራዊ፡ ባለጭንቅ። "ባላገር አባ ሕፃን ሞአን አባ ጣርማ" እንዲል። ይኸውም ስም ጻድቁ ከበሬ ጋራ ተጠምደው ፫ ፈር ማውጣታቸውንና መንፈሳዊ ተጋድሏቸውን ያሳያል።
ጣርማበር፡ (ማኅበረ፡ ጻዕር)፡ የተራራ ስም፡ ጉምና ካፊያ የማይለየው፡ አስታና ጓሳ የሚበቅልበት፡ ገመገም፡ የተጕለትና የይፋት ጫፍ። ጭንቅ ያለበት ማበር (ድግስ)፡ ወይም ማን አጥብቆ፡ የጣር፡ ባለጣር፡ ጣረኛ በር ሥርጥ ማለት ነው። (ጣር፡ ማበር (ጥማ) ጣርማ በር). አባን እይ።
ጣሽ፡ (ሾች)፡ የጣሰ፡ የሚጥስ፡ ወዳጅ፡ አፍራሽ።
ጣቍሳ፡ በበጌምድር ክፍል ያለ አገር። "ዐለፋና ጣቍሳ" እንዲሉ።
ጣቃ፡ (ዐረ)፡ የሸማ፡ የሐር ልብስ፡ የሻሽ ጥቅል፡ መዳ።
ጣቃ፡ (ግእዝ)፡ ጨለማ፡ ጭጋግ።
ጣቈሰ፡ (ጠቀሰ)፣ በነገር ነካ፡ ጐሸመጠ፡ ደፈረ።
ጣቈሰ፡ አሳበቀ፡ ኣዋሸከ።
ጣቈሰ፡ ዘር ደገመ፡ መልሶ ዘራ።
ጣቅማ፡ የንጨት ስም፡ ጕጣም ሻካራ ዕንጨት፡ ዐጣጥ መሳይ። ዳምዛን ተመልከት።
ጣቋሽ፣ የጣቈሰ፡ የሚጣቍስ፡ አፈኛ፡ አሳባቂ።
ጣቢ ፣ ጦላ፡ ቀልቃላ ሴት። "ጣቢ" ከጠበጠበ፣ "ጦላ" ከጦለ ይወጣል።
ጣቢታ፡ ዐይናማ እንጀራ፡ በግእዝ ግን "ፌቆ" ማለት ነው። ጢብኛን እይ፡ የዚህ ዘር ነው።
ጣቢያ፡ (ዐረ፡ ጣቢያህ)፡ በወንዝ ያለ የአለት ዋዲያት፡ የውሃ መታቈሪያ።
ጣቢያ፡ የባቡር መቆሚያ ስፍራ፡ የአይሮፕላን ማረፊያ።
ጣቢያ፡ የዘበኛ፡ የወታደር፡ የጦር ሰራዊት መሰብሰቢያ፡ መከማቻ፡ ሰፈር፡ ዐልፎ ዐልፎ የሚገኝ።
ጣባ፡ (ጸብኀ፡ መጽብኅ)፡ ጻሕል፡ ወጭት፡ የወጥ ማቅረቢያ፡ ማጥቀሻ፡ ከፍተኛና ዝቅተኛ የሸክላ ዕቃ። "ጣቢያን" እይ።
ጣብ (ኀዝል)፡ የመቃ ስንጣሪ፡ ልጆች እምድር ላይ እየጣሉ የሚጫወቱበት፡ ቁጥሩ ፮። ዠርባው ወደ ላይ ሲሆን ንጉሥ፡ ሆዱ (ውስጡ) ወደ ላይ ሲሆን ራስ ይባላል። በትግሪኛም ስሙ "ሸደድ" ነው፡ በጐዣም "ኋደሬ" ይሉታል። "ዐምባ ራስን" አስተውል።
ጣብ (ኀዝል)፡ የመቃ ስንጣሪ፡ ልጆች እምድር ላይ እየጣሉ የሚጫወቱበት፡ ቁጥሩ ፮። ዠርባው ወደ ላይ ሲሆን ንጉሥ፡ ሆዱ (ውስጡ) ወደ ላይ ሲሆን ራስ ይባላል። በትግሪኛም ስሙ "ሸደድ" ነው፡ በጐዣም "ኋደሬ" ይሉታል። "ዐምባ ራስን" አስተውል።
ጣቦ ፣ በጣሳ የሚቀርብ ምግብ፡ እንደ እንቀት ያለ፣ ወይም ሌላ።
ጣተ፡ ጣትን አነሣ፡ ቀሰረ።
ጣት፡ (ቶች)፡ የእጅና የእግር፡ የመንሽ፡ የሹካ ጫፍ፡ ዐጽቅ ቅጥይ፡ መያዣና መሐበ። "አውራ ጣት፡ ሌባ ጣት፡ መካከለኛ ጣት፡ የቀለበት ጣት፡ ታናሽ ጣት" እንዲለ። ጣት የወጣት ከፊል ነው፡ ምስጢሩም መጣትንና በላይ መኾንን ያሳያል። በግእዝም ፃት ይባላል።
ጣት ይጠባል፡ ሕፃን ነው፡ አላዋቂ ነው።
ጣና፡ (ጠኒን፡ ጠነ)፡ የባሕር ስም፡ በጐዣምና በበጌምድር መካከል ያለ የረጋ ውሃ፡ በውስጡ ፫ ደሴቶች ያሉበት፡ ጥቍር አባይ በላዬ የሚኼድበት። አባይን እይ።
ጣናት፡ ሕፃን፡ ዐራስ ልጅ፡ እንቦቀቅላ።
ጣናት ጣናቶች የባላገር ንግግር ነው። ዕጣንን ተመልከት።
ጣናቶች፡ ሕፃናት፡ ጨቅሎች፡ ዐራሶች።
ጣዕማ፡ (ጥዕመ)፡ የንጨት ስም፡ የቅጠሉ ሽታ ጣፋጭ የኾነ አነስተኛ ዛፍ፡ ሴቴ ጦሚት።
ጣዕማ በግእዝ፡ "ጣ" ማለት ነው።
ጣዖታም፡ ጣዖት አምላኪ፡ ባለጣፆት፡ አረመኔ።
ጣዖት፡ (ቶች)፡ ጠዐወ)፡ በጥጃ አምሳል፡ ከወርቅና ከብር፡ ከሌላም ማዕድን፡ ከንጨት የተበጀ ምስል፡ የግብጽ አሕዛብ ያመልኩት የነበረ፡ እስራኤልም በገዳም ሠርተው የሰገዱለት የወርቅ ጥጃ። ማንኛውም ሥዕል፡ ምሳሌ፡ የአሕዛብ ሥራ፡ ከወገብ በታች ጣዖት፡ ከወገብ በላይ ታቦት እንዲሉ።
ጣውንት (ቶች)፡ (ጸወነ)፡ ጐባን፡ የሌላውን ሰው ሚስት ያገባ፡ የተጠጋ ወንድ፡ የሌላዋን ሴት ባል ያገባች፡ የተጠጋች ሴት።
ጣውንትነት፡ ጐባንነት።
ጣዎስ፡ እጅግ የምታምር የህንድ ወፍ፡ ዥጕርጕር፡ በሶራ ላይ የምትሣል፡ ዐረብ የገነት ወፍ ይላታል፡ ቅዱስ መጽሐፍም በጣዎስ ፈንታ ጠዋዊስ ይላል (፪ዜና፡ ፱፡ ፳፩)።
ጣዝ፡ የውሃ መቅጃ፡ ጣሳ።
ጣዝሙት፡ (ጣዝማዊት)፡ የጣዝማ ወገን።
ጣዝማ (ሞች)፡ በመሬት ውስጥ ማር የምታበጅ ትንኝ፡ እንደ ንብ የማትናደፍ፡ በግእዝ ጸደና ትባላለች።
ጣዝማ፡ የጣዝማ ማር፡ ጣዝማ በዞፍ ከረጢት የምታሰናዳው፡ ለሳልና ለዕባጭ ይበጃል። (ተረት)፡ "ጣዝማ ይሰረስራል፡ ዳኛ ይመረምራል። "
ጣዝማ፡ የፍየል መልክ።
ጣዝማማ፡ ባለያ፡ ሴት፡ እንጀራና ወጥ፡ ዳቦና ጠላ፡ ጠጅ፡ ፈትል፡ ስፌት፡ በያይነቱ የምታውቅ፡ ከጠብ፡ ከጭቅጭቅ፡ ከንዝንዝ የምትርቅ፡ ዶንሴ፡ ሰላማዊት፡ የሴት ቍንጮ (ንግሥት)። የአማርኛ ገበታዋሪያን ተመልከት (ገጽ፡ ፶፯)።
ጣዠ፡ ዠ፡ ሞዠቅ፡ ጥሬ ዕርሻ ዐረሰ፡ ወረወር።
ጣዠ፡ ገረፈ፡ መታ፡ መለጠ። (ያማርኛ መወድስ)፡ "ሰማዕነ ጕደ በምድረ አምባሮ፡ አንድ ሰው ሚስቱን ድንገት ባለፋ መጫኛ ሲጣዥ፡ እንዘ ይብል ተንሥኢ ወልጅሽን ያዥ። . . .
."
ጣዩ፡ ያ ጣይ፡ ፀሓዩ።
ጣይ፡ (ፀሓይ)፡ በቁሙ፡ ጀንበር። ፀሓይና ጸዓሊ በአማርኛ ይተባበራሉ። (ግጥም)፡ "መሸ መሰለኝ ሊጨልም፡ እንደ ቀን ጣይ የለም። " ጣለን እይ።
ጣይ፡ (ጸዓሊ፡ ጠሓሊ)፡ የጣለ፡ የሚጥል፡ የሚወረውር፡ በጥባጭ። "ጠጅ ጣይ" እንዲሉ። ዛጐልን፡ ጠጠርን፡ ወሌን፡
ጣይን ተመልከት።
ጣይ ሞቄ፡ ጣይ የሚሞቅ፡ ገጣጣ ጥርስ፡ እንቅርብጭ።
ጣይ ሶራ፡ ድብልብል ነጭ ስንዴ፡ ፪ኛ ስሙ ያቡን እግር። ባለያ ሴት ስትጋግረው ዳቦው በፀሓይ የበሰለ ይመስላልና፡ ስሙ ጣይ ሶራ (የጣይ ሶራ፡ ባለፀሓይ፣ ግምጃ) ነጭ ሐር ተባለ።
ጣይ ቤዛ፡ (የጣይ ቤዛ)፡ ጥላ፡ ቅጠል።
ጣይቱ ብጡል፡ የዳግማዊ ምኒልክ ባለቤት (ሚስት)። "ይተጌ ጣይቱ" እንዲሉ።
ጣይቱ፡ የሴት ስም።
ጣይቱ፡ ያች ፀሓይ፡ ፀሓይዋ።
ጣይየሚጥል ፣ ጣለ።
ጣደ ፣ (ጸዐደ)፡ ምጣድን፡ ሌላውንም ሸክላ በጕልቻ ላይ አሰረረ፡ ፵ነ፡ አስቀመጠ።
ጣደ፡ ዋቢ አሳለፈ፡ አቀረበ፡ ሰጠ፡ ደቀነ።
ጣዲቁ፡ የሰው ስም፡ የወልደ ጣዲቅ (ጻድቅ) ከፊል።
ጣዲቅ፡ ጻድቅ።
ጣዲቋ፡ ጣዲቄ፡ የሴት ስም፡ የወለተ ጣዲቅ (ጻድቅ) ከፊል።
ጣድቃን፡ ጻድቃን።
ጣጅ፡ (ጸዓዲ)፡ የጣደ፡ የሚጥድ።
ጣጋ፡ አንዠቱ የተጣጋ፡ ደረቅ፡ ኰስማና ወንድ፡ ወይም ከሲታ ሴት።
ጣጣ፡ (ጣእጥአ፡ መቀቀ)፡ አደረቀ፡ ላጠ፡ አንገበገበ፡ አቃጠለ፡ ጕረሮን።
ጣጣ፡ (ፃእፃእ)፡ ጕዳይ፡ ሐሳብ፡ ችግር፡ መከራ። (ተረት)፡ "እምዬ ጣጣሽ በዛዬ። "
"ወይ ጣጣ በዚህም አያሶጣ። "
ጣጣ ፈንጣጣ፡ የፈንጣጣ ጣጣ ጠንቅ። ያለፈው ስም፡ የሚመጣው አንቀጽ ነው።
ጣጣ: የዛፍ ስም (ሜርቆ)።
ጣጣ: የዛፍ ስም ሲሆን ሜርቆ ማለት ነው።
ጣጣለ፡ መላልሶ ጣለ፡ ወራወረ።
ጣጣቴ፡ ሲተኵሱት የሚንጣጣ በሽታ፡ በ፲፱፻፲፪ ዓ፡ ም፡ የነበረ።
ጣጣቴ፡ የሚንጣጣ ጣጣ።
ጣጣኛ (ኞች)፡ ባለጣጣ፡ ጣጣው የበዛ።
ጣጣፈ፡ ከታተበ።
ጣጣፈ፡ ጠቃቀሙ፡ ሰፋፋ።
ጣጤ፡ ጣጢያም፡ ፈሳም።
ጣጥ አለ፡ ጡጥ አለ፡ ተፈሳ።
ጣጥ አደረገ፡ ጡጥ አደረገ፡ ፈሳ፡ ፈሱን ለቀቀ።
ጣጥ፡ ጡጢ፡ ፈስ።
ጣጥራስ፡ ያረመኔ ነገድ።
ጣጭ: የጠጠ ወይም የሚጥጥ፣ ጠራጊ።
ጣጭ: የጠጠ፣ የሚጥጥ፡ ጠራጊ።
ጣፈ፡ (ጸሐፈ)፡ ጻፈ፡ ከተበ፡ ቃልን፡ ነገርን፡ ሰብራና በወረቀት ላይ ሣለ፡ በማንኛውም ሰሌዳ ውስጥ አኖረ።
ጣፈ፡ ሰፋ፡ ጠቀመ፡ ለጠፈ፡ የልብስን ቀዳዳ ደፈነ።
