ሀ ለ ሐ መ ሠ ረ ሰ ሸ ቀ በ ተ ቸ ኀ ነ ኘ አ ከ ኸ ወ ዐ ዘ ዠ የ ደ ጀ ገ ጠ ጨ ጰ ጸ ፀ ፈ ፐ
ጸ፡ ፲፰ኛ፡ ፊደል፡ በግእዝ፡ አልፍ፡
ቤት፡ በአበገደ፡ ተራ፡ ቍጥር። በአኃዝነት፡
ጸ፺፡ በፊደልነት፡ ጸደይ፡ ይባላል።
ጸ፡ የሰ፡ ተወራራሽ። ምሳሌ: ጸጥ፡ ሰጥ። ጠና፡ ጨን፡ እይ።
ጸሐፈ)፡ ጣፈ፡ ጸፈ።
ጸሓፊ፡ ጣፊ፡ ጻፊ።
ጸሓፌ፡ ትእዝ፡ የማዕርግ፡ ስም፡ የንጉሥ፡ ትእዛዝ፡ ጻፊ፡
ማኅተም፡ ያዥ።
ጸለለ፡ ጋረደ፡ ጠለለ።
ጸለል፡ አለ፡ ተንጣለለ፡ ጠለለ።
ጸለመ፡ ጠቈረ፡ ጠለመ።
ጸሎት፡ ልመና፡ ጸለየ።
ጸረቀ): ዐለቀ፡ ሣሣ።
ጸረበ፡ ዕንጨትን፡ ሸለተ፡ ጠረበ።
ጸረገ፡ አድፍን፡ ጕድፍን፡ አስገለለ። ጠረገን፡ ተመልከት።
ጸረፈ፡ ሰደበ፡ ፀረፈ።
ጸራ: ቀጠነ፣ በሳ፣ አደረቀ።
ጸር፡ ጠላት። ጸር፡ ጸረረ።
ጸርቀለም (ጽሩይ፡ ቀለም)፡ መዳብ፡ የመዳብ፡ ስም። ጠርቀለም፡ ቀይ፡ ቀለም፡ የሚመስል፡ ብረት።
ጸርከል፡ በጋር፡ ክብ፡ መንደፊያ፡ መበገሪያ፡ መንታ፡
ብረት። ጸርከል፡ በፈረንጅኛ፡ ሰርክል፡ ይባላል፡ ሲጋርን፡
እንጂ፡ መበገሪያን፡ እያሳይም።
ጸበረቀ) ጸብረቀ)፡ አንጸባረቀ፡ (አንጸብረቀ)፡ ኣበራ፡ አብረቀረቀ፡ እብለጭለጨ፡ ማየት፡
ከለከለ፡ ውሃው፡ ብረቱ፡ መስተዋቱ፡ ብርሃኑ፡ (ዘፀ፴፬ - ፴ ፣ ፴፭)።
ጸበበ፡ ጠባብ፡ ኾነ፡ ጠበበ።
ጸበተ (ጸቢት፡ ጸበተ)፡ ዋኘ፡ በባሕር፡ ውስጥ፡ ሰለከ።
ጸባቲ፡ የጸበተ፡ የሚጸብት፡ ዋነተኛ፡ ቋትለኛ።
ጸባቴ፡ ዝኒ፡ ከማሁ፡ የደብረ፡ ሊባኖስ፡ ዳኛ፡
የገዳሙንና፡ ያገር፡ ግዛቱን፡ አስተዳደር፡ ባሕር፡ የሚዋኝ፡ የሚሠራ፡ ባሕር፡ መዝገቡን፡ የሚይዝ፡ ማለት፡ ነው። ጸባቲ፡ ግእዝ፡ ጸባቴ፡ ዐማርኛ፡ ነጋዲ፡
ነጋዴ፡ ያለውን፡ ይመስላል።
ጸብ፡ ጥል፡ ጠብ።
ጸብታ፡ ዝኒ፡ ከማሁ፡ ፃግታን፡ ተመልከት።
ጸብት (ጸብአ)፡ የጦር፡ መሣሪያ። ምሳሌ: የበዳ፡ ጸብት፡ እንዲሉ።
ጸነነ (ጸኒን፡ ጸነ)፡ ዘነበለ፡ ጋደለ።
ጸና (ጸንዐ)፡ ጠና፡ በረታ። ጸና፡ የካህናት፡ ጠና፡ የሕዝብ፡ ነው።
ጸናጽል (ጸንጸል)፡ የማሕሌት፡ መሣሪያ፡ (ግእዝ)።
ጸናጽሎች (ጸናጽል፡ ላጥ)፡ ኹለትና፡ ከኹለት፡ በላይ፡ ያሉ።
