Friday, June 6, 2025

- ፭ኛ ፊደል፡ በግእዝ አልፍ ቤት፡ በአበገደ። ስሙ፡ ሆይ፤ ጻፎች፡ ግን፡ ሃሌታ፡ ሀ' ይሉታል። ቍጥር፡ ሲኾን፡ ሀ—፭፡ ይባላል።

አለ ፊደል፡ ቈጠረ፡ ተማረ። (ተረት)፤ ሀ፡ ባሉ፡ ተዝካር፡ በሉ። ሀ፡ ብሎ፡ ፊደል፡ መዠመር፡ በከሣቴ፡ ብርሃን፡ ሰላማ፡ ጊዜ፡ መኾኑን፡ መዝገበ፡ ፊደል፡ እይ። ሥነ፡ ፍጥረትን፡ ቋንቋን፣ ፊደልን፡ ታሪክን፡ የሚመረምሩ፡ ያውሮጳ፡ ሊቃውንት፡ ግን፡ አንሲክሎፔዲ፡ በሚባል፡ መጽሐፋቸው፡ የግእዝን፡ ፊደል፡ በጥንታዊ፡ ተራው፡ አበገደ፡ ብለው፡ ከዓለም፡ ፊደል፡ ጋራ፡ ጽፈውት፡ ይገኛል። አንዳንድ፡ ሰዎች፡ ግን፡ መሠረተ፡ ቢስ፡ ሐሳባቸውን፡ ለማጽደቅ፤ ሰላማ፡ ከሣቴ፡ ብርሃን፡ ሀለሐመ፡ ብሎ፡ የዠመረበትን፡ ምክንያት፡ ጠይቀው፡ ሳያውቁ፡ ሳይረዱ፤ አበገደ፡ የውጭ፡ አገር፡ ሰዎች፡ ፊደል፡ ነው፡ ይላሉ።

ባይ: የሚያናፋ፣ አናፊ፣ ጯኺ አህያ። (ተማሪዎች "ትላንት የበላናት ሲሳይ፡ ባይ፤ ዐመድ ላይ ተንከባላይ፤ ዳውላን ዐዛይ" እንዲሉ)

አለ (ነቀወ): አናፋ፣ ጮኸ።

አለ: ፊደል ቆጠረ፣ ተማረ። ("አን" ይመልከቱ)

ሀሀ: የአህያ ጩኸት ወይም ማናፋት።

ሀሁ: ፊደል ቆጠራ፣ "አኡ"

ሃሌ ሉያ: አመስግኑ እግዜር። በተገናኘ መልኩ እግዜርን አመስግኑ ማለት ነው። በግእዝ "ሰብሕዎ ለእግዚአብሔር" ወይም "ግነዩ ለእግዚአብሔር" ይባላል።

ሃሌ ከመዙ ሃሌ: የጥንት ባልቴቶች ዘፈን አዝማች። "ሃሌ ከመዙ ምቀኛኸ ብዙ" እንዲሉ።

ሃሌ: ምስጋና፣ የምስጋና ቃል፣ የዋዜማና የዕዝል፣ የአቡንና የአንገርጋሪ፣ የአርያም፣ የሰላም ዜማ መነሻና መጀመሪያ። በአርባዕትና በሠለስት፣ በሌላውም ዜማ አልፎ አልፎ የሚገኝ ነው። "ጠጅ በብርሌ፤ ዜማ በሃሌ" እንዲሉ።

ሃሌታ: ከሃሌ ጋር ተመሳሳይ። ሃሌታ የአማርኛ ሲሆን ሃሌ የግእዝ ነው። "" ምዕላድ ሆኖ ተጨምሯል። የአንቀጽ ሃሌታ እንዲሉ። ሃሌታ ማለትም ሃሌ ማለት ነው።

ሀሎ: ጠንካራ የቈላ ግራር፣ በሐረርጌ በረሓ የሚበቅል፣ ምሥጥ የማይደፍረው፣ ዐፈር የማይበላው፣ ከሰል የሚሆን። የሀላዌውን ጥናትና ጥንካሬ፣ ነዋሪነቱንና አለመንቀዙን ያሳያል። በሺዋ ደሬ በትግሬ እንደተሠራ ይባላል።

ሀሚና: ለፍላፊ።

ሀሚናሚና: የልጆች ዘፈን።

ሀብ ሀብ አለ (ሀበበ): አፌዘ፣ አላገጠ። "አይ በሉ በሉ ወዲያ ወዲያ" አለ።

ሀብተ ሚካኤል: የሚካኤል ስጦታ።

ሀብተ ማርያም: የማርያም ስጦታ። (በሕዝብ አማርኛ "አብተ ማርያም" ይባላል)