ጣፈጠ፡ (ጻፈጠ)፡ ማር ማር፡ ጨው ጨው አለ፡ ጣመ፡ ጣም አገኘ፡ ምግቡ፡ ሽቶው፡ ነገሩ (ዘፀ፲፭፡ ፳፭። ማር፱፡ ፵፱)። ጻፈጠ የካህናት፡ ጣፈጠ የሕዝብ ነው።
ጣፈጠ፡ ጣፈጥ፡ የሰው ስም።
ጣፊ፡ (ፎች)፡ ጸሓፊ)፡ የጣፈ፡ የሚጥፍ፡ ጻፊ፡ ለጣፊ፡ ጠቃሚ፡
ሰፊ።
"ቁም ጣፊ" "ደብዳቤ ጣፊ" እንዲሉ።
ጣፊነት፡ ጣፊ መኾን።
ጣፊያ፡ (ጣፍያ)፡ የዝንጀሮ ቂጣና ጥርኝ መሳይ የሆድ ዕቃ፡ በግራ ጐን በጨጓራ ላይ ተለጥፎ የሚገኝ መናኛ ሥጋ።
ጣፋ፡ ከወርቅና ከብር፡ ከሌላም ማዕድን የተሠራ የጋሻ ልባጥና ጌጥ።
ጣፋ፡ የጋሻ ጌጥ፡ ጠፈጠፈ።
ጣፋ ጋሻ፡ ጣፋ ያለበት የጣፋ ጋሻ። ጠበረን ተመልከት።
ጣፋጭ፡ ጣፋጣ፡ (ጽዑጥ)፡ የጣፈጠ፡ የሚጣፍጥ፡ ጣም ያለው፡ ማር፡ ሸንኰራገዳ፡ ጥንቅሽ፡ ተምር፡
በለስ፡ ሱካር፡ ድንች፡ የመስለው ኹሉ (ሕዝ፫፡ ፫)።
ጣፋጭነት፡ ጣፋጭ መኾን።
ጣፌ ትዛዝ፡ (ጸሓፌ፡ ትእዛዝ)፡ ትዛዝ ጣፊ፡ የጥፈት ሹም።
ጣፎርዴ፡ ጥፍራም፡ ባለጌ።
ጣፎንጋ፡ (ጥፉነ፡ ሥጋ)፡ የማያምር ሰው፡ አፎንቻ፡ ሰውነቱ በስንፍና የታሰረ፡ ቀፍዳዳ ሰነፍ።
ጣፎንጋ፡ እኸል የማያበቅል፡ መጥፎ መሬት።
ጤቀ፡ ተሰደበ፡ ተጨነቀ።
ጤቀ፣(ጸየቀ)፡ ተበከለ፡ አደፈ፡ ተበላሸ።
ጤቀኛ፡ (ኞች)፡ ተሳዳቢ፡ ነገረኛ፡ ስም አጥፊ፡ ባለጌ።
ጤቅ፡ (ትግ፡ ጠይቂ)፡ የገጣባ መሸፈኛ፡ ድብዳብ።
ጤቅ፡ ክፉ ስድብ፡ ስም የሚያጠፋ፡ ዐጥንት የሚያሳድፍ።
ጤነ)፡ ጠየነ)፡ አጤነ፡ ዐሰበ፡ እስታወሰ፡ ልብ አደረገ፡ መረመረ፡ አስተዋለ። "እኔ ይህን ነገር አላጤንኩትም። "
ጤነኛ፡ (ኞች)፡ ዝኒ ከማሁ ለጤናማ።
ጤና፡ (ጥዕየ፡ ጥዒና)፡ ፈውስ፡ ሕይወት፡ ደኅና። "ጐመን በጤና" እንዲሉ።
ጤና ቢስ፡ በሽተኛ፡ የበሽታ ጐሬ፡ ተውሳካም፡ ታሞ አይድኔ።
ጤና አገኘ፡ ታሞ ዳነ፡ ተነሣ።
ጤና ይስጥልኝ፡ በመገናኘትና በመለየት ጊዜ የሚነገር የቃል ሰላምታ።
ጤናማ፡ (ሞች)፡ ጥዑይ)፡ ጤናም፡ ባለጤና፡ "ቃር አያውቅሽ"፡ ደኅና፡ ደኅነኛ።
ጤናማ ሆነ፡ ተሻለው፡ ተፈወሰ፡ ሻረ።
ጤናዳም፡ (ጤና አዳም)፡ የአዳም (የሰው) ጤና፡ ለመጋኛና ላልታወቀ ድንገተኛ ዕመም ኹሉ መድኀኒት የሚኾን፡ ሽታው ጣፋጭ፡ ቅመማዊ ተክል።
ጤንነት፡ ደኅንነት።
ጤዛ፡ የዝናም፡ የካፊያ ጠብታ፡ በሣር፡ በቅጠል ላይ የሚታቈር፡ የሚንቈረዘዝ። "ቤዛ" "ጢሰ (ተነ)"
"ጊሜ" ከማለት ይሰማማል።
ጤፉት፡ በግሼን ማሪያም የምትገኝ የትንቢት መጽሓፍ ስም።
ጤፍ፡ (ፎች)፡ የታናሽ እኸል ስም፡ የሣር ዐይነት ሙርዬ የሚመስል፡ ነጭ፡ ቀይ፡ ጥቍር፡ ሰርገኛ።
ጤፍ ዐጋይ፡ (ጠይፈ፡ ሐጋይ)፡ በግንቦት የሚዘራ የበጋ ጤፍ።
ጤፍን እቋተ፡ ኣጐረሠ፡ ከረተፈ፡ ሸረከተ፡ በቀላል ፈ: (የጤፍ አሰራር)።
ጥሕሎ፡ (ጥሒል፡ ጠሐለ)፡ በወጥ እየተጠቀሰ የሚበላ በሶ። ጥሕሎ ትግሪኛ ነው።
ጥለት ፣ ባለቀለም ፈትል ፣ ጣለ።
ጥለት፡ (ቶች)፡ በያይነቱ ቀለም የገባ ፈትል፡ በሸማ ዳር የሚጣል ዕድያት። "ቀይ ጥለት" "ጥቍር ጥለት" እንዲሉ።
ጥለት፡ (ጽዕለት)፡ መጣል፡ ውርወራ።
ጥለት፡ ያይን ጉም፡ ጢስ፡ ሐበላ፡ በገላ ላይ ያለ ድል ቋቍቻ።
ጥለኛ፡ (ኞች)፡ የተጣላ፡ ጥል ያለው፡ የነበረው፡ ባለጥል።
ጥሉላት፡ ሥጋና ቅቤ፡ ወተት፡ ዕንቍላል (ግእዝ)።
ጥላ ፣ በቁሙ ፣ ጠላ፡ አጠላ።
ጥላ፡ (ጽላል፡ ጽላሎት)፡ ጃን ጥላ፡ ድባብ፡ ከግምጃ፡ ከሰሌን፡ ከቀጤማ የተበጀ፡ የሚጨበጥ የፀሓይ ከለላ፡ የዳስ፡ የድንኳን፡ የቤት ውስጥ፡ የዛፍ ሥር። "ከጥላ ያረፉ፡ ከሞት የተረፉ" እንዲሉ። (የማሪያም ጥላ)፡ ድድኾ እመቤታችን በስደት ጊዜ የያዘችው።
ጥላ፡ ሩካቤ ብእሲ ወብእሲት፡ የቍስል ጠንቅ፡ ያጥንት ልጅ። ጣለን እይ።
ጥላ በረደ፡ አየሩ ነፈሰ፡ ቀዘቀዘ፡ ዐሥር ሰዓት ሆነ።
ጥላ ቢስ፡ ቀላል፡ ከውካዋ ሰው።
ጥላ ተመለሰ፡ ወደ ምሥራቅ ዞረ።
ጥላ፡ ትታ፡ አስቀምጣ። (ተረት)፡ "እንስራዋን ጥላ ውሃ ወረደች። "
ጥላ ኹን፡ የሰው ስም።
ጥላ ወጊ፡ ባንካሴ የሰውን ጥላ ወግቶ የሚያሳምም፡ ማርተኛ፡ ጠንቋይ፡ ምትሀተኛ።
ጥላ፡ የአካል ምሳሌ፡ የሰው፡ የዛፍ፡ የገደል፡ የማንኛውም ፍጥረት የቁመና ሥዕል፡ ባይን የሚታይ፡ በእጅ የማይጨበጥ፡ ጧት ወደ ምዕራብ ማታ ወደ ምሥራቅ፡ ዞሮ ይታያል፡ በቀትር ግን ይታጣል፡ ጨለማ በኾነ ጊዜም በእሳት፡ በመብራት አንጻር ይገኛል።
ጥላቂ፡ ጭላፊ፡ በጥልቂት፡ በጭልፋ የተቀዳ።
ጥላት፡ (ጸለሎ)፡ የከሰል፡ የሸክላ፡ የጣራ ጥቍር ጠለሸት። (ተረት)፡ "ጠላት ይቀባል ጥላት። "
ጥላት፡ ታቦት፡ ጸለየ፡ ጽላት።
ጥላቻ፡ ነቀፋ፡ ስልቸታ።
ጥላው ቀለለ፡ ሰውነቱ ጭር አለ።
ጥላው ከበደ፡ ሰውን ተነ።
ጥላዬ፡ የሰው ስም፡ "የኔ ጥላ" ማለት ነው።
ጥላይ፡ የተጠለለ፡ ቀረራ።
ጥል፡ (ጽልእ)፡ ቍርሾ፡ ብርቱ ጠብ፡ ዐምባ ጓሮ። "የዘመድ ጥል የሥጋ ትል፡ ጥል ያለሽ ዳቦ" እንዲሉ።
ጥል አበቀለ፡ አወጣ፡ አመጣ።
ጥልል፡ (ጥሉል)፡ የጠለለ፡ የጠራ። መዠመሪያውን "ል" አጥብቅ።
ጥልል አለ፡ ጥርት አለ፡ ጠለለ።
ጥልመት፡ (ጽልመት)፡ ጥቍረት፡ ጨለማ። "ጥልመት ፊት" እንዲሉ።
ጥልም (ጥሉም፡ ጽሉም)፡ የጠለመ፡ የሰጠመ፡ ስጥም።
ጥልም አለ፡ ስጥም አለ።
ጥልምያኮስ፡ መልአከ ጽልመት + ከሓዲ ማለት ነው።
ጥልቀት፡ መጥለቅ፡ የጀንበር ዕርበት። ደምን እይ።
ጥልቀት፡ ጥልቅነት (ምሳ፳፭፡ ፫)።
ጥልቂት፡ (ቶች)፡ ታናሽ አንኮላ፡ ሽክና፡ የውሃ መጥለቂያ፣ የጠለቀች ማለት ነው።
ጥልቅ ሆነ፡ ዝልቅ ሆነ።
ጥልቅ ባይ (ብዬ)፡ አለነገሩ የሚገባ፡ ችኩል፡ የርጎ ዝንብ።
ጥልቅ አለ፡ ዘው፣አለ፡ ሳይታሰብ ድንገት ገባ።
ጥልቅ አደረገ፡ ስጥም አደረገ።
ጥልቅ፡ የጠለቀ፡ ዝልቅ፡ ሩቅ፡ የቀጠነ፡ ቀጪን፡
ረቂቅ።
"ጥልቅ ባሕር" "ጥልቅ መርፌ" "ጥልቅ ነገር" እንዲሉ (መዝ፻፯፡ ፳፬። ፻፴፡ ፳)።
ጥልቅ፡ ግብት፡ ጥንቅር። (ተረት)፡ "አንዱ ባንዱ ሲሥቅ ጀንበር ጥልቅ። "
ጥልቅልቅ አለ፡ ተጥለቀለቀ፡ ፈጽሞ ዐረበ፡ ገባ ፀሓዩ።
ጥልቅልቅታ፡ ፍጹም ዕርበት፡ ሠርክ ምሽት፡ ወራውራን።
ጥልቅነት፡ ጥልቅ መኾን።
ጥልቆ፡ አነስተኛ መጥረቢያ፡ ስለታም፡ ዕንጨት ውስጥ የምትጠልቅ። ሰነሰነን ተመልከት።
ጥልቆች፡ የጠለቁ ውቅያኖሶች (ኢሳ፵፬፡ ፳፫)።
ጥልዝ አለ፡ ትልዝ አለ፡ ደከመ፡ የእሳት።
ጥልጣል፡ (ሎች)፡ በትግሬ ቈላ ያለ የአዳል ነገድ።
ጥልፊያ ፣ ዝኒ ከማሁ ለጠለፋ።
ጥልፍ፡ (ዕሱቅ)፡ የተጠለፈ፡ የተጌጠ፡ ሐረግ፡ አበባ፡ ዛላ፡
ዘለላ፡ የተሣለበት። "ጥልፍ ግላስ" "ጥልፍ ቀሚስ" "ጥልፍ ዝናር" እንዲሉ።
ጥልፍ፡ መር በዋልታ ብስ ዐልፎ፣ ዐልፎ የገባ ገመድ፡ ርስ በርሱ የተጠለፈ።
ጥልፍልፍ፡ የተጠላለፈ፡ ውስብስብ፡ ቍልፍልፍ።
ጥልፎች፡ የተጠለፉ ግላሶች፡ ቀሚሶች፡ ዝምዝሞች።
ጥሎ፡ ትቶ። "አገር ጥሎ ቈርበት ጠቅሎ። "
ጥሎ አይጥል፡ ፈጣሪ፡ መሓሪ፡ አምላክ፡ ፍጡሩን ፈጽሞ የማይጥል (ኢዮ፩፡ ፲፬፡ ፲፱። ፪፡ ፯። ፵፪፡ ፲ ፲፯)።
ጥሎሽ፡ ለልጃገረድ የሰርግ ለት በዕድመኛ በሰርገኛ ፊት የሚጣል ወርቅና ብር፡ ቀሚስና ኩታ፡ ካባ፡ ጌጥ በያይነቱ።
ጥሎሽ፡ መጣል፡ ማንደባለል።
ጥሎሽ፡ ትቶሽ፡ አውድቆሽ።
ጥሎሽ፡ ያመንዝራ ፍቅር።
ጥሎኸ፡ አንተን እሱ ትቶኸ።
ጥሎኸ ይለቅ፡ ልብሱ ይለቅ፡ አንተ ቁም፡ ዐዲስ ልብስ ለለበሰ ሰው ይነገራል።
ጥመመኛ፡ (ኞች)፡ ባለጥመም፡ ተንኰለኛ፡ ሀኬተኛ።
ጥመም፡ ክፉ ጥበብ፡ ተንኰል፡ ጥመት።
ጥመራ፡ የመጠመር ሥራ፡ መጠመር፡ መደረብ፡ መደመር።
ጥመት፡ ልግም፡ ሀኬት፡ ቸልታ።