ጸዐዳ፡ የጸዳ፡ ነጭ፡ ጥሩ፡ (ግእዝ)።
ጸየፈ (ጸይፎ ጸየፈ): ኰለተፈ፣ ኰልታፋ ኾነ፡ ለነበደ፣ ለፈደደ።
ጸየፈ: ተቈለፈ፣ ታሰረ፣ በትክክል መናገር አቃተው (የአንደበት ችግር)።
ጸደለ (ጸዲል፡ ጸደለ)፡ በራ፡ ሸበረቀ።
ጸደቀ (ጸድቀ፡ ረታ)፡ አውነተኛ፡ ኾነ፡ ከሐሰት፡ ከኀጢአት፡ ተለየ፡
ከዚህ፡ የተነሣ፡ ገነት፡ መንግሥተ፡ ሰማይ፡ ገባ፡ ከኵነኔ፡ ራቀ፡ በነፍስ፡ ተጠቀመ፡ በመንፈሳዊ፡ ክብር፡ ከበረ። ጠደቀን፡ አስተውል። ዳግመኛም፡ የጸደቀ፡ ምስጢር፡ ታድሶ፡ ረቆ፡
የሰውን፡ ከመቃብር፡ መውጣት፡ ያሳያል። (ተረት)፡ እጸድቅ፡ ያለ፡ መንኵሶ፡ እካስ፡ ያለ፡
ታግሦ። እጸድቅ፡ ብዬ፡ ባዝላት፡ ተንጠልጥላ፡ ቀረች።
ጸደቀ፡ ሥር፡ ሰደደ፡ ለማ፡ ለመለመ፡ አፈጠፈጠ፡
አቈጠቈጠ፡ ቅጠል፡ አወጣ፡ ከመድረቅ፡ ራቀ፡ የተክል፡ የዛፍ።
ጸደት፡ የአሞራ፡ ስም።
ጸደፈ (ጸድፈ)፡ ተንከባለለ፡ ገደል፡ ገባ። ጠደፈን፡ እይ።
ጸዳ፡ ጠዳ።
ጸዳል፡ ብርሃን፡ ጮራ፡ ጨረር።
ጸዳቂ፡ የጸደቀ፡ የሚጸድቅ፡ የለመለመ፡ የሚለመልም። ጸዳቂውንና፡ ተኰናኙን፡ የሚያውቅ፡ ፈጣሪ፡ ብቻ፡ ነው።
ጸዴ፡ የፊደል፡ ስም፡ ጸ።
ጸጅ፡ ጠጅ።
ጸገበ፡ ሆዱ፡ መላ፡ ጠገበ።
ጸገዴ (ጠገዴ)፡ በስሜን፡ አውራጃ፡ ውስጥ፡ ያለ፡ አገር፡
ሕዝቡ፡ ዐማርኛ፡ የሚናገር።
ጸጋ (ጸገወ)፡ ስጦታ፡ ሀብት።
ጸጋ፡ የሃይማኖት፡ ስም፡ ጌታችን፡ በአምላክነቱ፡
ጸጋን፡ ይሰጣል፡ በሰውነቱ፡ ከኛ፡ ጋራ፡ ይቀበላል፡ ብሎ፡ የሚያስተምር፡ ሃይማኖት።
ጸጎች፡ የጸጋ፡ ልጆች፡ የተክለ፡ ሃይማኖት፡ ቤተ፡
ሰቦች።
ጸጥ (ግእዝ)፡ መርጋት፡ ማረፍ፡ መቆም፡ መጨመት። ሰጥን፡ አስተውል።
ጸጥ፡ በል፡ ርጋ፡ ረፍ።
ጸጥ፡ አለ፡ ረጋ፡ ቆመ፡ ጨመተ፡ ሰጥ፡ አለ፡ ዐረፈ።
ጸጥ፡ አደረገ፡ አረጋ፡ አቆመ፡ አሳረፈ።
ጸጥተኛ (ኞች)፡ ህዱኣዊ፡ የረጋ፡ ጭምት፡ ዝምተኛ፡ ጸጥታ፡
ወዳድ።
ጸጥታ፡ ርጋታ፡ ዝምታ፡ ጸጥ፡ ማለት።
ጸጸተ፡ ቈጨ፡ አሳዘነ። ጠጠተን፡ አስተውል።
ጸጸት፡ ጠጠት፡ ቍጭት፡ ንስሓ።
ጸጸይ፡ ዝኒ፡ ከማሁ፡ የዘር፡ ወራት፡ ማለት፡ ነው።