ሀብተ ሥላሴ: የሥላሴ ስጦታ። (በሕዝብ አማርኛ "አብተ ሥላሴ" ይባላል)

ሀብተ ስንኩል: ሀብቱ የተሰነከለ፣ አግኝቶና ከብሮ የማያውቅ፣ አገኝ ሲል የሚያጣ፣ የቂጣ ገመዱ የተበጠሰ።

ሀብተ ሥጋ: ኃላፊ ዕድል፣ በተጨማሪም ብልጽግና።

ሀብተ ቢስ: ዕድለ ቢስ፣ ድህነት እንጂ ሀብት የሌለው፣ ችግረኛ።

ሀብተ ነፍስ: ጽድቅ።

ሀብተ ወልድ: የወልድ ስጦታ።

ሀብተ ወልድና: የልጅነት ሀብት፣ የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ መንግሥተ ሰማይን መውረስ። ይህ ደግሞ በምግባር፣ በሃይማኖት፣ በጥምቀት፣ በቁርባን ነው።

ሀብተ ገብርኤል: የገብርኤል ስጦታ።

ሀብተ ጊዮርጊስ: የጊዮርጊስ ስጦታ።

ሀብቱ/ሀብቴ: ከፊለ ስም፣ ወይም "የእርሱ/የኔ ሀብት" ተብሎ ይተረጎማል። ባላገር ግን "አብቱ/አብቴ" ይላል።

ሀብታ: የሴት ስም፣ ያች ሀብታም።

ሀብታም (ሞች): ሀብት ያለው፣ ባለ ሀብት፣ ባለጠጋ፣ ከበርቴ። ለሴት ወይዘሮ፣ ለወንድ መኰንን ማለት ነው።

ሀብት (ወሀበ): ዕድል፣ ስጦታ፣ ብልጽግና፣ ጌትነት፣ እዱኛ። ባላገር ግን "ካብት" ይላል። ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ሀብትን "የተከማቸ ሥራ" ብለውታል። ሀብት ከእግዚአብሔር፣ ከመላእክት፣ ከሰማዕታት፣ ከጻድቃን፣ ከታቦት ስም ሁሉ እየተናበበ የክርስትና ስም ይሆናል።

ሀብትህ ይመር: (የወንድ መጠሪያ ስም) እደግ፣ ርባ፣ ሥባ፣ ግዛ፣ ንዳ፣ ተሾም፣ ተሸለም፣ ጌታ ሁን ማለት ነው። ባላገርም "ካብትህ ይመር" ይላል።

ሀብትሽ በሀብቴ: የጋብቻ ውል ሲሆን "የምናገኘው የጋራችን፣ በመካከላችን የግል የለም" ማለት ነው።

ሀብትሽ ይመር: ማለፊያ ባል ይምጣልሽ፣ እመቤት ሁኚ።

ሀብቷ ቀና (ልጃገረድ): ታጨች፣ ባል መጣላት።

ሀች: የአመት ቅጽል።

ሀኖስ: ከጠፈር በላይ ያለ ሲሶ ውሃ ብጥብጥ።

ሀካኪ: የሚያክ።

ሀኬተኛ (ኞች)/ሀካይ: ሰነፍ፣ ልግመኛ፣ ክፋተኛ።

ሀኬተኛነት: ሀኬተኛ መሆን፣ ልግመኛነት።

ሀኬት (ሀከየ): ስንፍና፣ ልግም፣ ክፋት።

ሀየል: በሁለት ቀንዶቹ ላይ ብዙ የቀንድ አጽቅ ያለው የዱር ፍየል፣ የዋሊያ ወገን። በስሜን ተራራ ይገኛል። ሀየል ግእዝኛ ነው።

ሀያጅ: መንገደኛ።

ሀይ አለ: ከለከለ።

ሀይ: የሆን የመሰለ የአርበኛ ዘፈን አዝማች። "ሀይ ሀይ ሎጋው ሽቦ" እንዲሉ።

ሃይማኖተ ቢስ: መናፍቅ፣ መጥፎ ሃይማኖት ያለው፣ በሁለት ቢላዋ የሚበላ።

ሃይማኖተ አበው: የመጽሐፍ ስም። አበው ማለት አባቶች፣ የአንጾኪያና የእስክንድርያ፣ የጽርእ ሊቃነ ጳጳሳት በየጊዜው የጻፉት የሃይማኖት ምእላድ ነው። ምስጢረ ሥላሴንና ምስጢረ ሥጋዌን አምልቶ አስፍቶ የሚናገር ሲሆን በቅዳሴ ጊዜ የሚነበብ መልእክት ነው።