ጥሙር፡ (ሮች)፡ ፅሙር፡ ክዑብ)፡ የተጠሞረ፡ ድርብ፡ ኹለትዮ፡ ሦስትዮ፡ ማግ፡
ሐር፡ ጥለት።
ጥሙጋ፡ በይፋት ክፍል ያለ አገርና ነገድ።
ጥሙጎች፡ የጥሙጋ ጋሎች፡ ነገዶች፡ ወገኖች።
ጥማቂ፡ ጭማቂ፡ ውጤት፡ ዘይት፡ አንጥፍጣፊ፡ ፍሳሽ፡
የታጠበ ልብስ ሲጠመዘዝ የሚወጣ ውሃ፡ ከወይን የተዘጋጀ መጠጥ (ማር፲፬፡ ፳፭)።
ጥማተኛ፡ ውሃ ጥም የያዘው፡ ያቃጠለው።
ጥማድ፡ (ፅምድ)፡ ፪፡ የቀንበር በሬ።
ጥማዶች፡ ፬፡ በሮች፡ ካ፬ም በላይ ያሉ ብዙዎች የርሻ ከብቶች።
ጥም፡ ጥማት፡ መጥማት፡ መጠማት፡ የውሃ መሻት፡ ፍላጎት (ነሐ፱፡ ፲፭። ፪ቆሮ፡ ፲፩፡ ፳፯)።
ጥምለላ፡ ዐጠፋ፡ ቍልመማ።
ጥምልል፡ (ጥብሉል)፡ የተጠመለለ፡ ቍልምም።
ጥምልል አለ፡ ዕጥፍ፡ ቍልምም አለ።
ጥምልማይ፡ የጥምልምል ዐይነት፡ ወገን፡ አምልማሎ እግር።
ጥምልምል፡ (ሎች)፡ የተጥመለመለ፡ ሽባ፡ ዝልፍልፍ፡ ሽምድምድ።
ጥምልምል አለ፡ ተጥመለመለ።
ጥምልምል አደረገ፡ ዝልፍልፍ፡ ሽምድምድ አደረገ፡ አጥመለመለ።
ጥምቀተ ባሕር፡ (ባሕረ፡ ጥምቀት)፡ የጥምቀት ባሕር።
ጥምቀተ ክርስትና፡ የክርስትና ጥምቀት።
ጥምቀት፡ መጥመቅ፡ መጠመቅ።
ጥምቀት፡ የበዓል ስም፡ በጥር ፲፩ኛ ቀን የሚውል፡ ጌታችን ስለኛ ያደረገው ጥምቀት መታሰቢያ።
ጥምቅ፡ (ጥሙቅ)፡ የተጠመቀ፡ ክርስቲያን የኾነ።
ጥምቅ፡ ንጥር ማር።
ጥምብራ፣ የመክድ ጌጥ፡ ጥንብራ።
ጥምዘዛ፡ የመጠምዘዝ ሥራ።
ጥምዝ፡ ዝኒ ከማሁ፡ የተጠመዘዘ፡ የከረረ። "ጥምዝ ወርቅ" እንዲሉ።
ጥምዝ፡ የቅኔ አገባብ ስም።
ጥምዝ ጠጕር: አሻራ (የጸጉር ዓይነት)።
ጥምዝዝ፡ ዝኒ ከማሁ ለጥምዝ፡ ጥምዝዝ አደረገ፡ ጥምም፡ ዘወር፡ መለስ አደረገ።
ጥምድ፡ (ፅሙድ)፡ የተጠመደ፡ ቀንበር የተጫነው። "ጥምድ እንደ በሬ፡ ቅንት እንደ ገበሬ" እንዲሉ።
ጥምጠማ፡ ሽብለላ፡ ጥቅለላ፡ አሰራ።
ጥምጥማት፡ የመጠምጠም፡ የመደመር ኹኔታ።
ጥምጥም፡ (ጥዉም)፡ የተጠመጠመ።
ጥምጥም፡ መጠምጠሚያ።
ጥምጥም አለ፡ ተጠመጠመ።
ጥምጥም: የራስ መሸፈኛ።
ጥምጥሞሽ፡ ዝኒ ከማሁ፡ ጥምጠማ።
ጥሞና፡ (ጽሙና)፡ ብቻነት፡ ብቻ መኾን፡ ጸጥታ፡ ርጋታ። "ይህን ነገር በጥሞና ቀን እንነጋገረዋለን። "
ጥስቅ አደረገ፡ ሆዱን መላ አጠገበ።
ጥስቅ፡ የተጠሰቀ፡ የጠገበ ሆድ፡ ጥርንቅ ያለ ገላ።
ጥስጥስ፡ የጠሰጠሰ፡ አሮጌ፡ ከብት፡ ሰው።
ጥሶ፡ ሰብሮ፡ ረግጦ። ናደለ ብለኸ አናዳይን እይ።
ጥሶሽ፡ መጣስ፡ መዠመሪያ የሽሩባ ሥራ።
ጥሶሽ፡ አማስኖ ድንግል፡ ዳግመ በሣልስት ዕለት።
ጥረ ገቲ፡ (ጥሬ፡ ገትም)፡ ጥሬ ኀታሚ፡ አብዝቶ ቃሚ፡ ወፍራም ጕልበታም።
ጥረሾ፡ (ዎች)፡ ጥሬ ርሾ)፡ ያልቦካ፡ ያልሖመጠጠ፡ ደረቅ የገብስ ቂጣ፡ ገሃ፡ ደገኞች እንደ ቈሎ የሚቈረጥሙት።
ጥረቃ፡ ችንከራ።
ጥረት፡ (ጽዕረት)፡ ጭንቀት፡ ትጋት፡ ልፋት፡ ድካም (፪ቆሮ፡ ፯፡ ፲፩። ፪ጴጥ፡ ፩፡ ፭)።
ጥረገቲ ፣ ጥሬ ገታሚ ፣ ጥሬ።
ጥሩ፡ (ዎች)፡ የጠራ፡ የጠዳ፡ ንጹሕ፡ ነጭ፡ ጸዐዳ፡ ወለላ። "ጥሩ እንደ ብርሌ፡ ቀይ እንደ በርበሬ"።
ጥሩ፡ ማለፊያ፡ መልካም፡ "ጥሩ ቤት"፡ "ጥሩ ልብስ"፡ "ጥሩ ነገር"፡ "ጥሩ ሰው" እንዲሉ።
ጥሩ ሽታ ሰጠ: ላፍንጫ ጣፈጠ (አበባው፣ ሽቶው፣ ጠጁ፣ ወጡ)። የበጎ ሸተን እይ።
ጥሩ ቀን፡ ዝናምና ጉም፡ ደመና፡ ዐፈና የሌለበት ቀን፡ ብራ።
ጥሩ ታደፍ፡ የብር እኸል ከአበባና ካገዳ እኸል ጋራ።
ጥሩ ነኽ፡ ነሽ፡ የወንድና የሴት መጠሪያ ስም።
ጥሩ ኾነ፡ ጠራ፡ ኮለል አለ።
ጥሩ ወርቅ፡ በውስጡ ተንኰልና ቅልቅል፡ ግብዝ፡ ቂራጥ፡ መዳብ የሌለበት ወርቅ። "ጥሩ ወርቅ"፣ የሴት ስም።
ጥሩ ውሃ፡ አንዳች ነገር ያልተደባለቀበት፡ ኵል የሚመስል ውሃ።
ጥሩ ዝናብ፡ በረዶና የሰማይ ቍጣ ያላስከተለ።
ጥሩ፡ የብር እኸል፡ ስንዴና ገብስ፡ ጤፍ። "ጥሩ ታደፍ" እንዲሉ።
ጥሩ ገንዘብ፡ በሥራ፡ በድካም፡ የተገኘ፡ አፈፋ፡ ጐደፋ የሌለበት ገንዘብ።
ጥሩምባ፡ ከንሓስ የተበጀ የሰራዊት መጥሪያ፡ መሰብሰቢያ፡ በትንፋሽ የሚጮኸ። በጣሊያንኛ "ትሮምባ" ይባላል።
ጥሩር፡ (ዕሩር፡ ድርዕ)፡ የብረት ጥብቆ፡ የጦር ልብስ፡ ልብድ (ነሐ፬፡ ፲፮። ኤር፡ ፵፮፡ ፬)። የፈረስ ቤዛ (፪መቃ፡ ፩፡ ፳፮)። ጥሩር በግእዝ ደንብ እንደ ጥርር ቅጽል እንጂ ጥሬ አይኾንም፡ ሲበዛ ጥሩሮች ይላል።
ጥሩር፡ በተጕለት ውስጥ ያለ አገር። "ጥሩር አንዳርጌ" እንዲሉ። ይህ አገር በቀድሞ ዘመን ጥሩር የተሠራበት ወይም የጥሩር ሹም የነበረበት ይመስላል።
ጥሩር አንዳርጌ: የጥሩር አንዳርጌ።
ጥሩነት፡ ጥሩ መኾን።
ጥሪ ፣ (ጥራእ፡ ጽራሕ፡ ጽዋዔ፡ ጽውዓ)፡ በድምፅ፡ በደብዳቤ መጥራት። "የጥሪ ቃል"፡ "የጥሪ ወረቀት" እንዲሉ።
ጥሪ፡ (ጽርየት)፡ ጥራት፡ መጥራት። "የደም ጥሪ" እንዲሉ።
ጥሪ፡ ጥራት፡ ጠራ (ጸረየ)፡ መጥራት፡ መጮኸ፡ ና ማለት።
ጥሪት፡ ቁም ከብት፡ ማጀት፡ የጐረሠው፡ በራፍ የመለሰው፡ ማንኛውም ገንዘብ፡ ሀብት (ግብ፡ ሐዋ፪፡ ፵፭)።
ጥራር፡ (ተረረ)፡ አገልግል፡ መሶብ፡ ቅርጫት፡ ቀፎ፡ ጥላ፡
ካረግ፡ ከቀርክሓ ሥንጣሪ የተበጀ (ጐዣም)። ግእዝ ሙዳየ ዔረግ ከሚለው ጋራ ይሰማማል።
ጥራር፡ (ፅራር)፡ የንጉሥ ጥሩር። "ጃን ጥራር" እንዲሉ። ጃንን ተመልከት። ጥራር ጥሩር ሲባል፡ ጥሩር ደግሞ ጥሩር ለባሽ ባለጥሩር ማለት ይኾናል። ፅሩርን እይ።
ጥራቢ፡ (ጽራብ)፡ የንጨት፡ የደንጊያ፡ ስብርባሪ፡ ፍርፋሪ፡
ልላጭ፡ ልባጭ፡ ድቃቂ፡ ክልካይ።
ጥራት፡ (ጽርየት)፡ ጥሩነት፡ ጥዳት። "ጥራትና ንጋት" እንዲሉ።
ጥራን ፣ ትንሽ ነጋሪት፡ ፣ ጠራ።
ጥራን፡ (ጸውዐነ)፡ በሰፊ ነጋሪት አጠገብ የምትመታ ትንሿ ነጋሪት፡ የደባይ አማሪት፡ ለጦር፡ ለግብር፡ ሰው መጥሪያ።
ጥራን ቀንድ፡ በድባብና በጃን ጥላ፡ በካባና በልባልማ ላይ የሚጠለፍ ወርቅ ባለሿሿቴ።
ጥራን፡ የገንዘብ ሣጥን።
ጥራዝ፡ (ዞች)፡ የመጣፍ ስፌት፡ ቶታን።
ጥራዝ፡ ባንድነት የታሰረ ፭ ቅጽ፡ ወይም ፬ና ፰ ቅጠል ብራና ወረቀት ሲታጠፍ ፲፡ ፰፡ ፲፮ ይኾናል።
ጥራዝ ነጠቅ ፣ ያልተማረ ሰው ሲሉ፣ ሰምቶ የሚያወራ።
ጥራጊ፡ የተጠረገ፡ የቤት ውስጥ ጕድፍ፡ ቍሻሻ፡ ገለባ፡ የሣር ድቃቂ፡ ዐፈር፡ መሬት፡ ምናምን ኹሉ (ኤር፵፱፡ ፪)።
ጥራግ ፣ ጽራግ፡ ጸረገ።
ጥራጎ፡ ከሥሩ የተጠረገ፡ የታጨደ፡ ቅጠላቅጠል፡ መንጠር።
ጥራጥሬ፡ የጥሬ ጥሬ፡ ያበባ እኽል።
ጥሬ፡ (ጠረየ፡ ጥራይ)፡ ያልደቀቀና ያልበሰለ ማንኛውም ነገር። ሲበዛ ጥሬዎች ይላል። ጥሪትን እይ።
ጥሬ ሰዋስው፡ ቅጽል የማይኾን ስም።
ጥሬ ሰዋስው፡ የመጽሐፍ ስም፡ የግእዝ ጥሬ ዘርና ነባር ያለበት መጽሐፍ።
ጥሬ ሰው፡ ያልተማረ፡ ባላገር።
ጥሬ ሲገባ)፡ ቤታቸው፣ ሥራቸው።
ጥሬ ሥጋ፡ ያልተጠበሰ፡ ያልተቀቀለ፡ ሙዳ (ዘፀ፲፪፡ ፱)። "ሐበሾች በግራኝ ጊዜ ጥሬ ሥጋ በሉ"።
ጥሬ ሥጋውን በሉት፡ ዐሙት፡ ነቀፉት፡ ሰዎች አንዱን ሰው።
ጥሬ ብር፡ የብር ለውጥ የሚኾን ሌላ ገንዘብ፡ ወይም ዕቃ፡ ያይዶለ ብር ብቻ።
ጥሬ ዕርሻ፡ ዕዳሪ።
ጥሬ እኽል፣ ያልተፈጨና ያልተቦካ፡ ያልተጋገረ እኽል።
ጥሬ፡ ከውጭ አገር ቋንቋ ሳይተረጐም፣ በግእዝ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈ ቃል።
ጥሬ ካብ፡ ቃና፡ ኖራ ያልገባበት፡ በደንጊያ ብቻ የተበጀ ካብ።
ጥሬ ዘር፡ ካባት ዘር የወጣ ስም፡ ነባር ያይዶለ። "መብቀል በቀለ ብሎ በቅሎ"፡ "መነገድ ነገደ ብሎ ንግድ"፡ "መቅለም ቀለመ ብሎ ቀለም"፡ እንደዚህ ያለ፡ ይህን የመሰለ።