ጸፋ (ጸፍዐ፡ ጠፍሐ)፡ ጕንጭን፡ ከበሮን፡ በውስጥ፡ እጅ፡ መታ፡
አጨበጨበ፡ (ኢሳይያስ ፶፡ ፮፡ ሰቆቃው፡ ኤርምያስ ፫፡ ፴)።
ጸፋ፡ በጸናጽልና፡ በከበሮ፡ በጭብጨባ፡ ሰላምን፡
አዜመ፡ ሌላውንም።
ጸፍጸፍ (ጸፍጸፈ)፡ ጥፍጣፍ፡ የደንጊያ፡ የንጨት፡ ንጣፍ፡ (ሕዝቅኤል ፵፩፡ ፳፭፡ ፵፪፡ ፫)። ጠፈጠፈን፡ እይ።
ጻሕል፡ ዝርግ፡ ሳሕን፡ ወጭት፡ ከወርቅ፡ ከብር፡
ከመዳብ፡ ከንሓስ፡ የተበጀ፡ ዕቃ፡ (ንዋየ፡
ቅድሳት)፡ የቅዱስ፡ ቍርባን፡ መቀመጫ።
ጻማ (ጻመወ)፡ ድካም፡ ልፋት።
ጻማ፡ ገንዘብ (ገንዘበ፡ ጻማ)፡ የድካም፡ ገንዘብ፡ ወጥቶ፡ ወርዶ፡ ዐርሶ፡
ነግዶ፡ ጽፎ፡ ደጕሶ፡ ወዝን፡ አፍስሶ፡ የተገኘ፡ ገንዘብ። በግእዝ፡
ንዋየ፡ ጻማ፡ ይባላል፡ ባላገሮችም፡ ጣማ፡ ገንዘብ፡ ይሉታልና፡ ጣማን፡ እይ።
ጻድቁ፡ አቡነ፡ ገብረ፡ መንፈስ፡ ቅዱስ፡ ሠነጠቀን፡
እይ።
ጻድቅ (ቃን)፡ ደግ፡ ቅን፡ ገር፡ የዋህ፡ እውነተኛ፡ ሰው፡
ምግባሩ፡ የቀና፡ ሃይማኖቱ፡ የጸና፡ የገንዘብ፡ ወገን፡ ለነፍሱ፡ ያደረ። ጻድቁ፡ ያ፡ ጻድቅ።
ጻጻፈ፡ መላልሶ፡ ጻፈ፡ ማጫረ።
ጻፈ (ጸሐፈ)፡ ቃልን፡ ነገርን፡ በቀለም፡ ገለጠ፡ በብራና፡
በወረቀት፡ ውስጥ፡ አኖረ፡ ረ፡ ቀዳ፡ ገለበጠ፡ ጽፈትን፡ በእንጨት፡ በድንጊያ፡ በብረት፡ ላይ፡ ቀረጸ፡ ዐተመ። ጣፈን፡ ከተበን፡ ተመልከት።
ጻፊ (ፎች)፡ የጻፈ፡ የሚጽፍ፡ ጣፊ፡ ከታቢ።
ጻፊነት፡ ጻፊ፡ መኾን።
ጽሕማ፡ ከተስዐቱ፡ ቅዱሳን፡ አንዱ፡ ጢማም፡ ማለት፡
ነው።
ጽሕም፡ ጢም፡ ሪዝ።
ጽሕፈት፡ ጥፈት፡ ጽፈት።
ጽላልሽ (ጽላልኪ)፡ የቀድሞ፡ የቡልጋ፡ ስም።
ጽላተ፡ ሙሴ፡ እግዜር፡ ለሙሴ፡ የሰጠው፡ ወይም፡ ሙሴ፡
የቀረጸው፡ ጽላት፡ ፊተኛውና፡ ኋለኛው።
ጽላተ ኦሪት: የኦሪት ጽላት። ኦሪት በጽላቱ ላይ ያለው ጽሑፍ ነው፡ ወይም መላው ብሉይ።
ጽላተ፡ ኪዳን፡ ዝኒ፡ ከማሁ፡ የውል፡ የመሐላ፡ የሕግ፡
ጽላት።
ጽላት፡ ታቦት፡ ጸለየ።
ጽላት: (የቃል ኪዳን ጽላት ማለት አስሩ ትእዛዝ) የተጻፈበት ታቦት በሚባል ሣጥን የሚከተት ኹለት ገበታ፡ በግእዝ አንዱ ጽሌ ኹለቱ ጽላት ይባላል፡ ትርጓሜው መጸለያ ጸሎት ማቅረቢያ ማለት ነው። ይኸውም በምርኮ ጊዜ ነቢዩ ኤርምያስ ቀብሮት በሚጠት ለካህኑ ዮሴዕ በታምራት ተገለጠ ይባላል።
