ሀ ለ ሐ መ ሠ ረ ሰ ሸ ቀ በ ተ ቸ ኀ ነ ኘ አ ከ ኸ ወ ዐ ዘ ዠ የ ደ ጀ ገ ጠ ጨ ጰ ጸ ፀ ፈ ፐ
ኸ: የፊደል ስም፡ የ'ከ' ዲቃላና ወራሽ። "ግእዝ አሰርከኒ፣ ፈታሕከኒ፣ ወሰድከኒ ያለውን አሰርኸኝ፣ ፈታኸኝ፣ ወሰድኸኝ ማለቱን ያሳያል። " የ'ኀ'ና የ'ኸ' ድምጥ አንድ መሆኑንም በአቡጊዳ እይ። ዳግመኛም የ'ሀ'፣ 'ሐ' ተለዋጭ ሲኾን፡ "ይህ፣ ይኸ"፡ "ምንዛህ፣ ምንዣኸ"፡ "በረሓ፣ በረኸኛ" ይላል። ከ'ሀ'፣ 'ሐ'፣ 'ኀ'ም ተለይቶ በግስ መድረሻ
"ደለኸ"፣ "ጮኸ" ሲል ይገኛል። ከካዕብ እስከ ሳብዕ ያለውም፡ "ጮኹ"፣ "ጯኺ"፣ "ጩኻ"፣ "መጮኼ"፣ "ጩኸ"፣ "ጩኾ" እያለ ይነገራል።
ኸን (ከነ): እኛ ለሚሉ የአንቀጽ ዝርዝር። "አንተ እኛን አመንኸን፡ ወደድኸን! ሰጠኸን፡ ነሣኸን።
"
ኸኝ (ከኒ): ተመልሰሽ 'ኸን' ተመልከት።
ኸየደ/ኬደ: ኼደ፡ ረገጠ፡ ተራመደ፡ ዐለፈ፡ አገደመ፡ ወጣ፡
ወረደ፡ ገሠገሠ፡ አመነዘረ።
ኸያጅ/ኻያጅ (ጆች) (ከያዲ): የኼደ ወይም የሚኼድ፡ ዐላፊ፡ አግዳሚ፡ ወጪ፡ ወራጅ፡ ተራማጅ፡
ገሥጋሽ፡ መንገደኛ፡ ከሰው ሴት የሚኼድ፡
አመንዝራ፡ ሸርሙጣ። (ተረት) "የጨረቃ ኻያጅ የምስክር ፈራጅ።
"
ኹ: የ'ኩ' ወራሽ፡ "እኔ" ለሚል የአንቀጽ ዝርዝር ሲኾን፡ በግእዝ
"በላዕኩ፣ ሰገድኩ፣ መጻእኩ"
የተባለውን፡ "በላኹ፣ ሰገድኩ፣ መጣኹ"
ይላል።
ኹለመና (ኵለንታ): ፍጹምና ምሉዕ አካል፡ ገላ።
"አከለ"
ብለኸ
"አካልን"
እይ።
ኹለመናዬ: የሴት ስም፡ "የኔ ኹለመና"።
ኹለተኛ (ኞች): ተከታይ፡ ምክትል፡ ጡት አስጣይ፡ ታናሽ ወንድም።
"ስምዖን ለሮቤል ኹለተኛ ነው።
"
ኹለተኛ: ተወራጅ፡ ተጨማሪ፡ "ኹለተኛ ቄስ"፡ "ኹለተኛ ዲያቆን"።
ኹለተኛ: የተራና የማዕርግ ቍጥር፡ የስምና፣ የግብር ቅጽል፡ "ኹለተኛ ቍጥር"፡ "ኹለተኛ ማዕርግ"፡ "ኹለተኛ ደረጃ"።
ኹለተኛ: ዳግመኛ፡ ሌላ።
"ኹለተኛ እቤቴ እንዲህ ያለ ሰው ይዘኸ አትምጣ። " "ባለተክሊልን ሴት ኹለተኛ ወንድ አይቀርባትም"። በአኃዝ ሲጻፍ "፪ኛ" ይላል።
ኹለተኛው: የጊዜ በቂ፡ ዳግመኛው።
"እከሌ እቤታችን መጥቶ ሲጠይቀን ኹለተኛው ነው።
"
ኹለተኛይቱ: ሌላይቱ፡ ዳግመኛይቱ።
ኹለተኞች: የመዠመሪያዎች ተከታዮች (ለምሳሌ በ፩ኛ ዜና መዋዕል ፲፩:፳፩ ላይ እንደተጠቀሰው)።
ኹለቱ ቀንዶቿ ባለ ብዙ ባላ ባልቾ የኾኑ የበረዶ እንስሳ ወተታም የዋሊያ ወገን (ዘዳግም ፲፬፡ ፭): (የእንስሳ ዝርያ)።