ጥሬ፡ የቈሎ ስም፡ ቈሎ። "ተማሪው ጥሬ በልቶ ውሃ ጠጥቶ ይማራል"።
ጥሬ ገንዘብ፡ ብርና አላድ፡ ሩብ፡ ተሙን፡ መሐለቅ፡ ቤሳ፡ ለወረቀት ገንዘብ ያልተመነዘረና ለዕቃ ያልተለወጠ።
ጥሬ ጕሬ: የንጀራ ክምር፣ ዳቤ። "ጋሬን" እይ።
ጥሬ ጐመን፡ ያልተቀቀለ።
ጥሬ ጤፍ፡ ያልተፈጨ፡ ያልተሸመሸመ።
ጥሬ፡ ጥሪ፡ ላራስ የሚሰጥ ምግብ፡ ኅብስት፡ ዳቦ፡ ሙክት፡ ከብት፡ ገንዘብ፡
ሌላም በያይነቱ ስጦታ ኹሉ። "ያራስ ጥሪ" እንዲሉ። ጥሬ አስቀድሞ እየተነገረ ለስም በቂና ቅጽል ይኾናል።
ጥሬ ጥጥ፡ ያልተፈለቀቀ።
ጥሬ ጨው፡ ያልተደቈሰ።
ጥሬ ፈጅ፡ ጨረባ፡ በቋል።
ጥሬነት ፣ ጥሬ መኾን፡ አለመብሰል።
ጥሬና ብስል፡ ተቈልቶ፡ ተቀቅሎ፡ ተጠብሶ የበሰለና ያልበሰለ ባንድነት።
ጥሬና ብስል፣ የልጅ ነገር፡ የሚረባና የማይረባ።
ጥር፡ (ሮች)፡ የተጠራ። "ስመ ጥር" እንዲሉ።
ጥር ፲፭ኛ ወር ከመስከረም። ጠረረን አስተውል።
ጥር፡ የወር ስም (ጣራ)።
ጥርሰ ሸራፋ፡ ጥርሰ ሰባራ። ገረገመንን እይ።
ጥርሰ በረዶ፡ ጥርሱ፡ ጥርሷ በረዶ የሚመስል ወንድ፡ ሴት።
ጥርሰ ወላቃ፣ ጥርሱ የወለቀ፡ የተነቀለ፡ የተመነገለ።
ጥርሰ ዘርዛራ፡ ጥርሱ የተራራቀ።
ጥርሰ ገጣጣ፡ ጥርሱ ያፈነረ፡ ያፈነገጠ፡ ጣይ ሞቴ።
ጥርሰ ፍንጭት፡ የፊት ጥርሱ መካከል ክፍት የኾነ።
ጥርሳም፡ ጥርሰ ረዥም፡ ገጣጣ ሰው፡ ጣረ ሞት።
ጥርስ፡ (ዕሩስ)፡ የጠረሰ፡ ችርችም።
ጥርስ፡ ባውሬና በንስሳ፡ በሰው አፍ ውስጥ ያለ፡ ዐፅማዊ ወፍጮ፡ ምግብን ኹሉ የሚፈጭ፡ የሚያደቅ፡ የሚሰልቅ፡ የሚያልም፡
የፊት ጥርስ፡ ክራንቻ፡ መንጋጋ። ነቀሰን እይ። (ውሃ ጥርስ)፡ ችክ የማይዝ። (የባብ ጥርስ)፡ ዝምዝማት። (የዝኆን ጥርስ)፡ ቀንድ መሳይ፡ በውድ የሚሼጥ። (ዕሪያ ጥርስ)፡ ከማነሱ በቀር የዝኆን ጥርስ ይመስላል፡ ዕባጭ ይተኰስበታል። (ዕሪያ ጥርስ)፡ ጥርሱ የገጠጠ ሰው።
ጥርስ፡ ትክክለኛ ያልኾነ የልጠየቅ መልስ፡ የሙግት፡ የጥይቅ ስሕተት። "ጥርስ ነው" እንዲል መስካሪ።
ጥርስ ነው፡ ስሕተት ነው፡ ለጥይቁ ተገቢ መልስ አልተሰጠም።
ጥርስ አለ፡ ጠረሰ።
ጥርስ አወጣ፡ ሞረደ፡ ዘረዘረ፡ አበጀ።
ጥርስ አወጣ፡ ጥርስ አበቀለ።
ጥርስ፡ የሌማት፡ ያገልግል፡ የሰገጥ መግጠሚያ።
ጥርስ፡ የመኪና ኹሉ መግጠሚያና መዘወሪያ።
ጥርስ፡ የመጋዝ፡ የማጭድ ዝርዝር:። ዕንጨት መቍረጫ፡ ሣር ማጨጃ።
ጥርስ የማያስከድን፡ አጫዋች፡ አሥቂኝ፡ ካታ።
ጥርስ፡ የሸማኔ መምቻ ማግን የሚያቀራርብ፡ የሚሰገስግ፡ ከጐሽ መቃ ተፍቆ የተበጀ።
ጥርስ፡ የብጕንጅ፡ የዕባጭ ሰንኰፍ።
ጥርስ ገባ፡ ተጠላ፡ መወደድን ዐጣ።
ጥርሶ፡ ረዥምና ወፍራም ጠፍጣፋ ነጭ አደንጓሬ፡ ደንጐሎ።
ጥርሶች፡ ፪ና ከ፪ በላይ ያሉ መንጋጋዎች፡ ክራንቾች (ምሳ፴፡ ፲፬)።
ጥርር፡ (ፅርር)፡ የተጠረረ፡ ጥሩርን የለበሰ ሐርበኛ። ጥር ከዚህም ሊወጣ ይችላል (ሉቃ፬፡ ፩፡ ፲፪፡ ፲፬)። የምስጢር ጥቅስ ነው። ሐምበል።
ጥርቃሚ፡ የተጠራቀመ፡ ከያለበት የመጣ፡ ስብስብ።
ጥርቃሞ፡ ዝኒ ዓዲ፡ ከማሁ።
ጥርቅ፡ የተጠረቀ፡ የተሰመረ፡ ብረት ለበስ፡ ሣጥን፡ ስማርድ፡ የጦር መሣሪያ፡ መኪና።
ጥርቅም አለ፡ ተጠረቀመ፡ ዝም አለ።
ጥርቅም አደረገ፡ ጠረቀመ፡ ገረኘ፡ ኣጠበቀ፡ መናገር ከለከለ።
ጥርቅም፡ ዝኒ ከማሁ፡ ትርክም።
ጥርቅም፡ የተጠረቀመ፡ የገባ፡ የታሰረ፡ እስር፡ ዝግ።
ጥርቅምቃሚ፡ የተጠረቃቀመ፡ ውጥን።
ጥርቅምቅም፡ ዝኒ ከማሁ።
ጥርብ፡ (ጽሩብ)፡ የተጠረበ፡ የታነጠ። "ጥርብ ድንጋይ"፡ "ጥርብ ዋሻ"፡ "ጥርብ ዕንጨት" እንዲሉ።
ጥርብርብ፡ የተጥረበረበ፡ ሽቍጥቍጥ፡ ርግብግብ።
ጥርት፡ (ጸርይ)፡ ጥሩ መኾን። "ጥርት አለ"፡ ፈጽሞ ጥሩ ኾነ።
ጥርንቅ፡ (ድርንቅ)፡ የተጠረነቀ፡ የታሰረ፡ ጥብቅ የኾነ ወፍራም ገላ።
ጥርንቅ አለ፡ ጥብቅ አለ፡ አካሉ።
ጥርንቡሌ፡ (ትሪፖሊ)፡ ከትግሬ ካማራ ወደ ትሪፖሊ የዘመተ የጣሊያን ወታደር፡ አሽከር (ባንዳ)። "ትሪ" ፫፡ "ፖሊ" ከተማ ማለት ነው ይላሉ።
ጥርኝ፡ (ኞች)፣ ጽርኒ)፡ የዝባድ አውሬ፡ ድመት መሳይ፡ ጠረናም።
ጥርኝ፡ ዝባድ ሽቱ፡ ከጥርኝ ገላ የሚጠረግ ላብ፡ ኵክ መሳይ፡ በውድ የሚሼጥ፡ መድኀኒትነት ያለው።
ጥርኝ፡ የቀኝ ወይም የግራ ውስጥ እጅ፡ የዕፍኝ እኩሌታ። "ይህ ጠጅ በጥርኝ ይኼዳል። "
ጥርኝ፡ የፈረስ መልክ፡ ጥርኟን የሚመስል ፈረስ (ዘካ፩፡ ፰)። "ሺ ዳለች ሺ ቦራ ነበር የሺዋ ፈረስ፡ አንድ ጥርኝ ኾነ ቢቀር ቴዎድሮስ" (ኣዝማሪ)። በቅሎ ሲኾን "ግራ" ይባላል።
ጥርኝ፡ ያንድ እጅ ዝግኝ ጭብጥ። "ጥርኝ ዐፈር" እንዲሉ።
ጥርክርክ፡ ጥርኸርኸ፡ የተጥረከረከ፡ ዝርክርክ፡
ጕድፍድፍ፡ ኵልፍልፍ።
ጥርውዝ፡ የተንጠራወዘ።
ጥርውዝ ጥርውዝ አለ፡ ክልውስ ክልውስ አለ።
ጥርጊያ፡ ሌሊት ከጥቃቅን ኮከቦች ጋራ እንዳውራ መንገድ በሰማይ ተዘርግቶ የሚታይ ጭጋግ፡ ሰዎች ኹሉ የጦርነት ምልክት ነው ይሉታል።
ጥርጊያ፡ ተጠርጎና ተደልድሎ፡ ለጥ ቀጥ ብሎ ሰፊ ኹኖ የተሠራ የመንገድ ስፋትና ወለል (ኢሳ፲፩፡ ፲፮)።
ጥርጊያ ጐዳና፡ የጐዳና ጥርጊያ፡ ወይም የጥርጊያ ጐዳና።
ጥርጊያ፡ ጠረጋ፡ መጥረግ።
ጥርግ (ትግ፡ ጽሩግ)፡ የተጠረገ፡ የተመነጠረ፡ ምንጥር።
ጥርግ አለ፡ እብስ አለ፡ ፈጽሞ ኼደ፡ ነጐደ።
ጥርግ አደረገ፡ ሙጥጥ አደረገ።
ጥርጥስ አለ፡ ጭርጭስ አለ፡ ጠረጠሰ።
ጥርጥስ፡ የጠረጠሰ።
ጥሺ): ንሺ እቴ።
ጥሻ፡ (ሾች)፡ ትግ፡ ጣሻ)፡ ባንድነት ያደገ፡ የረዘመ፡ ብዙ ሣርና ቅጠል፡ ዳዋ፡ ደን፡ ሊጥሱት የሚቻል።
ጥሽ: የእንጨት ስም፡ በወይናደጋ አካባቢ የሚበቅል ታናሽ እንጨት፡ ርጥቡን የሚነድ። ዘሩ ማጠጠ ነው። የመጥረግ ምስጢር አለበት። በብዛት ሲነገር ጥሾች ይላል።
ጥሽ: የእንጨት ስም። በወይናደጋ አካባቢ የሚበቅል ታናሽ እንጨት፣ ርጥቡን የሚነድ። ዘሩ ማጠጠ ነው። የመጥረግ ምስጢር አለበት። በብዛት ሲነገር ጥሾች ይላል።
ጥቀርሻ፡ ዝኒ ከማሁ ለጠቀራ፡ ጪስ ያጠቈረው ሰንበሌጥ፡ የሸረሪት ድር፡ በጣራ ውስጥ ያለ ነገር ኹሉ።
ጥቀርሻ ጠገብ፡ ጥቀርሻ የጠገበ፡ ጦር፡ ጥቀርሻም።
ጥቁ፣(ጥቁዕ)፡ የተጠቃ፡ የተበደለ፡ ግፍ የጠገበ፡ የተቀበለ።
ጥቍማት፡ የጥፍር ውግታት፡ የዠርባ ዕከክ፡ ጭረት።
ጥቍም አደረገ፡ በጥቂቱ ወጋ፡ ጠቈመ።
ጥቍም፡ የተጠቈመ፡ የጥፍር፡ የእሾኸ፡ ታናሽ ውግ።
ጥቍረት፡ ጥቍርነት፡ ማዲያት መልበስ (ማሕ፩፡ ፲፩። ሰቈ፬፡ ፰)።
ጥቍሪት፡ ታሪኳ በተረታዊ ቃል የሚነገር ንግሥት፡ ሽማግሌን ኹሉ አጥፍታ "ቤቴን እሰማይ ላይ ሥሩ" ያለች። በባሶ የሠራት ከተማ ጥቍሪት ባዶ ይባላል፡ በቡልጋም ድልድይ ኣላት ይላሉ።
ጥቍራት፡ ንቅሳት፡ ውቅራት፡ የገላ ላይ ማኅተም።
ጥቍሬ፡ የጥቍር ወገን፡ ወይም ዐይነት። "ጥቍሬ ዝንጀሮ" እንዲሉ።
ጥቍሬታ፡ ማር፡ በጐታ፡ እንጀራው ማር ማር የሚል፡ ጥቍር ያገዳ እኽል። በጤፍ መስል ይለወጣል።
ጥቍር፡ (ሮች)፡ ጽልሙት)፣ ዝኒ ከማሁ፡ ከነጭ፡ ከቀይ፡ ከብጫ የተለየ ሥፍጥረት። ጥቍር አስቀድሞ እየተነገረ፣ ለማንኛውም ስም ቅጽል ይኾናል፡ ቅጽልነቱም የዐይነት ነው።
ጥቍር መጣፈጥ፡ ጥቍር አዝሙድ።
ጥቍር ሰማይ፡ ኒል መሳይ።
ጥቍር ሰው፡ ሻንቅላ፡ የአፍሪቃ ነገድ።
ጥቍር ስንዴ፡ አቶሳል።
ጥቍር ራስ፡ መነኵሴ፡ ያይዶለ ረድ፡ ዓለማዊ።
ጥቍር ቍራ፡ ፍጹም ጥቍር።
ጥቍር አለ፡ ግምን፡ ክስል አለ።