ጽላት: ክርስቲያኖች በቅድስት ሥላሴ፣ በማርያም፣ በመላእክት፣ በነቢያት፣ በሐዋርያት፣ በጻድቃን፣ በሰማዕታት፣ በደናግል፣ በመነኮሳት ስም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመንበር ላይ የሚያኖሩት ጠፍጣፋ ፬ ማእዘን የእንጨት ሰሌዳ። ኹለተኛ ስሙ ታቦት ይባላል፡ "ታቦትን" እይ።
ጽልመት (ጸልመ)፡ ጨለማ፡ ጥልመት፡ ጥቍረት።
ጽራሐ መስቀል፡ ጌታችን፡ በመስቀል፡ ላይ፡ የጮኸው፡ ጩኸት፡
ኤሎሄ፡ ኤሎሄ።
ጽራሕ (ጸርሐ)፡ ጩኸት፡ ዳግመኛም፡ ጩኸ፡ ተብሎ፡ ይተረጐማል።
ጽራእ፡ የቀበሌ፡ ስም፡ በትግሬ፡ አብርሀ፡ አጽብሐ፡
አጠገብ፡ ያለ፡ ሖመር፡ የሚበቅልበት፡ ስፍራ።
ጽራግ፡ ማሰሬ (መአስረ፡ ጽራግ)፡ በንጉሥ፡ ዐንገት፡ ላይ፡ ጽራግን፡ የሚያስር፡
ባለ ትልቅ፡ ማዕርግ፡ የቤተ፡ ክህነትና፡ የቤተ፡
መንግሥት፡ ሹም፡ ካህን፡ መኰንን። ጃንን፡
አስተውል።
ጽራግ፡ ጥራግ፡ የንጉሥ፡ ዐንገት፡ ጌጥ፡ መጥረግ፡
መጠረግ፡ መጽዳት፡ የሚስማማው።
ጽርሐ፡ አርያም፡ በአርያም፡ ያለ፡ የብርሃን፡ አዳራሽ። አርያምን፡ ተመልከት።
ጽርሐ፡ ጽዮን፡ የጽዮን፡ አዳራሽ፡ መንፈስ፡ ቅዱስ፡ ለሐዋርያት፡
የወረደበት።
ጽርሕ (ግእዝ)፡ አዳራሽ፡ ቤተ፡ ንጉሥ።
ጽርእ፡ የግሪክ፡ አገርና፡ ቋንቋ።
ጽርኦች (ጽርኣውያን)፡ የጽርእ፡ ተወላጆች፡ ግሪኮች።
ጽነት፡ ዝንባሌ፡ የክፉ።
ጽኑ (ጽኑዕ)፡ የጸና፡ ጥኑ።
ጽና (ጽናዕ)፡ ጥና፡ ጨክን፡ በርታ፡ ቻል፡ ታገሥ።
ጽና (ጽንሓሕ)፡ ጥና፡ የዕጣን፡ ማጨሻ፡ ማጠኛ፡ ባለ፳፬፡
ሻኵራ፡ ሲበዛ፡ ጽኖች፡ ይላል፡ (ዘኍልቍ ፲፮፡ ፲፯)።
ጽዕዱት (ጽዕድ)፡ የጸዳች፡ የተጣደች፡ የቤተ፡ ልሔም፡ ምጽዓድ። ጠዳን፡ አስተውል።
ጽዋ (ዎች) (ጽዋዕ)፡ ከሸክላ፡ ከማዕድን፡ የተሠራ፡ ዕቃ። ጥዋን፡ እይ።
ጽዮን (ጸወን): በኢየሩሳሌም የዳዊት ዐምባ ከተማ፡ የሙሴ ታቦት በድንኳን የነበረችበት (፪ዜና ፭፡ ፪)። "ታቦተ ጽዮን" እንዲሉ። ጋሻ፣ መከታ፣ መጠጊያ፣ መማጠኛ፣ መደወያ ማለት ነው።