ኹለታቸው (ክልኤሆሙ): እነዚያ ሰዎች፡ ወይም ሌሎች ፍጥረቶች።
ኹለት (ክልኤት): የቍጥር ስም፡ በአንድና በሦስት መካከል ያለ ያንድ ቤት ቍጥር። በአኃዝ ሲጻፍ "፪" ይባላል። የጊዜ በቂና ቅጽል ሲኾን፡ "ኹለተዬ"፣ "ኹለት ጊዜ"፣ "ኹለተግዜ" ይላል (ለምሳሌ በፊልጵስዩስ ፬:፲፮ ላይ እንደተጠቀሰው)።
ኹለት ልብ): አመንቺ፡ ወላዋይ (ለምሳሌ በመዝሙረ ዳዊት ፲፪:፪ ላይ እንደተጠቀሰው)።
ኹለት ምላስ: ሐሰትና እውነት ደባላቂ፡ ፪ ቋንቋ ዐዋቂ።
"ባ፩ ራስ ፪ ምላስ" እንዲሉ።
ኹለት ሠሪ: የኬልቄዶን ባህል፡ "ቃል የቃልን ሥጋ የሥጋን ይሠራል" ማለት ነው።
ኹለት፡ ሳምንት)፡ ዐሥራምስት (15) ቀን።
ኹለት ባሕርይ: አንድ አካል ለኾነው ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚነገር የቅዱሳን አበው እምነትና ባህል።
ኹለት አደረገ (ከልአ): ከፈለ፡ ለየ።
ኹለት አፍ: ጠመንዣ፡ ሰው።
ኹለት ኹለት: የሕፃን ርምጃ ቍጥር፡ ፪ ጊዜ ፪ (፬) ባለ።
ኹለት ኾነ: ተከፈለ፡ ተለየ፡ እየብቻ ኾነ።
ኹለት ፈርጅ: ነጠላ።
ኹለትነት: ኹለት መኾን።
ኹለትያ: ኹለት መቶ ድር።
ኹለትዮ: ኹለትነት ያለው ውስጠ ብዙ።
ኹለትዮሽ: ዝኒ ከማሁ (ልክ እንደ ኹለትዮ)።
ኹለቶ: መንታ፡ ዕጥፍ ድርብ።
ኹለቶች: መንቶች፡ ዐይንና ዦሮን፣ ጡትን፣ እጅን፣ ክንፍን፣ እግርን የመሰሉ ነገሮች።
ኹለንተና: ዝኒ ከማሁ (ልክ እንደ ኹለመና) (ለምሳሌ በሉቃስ ፲፩:፴፬ ላይ እንደተጠቀሰው)።
ኹለዬ (ኵልሄ): ኹለግዜ፡ ዘወትር፡ በየቀኑ።
ኹሉ (ኵሉ): ደቂቅ ቅጽል፡ መላው፡ ጠቅላላው፡ አንድ ሳይቀር። ስምን እያስከተለና እያስቀደመ በቅጽልነት ሲነገር፡ "ኹል ጊዜ"፣ "ኹለግዜ"፣ "ኹል ቀን"፡ "ሰው ኹሉ"፣ "ዓለም ኹሉ" ይላል። በአንድ ጊዜ ቅጽል ተቀባይና ቅጽል ሲኾን፡ "በዚህ ኹሉ ነገር ያሠኛል። " በቂ ሲኾን፡ "ኹሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት። " "ኹሉ አገርሽ። " "ያቶ እከሌ ገንዘብ ኹሉ በኹሉ ይህን ያህል ይኾናል። " (ተረት)
"ዝናም ባይመጣ ኹሉ ቤት፡ እንግዳ ባይመጣ ኹሉ ሴት። " "ኹልኸ"፣ "ኹላቸው"፣ "ኹላችኹ"፣ "ኹላ"፣ "ኹልሽ"፣ "ኹላችን" እያለ እስከ ፯ ይዘረዝራል።