ጥቍር ዐረብ: የሻንቅላ እስላም (የሻንቅላ ዘር)። (አዝማሪ): "የጐበና አሽከሮች ጠፍር የት ያውቃሉ፡ በነጋ በጠባ ባረብ ይጭናሉ" (ምሳሌያዊ አነጋገር)። ሰማያዊ ዐረብም ከጥቍር ይቈጠራል (የአረብ ቀለም)።
ጥቍር ዐረብ: ጥቍር ቀለም የገባ የበግ ቈዳ (ዘፀ፳፮፡ ፲፬) (ጥቁር ቀለም ያለው የበግ ቆዳ)።
ጥቍር አባይ (ኤፌሶን)፣ ውሃው፡ ሰማይ የሚመስል ዠማ። አባይን እይ።
ጥቍር አውጥ: ቅጠለ መራራ፡ ከሥንቆ፣ ከሥጊሚና፣ ከአሉማ ጋር ተቀቅሎ ባንድነት የሚበላ።
ጥቍር አዝሙድ፡ አበ ሱድ።
ጥቍር እንግዳ፡ ጕንዳን፡ በጨለማ የመጣ፡ ዋና የዘመድ እንግዳ፡ መጥቶ የማያውቅ።
ጥቍር ዕንጨት፣ ዞጲ።
ጥቍር ውሻ፡ ከጥቍረት በቀር ንጣት የሌለው።
ጥቍር ውሻ ውለድ አለ፣ ፈጽሞ ረገመ፡ ካደ።
ጥቍር ደንጊያ፡ አለት፡ ባሪያ፡ ድንጋይ።
ጥቍር ፈረስ፡ ዱሪ (ራእ፮፡ ፭)።
ጥቍር ፍየል፡ ከሰልማ።
ጥቍርቍር አለ፡ የጥቍር ጥቍር ሆነ፡ ጕስቍልቍል አለ።
ጥቍርነት፡ ጥቍር መኾን።
ጥቂቱን ለብዙ ገንዘብ ለዋጭ።
ጥቂት፡ (ጠቀ)፡ ትንሽ። ጥቂት አስቀድሞ እየተነገረ፡ ከተጸውዖ ስም በቀር ውስጠ ብዙነት ላለው ስም ኩሉ ቅጽል ይኾናል።
ጥቂት ምግብ መገበ: አባበለ፣ አረሳሳ፣ ደለለ፣ አታለለ፣ አሞኘ። "የማይሰጠውን፡ እሰጣለኹ፡ አለ (ሮሜ ፫፡ ፲፫)። ሸግላን እይ፡ የዚህ፡ ዘር፡ ነው።"
ጥቂት ጥቂት ሄደ፣ ተራመደ።
ጥቂቶች፡ ትንሾች (መክ፲፪፡ ፫)።
ጥቃሽ፡ የነገር ስላች።
ጥቃቅን በረዶ: በምድር ላይ ሽፍ ብሎ የሚታይ።
ጥቃቅን፡ ታናናሽ፡ ቅንጣት።
ጥቃቅኖች፡ ታናናሾች፡ ልጆች፡ ብላቴኖች፡ ወይም ሌሎች ነገሮች።
ጥቃተኛ፡ ጥቃት የበዛበት፡ ተጠቂ፡ ጥቁ።
ጥቃት፡ (ጥቅዐት)፡ ግፍ፡ በደል፡ ውርደት።
ጥቈማ፡ የመጠቈም ሥራ፡ ግብር።
ጥቅ ንጥቅን ተመልከት፡ የጠቀጠቀ ዘር ነው።
ጥቅለላ፡ ሽብለላ፡ ጥምጠማ፡ ሽፈና።
ጥቅል፡ (ጥቅሉል)፡ የተጠቀለለ፡ ሽብልል፡ ጥምጥም። "የወርቅ እንክብል"፡ "የሸማ ጥቅል" እንዲሉ።
ጥቅል ነፋስ፡ ኵርፊት፡ ዐውሎ ነፋስ።
ጥቅል ነፋስ): ዐውሎ ነፋስ፣ ኵርፊት።
ጥቅል፡ አንድነት ያለ፡ ወፍራም ሊጥ።
ጥቅልል አለ፣ ሽብልል አለ፡ ተጠቀለለ።
ጥቅልል አደረገ፡ ሽብልል አደረገ።
ጥቅማት፡ ስፌት።
ጥቅም፡ (ባቍዕ)፡ ረብ፡ ርባና፡ ትርፍ፡ ፋይዳ፡ ፈሎ፡ የሚጠቅም፡
የሚረባ ነገር ኹሉ፡ አገልግሎት (መዝ፲፱፡ ፲፩። ምሳ፲፡ ፪)።
ጥቅም፡ (ጥቁብ)፡ የተጠቀመ፡ የተረባ፡ የተሰፋ፡ ስፍ። የፊተኛው ስም፡ ያኹኑ ቅጽል መኾኑን አስተውል።
ጥቅምቅም፡ የተጠቃቀመ፡ የተጣጣፈ፡ ጨርቅ፡ ድሪቶ።
ጥቅምት፡ የወር ስም፡ ፪ኛ ወር፡ ከመሬት ብዙ ጥቅም የሚገኝበት፡ እኸልና ተክል ኹሉ ፍሬ የሚሰጥበት። በግእዝ ግን የተገነባች ማለት ነው፡ ፍጥረተ ዓለምን ያሳያል።
ጥቅስ፡ (ሶች)፡ የቃል፡ የነገር፡ ምስክር፡ ምሳሌ፡ ማስረጃ፡
ትች፡ ሐተታ።
"የጐመን ጥቅስ" እንዲሉ።
ጥቅሻ (ቅጽበት)፡ ምልክት፡ ያይን ጥሪ፡ ቅጥጥብ (ምሳ፯፡ ፳፭)። "ባይን ጥቅሻ በከንፈር ንክሻ" እንዲሉ።
ጥቅንጥቅ (ጠቀጠቀ)፡ ዝብዝብ፡ ውስብስብ።
ጥቅጠቃ፡ የመጠቅጠቅ ሥራ፡ ሽፈና፡ ደፈና፡ ረገጣ፡ ርምረማ።
ጥቅጥቅ ፣ ተቀራርቦ የተሠራ ብዙ መንደር፡ ችፍግ ያለ ከተማ፡ ርግጫ የበዛበት መሬት።
ጥቅጥቅ፡ (ቆች)፡ የተጠቀጠቀ፡ በመርፌ የተበሳሳ፡ ተቈርጦ፡ ተጐርዶ የሚሰጥ የደረሰኝ ወረቀት።
ጥቅጥቅ አለ፡ ችፍግ አለ።
ጥቅጥቆሽ፣ ጥቅጥቃት፡ የመርፌ ውግታት፡ ንቅሳት፡ ነዳላ፡ የድፎ ያንኮላ ጌጥ።
ጥቋቍር፡ (ሮች)፡ ውስጠ ብዙ ጥቍር።
ጥበሌ) ቀበሌ፡ የገደል፡ ማሚቶ፡ ድምፅን፡ የምትቀበል።
ጥበቃ፡ እረኝነት፡ ክልከላ፡ ዘብ፡ የመጠበቅ ሥራ (፪ሳሙ፡ ፯፡ ፰)።
ጥበበ ሰሎሞን፡ ጥበብ መንፈሳዊን፣ ጥበብ ሥጋዊን የተመላ የሰሎሞን መጽሐፍ።
ጥበበኛ (ኞች)፡ (ጥበባዊ)፡ ጥበብ ዐዋቂ፡ ብልኀተኛ፡ ሸረኛ፡ ተንኰለኛ፡ ጥመመኛ።
ጥበብ (ቦች)፡ ብልኀት፡ ዘዴ፡ ዕውቀት፡ ፍልስፍና። "ሰነፎች ግን ጥበብንና ትምህርትን ይንቃሉ" (ምሳ፩፡ ፯)።
ጥበብ መንፈሳዊ፡ የአምላክ፣ የመልአክ ረቂቅ ጥበብ።
ጥበብ ሥጋዊ፡ የአዳም፣ የሰው ጕልህ ጥበብ።
ጥበብ፡ በኩታ-በቀሚስ ዳር ያለ በብዙ ዐይነት ጥለት የተሠራ ጌጥ።
ጥበብ፡ ተንኰል፡ ክፉ ብልኀት፡ ጥመም። "ጥበብን ጥመም የሚያሰኘው እንደ እቶም ያለ ሥራ ነው"።
ጥበብ ኩታ: በጫፍና በጫፉ ከ፰ ላይ ጥበብ የተሠራበት (የተጣለበት)፡ ባለጥበብ ኩታ። "ጐዳን"፣ "ጠበበን" ተመልከት፡ "ቍጥኔን" እይ።
ጥበት፡ (ጽበት)፡ ዝኒ ከማሁ፡ ጭንቀት፡ ጠባብነት።
ጥቢ፡ ክረምት ውጭ መስከረም።
ጥባት፡ (ጽብሐት)፣ ንጋት፡ ወገግታ፡ ፈገግታ። የመስከረም መባት።
ጥብ፡ ዝኒ ከማሁ፡ የጨነቀ፡ ጭንቅ። "ዐጸባን" ተመልከት።
ጥብልቃና፡ ጥንታዊ በገና፡ (ጥብሉለ፡ ቃና)፡ ባለብዙ ቅኝት።
ጥብሳት፡ (ጥብሰት)፡ ትኵሳት፡ የመጥበስ ሥራ (ዘሌ፲፫፡ ፳፭)።
ጥብስ (ሶች)፡ (ጥቡስ)፡ የተጠበሰ። "ጥብስ እንጀራ" "ጥብስ እሸት" "ጥብስ ሥጋ" እንዲሉ።
ጥብስ ወጥ፡ ቍሌት።
ጥብር፡ የተጠበረ፡ ጌጠኛ።
ጥብቅ፡ (ጥቡቅ)፡ የጠበቀ፡ የማይፈታ፡ ብርቱ፡ ግትር፡ ፍንክች የማይል፡ ከራራ፡ ጠንካራ ማሰሪያ። "ዐደራ ጥብቅ፡ ሰማይ ሩቅ" እንዲሉ።
ጥብቅ አለ፡ ልጥፍ፡ ልጥቅ አለ።
ጥብቅ፡ እስራት፡ አገዛዝ።
ጥብቅ ወዳጅ፡ ወረት የለሽ፡ የታመነ።
ጥብቅ፡ የማይሰጥ፡ የማይቸር።
ጥብቅ፡ የተጠበቀ፡ ክልክል፡ እግድ፡ ዝሪት፡ መስኖ፡
ቁባት።
ጥብቅ ገባ፡ ነገር አዛነፈ፡ ከውሳኔ ዐለፈ፡ ሁለት መልስ ሰጠ።
ጥብቅነት፡ ጥብቅ መሆን፡ አለመበገር፡ አለመፈታት፡ አለመስጠት።
ጥብቅና፣ ዝኒ ከማሁ።
ጥብቆ (ዎች)፡ በጥብቅ ተሠርቶ የተሰፋ ግብግብ፡ ወይም ዐጪር የልጅ ቀሚስ፡ ኪታ (ዘፀ፳፭፡ ፯)።
ጥብብቅ፡ (ጠፋልሕ)፡ በመጣብቅ የተያያዘ ገንዘብ።
ጥብነት፡ ጥብ መሆን።
ጥብጠባ፡ የስቅለት ለት ገረፋ፡ ሽንቈጣ፡ ግሥገሣ፡ ሩጫ።
ጥብጣብ (ቦች)፡ የሱሪ መታጠቂያ፡ መሽቀቅ፡ የካባ ጌጥ፡ በጥብጣብ አምሳል የተሠራ። "ባለወርቅ ጥብጣብ" እንዲሉ።
ጥብጥባት (ጥብጣቤ)፡ ግርፋት፡ ሰንበር።
ጥብጥብ፡ የተጠበጠበ፡ የተበለተ፡ ግርፍ፡ ብልት።
ጥብጥቦ፡ ሽታ ያለው ቅጠል።
ጥቦቶች፡ ብዙዎች፡ ከአንድ በላይ ያሉ (ዘፍ፴፡ ፵። ዮሐ፳፩፡ ፲፭)።
ጥኑ፡ (ዎች)፡ ጽኑዕ)፡ የጠና፡ ብርቱ፡ ጠንካራ፡ የማይበገር፡ የማይፈታ። "ልበ፡ ጥኑ" "ነፍሰ፡ ጥኑ" እንዲሉ።
ጥና ፣ ጠንክር፣ ጠና።
ጥና፡ (ጽናዕ)፡ በርታ፡ ጠንክር፡ ቻል።
ጥና፡ (ጽንሓሕ)፡ የቤተ መቅደስ ዕጣን ማጠኛ፡ ጽና። "ሲበዛ ጥናዎች ጥኖች" ይላል።
ጥና፡ ዝኒ ከማሁ። "እከሌ በጥና ታል። "
ጥና): ማናፋት፣ ማያያዝ፣ ማቃጠል፣ ነፋስን መሳብ፣ ማቀበል።
ጥና): አናፋ (አመብኵሐ)፡ ከሰልን በወናፍ እፍ እፍ አለ፣ ነፋስ ሰጠ፣ አያያዘ፣ አቃጠለ፣ አቀጣጠለ (ኢሳ፶፬፡ ፲፮)። አናፋ አደራራጊ ብቻ ሲመስል በአድራጊነትም መፈታቱን አስተውል።
ጥናት፡ (ጽንሐት)፡ መማለድ፡ መቀመጥ፡ መቈየት። "ደጅ ጥናት" እንዲሉ።
ጥናት፡ (ጽንዕ፡ ጽንዐት)፡ ጥንካሬ፡ ብርታት፡ መጥናት።
ጥናት፡ ማጥናት፡ የቃል ትምርት።
ጥን) ፉን: ከንፈረ ሥንጥቅ።
ጥን) ፉን: ፈነዳ።
ጥንሰሳ፡ የመጠንሰስ ሥራ፡ ብጥበጣ።
ጥንስስ መሰለ፡ ደመነ፡ ጠቈረ፡ የሰማይ፡ የባሕር፡ የፊት።
ጥንስስ፡ የተጠነሰሰ፡ የጠላ ርሾ፡ ፅንስ።
ጥንቀቃ፡ የመጠንቀቅ ሥራ።