ጽዮን ማርያም: የጽዮን ማርያም።
ጽዮን: በትግሬ ያለ የአኵስም ዐምባ።
ጽዮን: በአብርሀ ዐምባ በአኵስም ቤተ ክርስቲያን ያለች የመቤታችን ታቦት ኅዳር ፳፩ ቀን የምትነግሥ። ከሣቴ ብርሃን ሰላማ ከሚካኤል ታቦት ጋራ ከቅዱስ አትናቴዎስ ተቀብሎ ያመጣት። ታቦቷን ጽዮን ማለት ኀዳሪ በማኅደር ነው፡ "አኵስም ጽዮን" እንዲሉ። "ታቦትን" እይ። ያትናቴዎስ መኾኗንም ባ፬ኛው ዮሐንስ ጊዜ ኹለት የአርመን መነኮሳት ያነሡት ፎቶ ግራጁ (ሥዕሏ) ይመሰክራል። ክብረ ነገሥት ግን በቀዳማዊ ምኒልክ ዘመን ከኢየሩሳሌም በሌዋውያን እጅ ወደ ኢትዮጵያ የመጣች ጽላተ ሙሴ ነች ይላል።
ጽዱ፡ የጸዳ፡ ጥዱ።
ጽዳት፡ ጥዳት። ጸዳ፡ የካህናት፡ ጠዳ፡ የሕዝብ፡ ነው።
ጽድቅ፡ ለደግ፡ ሰው፡ የሚሰጥ፡ የውነት፡ ሥራ፡
ዋጋ፡ ወይም፡ ክብር። በግእዝ፡
ግን፡ እውነት፡ ማለት፡ ነው። መነኰሰ፡
ብለኸ፡ መንኳሽን፡ ተመልከት።
ጽድቅና፡ ኵነኔ፡ ክብርና፡ ቅጣት፡ ጥቅምና፡ ጕዳት።
ጽጉብ፡ የጠገበ፡ ጥጉብ።
ጽጌ (ጸገየ)፡ አበባ፡ በያይነቱ።
ጽጌ፡ ረዳ፡ ከእሾኻም፡ ዕንጨት፡ ከረዳ፡ የሚገኝ፡ ነጭ፡
አበባ፡ ሽታው፡ ልብ፡ የሚመሥጥ። ረዳን፡
እይ።
ጽጌ፡ የሴት፡ ግዳጅ፡ (ትክቶ)።
ጽፈት (ጽሕፈት)፡ ጥፈት፡ ክታብ፡ በቀለም፡ ተገልጦ፡ የሚታይ፡
ቃል፡ ነገር።
ጽፋት (ጽፍዐት፡ ጥፍሐት)፡ መጽፋት፡ መጸፋት፡ በጥፊ፡ መምታት፡ መመታት፡
ዜማ፡ ጭብጨባ፡ ቸብቸቦ፡ ዐቢይና፡ ንኡስ።
ጾመ (ጸዊም፡ ጾመ)፡ እህል፡ ውሃ፡ ተወ፡ ጦመ፡ ለተወሰነ፡ ጊዜ።
ጾመ፡ ድጓ (ድጓ፡ ጾም)፡ በሑዳዴ፡ የሚባል፡ የጾም፡ ድጓ።
ጾም፡ በቁሙ፡ ጦም።
ጾረ (ጸዊር፡ ጾረ)፡ ተሸከመ፡ ያዘ። ጦረን፡ እይ።
ጾር፡ ሸክም፡ (ግእዝ)።
ጾር፡ በቁሙ፡ ጦር፡ በትከሻ፡ የሚሸከት፡ (ዐማርኛ)።
ጾር፡ ፍትወት፡ ሥጋዊ፡ ፈተና፡ ሴትን፡ መፈለግ። ምሳሌ: ባሕታዊው፡ ጾር፡ ተነሣበት፡ ይህ፡
አነጋገር፡ እስኪትን፡ ያመለክታል።
ጾታ፡ ወገን፡ ነገድ፡ ጓዝ፡ (ግእዝ)።
ጿሚ (ጸዋሚ)፡ ጧሚ። ጽንፍ፡ ዳር፡ (ግእዝ)። ጥንፍን፡ እይ።
No comments:
Post a Comment