ኹል (ኵል): ዝኒ ከማሁ (ልክ እንደ ኹሉ)፡ አገባቡን ባለፈው ተመልከት።
ኹልት: የተኾለተ፡ ኹለት የኾነ የተከፈለ።
ኹሏ/ኹላ: መላዋ (ለምሳሌ በዘፍጥረት ፲፩:፳ ላይ እንደተጠቀሰው)።
ኹሽ (ኩኪ): ለቅርብ ሴት የአንቀጽ ዝርዝር። "እኔ አንቺን አሰርኹሽ፡ ተበተብኹሽ፡ ወደድኩሽ፡ ጠላኹሽ።
"
ኹት (ክዎ): ለሩቅ ወንድ የአንቀጽ ዝርዝር።
"እኔ እሱን ባረክኹት፡ መረቅኹት።
"
ኹነታ/ኹናቴ/ኹኔታ (ክዋኔ): ተፈጥሮ፡ አካል፡ መልክ፡ ቁመና፡ አኳዃን፡ ጠባይ፡
ዐመል፡ ሐሳብ፡ ሥራ። "ይህ ሰው ኹኔታው አይታወቅም። "
ኹነኛ: ጠቃሚ፡ ወዳጅ፡ ተሰማሚ ሰው።
ኹን: ተቀመጥ።
"እዚህ ኹን" እንዲሉ።
ኺድ: የቅርብ ወንድ ትእዛዝ አንቀጽ፡ "ከዚህ ወደዚያ ዕለፍ፡ ተራመድ።
" "ውሻን ና ኺድ" እንዲሉ።
ኺድ: የዜማ ምልክት ፊደል አይዶለም።
ኺዶ/ኼዶ: ዐልፎ፡ ተራምዶ።
ኺጃ (ወሎ): አኺዶ (ሆሴዕ ፲:፲፩)።
ኻ (ከአ): ለቅርብ ወንድ የስምና የአንቀጽ ዝርዝር።
"ጕድኻ፣ ድንቅኻ"፡ "በላ፣ ከልኻ። "
ኻ (ከአ): ለቅርብ ወንድ የስምና የአንቀጽ ዝርዝር።
"ጕድኻ"፣ "ድንቅኻ"፡ "በላ"፣ "ከልኻ"።
ኻባ: ካባ (ካበ)።
ኻት (ካ ሃ): ለሩቅ ሴት የአንቀጽ ዝርዝር። "አንተ እሷን ገደልኻት። "
ኻቸው (ኮሙ): ለሩቆች ወንዶችና ሴቶች የአንቀጽ ዝርዝር።
"አንተ እነሱን መረቅኻቸው።
"
ኻች (ካች) (ከተተ): ካንድ ዓመት በፊት ያለፈ የወዲያኛው ዓመት ቅጽል።
"ካች ዓምና"
እንዲሉ። የኻች ምስጢር ፍጻሜና ኅልፈት ነው።
ኻች: ያለፈ።
ኻያ: ካያ (ከላ)፡ የቍጥር ስም፡ ያ፲ ቤት ቍጥር፡ ኹለት ዐሥር። በአኃዝም "፳" ተብሎ ይጸፋል። አንቀጹ 'ከላ' (ከልአ) ስለ ሆነ፡ "ሀያ" ወይም "ሐያ" ብሎ መጻፍ ስሕተትና አለማወቅ ነው። የተራና የማዕርግ ቍጥር ሲኾን "ኻያኛ"፣ "ኻያኛው" ይላል። "ከን" ተመልከት።
ኻያጅነት: ኻያጅ መኾን፡ መንገደኛነት፡ አመንዝራነት።
ኼደ: ረገጠ፡ ዐለፈ (ኸየደ)።
ኼደት (ኪደት): መኼድ።
ኼደት አለ: ዐለፍ፡ ራመድ አለ።
ኼደት ኼደት አለ: ራመድ ራመድ አለ።
ኾለተ: ኹለት አደረገ፡ ኹለት አለ።
ኾራ (ኩሬ): ዐምቦ፡ ከብት ሲጠጣው ጨው ጨው የሚል ውሃ ዐፈር። "ኾራ" በኦሮሞ 'ዐምቦ' በአማርኛ ነው፡ ምስጢሩ ከኩሬነት አይወጣም። "ኮራን" ተመልከት።
ኾነ (ኮነ): በጀ፡ ሰላ፡ ቀና፡ ረባ፡ ጠቀመ፡ ፈየደ፡ ተሰማማ።