ጥንቍሌ፡ የጥንቍል። በጕራጌ ቋንቋ ግን፡ ጭንቍላ ማለት ነው።
ጥንቍል፡ የተጠነቈለ፡ የተወጋ፡ ድንቍል።
ጥንቁቅ፡ ዝኒ ከማሁ ለጠንቃቃ፡ ኵስትር፡ ስሕተት፡ ግድፈት፡ ጸያፍ የሌለበት።
ጥንቁቅነት (ጥንቅቅና)፣ ኵስትርነት።
ጥንቃቄ፡ ዝኒ ከማሁ፡ ዝግጅት፡ ትጋት፡ ንቃት። ጥንቃቄ ግእዝኛ ነው።
ጥንቈላ፡ ርት፡ አስማት፡ ደገማ፡ ኮከብ ቈጠራ።
ጥንቅር አለ፡ ጥልቅ አለ፡ ፀረበ።
ጥንቅር፡ የገባ፡ የጠለቀ።
ጥንቅሽ፡ (ሾች)፡ ትግ፡ ጠቀሰ፡ ተቀለሰ)፡ ዐንገተ ቀላሳ፡ አገዳ፡ ማር ማር የሚል፡ ጣፋጭ ዘንጋዳ፡ ማሽላ፡ መጥቀሻ፡ መሳይ።
ጥንቅቅ አለ፡ ዙስትር አለ፡ ተጠነቀቀ።
ጥንቅቅ፡ ዝኒ ዓዲ፡ ከማሁ ለጥንቁቅ።
ጥንበ በላ (ሎች)፡ ጥንብ የሚበላ።
ጥንበኒ፡ ግመኒ፡ ግም አስተኔ።
ጥንቡን ጣለ፡ ረከሰ፡ የሚገዛው ዐጣ፡ ወደቀ።
ጥንቡዝ፡ (ጐንደር)፡ ዕድር።
ጥንባም፡ ጥንብ የወደቀበት፡ ያለበት ስፍራ።
ጥንባታም፡ ግማታም፡ ባለጥንብ።
ጥንባት፡ ግማት፡ ጥንብ፡ ጥንብ መሸተት።
ጥንብ፡ (ቦች)፡ የጠነባ፡ ግም፡ ውዳቂ (ኤር፲፮፡ ፰። ሉቃ፲፯፡ ፴፯)።
ጥንብ መባሉ ልብድና ጠፍር ከሌለበት የትም መውደቁን ያሳያል።
ጥንብ፡ መጥፎ ሰው።
ጥንብ አሞራ፡ የጥንብ አሞራ።
ጥንብ፡ የኮርቻ ዕንጨት።
ጥንብራ፡ (ጠበረ)፡ በሰይፍ እጀታ ላይ የሚደረግ ክብ የወርቅና የብር ጌጥ። መክድን እይ።
ጥንብርብር፡ ድንብርብር።
ጥንብዝ አለ፡ ፈጽሞ ሰከረ።
ጥንብዝ፡ የጠነበዘ።
ጥንብዝብዝ፡ ጥንግርግር።
ጥንብፍ፡ የተጠነበፈ፡ በሰይፍ ተመቶ፡ በጦር ተወግቶ፡ የተጋደመ፡ ጥንብኛ የወደቀ።
ጥንቦ፡ የመንቀፍና የማዋረድ ቃል።
ጥንተ መድኀኒት: ጤናዳም፣ እኹል ገብ። ጌታችንና እመቤታችንም ለነፍስ ጥንተ መድኅኒት ይባላሉ።
ጥንተ ስቅለት: ጌታችን የተሰቀለበት መጋቢት ፳፯ ቀን። ጥንትነቱ ዛሬ ለሚዘዋወረው ነው።
ጥንተ ነገር: ሥረ ነገር።
ጥንተ ዕለት: የቀን መዠመሪያ፣ እሑድ።
ጥንተ ደዌ: ልክፍት።
ጥንተ ጠላት: ሰይጣን፣ እባብ።
ጥንተ ፍጥረት: የፍጥረት መዠመሪያ፣ እሑድ።
ጥንቱን: ፊቱን፣ ዱሮውን፣ ቀድሞውን፡ ሲዠመር ዠምሮ። (ግጥም) "ጥንቱን ነበር እንጂ ሰው አልኾንም ማለት፡ አዳምና ሔዋን የተፈጠሩ ለት። "
ጥንት አስቀድሞ፣ ወጠነ።
ጥንት: ሥር መሠረት፣ መዠመሪያ፣ ዱሮ፣ ቀድሞ፣ አስቀድሞ።
ጥንቸል፡ (ሎች)፡ ያውሬ ስም፡ የሽኮኮ ዐይነት።
ጥንከራ፡ ጥንካሬ፡ ጥናት፡ ብርታት።
ጥንክር፡ የጠና፡ ጥጥር፡ ጠንካራ።
ጥንክርና፡ ጥንክር መኾን (ኢዮ፮፡ ፲፪)።
ጥንዝዛ፡ ሲኼድ ዕዝ፡ ጥዝ የሚል፡ በክንፍ በራሪ፡ መናኛ ማር ሠሪ፡ በደረቅ ዕንጨት ውስጥ ዐዳሪ፡ ሦስት ዐይነት መልክ፡ ፍጹም ጥቍር፡ ነጭና ጥቍር፡ አረንጓዴ ፍጥረት። ጥቍሩ መርዝ አለው፡ አረንጓዴው ግን ሰላማዊ ነው፡ ልጆች እግሩን በክር እያሰሩ ይጫወቱበታል። (ጠዘዘ)ን ተመልከት። ካህናትም ሕንዝዝ ይሉታል።
ጥንዡት፡ (ቶች)፡ የንጨት ስም፡ በወይናደጋ ቈላ የሚበቅል ነጭ ዕንጨት፡ እሾኻም። የጠላ ጋንን፡ ዐራስን ያጥኑበታል፡ ሲሰብሩት ቅልጥም ይላል። ዘሩ ጠነዛ ነው።
ጥንድ፡ የዕጽፍ ቍጥር። ፪፡ በሬ፡ ፪፡ ድር፡ ቀንጃ፡ ነጠላ፡ ያይዶለ፡
"ጥንድ በሬ" "ጥንድ ተቀንጃ" "መቶ ጥንድ ድር"፡ ፩፡ ፪፡ ፫፡ · · ፲፡ ጥንድ እንዲሉ።
ጥንድ፣ ጥምድ፣ ጠመደ።
ጥንግ፡ (ጎች)፡ ፅንጉዕ፡ ፅፉር)፡ የጠፍር ኳስ፡ ዕሩር።
ጥንግ፡ ድርብ፡ ሥራው፡ እንደ፡ ጥንግ፡ ውስብስብ፡ የኾነ፡
ማለት፡ ነው።
ጥንግ ድርብ፡ በጥንግ ዐይነት የተሠራ ድርብ፡ ጥበብ፡ ውስብስብ።
ጥንግርግር፡ ጥንብርብር።
ጥንጣን፡ (ኖች)፡ የትል ስም፡ ዕንጨትን ዐመድ የሚያደርግ ትል። በግእዝ ጽንጽንያ፡ ቍንቍኔ ይባላል። "ጥንጣን በላው" እንዲሉ።
ጥንጣን ሆነ፡ በጣም ደቀቀ፡ ላመ፡ ተሰለቀ።
ጥንጣን፡ ጥንጣን ያደቀቀው የንጨት ዶቄት።
ጥንጥናት፡ የማጠንጠን ሥራ፡ ጥቅልላት፡ ጥምጥማት።
ጥንጥን፣ (ጽንጹን)፡ የጠነጠነ፡ የነቀዘ።
ጥንጥን፡ የተጠነጠነ፡ ልቃቂት፡ ድውር።
ጥንፋፊ፡ የንፍሮ፡ የግንፍል፡ ሥጋ ውሃ።
ጥንፍ፡ (ጸነፈ፡ ጽንፍ)፣ ዳር፡ ዳርቻ፡ መጨረሻ።
ጥንፍፍ አለ፡ (ተጠነፈፈ)፡ ዐለተ፡ ተወረሰ፡ ተጠነገደ።
ጥንፍፍ አደረገ፡ ሰውን፡ ከብትን በጦር፡ በበሽታ ፈጀ፡ ጨረሰ፡ ጠነደ።
ጥንፍፍ፡ የተጠነፈፈ፡ ውሃ የወጣለት ንፍሮ።
ጥከ) መክላት: መከልከል።
ጥከክ)፡ ትክትክ (ስም)፡ የሕፃን ጕንፋን፣ ሳል።
ጥዋ፡ (ጸውዐ፡ ጽዋዕ)፡ ከወርቅ፡ ከብር፡ ከማዕድን፡ ከሸክላ፡ በዋንጫና በመንቀል ዐይነት የተሠራ፡ የቍርባን፡ የማኅበር፡ የደጀ ሰላም ዕቃ። ሲበዛ ጥዎች ይላል።
ጥዋ ሕይወት፡ (ጽዋዐ ሕይወት)፡ በቍርባን ጥዋ አምሳል የተበጀ፡ ማኅበረተኛ የሚሳተፍበት (ጠበል የሚጠጣበት)፡ ፩ የሕይወት ጥዋ በየወሩ እማኅበር ቤት የሚዞር።
ጥዋ ተርታ፡ በተርታ መጠጥ ማደያ፡ ጥዋ። "ዕድል ፈንታ ጥዋ ተርታ" እንዲሉ።
ጥውለጋ፡ መጠውለግ (፩ነገ፡ ፰፡ ፴፯)።
ጥውልውል ፣ የተጥወለወለ፡ የዞረ፡ የሚዞር።
ጥውልውል አደረገ፡ አጥወለወለ። ጦለን እይ፣ ከዚህ ጋራ አንድ ነው።
ጥውልግ፡ (ምጽልው)፣ ዝኒ ከማሁ።
ጥውልግ አለ፡ ልውጥ አለ።
ጥውር፡ (ጽዉር)፡ የተጦረ፡ የታገዘ፡ የተረዳ፡ የሰው በልቶ ጠጥቶ የሚኖር።
ጥዝ አለ፣ ጠጣ።
ጥዝ አለ፣ ጮኸ። (ጠዘዘ)።
ጥዝ ጥዝ ባይ፡ ንብ፡ ክራር።
ጥዝ ጥዝ አደረገ፡ ብዙ ጊዜ አጮኸ። ጥንዝዛን እይ፡ የዚህ ዘር ነው።
ጥዝል ሆድ፡ ከረቦ ሆድ።
ጥዝል፡ የተጠዘለ፡ የተመደወተ፡ ምድል።
ጥዝር ፣ ንፍ ፣ ዝጥር።
ጥዝታ፡ ጥዝ ማለት፡ ጩኸት።
ጥዝጠዛ፡ ነደፋ፡ የንብና የተርብ፡ ጦርነት።
ጥዝጣዜ፡ ንዝናዜ።
ጥዝጥዝ አደረገ፡ መልሶ መላልሶ ጠዘጠዘ።
ጥዝጥዝ፡ የተጠዘጠዘ፡ የተነደፈ።
ጥየቃ፡ (ጥያቄ)፡ ምርመራ፡ ሐተታ፡ እህታ።
ጥየታ፡ ስብሰባ፡ አሰራ።
ጥዩፍ፡ ጥይፍ፡ የተጠየፈ፡ ሸቍራራ፡ ንቁፍ፡ የነቀፈ።
ጥያራ፡ አይሮፕላን፡ ሰው ሠራሽ አሞራ፡ በነፋስ፡ በእሳት፡ በቤንዚን ኀይል በአየር የሚበር፡ የሚከንፍ፡ የሰማይ ባቡር። እንደ አውሮሮጳ አቈጣጠር ባ፲፱፻፫ ዓ፡ ም፡ አይሮፕላንን መዠመሪያ ያወጡ አርቢልና ዊልበር ወንድማማች ኣሜሪካውያን ናቸው ይባላል።
ጥያቄ (ዎች)፡ ጥየቃ፡ መጠየቅ። "ጥየቃ" ዐማርኛ፡ "ጥያቄ" ግእዝ ነው።
ጥያቄ፡ በመጠየቅ ጊዜ በቃል መጪረሻ የሚጨመር ንኡስ አገባብ፡ ወይ ን።
ጥይር፡ የተጠየረ፡ ዝግጁ፡ ቈፍጣና፡ ኵሩ።
ጥይቅ፡ ሙግት፡ ክርክር፡ ተጠየቅታ።
ጥይቅ፡ የተጠየቀ፡ ምርምር።
ጥይት፡ (ስም)፡ የታሰረ እሸት። ብዙው ጥይት ባንድ ዝናር እንደሚያዝ፡ ብዙው እሸት ባንዲት ልጥ (ገመድ) መታሰሩን ያሳያል።
ጥይት፡ (ቶች)፡ (ቅጽል)፡ የተጠየተ፡ ጥይት የኾነ፡ ርሳስ፡ ዐረር፡ ከቀለሕ ጋራ የተዋደደ፡ ቱባ፡ ክልስ (ቸሬ)፡ ከሽጕጥና ከጠመንዣ፡ ከመትረየስና ከመድፍ ውስጥ የሚተኮስ።
ጥይት፡ በጥይት የተመታ፡ የተገደለ።
ጥይፍተኛ፡ (ኞች)፡ የጥይፍ ወገን፡ ባለጥይፍታ፡ ተጠያፊ። ከዚህ የቀረውን ትርጓሜ በጸየፈ ተራ ተመልከት። "ጠየፈ" የሕዝብ፡ "ጸየፈ" የካህናት ነው።
ጥይፍታ፡ ነቀፋ፡ ጥላቻ፡ ሥቅቅታ።
ጥደት፡ (ጽዕደት)፡ መጣድ።
ጥዱ ፣ የሰው ስም፣ ጠዳ።
ጥዱ፡ (ጽዕድው)፡ የጠዳ፡ የጠራ፡ ጥሩ፡ ነጭ፡ እድፍ፡ ጕድፍ፡
እንከን የሌለበት።
ጥዱ፡ የባላባት ስም፡ ከሺዋ ባላባቶች አንዱ። "ሞረት የጥዱ ልጅ" እንዲሉ። ጥድን ተመልከት።
ጥዱ፡ ያ ጥድ፡ የርሱ ጥድ።