ሃይማኖተ ጐደሎ: ኦሪትን አምኖ ወንጌልን ያላመነ።

ሃይማኖተኛ (ሃይማኖታዊ): ባለሃይማኖት፣ ሃይማኖቱ የጸና፣ ቁም ነገራም፣ የተናገረውን የማያስቀር፣ ባለማተብ።

ሃይማኖት (ሀይመነ): አሚን፣ ማመን፣ እምነት፣ አምልኮ። "ፋሲል ይንገሥ፤ ሃይማኖት ይመለስ" እንዳሉ ዐፄ ሱስንዮስ።

ሃይማኖት ያውርድ: የደግ ሰው ፈሊጥ፣ ዘዬ፣ ሰላምታ ሲሰጥ የሚናገረው። "እንዴት ዋላችሁ፤ ሃይማኖት ያውርድ" እንዲሉ። ያምጣ፣ ያብዛ፣ ያስፋ፣ ይጨምር ማለት ነው።

ሃይማኖቶች (ሃይማኖታት): የአይሁድ፣ የክርስቲያን፣ የእስላም፣ የቡዳ፣ የሌሎችም አረማውያን እምነቶች።

ሀገረ ሕይወት: መንግሥተ ሰማይ።

ሀገረ ሰላም: ኢየሩሳሌም።

ሀገረ ሰብ (ሰብአ ሀገር): የአገር ሰው፣ ባላገር።

ሀገረ ስብከት: ከሐዋርያት አንዱ ወንጌልን የሰበከበት አገር።

ሀገረ ናግራን: ረዥም ተራራ ያለበት የሐባብ ጠረፍ። የሰማዕታተ ናግራን ቤተ ክርስቲያን የነበረችበት ይመስላል።

ሀገራዊ: አገሬ፣ የአገር ባላገር፣ ሰው፣ ዕድር፣ ልማድ፣ ቋንቋ። ፈረንጆች "ናሲዮናል" ይሉታል።

ሀገር: በቁሙ አገር።

ሀጭ/ሆጭ: መቅረብ፣ መሰጠት።

ሁሉ: በቁሙ።

ሁከተኛ: እውከተኛ።

ሁከት (ሆከ): እውከት፣ ግርግርታ፣ ፍጅት፣ ብጥብጥ።

ሂማልያ: በዓለም ካሉት ተራሮች ሁሉ የሚበልጥ ተራራ፣ በሺንና በህንድ መካከል ያለ።

ሂኣ: የሲቃ ጩኸት፣ ማፋቅ። "ሂኣ ሂኣ እለ" "ሂያ ሂያ አለ"

ሂያ: መግዘፍ፣ ማጓራት። "ሂያ ሂያ አለ" ማለት ገዘፈ፣ አጓራ።

ሂድ: ወግድ፣ ሄደ፣ ተራመደ።

ሄጳጳ: የዛጔ ነገድ ስም።

: የሳድስ ፊደል ድምፅ ሥረ መሰረት ወይም ሥረይ።

ህምህም አለ (ትግ. ሀመመ): ጉምጉም አለ፣ አጉረመረመ።

ህምህም: ማጉረምረም።

ህምህምታ: ጉርምርምታ።

ህንደኬ: በደቡባዊ ህንድ ያለ አገር፣ የሐዋርያው ቶማስ ሀገረ ስብከት። የኖባ ንግሥት ከተማዋ መርዌ የምትባል።

ህንዳውያን: የህንድ ሰዎች፣ የህንድ ተወላጆች።

ህንድ: የወንዝ ስም። በእስያ ክፍል የሚገኝ አገር ሲሆን በውስጡ ያሉ ሕዝቦች መዳብ የሚመስሉ ናቸው። የነገድ ስም ነው። አገሩም ህዝቡም በወንዙ ስም ተጠርቷል።

ህዋ: ክፍት።

ህጥር: ሽቱ።

ባይ: የሚል ሐርበኛ።

: ንብ ከቀፎ ወጥቶ ሲሄድ የሚደረግ ጩኸት። በግእዝ "ኦኦ" ሲሆን "ቁቁ" እንደማለት ነው።

: የወንዶች ዘፈን አዝማች፣ የሆይ ከፊል። "ሰርገኛው ይላል"

ሆሆ: ንብ ከቀፎ ወጥቶ ሲሄድ የሚደረግ ጩኸት።

ሆሆይ: የአንክሮና የአጋኖ ቃል ነው። "ሆሆይ የኔና ያንተ ነገር እንዲህ ሆኖ ቀረ"