"ይህ ልብስ ምንም ሰውን ደስ ባያሠኝ ለኔ ኾኖኛል። " "ይኾንልኛል ብዬ ጐሽ ጠመድኹ፡ ባይኾንልኝ ፈትቼ ለቀቅኹ።
"
ኾነ ብሎ: ዐስቦ፡ ዐውቆ፡ ወዶ። ከዚህም በቀር
"ኾነ"
እየተመላለስ በንግግር ውስጥ ከአገባብ ጋራ ይነገራል። "በደን መካከል ስትኼድ ነብር የመጣ እንደ ኾነ ምን ትኾናለኸ?" "ሰው እንዳይኾን የለምና የቀረኹ እንደኾን እንድትጠይቀኝ ይኹን። " "ዕውሩ ላሜኅ ደንጊያ ወርውሮ የገደለው ሰው ይኾናል፡ ቢኾን ባይኾን ምን ተዳበጧት የመጣኸ እንደኾን ታገኘኛለኸ። " "እከሌ ሰዎች ሲጣሉ የሸሸው ምስክር እንዳይኾን ይኾናል"። "ሲኾን አንተ ና፡ ሳይኾን ሰው ላክ። " "አይኾንም እንጂ ከኾነማ ከመጋዞ"
ይላል ጕልማ። ኀላፊውን ትንቢት አንቀጽ ሲያስቀር፡ "ይመጣል ኾነ"፣ "ይኼዳል ኾነ" ይላል፡ ፍችውም
"ነበረ"
ነው።
ኾነ: ሰነበተ፡ ከረመ።
"ደኅና ኹን።
"
ኾነ: ባሕርዩን ሳይለቅ ሌላ መልክና አካል ገዛ። "አምላክ ሰው ኾነ"፡ "ሰው አምላክ ኾነ"።
ኾነ: ተለወጠ፡ ዐይነቱ፡ ጭገሬታው ጠፋ።
"የሎጥ ሚስት የጨው ዐምድ ኾነች።
" "ደግ ኾነ ክፉ ኾነ" ቢል የጠባይን መለወጥ ያሳያል።
ኾነ: ተቀመጠ፡ ቈየ፡ ዘገየ፡ ኖረ (ለምሳሌ በዮሐንስ ፲፬:፫ ላይ እንደተጠቀሰው)። "እስከ ዛሬ ድረስ ያልጠየቅኸን የት ኾነኸ ነው?"
ኾነ: ተወለደ፡ ረባ፡ በዛ (ለምሳሌ በዘፍጥረት ፴፪:፭ ላይ እንደተጠቀሰው)።
ኾነ: ተደረገ፡ ተነካ።
"እከሌ ምን ኾነና ሞተ?" "የዚህ ሰው ራሱ ምን ኾነ?" "የኾነ ኾኖ ነገሩ በምን ዐለቀ?"
ኾነ: ተገባ።
"በኾነ ባልኾነ ከሰው አትጣላ።
"
ኾነ: ተገኘ።
"የኾነውን ያኽል ላክልኝ።
"
ኾነ: ተገኘ፣ ተፈጠረ፣ ተፍለከለከ፣ ተርመሰመሰ፣ ወጣ (የትል) (ዘጸአት ፲፯፡ ፳። ዘኍልቍ ፭፡ ፳፪)።
ኾነ: ተጨበጠ፡ ተወደደ፡ "እኽል ነፍስ ኾነ።
"
ኾነ: ተፈጠረ፡ ነበረ።
"እንዳልኾነ ኾነ" እንዲሉ።
ኾነ: ወረደ፡ መጣ (ለምሳሌ በኤርምያስ ፩:፬ ላይ እንደተጠቀሰው)።
ኾነ: ደረሰ።
ኾነ: ደረሰ፡ ተፈጸመ።
"እኔ ያልኹት ባይኾን ከምላሴ ጠጕር ይነቀል"
እንዲሉ።
ኾኖ: ተደርጎ፡ ተሠርቶ።
ኾኖም አያውቅ:
"ባንድ ከተማ ፪ ንጉሥ"፡ "ባ፩ ዐልጋ ፪ ዐራስ"፡ "ባ፩ ራስ ፪ ምላስ"።
ኾደደ: ዐረሰ፡ ጦመኾደደ።
ዃላ: ጊዜና ስፍራ (ኋላ)።
ዃኝ (ኞች): የኾነ ወይም የሚኾን፡ ረቢ፡ ጠቃሚ።
No comments:
Post a Comment