ጥዱፍ፡ (ጽዱፍ)፡ የጠደፈ፡ ገደል የገባ፡ የተንከባለለ፡ ችኵል።
ጥዱፍነት፡ ችኩልነት።
ጥዳቂ፡ የቈየ ሥር የሰደደ ሳል።
ጥዳት፡ (ጽዕዳዌ)፡ ጥራት፡ ጥሩነት፡ ንጽሕና፡ ንጣት።
ጥድ (ዶች)፡ (ጽሕድ)፡ የዛፍ ስም፡ በዓለም ሁሉ የታወቀ ዕንጨት፡ ሽታው የሚጣፍጥ፡ ልዝብ የሆነ ሳንቃው በውድ ይሸጣል፡ ለቤት ሕንጻ ይሰማማል።
ጥድቅ፡ ጽድቅ።
ጥድፈት፡ (ጽድፈት)፡ ዝኒ ከማሁ፡ ገደል መግባት።
ጥድፊያ፡ ችኰላ፡ መቸኰል፡ ፍጥነት።
ጥዶ ዘለል፡ እብድ፡ ወፈፌ።
ጥዶ፡ ጭኖ አስቀምጦ።
ጥዶሽ፣ ዝኒ ከማሁ።
ጥጃ ፣ እንቦሳ፣ ጠዳ።
ጥጃ (ጆች)፡ የላም ልጅ፡ ከእንቦሳ የሚበልጥ፡ የተወለደ ለት እናቱ ልሳ ያጠዳችው (፩ሳሙ፡ ፲፱፡ ፴፪)።
ጥጃ ሣር፡ (የጥጃ ሣር)፡ ያገር ስም፡ የወግዳ ማፍ።
ጥገታም፡ ጥገት ያለችው፡ ባለጥገት።
ጥገት (ቶች)፡ የምታጠባ፡ የምትታለብ፡ ጥጃ ያላት ላም።
ጥገና፡ አሰራ፡ ጥቅለላ፡ ቆከማ፡ ፍወሳ፡ ዕገዛ፡
ድገፋ፡ ርዳታ፡ ዕደሳ።
ጥገናም፡ ባለጥግን፡ ፈረስ፡ በቅሎ፡ በራ፡ አህያ።
ጥገን፡ የጕልበት ዕብጠት፡ በጥቶ ማውጣት፡ መጠገን፡ መፈወስ የሚገባው በሽታ።
ጥገን ያዘው፡ ዐበጠ፡ ታመመ፡ ውሃ ወጣበት፡ ጕልበቱ፡ ግልገል፡ ሰኰናው።
ጥገኛ፡ (ጥጉዕ፡ ፅጉዕ፡ ጽዉን)፡ የተጠጋ፡ የተማጠነ፡ ሰውን ጥግ ያደረገ፡ በሌላ መንግሥት ጥግ ያደረ፡ ባለጥግ ጠባቂ ያለው።
ጥገኞች፡ የተጠጉ፡ ጥግ የያዙ።
ጥጉብ፡ (ጽጉብ)፡ የጠገበ፡ የወፈረ፡ ወፍራም፡ መጣፍ፡ ጥራዘ ብዙ።
ጥጊ ፣ አበባ፡ ጽጌ።
ጥጋበኛ (ኞች)፡ ጥጋብ የበዛበት፡ ባለጥጋብ፡ ድኻ አጥቂ።
ጥጋብ፡ የሆድ ምላት በመብል በመጠጥ (መክ፭፡ ፲፪)። "የካባን ራብ የዳባን ጥጋብ የሚያውቅ የለም። "
ጥጋት፡ (ትግ ፅግዒ)፡ ጭፍልቅ፡ ትርታሮ (ኤር፬፡ ፫)።
ጥጋት፡ ዕዳሪ፡ ማረሻ ያልዞረበት መሬት (ጐዣም)።
ጥጋት፡ ጥግ።
ጥጋት፡ ጥግ፡ ጠጋ።
ጥጋጥግ፡ የጥግ ጥግ፡ ብዙ ጥግ።
ጥግ፡ (ፅግዕ፡ ጸወን)፡ ሥር፡ ታች፡ ግርጌ (፩ሳሙ፡ ፳፡ ፳)። "የገደል ጥግ" "የቤት ጥግ" እንዲሉ።
ጥግ፡ የድኻ ረዳት፡ ደጋፊ፡ ሀብታም ሰው።
ጥግ ያዘ፡ ጥግን ገንዘብ አደረገ።
ጥግ ጥጉን ኼደ፡ ታች ታቹን፡ ሥር ሥሩን ዐለፈ። (ተረት)፡ "ዳቦ ሲያይ ልብ ልቡን፡ ዳገት ሲያይ ጥግ ጥጉን። "
ጥግር፡ የተጠገረረ፣ የተደበለለ፣ ተሸካሚ።
ጥግር፡ ድብል፡ እንደ ጠገራ ያለ ከባድ ሸክም።
ጥግታ፡ ዝኒ ከማሁ።
ጥግነት፡ ጥግ መሆን።
ጥግናት፣ ዝኒ ከማሁ፡ እስራት፡ ጥቅልላት።
ጥግን (ኖች)፡ የተጠገነ፡ የታደሰ፡ የዳነ፡ እስር፡ ጥቅል።
ጥግንግን፡ የተጠጋገነ፡ እስርስር።
ጥጐር፡ በቡልጋ ክፍል ያለ ቀበሌ።
ጥጎች፡ ሥሮች፡ ታቾች።
ጥጥ (ጦች)፡ የታወቀ ተክል፡ በቈላ አገር ፍሬው ተዘርቶ የሚበቅል፡ ተፈልቅቆ፡ ተዳምጦ፡ ተባዝቶ፡ ተፈትሎ፡
ድርና ማግ ኹኖ ተሠርቶ የሚለበስ። በግእዝ ጡጥ ይባላል።
ጥጥ ፍሬ፡ የጥጥ ፍሬ፡ ጥፍጥሬ። ጣፈጠን እይ።
ጥጥር (ሮች)፡ የጠጠረ፡ ጥኑ፡ ጠንካራ።
ጥጥር) ቍጥር፡ (ጥቋ) መቋጠር።
ጥጥት አደረገ፡ ሽምጥጥ አደረገ። ፬ኛውን ና እይ።
ጥጥት፡ ጭልጥ።
ጥፈራ፡ ዝኒ ከማሁ።
ጥፈት፡ (ጽሕፈት)፡ የቃል፡ የነገር፡ ሥዕል፡ ምሳሌ፡ በብራና ላይ ተሥሎ የሚታይ ፊደል። (ቀወመ) ቆመ ብለኸ ቁምን እይ።
ጥፈት ቤት፡ (ቤተ፡ ጽሕፈት)፡ ደብዳቤ ማዘዣ፡ ማንኛውም ጕዳይ የሚጣፍበት የጥፈት ቤት።
ጥፉ፡ (ጥፉእ)፡ የጠፋ፡ ብላሽ፡ ከንቱ፡ በክ፡ ክፉ፡ የማያምር።
ጥፉ፡ በረሓ፡ ምድረ በዳ፡ ደረቅ ስፍራ፡ ነውረኛ ሥራ (ዘኍ፳፲ ፭። ሕዝ፳፡ ፵፬)።
ጥፉዎች፡ ጥፎች፡ የጠፉ፡ ከንቱዎች (፩ቆሮ፡ ፩፡ ፲፰)።
ጥፊ፡ (ጥፍሕ)፡ ውስጥ እጅ፡ የውስጥ እጅ በትር (ዮሐ፲፰፡ ፳፪። ፲፱፡ ፫)። ወጥንን፡ ቃሪያን ተመልከት።
ጥፊ፡ (ጽፍዐት)፡ ሽውታ፡ ያይን ዕብጠት፡ ምች።
ጥፋተኛ፡ (ኞች)፡ በደለኛ፡ ክፉ አድራጊ።
ጥፋተኛ የሚጠጋበት ጣዖታዊ ብረት: በቃልቻና በባላባት ቤት የሚቀመጥ። እሱን ከጫጩ (ዛጐል) ጋራ ይዞ የኼደ ሰው ይቅርታና ዕርቅ ሰላም ይደረግለታል።
ጥፋት፡ (ጥፍአት)፡ ሞት፡ ኅልፈት፡ እንዳልነበረ መኾን (ዘፍ፮፡ ፲፯። ፩ቆሮ፡ ፲፭፡ ፵፪)።
ጥፋት፡ የማይገባ ሥራ፡ ስርቆሽን፡ ስካርን፡ ዝሙትን የመሰለ ነውር ነገር።
ጥፌ፡ ቅጠሉ ጫት የሚመስል ዕንጨት፡ ችፌ የሚያጠፋ። "ጥፌ ለችፌ" እንዲሉ። ለሰላቢ ይበጃል እያሉ በሞፈሩ የከተራ ለት በሙሉ ቀን ይተልሙበታል።
ጥፌ፡ ዝኒ ከማሁ ለጥፉ፡ ከባለቤቱ የራቀ። "የጥፌ ብር" እንዲሉ።
ጥፍረ መጥምጥ፡ የጥፍር ሥር ቍስል፡ መርዝ የሚባል፡ ጥፍርን የሚመጠምጥ፡ የሚነቅል ደዌ። መድኀኒቱም ዕፀ ዘዌ ነው።
ጥፍራማ፡ ነብር፡ አሞራ፡ ካቤላ፡ ከብት። "ነብር ጥፍራማ" እንዲል መስታድርት።
ጥፍራም፡ (ሞች)፡ ባለረዥም ጥፍር፡ ጥፍሩን የሚያሳድግ፡ የማይቈርጥ፡ ናዝራዊ፡ ባሕታዊ።
ጥፍራም ሆነ፡ ጥፍሩ አደገ፡ ረዘመ።
ጥፍር፡ (ሮች)፡ ጽፍር)፡ የእጅና የእግር ቤዛ፡ ወይም ጌጥ። የእንስሳት ሰኰና ኮቴ ይባላል። የአራዊት የቀንጠፋ እሾኸ፡ የአዕዋፍ ሜንጦ ይመስላል።
ጥፍር፡ (ጥፉር፡ ፅፉር)፡ የተጠፈረ፣ የታሰረ፣ የተማገረ፣ የተታታ ዐልጋ።
ጥፍር ቍርጫ፡ የልጃገረድ ጥፍር ቈረጣ።
ጥፍር አንዶ፡ ጥፍር እንዶ፡ ወተታም ዕንጨት፡ ልጡ ነጭ ሐርና ጥፍር የሚመስል፡ እረኞች ልጡን ቍግ ያደርጉታል። "አንዶ እንዶ" እንደ ማለት ነው።
ጥፍት፡ (ጥፍአት)፡ ዕልም፡ ድርግም።
ጥፍት አለ፡ ውድም አለ።
ጥፍን፡ የተጠፈነ፡ በኹለት በኩል የታሰረ፡ የተተበተበ፡ በላይና በታች ከተፈለፈለ ዕንጨት ጋራ የተዋደደ፡ ግፍና ጫፉ የተዘጋ የሸማ ጥርስ እስራት።
ጥፍጠፋ፡ የመዘርጋት፡ የማሣሣት ሥራ።
ጥፍጣፍ፡ (ጸፍጸፍ)፡ ንጣፍ፡ ደንጊያ፡ የተወቀረ፡ የተጠረበ፡
የመሬት፡ ልባጥ።
ጥፍጥ፡ (ጽፍጥ)፡ ጣፋጣ (መዝ፻፵፩ ▪ ፬። ነሐ፰፡ ፲፱ መክ፭ ▪ ፲፪)።
ጥፍጥሬ፡ ጥጥ ፍሬ በማለት ፈንታ ባላገር ጥፍጥሬ ይላል።
ጥፍጥሬ፡ ጥፍጥ ፍሬ፡ በክፉ ቀን እንትክትኩ ዋና ምግብ መኾኑን ያሳያል።
ጥፍጥነት፡ ጥፍጥ መኾን።
ጥፍጥፍ፡ (ጽፍጹፍ)፡ የተጠፈጠፈ፡ እበት፡ ወይም ኩበት፡ የሠም፡ የትንባኾ ልጥልጥ።
ጦለ፡ (ጠወለ። ዕብ፡ ጣል፡ ነሣ፡ ወሰደ)፡ ዞረ፡ ተንሰዋለለ።
ጦለበ፡ (ጸለበ)፡ ሰቀለ፡ አንጠለጠለ፡ ገደለ፡ ወስፈንጠርኛ። ዘመን አመጣሽ ቋንቋ ነው። (ግጥም)፡ "ፍቅር አይገድልም ሲሉ፡ ቄሱን ጦለበው አሉ። "
ጦለጦለ)፡ ጦለ)፡ አንጦለጦለ፡ ቶሎ ቶሎ አስኬደ፡ ዕረፍት ነሣ፡ አንቀዠቀዠ። (ጦነጦነ)ን እይ።
ጦለጦለ)ን፡ አይ፡ የዚህ ደጊም ነው።
ጦለጦል፡ ጦልጧላ፡ የተንጦለጦለ፡ የሚንጦለጦል፡ ጦንዉና።
ጦሊት፡ (ጦልዐ)፡ ያንገት ልብስ፡ መጠብር፡ ነጠላ፡ ጥቍር ጥለት ያለው።
ጦሌ፡ የጦላ ዐይነት።
ጦሎታ፡ (ጠወለ)፡ ቍግ፡ የጅራፍ ጕተና፡ ማፍ፡ የሚጮኸ፡ ውልብልቢት በነፋስ ኀይል።
ጦመ፡ (ጾመ)፡ እኸል ውሃ ሳይቀመስ ዋለ፡ ከሥጋ፡ ከቅቤ ተከለከለ።
ጦመ ሕርቃል፡ ዘወረደ ያርባ ሑዳዴ መዠመሪያ ሳምንት።
ጦመ ልጓም፡ (ልጓመ፡ ጦም)፡ የምሳሌ አነጋገር፡ ልጓም ሠም፡ ጦም ወርቅ። ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓ ጾም ልጓም ካለው የመጣ ነው። አርባ፡ ሑዳዴ፡ ወይም ኣክፍለት። "እንኳን ጦመ ልጓሙን ፈታልኸ" እንዲሉ። (የጦም)፡ በጦም የማይበላ፡ የሥጋና የቅቤ ወጥ፡ መጦም የሚያሻው፡ የሚያስፈልገው ማለት ነው። (የጦም ወጥ)፡ በጦም ቀን የሚበላ የክክና ያትክልት ወጥ፡ በቅባኑግ፡ በዘይት የተሠራ።