ሆሞር ዛፍ: ሖሞር።

ሆሣዕና: የበዓል ስም። ከትንሣኤ በፊት ባለው እሑድ የሚከብር በዓል። ጌታችን በአህያ ተቀምጦ እሴተ መቅደስ ሲገባ፣ ሕዝበ ሰሌንና የወይራ ቅጠል ይዘው ሆሳዕና እያሉ ስለተቀበሉት ቀኑ ሆሳዕና ተባለ። ትርጉሙም "አድነን" ማለት ነው።

ሆረጠ: አፍን ፈጀ።

ሆሮ: በመዝገበ ቃላት ላይ የለም።

ሆታ: ማለት።

ሆቴል: ቤተ ነግድ፣ የንግድ ቤት።

ሆነ: ተደረገ።

ሆዋ ይላል: ይደነፋል፣ ያወካል።

ሆዋ: ሆታ፣ ድንፋታ፣ ውካታ።

ሆያ ሆዬ: የእረኞች ዘፈን አዝማች። (ሁለት ጊዜ "ሆይ") "ሆያ ሆዬ ጉዴ ለዝና መውደዴ"

ሆዬ (ሆይዬ): "የኔ ሆይ" ማለት ነው።

ሆይ: ቃለ አክብሮና አንክሮ፣ ወይም አጋኖ፣ አራህርሆ፣ አህስሮና አፍርሆ። ለቅርብ ሰሚ የሚነገር ቃል። "አምላክ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ ጃን ሆይ፣ በሬ ሆይ፣ ሐናንያ ሆይ" የአምስተኛው ፊደል የሀ ስም ሲሆን ኗሪ፣ ዃኝ ማለት ነው።

ሆደ መጋዝ: አዞ፣ ክፉ ሰው።

ሆደ ሰፊ: ቻይ፣ ታጋሽ፣ ትግስተኛ።

ሆደ ባሻ: በጥቂት ነገር የሚያዝን፣ የሚያለቅስ፣ የሚከፋ።

ሆደ ዘርጣጣ: ስትጮህ ሆድ ሆዱን የምትል የቆላ ወፍ።

ሆደ ገር: የዋህ ሰው፣ ጭካኔ አልባ።

ሆደ ጨረቃ: የሆዱ ጠጕር ጨረቃ የሚመስል ፈረስ።

ሆዱ ሻከረ: ነገር ገባው።

ሆዱ ቈረጠ: አገኛለሁ ማለትን ተወ፣ ተስፋ አጣ።

ሆዱ በለጠው: ከሰው ተለይቶ በላ።

ሆዱ አይበልጠውም: ብቻውን አይበላም።

ሆዱ ጠቡቷል: አይርበውም።

ሆዳም (ሞች): በላተኛ። "የሰጠ ይድከም" (ተረት) "ለሆዳም በሬ ጭድ ያዝለታል"

ሆዴ: "የኔ ሆድ" ወዳጄ።

ሆድ (ዐሳብ): ጠባይ።

ሆድ ሆዱን: የወፍ ስም (የርግብ አይነት)

ሆድ ሰጠ: ሀሳቡን ነገረ።

ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ: የማያደርገውን ለሚናገር ሰው የሚሰጥ መልስ።

ሆድ ቍርጠት: የሆድ በሽታ።

ሆድ ዕቃ: በሆድ ውስጥ ያለ አንጀት፣ ጉበት፣ ልብ፣ ኩላሊት፣ ሳንባ፣ ጣፊያ፣ ጨጓራ፣ ሽንፍላን የመሰሉ ሁሉ ናቸው።

ሆድ ዝማ: የሆድ በሽታ፣ እህታ ማማጥ።

ሆድ: የመብልና የመጠጥ ቋት ወይም ከረጢት። "ኮዳ" ከሚለው ጋር ይሰማማል። (አህያ ሆድ) ማለት ታጥቦ ትንሽ ፈገግ ያለ ልብስ። "የወፍ ወንዱ የሰው ሆዱ አይታወቅም" እንዲሉ።

ሆድና ዠርባ: ፍቅር፣ አንድነት፣ ስምምነት የሌለው።

ሆጭ - መቅረብ፡ መሰጠት፥ ሖጭ

No comments:

Post a Comment

ሽፋን

  ሀ   ለ   ሐ   መ   ሠ   ረ   ሰ   ሸ   ቀ   በ   ተ   ቸ   ኀ   ነ   ኘ   አ   ከ   ኸ   ወ   ዐ   ዘ   ዠ   የ   ደ   ጀ   ገ   ጠ   ጨ   ጰ   ጸ   ፀ   ፈ   ፐ