ጦመ ነነዌ፡ የነነዌ ሰዎች የጦሙት የ፫ ቀን ጦም (ዮና፫፡ ፭፡ ፯)።
ጦመ ፈቃድ፡ የነቢያትና የሐዋርያት፡ የጽጌ ጦም።
ጦመኛ፡ (ኞች)፡ ባለጦም፡ ጦም ወዳድ፡ ጧሚ፡ ውሎ ውሎ የሚበላ፡ ሥጋና ቅቤ የማይቀምስ። (ተረት)፡ "ከመረቁ አውጡልኝ፡ ከሥጋው ጦመኛ ነኝ። "
"ሰይጣን ጦመኛ ሲኾን ዘላለም ሰይጣን ነው። "
ጦሚት፡ (ጠወመ)፡ የታናሽ ዛፍ ስም፡ ዕንጨቱን ቀልሰው፡ አጕብጠው፡ ሙጭ የሚያደርጉት የጣዕማ ዐይነት።
ጦም፡ (ሞች)፡ ጾም)፡ የጽድቅ ልጓም፡ ጊዜ ሳይደርስ እንዳይበላ፡ እንዳይጠጣ የሚከለክል ሕግ፡ በቅዱስ መጽሐፍ የታዘዘ፡ የጸሎት ወንድም። (ተረት)፡ "ከነገሩ ጦም ዕደሩ። "
ጦም አረዠን፡ የገብስ ስም፡ ወደ ጥቍረት የሚያደላ ገብስ። ትርጓሜው "ጦም አራዠን" ማለት ይመስላል።
ጦም ዐዳሪ፡ ምንም የሌለው ምስኪን።
ጦም የሚባሉ ፯ ናቸው። የሐዋርያት ጦም፡ ዐርብ፡ ሮብ፡ ፍልሰታ፡ የነቢያት ጦም፡ የልደትና የጥምቀት ገሃድ፡ ነነዌ፡ ሑዳዴ። የቀድሞ ተዋሕዶዎች ግን ስለ ፍልሰታና ብሥራተ ገብርኤል ባርብ ሮብ ሥጋ ይበላሉ፡ ስለ ጰራቅሊጦስም ስምንት ቀን ፋሲካ ያደርጉ ነበር ይባላል።
ጦሰኛ፡ (ኞች)፡ ባለጦስ፡ ርተኛ፡ ሰበበኛ።
ጦሳ፡ ዘዋሪ፡ ዕርፊተ ቢስ። ጣቢን እይ።
ጦስ፡ (ፀወሰ። ዕብ፡ ጣሽ፡ ተወ)፡ በያይነቱ ውጥንቅጥ፡ እኸል፡ ቅቤም ሳይቀር፡ ደንቃራ፡ ማርት፡ በበሽተኛ ላይ አዙረው በመንገድ የሚጥሉት፡ የሚተዉት፡ ደዌን ከታመመው ወዳልታመመው ማስተላለፊያ፡ የረገጠው ልምሾ (ሽባ) ይኾናል። በጕራጌ አገር ግን ፉጋ የሚባል ነገድ ተቀብሎ ወስዶ ይበላዋል።
ጦስ፡ ሰበብ፡ መዘዝ፡ ምክንያት።
ጦስራኤል፡ የቀበሌ ስም፡ በላይ ወግዳ በስተምሥራቅ ያለ አፋፍና ገደል፡ የእስራኤል መዘዝ ማለት ይመስላል። ጕዲትን እይ።
ጦስኝ፡ (ጥስን)፡ የቅጠል ስም፡ ዐጪ የሚጣፍጥ፡ ለወጥ ቅመም የሚኾን። ሕፃናትንም ትክትክ በያዛቸው ጊዜ እናቶቻቸው ከወተት ጋራ አፍልተው ያጠጧቸዋል።
ጦስኝ፡ ንጋት። ጤት:የፊደል ስም፡ ጠ፡ በርና ቀጪን የሐረግ ዐይነት ቅጠል፡ በዋና ደጋና በወይናደጋ የሚበቅል፡ ሽታው የሚጥም፡ የጠ፡ ዲቃላ፡ የጸፀ፡ ወራሽ፡ ወይም፡
ተለዋዋጭ።
(ማስረጃ)፡ ጠመቀ ጨመቀ፡ ጸቈነ፡ ጨቈነ፡ ጸረረ፡ ጠረረ፡ ወረረ፡
ጸርሰ ጨረሰ። አንዳንድ ጊዜም የቀ፡ ወራሽ ኹኖ ይገኛል። ቂርቆስ፡ ጨርቆስ፡ ቃቂል፡ ቃጭል፡ እንቃቅላ፡
እንጭላ።
ጦረ፡ (ጾረ)፡ ዐዘለ፡ ተሸከመ፡ ቻለ፡ ዐገዘ፡ ረዳ፡ አገለገለ፡
ያዘ።
ጦረ፡ ተሸከመ ፣ ፣ ጠወረ።
ጦረኛ (ኞች)፡ ሐርበኛ፡ ዠግና፡ የጦር ገበሬ፡ የጦር ዐቅድ ዐዋቂ (፩ሳሙ፡ ፲፯፡ ፴፫፡ ሕዝ፴፱፡ ፳)።
ጦር (ሮች)፡ (ጾር፡ ኲናት)፡ በሶማያ ላይ የተዋደደ፡ በጐንና በጐን ስለት፡ በስተጫፍ ሹለት ያለው፡ በትከሻ ላይ የሚያዝ፡ አበታ፡ ኦፎቄ፡ ዘገር፡ ጣምራ፡ ሠላጢን፡
ጭሬ፡ የቦ
(ዮሐ፲፰፡ ፫)። (ግጥም)፡ "ጦር ይቅር ይላሉ፡ ጦር እንዴት ይቅር፡ ለለመደው ሰው ይላል ቅር ቅር። "
ጦር (ን) ደፋ፡ ዘቀዘቀ፡ ጀንፎን ወደ ላይ፡ አፍሬን ወደ ታች አደረገ።
ጦር፡ (ንዋየ፡ ሐቅል)፡ የጦር መሣሪያ፡ የበዳ፡ ጸብት፡ ፍላጻ፡ በሎታ፡ ወንጭፍ፡
ጐመድ፡ ሰይፍ፡ ጠመንዣ፡ ሽጕጥ፡ መትረየስ፡ ታንክ፡ አይሮፕላን፡ ቦምብ፡ የመሰለው ኹሉ። መምህራን ግን "ጾር" ይሉታል። ደረቀ ብለኸ ደረቅን ተመልከት። ደበቀን ዐፈለን ሁለተኛውን ሻረ እይ። (ተረት)፡ "ሞት ሲደርስ ቄስ፡ ጦር ሲደርስ ፈረስ። "
ጦር፡ (ፍትወት)፡ ሥጋዊ ፈቃድ፡ ማንኛውም ፍላጎት፡ በባሕታዊና በመነኵሴ ላይ የሚነሣ ምኞት፡ ያሳብ፡ ትግል። ጦር የተባለውም በውስጠ ምስጢር እስኪት ነው። ጾርን አስተውል።
ጦር መሪ፡ አበ ጋዝ፡ ፊታውራሪ፡ አዝማች።
ጦር ማቋሚያ፡ አባት ለልጁ በተላይ የሰጠው መሬት።
ጦር ሠራ፡ ክተት አለ፡ አዘጋጀ።
ጦር ሠራ): ሰራዊት ሰበሰበ፣ አሰለፈ።
ጦር ተፈታ፡ ተሸነፈ፡ ድል ሆነ።
ጦር ነቀለ፡ በጦር መዠመሪያ ቈሰለ። "ልጅ ካሳ (መይሳ) ከደጃች ብሩ ጐሹ ጋራ ዘመቱና አንድ ጦር ነቅለው ገቡ" (ታሪ ቴዎ)።
ጦር ነቀለ፡ የተወረወረ ጦርን በጋሻው መለሰ።
ጦር ነቀለ፡ ጦርን አነሣ፡ ያዘ።
ጦር ነቀል፡ ጦር መላሽ፡ ዐፍለኛ፡ ጐበዝ፡ ያባቱን ጦር ያነሣ።
ጦር፡ የንጨት እሾኸ፡ የንስሳ ቀንድ፡ የንብ፡ የተርብ፡ የናዜራ፡ የባብ፡
የጊንጥ መርዝ።
ጦር ጠማሽ፡ ውጊያ፡ ዘመቻ፡ ግዳይ ፈላጊ፡ ወያኔ፡ ፋኖ።
ጦር፡ ጭፍራ፡ ሰራዊት፡ ወታደር፡ ነፍጠኛ፡ ዘማች፡
ጋሻ ጦር የያዘ። "የእግር ጦር" "ጦር መጣ" እንዲሉ።
ጦሽ አለ፡ (ዕብ፡ ጣሽ፡ በረረ)፡ ጮኸ፡ ድምጥ ሰጠ፡ እሳት የገባ ዕንጨት፡ ተበተነ፡ የፍም።
ጦቢት፡ ደግ፡ ጻድቅ፡ የሚያምር ማለት ነው።
ጦቢያ (ኢትዮጵያ)፡ ጦቢያ የሕዝብ፣ ኢትዮጵያ የካህናት አነጋገር ነው። በጦብያና በጦቢት ዘይቤ ቢፈቱት ግን "ማለፊያ መልከ መልካም" ማለት ይሆናል (ማሕ፩፡ ፭፡ ፮)።
ጦቢያ፡ ቅንቦ፡ ወተታም ዕንጨት፡ ወተቱ ለመጋኛና ለቁርባ መድኃኒት ይሆናል፡ የቆላ፣ የበረሃ ማለት ነው። ከፍሬው ጋራ ነጭ ሐር የሚመስል ጥጥ ይገኛል።
ጦቢያው ሰገድ፡ የሴት ስም፡ ይኸውም ማክዳን ያያል።
ጦቢያው ሰገድ፡ ጦቢያው የሰገደላት እመቤታችን ድንግል ማርያም::
ጦቢያው፡ የሰው ከፊል ነው። የጦቢያ ሰው ያሰኛል።
ጦነጦነ)፡ አጦነጦነ፡ አስቸኰለ፡ ዕረፍት አሳጣ።
ጦና፡ የወላሞ ባላባት ስም።
ጦንጧና፡ ችኵል፡ ዕርፊተ ቢስ፡ ጦልጧላ።
ጦዘ፡ (ፀዊስ፡ ፆሰ)፡ ተጠመዘዘ፡ ከረረ፡ ደሰነ። (ዞጠ)ን አስተውል።
ጦዘጦዘ)፡ ጦዘ፡ አንጦዘጦዘ፡ አንከወከወ።
ጦዘጦዝ፡ ጦዝጧዛ፡ የተንጦዘጦዘ፡ ከውካዋ፡ የማይሞላለት።
ጦጢት፡ እንስት ጦጣ።
ጦጣ (ጦች)፡ እንደ ዥንጀሮ ሰው የሚመስል፡ የዱር አውሬ፡ እዛፍ ላይ የሚያድር፡ ፊተ ነጭ፡ አቦልሴ። ከብልጠቱ የተነሣ ጦጣ ጠይብ ነው ይባላል። (ተረት)፡ "ጦጣ ባለቤትን ታሶጣ። "
"ሲወጡ፣ እንደ፣ ጦጣ፡ ሲወርዱ፡ ዐሳር መጣ። " ሸመጠጠ ብለኸ ሽምጠጣን ተመልከት።
ጦጤ፡ ከነጭ ማሽላ ቂጣ የተዘጋጀ፡ ጠላ ንጣት ያለው።
ጦጤ፡ የገብስ ስም፡ እንደ ጦጣ ነጭነትና ኣቦልሴነት ያለው ገብስ።
ጦጥልሽ፡ በጐዣም ክፍል በመተከል ውስጥ ያለ ቀበሌ።
ጦፈ፡ (ዕብ፡ ጻፍ፡ ፈሰሰ፡ ተንጠባጠበ)፡ ቀለጠ፡ ጧፍ ሆነ፡ ነደደ፡ ተቃጠለ፡ ተንቀለቀለ።
ጦፈ፡ አበደ፡ ተማረ።
ጧ አለ፡ (ዕብ፡ ጻዋሕ)፡ ወደቀ፡ ተኛ፡ ተዘረረ፡ ተዘረጋ፡ ዟ አለ።
ጧ አለ፡ ተቀደደ፡ ተበጠሰ፡ ቷ አለ።
ጧ አለ፡ ተበጠሰ። (ጧጧ).
ጧ አለ፡ አለ ልክ ሣቀ።
ጧ አደረገ፡ መታ፡ በጠሰ።
ጧሚ፡ (ዎች)፣ ጸዋሚ)፡ የጦመ፡ የሚጦም።
ጧሪ፡ የጦረ፡ የሚጦር፡ ጠዋሪ፡ ዐጋዥ፡ ረዳት፡
ተሸካሚ፡ ቻይ።
ጧት፡ (ጽባሕ)፡ ማለዳ፡ ወፍ ሲጮኽ፡ ከንጋት እስከ ፀሐይ መውጣት ያለ ጊዜ። አማርኛን አስተካክለው የማያውቁ ሰዎች ግን "ጠዋት" "ጥዋት" እያሉ ይጽፋሉ።
ጧት፡ (ጽባሕ)፡ ማለዳ፡ ወፍ ሲጮኽ፡ ከንጋት እስከ ፀሐይ መውጣት ያለ ጊዜ። አማርኛን አስተካክለው የማያውቁ ሰዎች ግን "ጠዋት" "ጥዋት" እያሉ ይጽፋሉ።
ጧት ንጋት፣ ጠባ፡ (ጸብሐ)።
ጧጧ)፡ አንጧጧ፣ አንጣጣ፣ ተንጧጧ፣ ተንጣጣ።
ጧፍ፡ (ፎች)፡ በሠም የተነከረ የሸማ መብራት፡ ፋና፡ እየቀለጠ የሚነድ። ጧፍ ዕጣን እንዲሉ።
ጧፍ፣ የሠም መብራት፣ ጦፈ።
No comments:
Post a Comment